Sunday, 01 September 2024 20:15

እንደ ጠመንጃቸው ብዛት፣ አሜሪካውያን በየመንገዱ አለመጨራረሳቸው ይገርማል?

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(0 votes)

  የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ሰሞኑን መግለጫ ሰጥቷል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ የተፈጸመው ከ7 ሳምንታት በፊት ነው። ኤፍቢአይ ተጨማሪ የምርመራ ውጤት ወይም አዲስ መረጃ አግኝቶ ይሆን?
ይመስላል። ግን አይደለም። ከቁጥር የሚገባ አዲስ ግኝት የለም ብሏል - ቢቢሲ በሐሙስ ዕለት ዘገባው። እና ታዲያ ጋዜጠኞችን ሰብስቦ መግለጫ መስጠት ለምን አስፈለገ? ቢቢሲ ሁለት ምክንያቶችን ጠቅሷል።
አንደኛው ምክንያት፣ የመንግሥት ተቋማት ወቅታዊ መረጃ ለዜጎች የመስጠት ኀላፊነት አለባቸው። ሌላው ሌላው ቢቀር፣ ቢያንስ ቢያንስ የጋዜጣዊ መግለጫ ልማድ ገና አልተለወጠም። ከፋም-ለማም… የመንግሥት ባለሥልጣናት በየጊዜው ጋዜጣዊ መግለጫ ያዘጋጃሉ። አዲስ መረጃ ባይኖራቸውም እንኳ… ያው አዲስ መረጃ እንደሌለ ለመንገር… ይናገራሉ።
“ይኸኔኮ… ጥበበኛው ኤፍቢአይ ጉደኛ ምሥጢሮችን ፈልፍሎ አግኝቶ ይሆናል” ብለው የሚያስቡ ሰዎች በከንቱ እንዳያስቡ ይጠቅማል።
“ይኸኔኮ እጅግ የረቀቁ የሤራ መረቦችን እየመዘዘና እያፍታታ፣ የተደበቀውን እየገለጠና እያበጠረ… ምርመራውን አጠናቅቆ ይሆናል”… ብለው የሚጓጉ ሰዎችም ይኖራሉ። ለኤፍቢአይ ብርቱ አድናቆት ቢኖራቸው ነው። ወይም የወንጀል ምርመራዎችን አቅልለው ስለሚያዩ ሊሆን ይችላል።
እንደ ልብ-ሰቃይ ፊልም በአንድ ሰዓት ተኩል ውስጥ ምርመራው ወደ ፍጻሜ እንዲደርስ ይጠብቃሉ። አንድ ወር ተኩል እንዴት ይፈጃል? የሆነ ሤራ ቢኖር ነው ብለው መጠርጠር ይጀምራሉ። ወይም ለኤፍቢአይ የነበራቸው በብርሃናት የተከበበ ደማቅ ምስል እየደበዘዘ ይጠፋባቸዋል። እነዚህ አድናቂዎች ናቸው።   
ከኤፍቢአይ እንበልጣለን ብለው የሚያስቡ ሰዎች ደግሞ አሉ - ኤፍቢአይን የሚንቁ። ምርመራ እስኪያልቅ ድረስ ለመጠበቅ ይቅርና ምርመራ እስኪጀመር ድረስ በትዕግሥት የመጠበቅ ፍላጎት የላቸውም። ግምትና መላምት ለመናገር ጊዜ አይፈጅባቸውም። ምን ችግር አለው? መገመት ነውር የለውም። ነገር ግን፣ “እርግጠኛ ነኝ” ብለው ለመደምደምም ከጥይት ጋር ይሽቀዳደማሉ።
ቢችሉና ሥልጣን ቢኖራቸው ደግሞ ወዲያውኑ ክስና ፍርድ እዚያው በዚያው ሰጥተው ይጨርሳሉ። ሥልጣን ባይኖራቸውም ግን ዝም አይሉም። ያወራሉ። አሉቧልታ ይዘራሉ። እየተቀባበሉ ያባዛሉ። እያስፋፉ ያዛምታሉ።
ኤፍቢአይ እንዲህ ዐይነት የወሬና የአሉቧልታ ግርግር ለመከላከል በማሰብ “ወቅታዊ መረጃዎችን” ለመስጠት ቢተጋ አይገርምም። ወይም ደግሞ ምንም አዲስ መረጃ የለም ብሎ መግለጫ ይሰጣል። ይሄ ራሱ እንደ አዲስ መረጃ ተቆጥሮ በዜና አውታሮች ይሰራጫል። የኤፍቢአይ ወቅታዊ መግለጫ ለመስጠት የፈለገው በዚህ ምክንያት ነው? አንድ ምክንያት ነው።
ግን ሌላ ሁለተኛ ምክንያት እንዳለ ቢቢሲ ጠቅሷል። ኤፍቢአይ የዛሬ አራት እና ሦስት ዓመት የራሱን ስም የሚያጎድፍ ትልቅ ስህተት ሰርቶ የለ?
“ዶናልድ ትራምፕ ከራሺያ መንግሥት ጋር አሢረዋል” በሚል ሰበብ በርካታ ወራትን የፈጀ ከንቱ ምርመራ አካሂዷል። ለምርመራ የሚያበቃ ተጨባጭ የጥርጣሬ መነሻ አልነበረውም። ይልቅስ ኤፍቢአይ ራሱ ነው “ተጠርጣሪ” ሆኖ ያረፈው።
ፖሊስ በአፍሪካና በአረብ አገራት ውስጥ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሲሆን እንደሚታየው፣ “ኤፍቢአይም የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የባለሥልጣናት መገልገያ ሊሆን ነው እንዴ?” የሚል ጥርጣሬ ተፈጥሯል። ቢያንስ ቢያንስ በርካታ ዜጎች አዝነውበታል። ዛሬስ?
ያኔ “ዶናልድ ትራምፕ የወንጀል ተጠርጣሪ ናቸው” ብሎ ትልቅ ስህተት ሠራ። አሁን ደግሞ፣ “በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ወንጀል በብቃት አልመረመረም” ተብሎ ቢወቀስ ለኤፍቢአይ ብቻ ሳይሆን ለአገሬው ለአሜሪካም መጥፎ ጠባሳ ይሆናል።
ታዲያ፣ ኤፍቢአይ እንደያኔው ዛሬም ሌላ ስህተት ላለመፈጸም ቢጠነቀቅ፣ ስህተት ሳይሆን የሚያስጠረጥር ነገር እንዳይታይበት መጠንቀቅ የለበትም? ከመጠንቀቅም አልፎ ቢጨናነቅ አይፈረድበትም። “ወቅታዊ መግለጫ” መስጠት የሚመጣው እዚህ ላይ ነው።
በእርግጥ፣ የወንጀል ምርመራውን በብቃት ማካሄድ ማለት፣ ጋዜጠኞችን ሰብስቦ ከካሜራ ፊት መግለጫ በመስጠት ማለት አይደለም። ቢሆንም ግን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ብቅ እያለ፣ “እየበረታሁ ነው” ብሎ ቢናገር ክፋት የለውም። “ምርመራው ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብሎ እንደ አገራችን ፖለቲከኞች ቢናገርስ? ኤፍቢአይ ማለቴ ነው። አባባል ከአገራችን ባይበደርም፣ በአባባል ዕጥረት ሳቢያ ዝም አይልም።
የግድያ ሙከራው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ውጤት ባያገኝም፣ ሥራ እንዳልፈታና ቸል እንዳላለ እንዲታወቅለት ይፈልጋል።
“ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ እንቅልፍ አይወስደኝም፤ የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም” የሚል መልእክት ለማስተላለፍም መግለጫ ይሰጣል። ሁለተኛው ምክንያት ይኸው ነው።
በዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸመው ቶማስ ክሩክስ የሀያ ዓመት ወጣት ነው። በሞባይልና በኢንተርኔት ዘመን፣ አብዛኛው ወጣት “ተከፍቶ የሚነበብ መጽሐፍ ነው” ይባል የለ? በፌስቡክ፣ በኢንስታግራም፣ በቲክቶክ፣ በዩቱብ ላይ ምን ተናገረ? ምን ጻፈ? ምን አነበበ? ምን አደመጠ? የትኞቹን ቪዲዮዎች ተመለከተ? ከማን ጋር መልእክት ተለዋወጠ? በጉጉል ምንና ምን “ሰርች” አደረገ? የሰዓታትና የሴኮንዶች፣ የዕለታትና የዓመታት ሁሉ… እየተመዘዘ እየተከመረ ይመረመራል። ይበረበራል።
የብዙ ዓመታት መረጃዎችን መርምረናል ብለዋል - የኤፍቢአይ ሰዎች።
ለምርመራ፣ አንድ ሺ ገደማ ሰዎችን አነጋግረን በጥያቄ አፋጥጠን ብዙ መረጃ ተቀብለናል ብለዋል።
ከቤተሰብ ጀምሮ፣ ወዳጅ ዘመድ፣ የሰፈርና የትምህርት ቤት እኩዮች፣ አስተማሪዎችና አሠልጣኞች ሁሉ ተጠይቀዋል። ቶማስ ክሩክስ የኢላማ ተኩስ ክለብ አባል ነው። በየጊዜውም ለተኩስ ልምምድ ይመላለስ ነበር ተብሏል። እንዲያውም፣ ትራምፕን ለመግደል ከመሞከሩ በፊት በዚያው ሳምንት ለልምምድ ብቅ ብሎ ነበር።
ኤፍቢአይ… እልፍ ሰዎችን በማነጋገር ብዙ መረጃዎችን ሰብስቧል። የግድያ ሙከራ በተፈጸመበት ዕለትና ቦታ በአካል የነበሩ የዐይን ምስክሮችም ብዙ ናቸው። ከተለያዩ ሰዎች የተቀረጹ ቪዲዮዎችንም ሰብስቦ ማየት ያስፈልጋል፡…
አንዳንድ ሰዎች የጥቂት ሴኮንድ፣ አንዳንዶቹ የጥቂት ደቂቃ ቪዲዮዎችን ቀርጸዋል። የሁሉም ሲደመር ግን የብዙ መቶ ሰዓታት ነው። ከ10 ቀን በላይ ቁጭ ተብሎ ቀን ተሌት ካልታየ አያልቅም። አንድ ቪዲዮ አልቀረኝም ባይ ነው ኤፍቢአይ።
በዐጭሩ፣ “ምርመራዬ ላይ እየበረታሁ ነው” የሚል ነው የመግለጫው መልእክት። ነገር ግን፣ ይሄ ሁሉ በአብዛኛው አዲስ ግኝት አይደለም። አዲስ መረጃ ተጨምሮበትም ግን፣ ምርመራው ወደ ፍጻሜው ፎቀቅ አላለም።
ትልልቆቹን ጥያቄዎች የሚመልስ አልሆነም።
“ቶማስ ክሩክስ ምን አስቦ ወይም በምን ተለክፎ ነው ትራምፕን ለመግደል የተነሣሣውና የሞከረው?” ለሚለው ጥያቄ ገና መልስ አልተገኘለትም። የወንጀሉ ክብደትና የክሱ ዐይነት ከዚህ ጥያቄ ጋር የተቆራኘ ነው። ከአእምሮ ሕመም ጋር የተያያዘ ወንጀል አይደለም። በግልፍታና በጊዜያዊ ስሜት የተፈጸመ ወንጀል አይደለም። ለበርካታ ቀናት ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ወራት ሲያስብበትና ሲዘጋጅበት የነበረ ጉዳይ ነው። ከባድ ነው።   
ግን ደግሞ በግል የተፈጸመ ወንጀል ይመስላል ተብሏል። እስካሁን በተካሄደው ምርመራ፣ ቶማስ ክሩክስ አባሪ ተባባሪ እንዳልነበረው የሚያሳይ ነው። የሀገር ውስጥ ወይም የውጭ ሀገር ድርጅቶች ሤራ እንደሌለበት ምርመራው ያሳያል ብሏል - ኤፍቢአይ።
እና ምንድነው የወንጀሉ ሰበብ? ገና ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።
ሌላ ትልቅ ጥያቄም አለ።
“አንድ ወጣት፣… ያለ ተጨማሪ እገዛ፣ አባሪ ተባባሪ ሳይኖረው፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የዘንድሮ ዋና የምርጫ ተፎካካሪ ላይ የግድያ ሙከራ ለመፈጸም የቻለው እንዴት ነው? ዝነኞቹ “የሲክሬት ሰርቪስ” የጥበቃ ባለሙያዎች ምን ሆነዋል? ይሄም ገና የተሟላ መልስ አላገኘም።
በዐጭሩ፣ የኤፍቢአይ ምርመራ ብዙም እየተራመደ አይደለም - ምርመራው ላይ እየበረታ ቢሆንም። ለማሾፍ አይደለም። ያጋጥማል። እየበረታ ቢሆን እንኳ፣ ብርታት ሁልጊዜ ቶሎ ይሳካል ማለት አይደለም።
እንደ መጽናኛ፣ ኤፍቢአይ “አንድ ሁለት አዲስ መረጃዎችን” በይፋ አቅርቧል። ቶማስ ክሩክስ ለግድያ የታጠቀው ጠመንጃ በፎቶ ተነስቶ ታይቷል። በእርግጥ ጠመንጃው ምን ዐይነት እንደሆነ ካሁን በፊትም ይታወቃል - በፎቶ መታየቱ ነው አዲሱ ነገር።
ጠመንጃው “ዲፒኤምኤስ” በተሰኘ ኩባንያ የተመረተ ነው። ልዩ ዐይነት መሣሪያ አይደለም። እንዲያውም በአሜሪካ እጅግ እየተለመደ የመጣ የጠመንጃ ዐይነት ነው - ኤአር-15 የሚሉት።
Gun Digest shooter’s Guide to AR-15 የተሠኘ መጽሐፍ ላይ በምዕራፍ 19 እንደተገለጸው፣ “ዲፒኤምኤስ” የሚያመርታቸው ኤአር ጠመንጃዎች በጥራት ደረጃቸው “ጥሩ” የሚባሉ ናቸው። ዝቅተኛው ዋጋ 720 ዶላር ነው። ከ2000 ዶላር በላይ የሚያወጡም አሉ ይላል Gun Digest።
ኤአር15 - ተወዳጁ ጠመንጃ
አልሞ ተኳሾቸ፣ ኤአር15 ጠመንጃዎችን አይመርጡም ይባላል። ለምን? ከሌሎች ጠመንጃዎች ጋር ሲነጻጸር፣ የኤአር ጥይቶች ደቀቅ ያሉ ናቸው። በዚያ ላይ ጠመንጃው ለረዥም ርቀት አይሆንም። ረዥም ርቀት ማለት፣… ለምሳሌ ከ1000 ሜትር ርቀት መተኮስና መምታት አይችልም።
ከ300 እስከ 600 ሜትር ርቀት ድረስ ግን፣ ኢላማ ለመምታት ግን ብዙም አያስቸግርም። የሚናቅ አይደለም።
በዚያ ላይ የጠመንጃው ክብደት ቀለል ያለ ነው። በፍጥነት አከታትሎ ለመተኮስ ስለሚመችም ብዙዎች ይመርጡታል።
እናም፣ ኤአር15 በአገረ አሜሪካ ሲቪሎች በብዛት የሚሸምቱት ጠመንጃ ለመሆን በቅቷል። ከሠላሳ ዓመታት በፊት በአሜሪካውያን እጅ ውስጥ የነበሩ ኤአር ጠመንጃዎች 400ሺ እንደነበሩ ያስታውሳል የዎል ስትርት ጆርናል ዘገባ። ዛሬ የኤአር ጠመንጃዎች ቁጥር ከ20 ሚሊየን እንደሚበልጥ ዘገባው ይገልጻል።
ለወትሮ በአሜሪካ የተፈበረኩ ጠመንጃዎች ከረዥም ርቀት በትክክል አነጣጥሮ ኢላማ ለመምታት ታስበው የሚዘጋጁ ናቸው።
ኤአር ጠመንጃዎች ግን ዲዛይናቸው እንደ ክላሺንኮቭ ነው። ለአጭር ርቀት በእሩምታ ለመተኮስ እንዲያገለግሉ በማሰብ ነው የመጀመሪያ ዲዛይናቸው የዛሬ 70 ዓመት ገደማ የተነደፈው።
እንደወዳጆቹ ብዛት ጠላቶቹም ብዙ ናቸው
ለእግረኛ ጦር ጥሩ የወታደሮች ትጥቅ ሊሆን እንደሚችል ብትገምቱ አልተሳሳታችሁም። ለአጭር ርቀት ኢላማና ለእሩምታ ተኩስ… ሌላ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል። የወታደሮች የውጊያ መሣሪያ ነው። ለዚያውም የአሜሪካ ወታደሮች ትጥቅ። ኤም16 በሚል ስያሜው ይታወቃል።
ነገር ግን… ስለ አሜሪካ አይደል የምናወራው? ብዙም ሳይቆይ ጠመንጃው እንደማንኛውም ምርት ለአሜሪካዊያን በሽያጭ እንዲቀርብ፣ “ማስተካከያ” ታክሎበት ወደ ገበያ ተቀላቅሏል።
ወታደሮች የሚታጠቁት ኤአር በእሩምታ መተኮስ ይችላል። ለሲቪሎች የተፈበረከው ኤአር ግን በእሩምታ መተኮስ አይችልም። በርካታ ጥይቶችን የሚጎርስ ካዝና አለው። ግን አከታትለው መተኮስ የሚችሉት፣ የጠመንጃውን ቃታ አከታትለው እየተጫኑ ነው። አንዴ ቃታውን ተጭነው በመያዝ በእሩምታ መተኮስ አይችሉም። “ኦቶማቲክ” አይደለም። “ሰሚ-ኦቶማቲክ” ይሉታል አንዳንዶቹ።
አንዴ ተኩሰው እንደገና ጥይት ማጉረስና ማቀባበል አያስፈልገውም። ቃታውን አከታትለው እየተጫኑ መተኮስ ብቻ! እንደጣትዎ ፍጥነት ነው የተኩሱ ፍጥነት።
ይህን በመሳሰሉ ምክንያቶች ኤር15 በአሜሪካውያን ዘንድ ተመራጭ ጠመንጃ ሆኗል። እንዲያውም፣ የግለሰብ ነጻነት ምልክት እስከመሆን ደርሷል። ጠመንጃ የመታጠቅ መብት (the right to bear arms) በአሜሪካ ሕገመንግሥት ውስጥ፣ ከሐሳብ ነጻነት ቀጥሎ የሚጠቀስ ትልቅ ቦታ የተሰጠው ቁም ነገር ነው። የሐሳብ ነጻነት ላይ ያተኮረው የሕገመንግሥት አንቀጽ first ammendmet ይሉታል። ቀጥሎ የተጻፈው አንቀጽ፣ ጠመንጃ የመታጠቅ መብት ነው። second ammendment እያሉ ይጠሩታል።
ኤአር15 የዚህም መብት ዋነኛ ምልክት ሆኗል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በገበያ ስፍራዎች፣ በመዝናኛ ቦታዎችና ሰዎች በሚበዙበት አካባቢ በጭፍን በጅምላ መግደል ለሚፈልጉ ወንጀለኞች፣  ኤአር15 በጣም አመቺ ጠመንጃ ሆኖላቸዋል። የትጥቅ ቁጥጥርና ክልከላ መጠናከር አለበት ብለው የሚሟገቱ ፖለቲከኞች፣ ኤአር ጠመንጃዎችን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
በዐጭሩ፣ ኤአር15 ብዙ ወዳጆችና ጠላቶች ያሉት ጠመንጃ ነው።
በተለያየ ሞዴል፣ ከተዛማጅ ቁሳቁስ ጋር በተለያየ የጥራት ደረጃ የተፈበረኩ ጠመንጃዎች፣ በየከተማው በገበያ መደብሮች ለሽያጭ ይቀርባሉ።
ዋጋቸው፣ እንደየ ሞዴላቸው ይለያያል። የተገጠሙላቸው ተዛማጅ ቁሳቁሶችም በተለይ የማነጣጠሪያ መነጽር የጥራት ደረጃ በጠመንጃዎቹ ዋጋ ላይ ትልቅ ልዩነት ያመጣል።
በ100 ዶላር ወደ ኦቶማቲክ
ኤአር15 ከመነሻ ዲዛይናቸው ለእሩምታ ተኩስ የታሰቡ ቢሆንም፣ ኦቶማቲክ ጠመንጃዎችን ለወታደሮች ትጥቅ ካልሆነ በቀር ለሲቪሎች መሸጥ ክልክል ነው። እናም፣ ከፋብሪካ ሲወጡና ለገበያ ሲቀርቡ “ኦቶማቲክ ጠመንጃ” አይደሉም። ነገር ግን “ሞደፊክ” ይገጠምላቸዋል።
“የእሩምታ ሞደፊክ” መስራትና መሸጥ የተከለከለ ቢሆንም በሕገወጥ መንገድ መግዛት ይቻላል - በ50 ዶላር፣ ቢበዛ በ100 ዶላር።
አሁን ደግሞ፣ ቤት ውስጥ በቀላሉ ማምረት ይቻላል። እንደ ወረቀት ሕትመት ነው። ቁሳቁሶችን ማተም የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች (3ዲ ፕሪንተሮች) እንደ ልብ ገበያ ላይ ይገኛሉ። ሁለት ማተሚያዎችን በመጠቀም ሞደፊክ እየሰራ ሲሸጥ የነበረ ወጣት፣ በቀን ለ400 ጠመንጃዎች የእሩምታ ሞደፊክ መስራት እንደሚችል ተናግሯል። በ60 ዶላር ነው የሚሸጣቸው።
በፋብሪካ ሳይሆን በቤት ውስጥ በማተሚያ ማሽን የተሰሩ ሞደፊኮችን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል? ለነገሩ፣ ሙሉ ሽጉጥና ጠመንጃ “የሚያትሙ” አሉ።
አገሬው የጠመንጃ አገር ነው። የቶማስ ክሩክስ አባት እንኳ የ13 ጠመንጃዎች ባለቤት እንደሆነ ተዘግቧል። አንዱን ጠመንጃ ለልጁ ሰጥቶታል - በሕጋዊ መንገድ ማለት ነው። ብዙ አሜሪካዊያን በቤታቸው ከአንድ ጠመንጃ በላይ አላቸው። ምናለፋችሁ ከ400 ሚሊዮን ጠመንጃ በሲቪሎች እጅ የተያዘበት አገር ነው።
ከእነዚህ ውስጥ ገሚሶቹ ሽጉጦች ገሚሶቹ የአንጋች ጠመንጃዎች ናቸው። ከጠመንጃዎች መካከልም 20 ሚሊዮን ያህሉ ኤአር15 ናቸው - ባለ 30 ጥይት ካርታ የሚጎርሱ ጭምር።
በዚህ ሁሉ መሃል አሜሪካውያን በየመንገዱ አለመጨራረሳቸው ይገርማል። ከነጻነትና ከኀላፊነት፣ ከስልጣኔና ከሕግ አክባሪነት ባህል ጋር አብሮ መሄድ ያለበት ነገር ሳይሆን አይቀርም። ካልሆነ ግን ራስን ከጥቃት ለመጠበቅ ሳይሆን ለመጨራረስ እንደሚውል በብዙ አገሮች አይተነዋል።



Read 283 times