Sunday, 01 September 2024 20:18

እኛ የመጀመሪያዎቹ! (የእኛነት አባዜ)

Written by  ሲራክ ወንድሙ
Rate this item
(3 votes)

  እናንተዬ፤ የአሁኒቱን ኢትዮጵያ ሳስብ በጎረቤት ቡና ላይ የተገኘች ስስታም ህፃን ልጅ ትመስለኛለች። ስስታም ህፃን በሁለት እጁ ቡና ቁርስ አስጨብጠውት ሰሀኑ ላይ ያለውን ማንም እንዲነካ አይፈልግም። ሁሉም የእሱ መሆን አለበት። ከባሰበትም የጀበናው ቡና የኔ ነው ብሎ፣ ለወግ የተገናኘን ጎረቤት በሳቅ ሊደፋ ይችላል። ይሄ ልጅ ስስቱ እንደጠናበት ሲያድግ ደግሞ ሌላ ጉድ ይመጣል፡፡
ለምሳሌ፤የቀደምት የማንነት ጥያቄና አዙሪትን በተመለከተ እንደ ኢትዮጵያ የአለም ታሪክን የሚሻማ ሀገር አለ ከምትሉኝ፣ ድፍን ስምንት ብር ከመንገድ አገኘሁ ብትሉኝ ለማመን ይዳዳኛል፡፡ የጉድ ሀገሮች ነን እኮ!
በእውነቱ የዓለም ውድ ንብረት ሆኖ፣ የኛ ነው ብለን ያልተከራከርነው ምን አለ? አስታውሱኝ እስኪ..ኪነጥበብ ካሉን አዎን እኛ ነን የመጀመሪያዎቹ .... የስነ ህዋ ጠፈር ጥናት ካሉን፣ እንዴ እከሌ ከአለም ቀድሞ ይህን ብሏል... ስነ - ንዋይ ከተባለም፣ የማንጠራው ስም የለም። ዲሞክራሲ ....ፍልስፍና .... ስነ ህይወት.... ስነ ህንፃ...ህዝብ አስተዳደር ... አርኪኦሎጂ ...ሁሉንም የጀመርነው እኛ ነን፡፡
እሺ እኛ እንጀምረው፤ ታዲያ ያ ሁሉ የት ገባ? እንዴት ሁሉንም በአንዴ አጣን? በነገራችን ላይ ከሽሚያችን የተነሳ የሰው ልጅን በሁለቱም ቲዮሪ የፈጠርን ህዝቦች ነን። በ creationist theory ግሽ አባይ ላይ፣ አዳምን ከአፈር እግዜር ራሱ ፈጥሮታል። ወዲያ ወደ ታች ደግሞ አፋር ላይ በ scientific theory ሉሲ ወይም ድንቅነሽን በድንቅ ሁኔታ አግኝተናታል። እኔ ግን ስጠረጥር አዳምና ድንቅነሽ እዛው ባህር ዳር ጫካ ውስጥ የሚተዋወቁ ይመስለኛል። ያ ዘመን ፈረስ ስለሌለው አዳም ድንቄን እየጋለበ የትም ሲፋንን፣ ድንቄ በምሬት ጥላው ሄዳ፣ ያ የአፋር ሙቀት ቀቅሎ ገድሏት ነው ብዬ እጠረጥራለሁ። የምርም አዳም ይህን በደል ፈፅሞ ከሆነ፣ ሳይመሽ ሳይነጋ ለፍርድ ይቅረብልን፤ ጨካኝ ነው።
ሌላው ቀርቶ መርቅነን ሁሉን የኔ ነው የምንለውን ጫት እንኳን፣ አሳልፈን መስጠት አልሆነልንም። ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን በፊት ጫትንም ያገኘነው እኛ ነን ብለናል። መረጃችን ግን ምርቃናው ካልሆነ በቀር ትንሽ አደናጋሪ ነው። ወይም አዳም ድንቄን እስክትማረር እየጋለበ፣ ያንን ሁሉ መንገድ እንድትሰደድ ያደረገው መርቅኖ ነው በሉኝና፣ እኔም መርቅኜ ልመናችሁ፤ ካልሆነ እንዲህ ያለን ነገር ለጠላታችሁም አይስጥ ባይ ነኝ።
በቅርብ ጊዜ አንድ ፈላስፋን በተመለከተ የኛ ነው አይደለም፣ የሚሉ ሞቅ ያሉ ክርክሮችን በመጻሕፍት ሁላ ታትመው ሳይ፣ እኛ ግን ሁሉን ከአለም ነጥቀን ነጥቀን የራሳችንን አለም ልንገነባ ነው እንዴ አስብሎኛል?  ሀገሪቱን የሚያድነው የፈላስፋው ሀሳብ ነው ወይስ ዜግነቱ? ግራ እኮ ነው የሚያጋባው፤ ነገረ ሥራችን፡፡ የሆነስ ሆነና ሰውየው የኛ ከሆነ ሊያውም አማኝና ግብረ ገብ በሚባለው ማህበረሰብ ውስጥ ይህን ያህል ስንፍና እና በሁለት ያደቆነ ትርጉም መፅሐፍ፣ እግዜርን መግደል ከየት አመጣን?
ቀደምት የረቂቅ የሙዚቃ ፈጣሪዎች ከነበርን፣ ይሄ ሁላ ውጫጭ የማይገባንን ከበሮና ድለቃ እያጋተን፣ ለምን ጆሯችን መሀን ሆነ? ያሬድ ሆይ፤ ዝም ብለህ ታየናለህ? ምነው ያሬድ ምነው?!
ያ የአራራቱ ዘመዳችን ኖህ፣ ውሃውን ያኔ ምን ሹክ እንዳለው አናውቅም። “ይኸው ኧረ ኖህ ሰማይ ቤት ነው” ብንልም፣ “የለም ሀገሩ እዚህ ነው” እያለ በየክረምቱ የሚሞላው ጎርፍና የሚሞተው የወገናችን ቁጥር ሰማይ ቤት ካለው አይተናነስም እኮ፡፡ ለኖህ ንገርልን ወይ የመርከብ አሰራሩን ይንገረን፤ አሊያም ዜግነቱን አጣርቶ ወደሚበጀው ሀገር ይጠጋ። እኛ በእሱ የተነሳ ጠዋት ቁርስ ሰፈራችን በልተን፣ ለራት በጎርፍ እየተንከባለልን ወንድም ሀገር ሱዳን መገኘት ሰልችቶናል። ዘፈናችን ሁሉ ተለውጦ ሴቶቻችንን የምናሽኮረምምበት ግጥም ራሱ፤
«ዝናብ ጥሏል አሉ - ጋራ ጋራውን
ጎርፍ ያመጣሽ እንደሁ - ልጠብቅ ወንዙን" የሚል ሆኗል።
ደግሞ የዜጋችን ብዛቱ፤ ኤዞፕም እኮ የኛ ነው። ግን ደህና ነው? ዛሬም ተረት አላለቀበትም። ይኸው እሱ ተክሎት በሞተው የተረት አዚም፣ ምሳና ቁርሳችን ሁሉ ተረት ሆኗል። ከቅዠት ትርክቶቻችን መብዛት የተነሳ አያሌ የዓለማችን ታላላቅ ሀገራትን እንደፈጠርንም እንደገዛንም ይነገራል። ለአብነት ያህልም፣ እስያን የፈጠራት እስያኤል የሚባል የኢትዮጵያ ንጉስ ነው የሚለውን የታሪክ አንጓና ፖርቹጋልን ጥንት ኃያላን የኦሮሞ ገዢዎች አንቀጥቅጠው እንደገዟት አትቶ፣ የስሟንም ስያሜ አመጣጥ ( port - of - gal ) ነው ፤ በሚል የፃፉልንም አሉ።
ከዚህም ባሻገር ከሰባቱ የዓለም ታላላቅ ቅርሶች መካከልም የቻይናን ግዙፉን ግንብና በግብፅ የሚገኘውን የጋዛ ፒራሚድም የገነባነው እኛ ነን፤ የሚለው መከራከሪያም የሚጠቀስ ነው። አሁን ሳይንስ የደረሰበት የስነ ጠፈር መነሻው የኛ መጽሐፎች ... የHollywood እና የNetflix ጣቢያዎች ላይ የሚታዩ ልዩ ልዩ ፊልሞችና ዓለማት፣ ከእኛ የድግምት መጻሕፍት  የተሰረቁ ሀሳቦች፣ መላ ምቶችና ሁነቶች ናቸው። ጀርመን የምትሰራቸው ከእፅዋት የተቀመሙ ልዩና ውድ መድሃኒቶች እንዲሰሩ እፅዋቱ የተወሰዱት ከእኛው ነው። ኧረ ኡኡኡ!!
በቅርብም በግሌ ከምጠብቃቸው ትርክታዊ ግኝቶች መካከል ሳይንስ መልስ ያጣለትን  የቤርሙዳ ትሪያንግል ሚስጥርን በተመለከተ ”በላይነሽ የምትባል የመሀል ሀገር ጠንቋይ፣ ከንጉስ እንትና ጋር በ16ኛው ክፍለ ዘመን ተጣልታ ከሀገሪቱ በመሰደድ እዛው ባህር መሀል ቤቷን ሰርታ ትኖራለች። የትኛውም መርከብና አውሮፕላን በዚያ ሲያልፍ መንፈሷን ልካ በጥፊ እያጠናገረች ደብዛቸውን ታጠፋለች” የሚል ሀተታ የያዘ መፅሐፍ ይታተምና፣ እንደ መፍትሔም ህዝቡ ጎዳና ላይ ለሦስት ቀናት በደረቱ ተኝቶ፤ “በልዬ እናቴ ማሪን ማሪን” እያለ ካልተማፀናት፣ እንዲህም ገብስማ ዶሮ አርዶ ካልገበረ፣ ይሄ እንደሚቀጥል በጥብቅ የሚያሳስቡ ፀሀፍት በመፅሐፍ ፣ በቲቪና በሬዲዮ የሚመጡ ይመስለኛል።
እኔ ግን የሚገርመኝ ህዝቡን ፈዛዛ የዳንግላ በግ አድርገውት ነው መሰለኝ፣ በ’ዚህ የተረትና የአፈ ታሪክ ጉልቻ ላይ እየወዘቱ እንዳሻው ማማሰል ስምን ተጠይቆ ከመመለስ አቅልለውታል። ከእኛ በቀር ሌላው የዓለም ሀገራት ምንም መፍጠር የማይችል ሽባ አድርገን የማሰብ አባዜን - መከበርን ከፈለገ ቁንን ገፃችን የመጣ ይሁን ከሌላ ባይገባኝም ስጋቴ በዚህ አያያዛችን፣ አንድ ቀን ከእንቅልፌ ስነቃ ኤፍል ታወርን ጂማ ላይ ፣ የግብፅ ፒራሚድን ድሬዳዋ ፣ የቻይናውን ግንብ ሱርማ ሱዳን ድንበር ላይ፣ የዱባዩን ፎቅ መሀል ፒያሳ ... ታጅ መሐልን መቀሌ ላይ በቅለው አይቼ በድንጋጤ እንዳልሞት ነው።
ሽፍታ አንወድም እንላለን፤ ግን ብሔራዊ የማንነት የስልጣኔ ቅሚያ ላይ እንደኛ የተሳተፈ የለም። ትንሽ አቅም ቢኖረንማ ተዋግተን ማሳመናችን የማይቀር ነበር። ብክነታዊ የወጥመድ እትብቶች ውስጥ የደቀቀ፣ የደከመ፣ እርዛት ያጠቃው ታሪካችን፣ ሀገራዊ ግለኝነት የሚያጠቃው ነው። ይህን ስል ግን ምንም አይነት የታሪክ ባለቤት አይደለንም እያልኩና ማንነታችን ላይ ለመዘባበት የተነሳሁ እብሪተኛ ሆኜ ሳይሆን፣ ያልተጠና ፍሬ አልባ የወሬ ትርክቶች የትም እንደማያደርሱንም እንዳላደረሱንም  ለመጠቆም ነው።
በተረት ተረት የተገነባ ስልጣኔና ሀገር፣ መሀሉ የመሰረት እየተባለ ቢቀጥልም ተረቴን መልሱን አፌን ከረሰ በዳቦ አብሱ ወይም ተዉት በሚል መደምደሚያ የሚዘጋ ነው። አሁን መሬት ላይ ያለን ሀገራዊ  መልክም ከዚሁ የሚርቅ ጠባይ የለውም። ከሁሉም ሳይንሳዊና ባህላዊ እሴት ርቆ በኢኮኖሚ አንድ የገንዘቡ ዋጋ በመቶ እጥፍ ከመሪ ሀገራቱ የራቀ፣ በፖለቲክስ ከዘመን ዘመን መረጋጋት አቅቶት በሽብርና ጦርነት የሚታመስ፣ በማህበራዊ የኑረት ቀለሙ መሀል ሰፋሪና አቋም አልባ ነው። ሆኖም ግን ሁሉም የኛና የኔ በሚል የምላስ ጀግንነቱ ከአለም ቀደምት፣ መሬት ላይ ባለው እውነታ ግን የተረት ብክነትና ክህነት ያጠቃን ህዝቦች መደብ ነን።
ለነገሩ እኔን ራሱ አትመኑኝ ባንዳ ነኝ። ልክ ናችሁ፤ አሜሪካንስ ቢሆን የምን ኮለምበስ የምን አሜሪጎ ነው፣ አማረ የሚባል የደቡብ ሰው ነው ያገኛት። ስያሜዋንም ያገኘችው ከአማረ ነው።  ወደ ስፖርቱም ኑ፤ ሁሉም የኛ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሳሙኤል ኢቶ ሀገሩ የት ነው ታውቃላችሁ? ባስኬቶ ነው። ኦባማ የሲዳማ ልጅ ነው። ሮናልዶ የአለታ ወንዶ...ኩንዴራ የመተሀራ ...ኤስኮባር የባህር ዳር...ማጄላን የሚዛን አማን ሰው ነው። ካላወቃችሁ ጠይቁ!
 ሌዮናርዶ ዳቪንቺ ሞናሊዛን የሳላት፣ ጦሳ ሜዳ ላይ ከብቶቿን ስታግድ ያያትን የወሎ ሴት ነው እንጂ ከየት አመጣ እሱ? ሲሲፈስስ ቢሆን እዚህ ራስ ዳሽን ተራራ ስር ድንጋይ እያንከባለለ የሚጫወት አንድ ቀውስ ገበሬ እንጂ፣ የምን እርግማን የምን አማልክት? ግሪኮች ሰርቀውን ነው ባካችሁ። ዝም በሉ፤ የሚቃወሟችሁን አትስሙ፤ ሁሉም የኛ ነው። እኛ ነን የጀመርነው። እኔም የእናንተ ነኝ። ሆሆሆ! ጉድ ነው እኮ እናንተዬ!

Read 311 times