Sunday, 01 September 2024 20:16

“ማነው ምንትስ?”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 እንደሚከተለው ዓይነት የቻይናዎች ተረት አለ።
በአንድ ትልቅ ተራራ ላይ የሚኖር አንድ ዘጠኝ እራስ ያለው ግዙፍ ወፍ አለ። በአካባቢው ካሉት ወፎች ሁሉ ዘጠኝ አፍ፣ ለማስፈራራት ስለሚችል፣ ማንም ቀና ብሎ የሚያየው የለም። ስለዚህ እሱ በሚንቀሳቀሰበት ቦታ ሁሉ ዝር የሚል አንድም ሌላ ወፍ ባለመኖሩ ምድሩም፣ ዕፅዋቱም፣ ዛፉም የራሱ ሆኗል። ዛፉ ላይ በስሎ የተንዠረገገው ፍሬ፣ ረግፎ አገር ምድሩን የሞላው ፍሬ፣ የራሱ ጥም ማርኪያ ነው።  የጎጆ መቀለሺያው የመስክ ሣር ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር ነው። ሁሉ በእጄ ሁሉ  በደጄ ያለ የኮራ ወፍ ነው። አንድ ሊፈታው ያልቻለው ችግር ግን አለ። ይኸውም በጠማው ጊዜ ውሃ ሲጠጣ፣ በራበውም ጊዜ ምግብ ሲበላ አንደኛው ራሱ ጎንበስ ባለ ጊዜ፣ ሌሎቹ ስምንቱ ራሶች ተሻምተው አፋቸውን ይልካሉ። በሽሚያው ወቅትም አንዱ አንደኛውን መግፋቱና መጠቅጠቁ አልቀረም። በዚያ ላይ ሁሉም በተለያየ አቅጣጫ የሚያዩ ስለሆነ፣ “በእኔ አቅጣጫ እንብላ በእኔ አቅጣጫ እንብላ” እየተባባሉ እየተጠማዘዙ ይተጋተጋሉ። ይደማማሉ። ይቆሳሰላሉ፡፤ አንደኛው በደሉን ሲናገር ሌሎቹም የየበኩላቸውን በአንድ ጊዜ ስለሚናገሩ ጫጫታ ይሆናል። የጨረባ ተዝካር እንደሚባለው መሆኑ ነው።
ከተራራው ግርጌ ባህር ውስጥ የምትኖር አንዲት ብልህ የባህር-ወፍ አለች። ባለዘጠኝ እራሱ- ወፍ እርስ በርስ እየተሻሙ፣ እየተጠቃጠቁ ደማቸውን ሲያዘሩ፤ ላባቸውም እየተነቀለ ሲወድቅ አስተዋለችና በመገረም ሳቀችባቸው።
“በማን ላይ ነው የምትስቂው?” ሲሉ ጠየቋት።
“በሁላችሁም ላይ” አለች የባህሩዋ-ወፍ፤ አሁንም ከትከት ብላ እየሳቀች።
“ለምንድን ነው የምትስቂብን?” ሲሉ ደግመው ጠየቋት
“ያገናችሁትን ጥራጥሬ ለመብላት በምታደርጉት ትግል፣ የምትቋሰሉበትንና የምትዳሙበትን ትርዒት እያስተዋልኩ ነዋ! ጥራጥሬውን ማንም ያግኘው ማን ወደ አንድ ሆድ እንደሚገባ፣ የማንኛችሁም ጭንቅላት ለማሰብ አለመቻሉ፤ በጣም አስገርሞኝ ነው የምስቅባችሁ።” አለቻችው።
***
የዘጠኝ እራስ ችግር በሀገራችን በተለያዩ ዘመናትና ሁኔታዎች ውስጥ የታየ ነው። በታሪክ፤ ከነገሥታት የግዛት ዘመን ጀምሮ፣ በየመንግሥታቱ ላይ ሁሉ የታየ ነው። በተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ውስጥ ሁሉ የታየ ነው። በየሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት ውስጥ ነጋ ጠባ የሚታይ ጉዳይ ነው። በመስተዳድር አካት ሁሉ ከታህታይ እስከ ላዕላይ መዋቅሩ ድረስ ካንሰር-አከል በሽታ ሆኖ የቆየ ችግር ነው። ዘጠኝ እራስ ላይ ያሉ ዘጠኝ አፎች፣ ዘጠኝ የተለያዩ ጉዳዮችን በአንደ ጊዜ ያወሳሉ። አንዱ አንዱን አያዳምጥም። አንዱ ለአንዱ አጀንዳ ልቡን አይሰጥም። የትኛውንም አጀንዳ መናቆሪያና መጠላለፊያ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። የትኛውንም ምግብ ይሻማሉ። ለዚያ ምግብ ሲሉም ይታገላሉ። ለዚያ ምግብ ሲሉ ይቋሰላሉ። ለዚያው ምግብ ሲሉ ይገዳደላሉ። በመጨረሻ የየመስዋዕትነቱ ሁሉ ፍሬ ለማን ጥቅም እንደሚውል  አያስተውሉም። ከቶውንም “አገር አገር” የሚሉት ከልባቸው ከሆነ ድካሞቹን፣ ጥረቶቹንና መስዋዕትነቶቹን ሁሉ አዋህደው ለሀገር ሊያውሉ በተገባቸው ነበር።
ስለአንድነት በሚነሱ መድረኮች ሁሉ ይኸው ችግር በየዘመኑ ፈጥጦ ይታያል። ስለአገር ኢኮኖሚ ችግሮች ለመወያየት በሚታደሙ ምሁራን መካከል የሚታየው አለመግባባትም የዘጠኝ እራስ ችግር ነው። ስለ ከፍተኛ የፖለቲካ ችግር ለመወያየት ባንድ አዳራሽ በሚቀመጡ (ያውም እሺ ብለው ከተቀመጡ ነው) የተለያየ ቡድን አቀንቃኝ የፖለቲካ ሰዎች መካከል ገና “ሀ” ብለው በዲሞክራሲ ፅንሰ-ሀሳብ ላይ ውይይቱን ሲጀምሩ የሚጣሉት፤ በዚሁ በዘጠኝ እራስ ባህሪ መዘዝ ነው። የሁሉም ድካም አንድ ሀገር ለማዳን መሆኑን ይዘነጋሉ።
ዛሬ በሀገራችን ከራስ ጠጉር እስከ እግር ጥፍር ድረስ በተሰራጨው በሙስና ጉዳይ ላይ እንኳ ተስማምቶ ተወያይቶ የሙስናውን ቁንጮ ለመለየት በወገንተኝነት፣ የሥልጣን ጡት- በመጣባት፣ በታግሎ- አደግነት፣ ወዘተ እርስ በርስ በሚደረጉ ሽኩቻዎች “ግምገማው” ግቡን ሳይመታና እውነቱ ሳይወጣ፣ ጉዱ በየጓዳው በምሥጢር እንደተቋጠረ ይቀራል። የሙስና መጥፋት ለሀገር ደህንነት የሚበጅ መሆኑ ከታመነ፣ በሙስና ተጠያቂው አለቃም ይሁን ምንዝር፣ የፓርቲ አመራርም ይሁን ተራ ዜጋ፣ ማንም ይሁን ማን ሙስናው በወጉ ተገልጦ ሊታይ፣ በአግባቡም ሊጠየቅና ሊወገዝ፣ ለህዝብም ሊነገር ይገባል፡፡ በዘጠኝ እራስ ምክንያት አንድ አገር እንዳለን መርሳት የለብንም።
አለበለዚያ ታዋቂው ያገራችን ገጣሚ፤ “ማነው ምንትስ?” በሚለው ግጥሙ ውስጥ እንዳለው፡-
“…ለሰባት ዕምነት ሲምሉ፣ በሰባት ምላስ ሲያወሱ
ባንደኛው ሲነካከሱ
በሌላው ሲሞጋገሱ
በሦስተኛው ሲካሰሱ
ሌት ዓይኑን ላፈር ያሉትን፣ ሳይነጋ የሚያወድሱ
እነሱን አርጎብን ጨዋ፣ ሸንጎ የባሕል አዋይ
የሥነ-ስርዓት ደላዳይ
መራጭ ቆራጭ ቀናን ከአባይ
ጨዋ መሳይ፣ ንፁሕ መሳይ
ከኔ ምንም ላይሻሉ፣ ደሞ እኔን ምንተስ ባይ”
ማለት ግድ ይሆንብናል። ያም ሆኖ ዛሬም ደግመን ለአንድ አገር የማሰቡን ነገር ለሁሉም አደራ ከማለት ወደ ኋላ አንልም።


Read 595 times