በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመቀነስ የወንጀል ሕጉን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ሕጎች መሻሻል እንደሚገባቸው ተነግሯል። የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማሕበር የሕግ አማካሪ ወይዘሪት ሕይወት ሙሴ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በወንጀል ሕጉ ላይ ያልተጠቀሱ ጾታዊ ጥቃቶች በመኖራቸው ሳቢያ ለወንጀል ድርጊቶቹ ተመጣጣኝ ፍርድ እየተሰጠ አለመሆኑን አመልክተዋል።
ወይዘሪት ሕይወት፤ ማሕበራቸው በወንጀል ሕጉ መሻሻል ያለባቸውን ክፍተቶች በመመርመር፣ የሕግ ለውጥ እንዲደረግ የተለያዩ ስራዎችን አጠናቅቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማስረከብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አክለውም፤ የወንጀል ሕጉና ተያያዥ ፖሊሲዎች ተፈጻሚነታቸው እንዲጠናከር ማሕበራቸው እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ያብራሩት የሕግ ባለሙያዋ፣ እነዚሁ ሕጎችና ፖሊሲዎች ተሻሽለው ለሌሎች አስተማሪ ውጤትን እንዲያመጡ የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
“ተጎጂዎች ወደ ማሕበራችን ከማመልከታቸው በፊትም ሆነ ጥቃቶች እንደደረሱ መረጃዎች ሲመጡ ወይም ተጎጂዎቹ ሲያመለክቱ፣ የማሕበራችን ባለሞያዎች ፖሊስ ጣቢያ ድረስ በመሄድ ድጋፍ ያደርጋሉ። ፍርድ ቤት በመገኘት የጉዳዩን ሂደት ይከታተላሉ። በሕግ አግባብ ውሳኔ መሰጠቱን ከመከታተል ባለፈ፣ ከባለጉዳዮቹ ጋር ጉዳዩ ዳር እስኪደርስ ድረስ የክትትል ስራ እንሰራለን።” ሲሉ ማሕበራቸው ሌሎች ለተጎጂ ሴቶች የሚያደርገውን ድጋፍ ዘርዝረዋል።
ማሕበራቸው የወንጀል ሕጉ ላይ በርካታ ስራዎች መሰራት “ይገባቸዋል” ብሎ እንደሚያምን የጠቆሙት ወይዘሪት ሕይወት፤ “የቤተሰብ ሕጉና (የስራ ሕጉን) ጨምሮ -- ተያያዥ ሕገ መንግስታዊ አንቀጾችን ስንመለከት የሴቶችን መብት ያካተቱ የተዘረዘሩ ነጥቦች አሉ። ይሁንና ተፈጻሚነታቸው እጅግ አናሳ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የወንጀል ሕጉ አስተማሪ ቅጣት እንዲኖረውና በሕጉ ላይ “ይስተዋላሉ” ያሏቸው ክፍተቶች ተመርምረው እንዲስተካከሉ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማሕበር ዕንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
በቅርቡ በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ባሰናበተው በሕጻን ሔቨን ዓወት ላይ የተፈጸመው ጾታዊ ጥቃት ዙሪያ ማሕበራቸው ምን ዓይነት ዕንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ከአዲስ አድማስ የተጠየቁት፣ ወይዘሪት ሕይወት፣ ማሕበራቸው ጉዳዩ ሚዲያ ላይ ከመውጣቱ በፊት እንደሚያውቅና በአማራ ክልል፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማሕበር የባሕር ዳር ከተማ ቅርንጫፍ ይከታተለው እንደነበር ጠቅሰዋል። የሕጻን ሔቨንን እናት ከማግኘት ባለፈ፣ ማሕበራቸው የወንጀል ድርጊቱን የፍርድ ሂደት ሲከታተል መቆየቱንም የሕግ ባለሞያዋ አስረድተዋል።
“በተከሳሽ ላይ የተፈረደው የ25 ዓመት ፍርድ ‘ይበቃል’ የሚያስብል አይደለም። ያንሳል። ከዚህ የበለጠ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ሂደቶች ይኖራሉ። ባለሞያ በመመደብ፣ ጉዳዩ በሚታይበት ችሎት ተገኝቶ ይግባኝ የሚቀርብበት መንገድ ካለ የማየት ስራዎችን ለመስራት እየሞከርን ነው። በሌላ በኩል የተወሰነው ውሳኔ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ማሕበሩ እስከመጨረሻው ይከታተላል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች መባባስ ምክንያቶች አንዱ የወንጀል ሕጉ ክፍተትና የቅጣቱ አናሳ መሆን “ነው” የሚሉት ወይዘሪት ሕይወት፣ ሕጉ ሲወጣ በነበረበት ወቅት ላይ የተወሰነ በመሆኑ አሁን ላይ የሚወሰኑ ቅጣቶችን ተመጣጣኝነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱን ተናግረዋል። ለዚህም እንደአብነት የሚጠቅሱት አሲድ በፊትና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ በመድፋት የሚፈጸመውን ጥቃት ሲሆን፣ ለዚህም ጥቃት የሚመጥን ቅጣት በወንጀል ሕጉ ውስጥ ባለመኖሩ ምክንያት ለወንጀል ድርጊቱ መስፋፋት ሰበብ መሆኑን አመልክተዋል።
“ወቅቱን ያማከለ ድንጋጌ መኖር አለበት። ማሕበረሰቡ ተጠያቂነትንና የሃላፊነት ስሜትን ማጎልበት አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ድንጋጌዎች አሉ። የአቅም ግንባታ ስልጠና ያስፈልጋል።” ሲሉ፣ የማሕበራቸውን የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች “አሳስቦኛል” ያለ ሲሆን፣ “ወንጀል ፈጻሚዎች አስተማሪና ተመጣጣኝ ቅጣት ባለመቀጣታቸው እና ወንጀል ሰርቶ ያለመያዝ ልምድ በመበራከቱ” የጥቃቶቹ መስፋፋት መንስዔ መሆናቸውን ጠቁሟል። ጉባዔው ይህንን የጠቆመው ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ኢሰመጉ “የፌደራል መንግስት ከወንጀል ሕጉ ዓላማና ግብ አንፃር የሴቶችና ሕፃናትን አስገድዶ መድፈር እና ጥቃት የሚመለከተው ክፍል ላይ ተገቢውን ጥናት በማድረግ፣ ሕጉ ለሚፈጸሙት ወንጀሎች ተመጣጣኝና አስተማሪ በሆነ መልኩ እንዲሻሻል ጥረት እንዲያደረግ” ጥሪውን አቅርቧል። በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሴቶቸና ህጻናት መብትን የሚመለከቱ ሕግና ፖሊሲዎች እንዲጸድቁ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደረግም ጉባዔው ጥሪ አድርጓል።
Sunday, 01 September 2024 20:14
Published in
ዜና