የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ፣ የሁለቱ ሀገራት የውስጥ ጉዳያቸው ብቻ ሳይሆን፣ የበዛ የውጪ ሀገራት ተፅእኖ ያለበት ነው፡፡ አረቦች ኢትዮጵያን ለማዳከም ሲሉ፣ የኤርትራ አማፅያንን በገንዘብ፤ በወታደራዊ ስልጠና እና በጦር መሳሪያ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መሃል (ከመገንጠሉ በፊትም ሆነ በኋላ) ፀንቶ የዘለቀው ችግር መሰረቱ ከውስጥ ቢሆንም፣ የችግሩ ራስ ግን በአብዛኛው ከውጪ ነው፡፡ ራቅ ያለውን ታሪክ ስንፈትሽ ቱርኮች፤ ግብፆችና ሱዳኖች ፤ ቀረብ ያለውን ታሪካችንን ስንከልስ ጣልያን፤ እንግሊዝና ፈረንሳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በቀይ ባህር ላይ ተፅእኗቸውን ለማሳረፍ ብሎም በቀጠናው ላይ በብቸኝነት ጎልቶ ለመውጣት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አሁን ኤርትራ ተብሎ በነፃና ሉኣላዊ መንግስትነቱ የሚታወቀው ሀገር፣ የኢትዮጵያ የግዛት አካል ሆኖ የኖረ ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ለተከሰተው የ50 አመት የጣልያን ቀኝ ግዛትና የ10 አመት የእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳዳር ካልሆነ በቀር፣ የኤርትራ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጣም የተሳሰረና ያልተቋረጠ የሀይማኖት፤ የባህልና የቋንቋ ትሰስር ነበረው፤ አለው፡፡ ማስረጃችን ባህል፣ ታሪክና ህግ ነው፡፡
የኤርትራ ክፍል በተፈጥሮ በታደለው አቀማመጥና ስትራቴጂያዊ ሁኔታ፣ የምእራቡም ሆነ የአረቡ አለም አይኑን ያሳረፈበት ነበር፡፡ አረቦች ይህን የኢትዮጵያ ክፍል በመቆጣጠር ቀይ ባህርን “የአረብ ባህር” ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሳይገቱ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት በሆነችው በግብፅ አጋፋሪነት፣ የኤርትራን ግዛት በአረብ አገራት ካርታ ውስጥ በማካተት ኤርትራ “የአረብ አገር” ናት ሲሉም አወጁ፡፡ ለምእራቡ አለም ይህ የኢትዮጵያ ሰሜን ክፍል የነበረው ግዛት ወደ አፍሪካ የመግቢያ በር በመሆኑ ሃያላኑ ሀገራት አብዝተው ተመላልሰውበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቀይ ባህር ላይ የጦር መሰረት በመጣል የበላይነትን ማስመስከሪያ ሜዳቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የጥንት ነገስታት ከተቀረው አለም ጋር ሲያደርጉት የነበረው የንግድና የፖለቲካ ግንኙነት ሲያልፍ የነበረውም በዚህ በኩል ነው፤ ወደ ኢትዮጵያም የሚገባው በዚህ በኩል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በባእዳን ጥቃት ሲደርስባት የነበረው በዚህ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በኩል ነበር፡፡ የመከላከል ውጊያም የተደረገው በዚህ አካባቢ ነው፡፡ ብዙ ደምና አጥንት ተገብሮበታል፡፡
አፄ ዮሐሃንስ በ1881 ዓ.ም መተማ ላይ ሲሞቱ፣ ጣልያኖች በቀይ ባህርና በመረብ ምላሽ የነበራቸውን ይዞታ ይበልጥ አስፋፍተው ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት አሳጧት፡፡ ይህን መደላድል ከመያዛቸው በፊት ጣልያኖች ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ባደረጉት ስምምነት፣ ምፅዋን ከመተማ ጦርነት በፊት፣ አሰብን ከሦስት አመታት በኋላ በእጃቸው አስገቡ፡፡ አሰብ ላይ መሰረቱን አድርጎ የጣልያን መንግስት፣ የባህረነጋሽ ግዛቱን ኤርትራ የሚል የመታወቂያ ስም ሰጥቶ የቅኝ ግዛቱ አካል አደረገው፡፡ ጣልያን በያዘው የኢትዮጵያ የሰሜኑ ግዛት ይዞታ ሳይገታ ወደ ውስጥ ለመዝለቅ እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ ይህን መስፋፋቱን ዶጋሊ ላይ በ1879 ዓ.ም አሉላ አባነጋ ድል በማድረግ፣ ለጊዜውም ቢሆን የጣልያንን ግስጋሴ ገታው፡፡
አሉላ ዘመኑን በሙሉ ከጣልያን ጋር ሲዋጋ የነበረው፣ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ባህር በር የነበረውን ምጽዋን በጠላት እጅ እንዳይወድቅ ለማድረግ ነበር፡፡ እንግሊዞች ምፅዋን ለጣልያኖች እንዲያስተላልፍ ሲጠይቁት የሰጣቸው ምላሽ፣ የህይወት ዘመን እምነቱን ይመሰክርለታል፡፡ ለእንግሊዝ መልእክተኛ በላከው ደብዳቤ፤ “እኔ የሮም ገዢ ስሆን ብቻ ጣልያን ሰሃቲን ያስተዳድራል” ብሏል፡፡ አፄ ዮሐንስም ቢሆን ለእንግሊዝ ንግስት በላከው ደብዳቤ፤ “ምፅዋ የኢትዮጵያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የግዛት አካል የሆነውን ክፍል የመነጠል ፍላጎቱም ሆነ ስልጣኑ የለኝም” ሲል በግዛት አንድነት ላይ ቀናኢ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ እኒህ ሁለት በኢትዮጵያ ታሪክ ገናና የሆኑ ሰዎች፣ ለግዛት አንድነት ሲታገሉ፣ የልጅ ልጆቻቸው የሆኑት የአካባቢው ተወላጆች፣ በፈጠራ ታሪክ “አሰብም፤ ምፅዋም፤ ኤርትራም በሙሉ የኢትዮጵያ ሆኖ አያውቅም፤ ፈጠራ ነው” ሲሉ ተዘባበቱበት፡፡
“ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ተገዢ ነች” የሚለውን አቋም፣ ከኤርትራውያን በላይ የህውሓት ሰዎች አቀነቀኑት፡፡ የዚህ የፈጠራ ታሪክ ደራሲው ኢሳያስ፣ አርታኢው መለስ ዜናዊ ነው፡፡ መለስ፤ “የኤርትራ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት” በተሰኘ ፅሁፉ፤ “ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ነበረች ወይም ነች የሚለው የታሪክ መሰረት የለውም፤ ተረት ነው፡፡” ብሏል፡፡ የህውሓት ካድሬም በዚህ አስተምህሮ የተጠመቀና የቆረበ ነው፡፡
የኤርትራን የመገንጠል ጥያቄ አግባብ ነው እንዲያሰኝ የተጠቀሰው ሰነድ የውጫሌ ውል ነው፡፡ የውጫሌ ውል አፄ ዮሐንስ ከሞቱ ሁለት ወራት በኋላ የተፈረመ ውል ነው፡፡ ውሉ በአፄ ምኒልክ እና በጣልያን መሃከል የተፈረመ ነው፡፡ እንደ ደራሲዎቹ (ኢሳያስ እና መለስ) ከሆነ፤ የኤርትራ ህዝብ በዚህ ውል ለጣልያን ተሸጧል፡፡ ይህ ድርሰት የውሸት ፈጠራ እንጂ እውነትነት የለውም፡፡ የታሪክ ምስክር የለውም፡፡ በህውሓት እና በመሰሎቹ የሚቀነቀነው ታሪክን የማፋለስና ጥላሸት የመቀባቱ አካሄድ፣ ችግርን እንጂ የመፍቻ ቁልፍ ሲያቀብል አላየንም፡፡ ታሪክ አይካድም፤ አይፋቅም፡፡ ታሪክ በቢሆን አይፃፍም፡፡ ታሪክን እንደ ዘመኑ ሁኔታና እንደ ቅደምተከተሉ መቀበል ይገባል፡፡ ካልሆነ አጉል አወዳደቅ ላይ ይጥላል፡፡ ልክ እንደ ሻእቢያ እና ህወሓት፡፡ ይህ የተሳሳት የታሪክ ትርክት የሻእቢያ ፈጠራ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱን የውሸት እውነት ነው፣ የክፋት ትረካ የምለው፡፡ እንዲህ አይነት በታሪክ ላይ የሚደረግ ክፋት ፍሬው መከራ ነው፡፡ በዚህ የክፋት ትረካ የሰሜኑ ክፍል መከራን እያጨደ ነው፡፡ ህወሓት ጥብቅና የቆመለት የኤርትራ መንግስት ርህራሄን አላደረገለትም፡፡ መከራ የአርባ ቀን እድልህ ነው የተባለ ይመስል፣ የትግራይና የኤርትራ ህዝብ የዚህ ሰለባ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ታሪክ በአፈታሪክና በፈጠራ አይፀናም፤ መከራን የሚጠራው ይህን የመሰለ የተዛባ የታሪክ ፈጠራ ነው፡፡
ለአድዋ ጦርነት ሰበብ የነበረው የውጫሌ ውል፣ ጣልያን አድዋ ላይ ድል ስትደረግ ተሰረዘ፡፡ የአድዋን ድል ተከትሎ በምኒልክ እና በጣልያን መካከል አዲስ ስምምነት ተፈረመ፡፡ ይህ ስምምነት የወደፊቱን የኤርትራ እጣ ፈንታ የሚወስነውን አንቀፅ በውስጡ ያካተተ ነው፡፡ በዚህ አንቀፅ መሰረት ጣልያን በማንኛውም ሁኔታ በኤርትራ ላይ ያላትን የማስተዳደር ስልጣን የምታጣ ከሆነ፣ የያዘችውን ግዛት ለማንም ሳይሆን ለኢትዮጵያ አሳልፋ እንደምትሰጥ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ይህ ስምምነት የቀደመውን የውጫሌ ውል ስህተት በማረም የወደፊቱን የኤርትራ ህልውና መልስ የሰጠ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ተከታትሎ የሚያስፈፅመው ባለመኖሩ ነው እንጂ፣ ይህ አንቀፅ ጠባቂና ጠበቃ ቢኖረው ኖሮ፣ የቅኝ ግዛት ጥያቄን እስከ ወዲያኛው በቀበረው ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ለሌላ ዙር ችግር መወለድ ሰበብ ሆነ፡፡ በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ይህ አንቀፅ እንዲጠቀስ አይፈልግም ነበር፡፡ አንቀፁ ቢጠቀስ የህውሓት/ኢህአዴግ፤ “ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ተገዢ ነች” የሚለውን አቋሙን እርቃኑን ያቆምበት ነበር፡፡ የአልጀርስ ስምምነትም ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ እንደ ህወሓት የታሪክ ፈጠራ ከሆነ፤ የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ታሪክ የ100 አመት ነው፡፡ ውልደታቸውም በተመሳሳይ ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምኒልክ ስትፈጠር፣ ኤርትራ በጣልያን ተፈጠረች፡፡ የዚህ መርዘኛ የሆነ የታሪክ ፈጠራ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት፣ ኤርትራ ወደቦችዋን ጨምራ የጣልያን ቅኝ ነች የሚለውን ትረካ ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት ነበር፡፡ በመለስ፤ “የኤርትራ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት” በሚለው ፅሁፍ ውስጥ፤ “ኤርትራ በቅኝ ግዛት የተያዘች ናትና ነፃ መውጣት ይገባታል” ይላል፡፡ ከኤርትራውያን በላይ ኤርትራ ነፃ መሆን ይገባታል ብሎ የተከራከረ መለስ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በገብሩ አስራት መፅሐፍ (ሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ) ውስጥ የሰፈረውን እማኝ ልጥቀስ፡፡ ኤርትራዊው ፕሮፌሰር ተስፋፅዮን መድሃኔ ለፃፈው “የኤርትራ ጠመንጃ አፈሙዝ ቁልቁል ይዘቅዘቅ” ለሚለው አንድነትን አወዳሽ ፅሁፍ፣ መለስ እንደ መልስ ምት የፃፈው፣ “የኤርትራ ጠመንጃ አፈሙዝ ቁልቁል አይዘቅዘቅ” የሚለው ፀረ-አንድነት አቋሙ ምስክር ነው፡፡ ኤርትራዊው ፕሮፌሰር አንድነትን ሲያቀነቅን፣ መለስ ኮነነው፤ ነቀፈው፡፡ ለኤርትራ አንድነት ሳይሆን መገንጠል ነው የሚበጃት አለ፡፡ መገንጠል አይበጀንም ያለን ኤርትራዊ ፕሮፌሰር፣ መገንጠል ነው የሚበጃችሁ ያለው መለስ ነው እንግዲህ፡፡ እንደ መለስ የታሪክ ፈጠራ፣. ኤርትራ ቅኝ ተገዢ ስለነበረች፣ ነፃነት ይገባት ነበርና ነፃም ሆነች፡፡
በኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥም ሆነ ነፍጥ አንግበው ሲታገሉ በነበሩ ቡድኖች ዘንድ የኤርትራ ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡ አንዳንዶች የኤርትራ ጥያቄ የብሄር ጥያቄ ነውና ከሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲደረጉ ከነበሩት የብሄር መብት ጥያቄዎች ተነጥሎ አይታይም ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው የሚል ነበር፡፡ ኢህአፓ ህወሓት እና ኦነግ የዚህ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ሃሳብ አጋፋሪዎች ነበሩ፡፡ በታሪክ ቅደም ተከተል ኢህአፓ እና ህወሓት ቀዳሚዎቹ አቀንቃኞች ሲሆኑ፤ ኦነግ ለአሻንጉሊትነት ባስፈለገበት ጊዜ ይህን የታሪክ አተላ እንዲሸከም ተደረገ፡፡ ሻእቢያ ለሚያራምደው የቕኝ ግዛት ጥያቄ ማስፈፀሚያ እንዲሆኑ የመረጣቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ህብረብሄር እና ብሄር ተኮር ድርጅቶችን ነው፡፡ ለዚህ በቂ ምክንያት ነበረው፡፡ ለምሳሌ ህብረብሄራዊው ኢህአፓ በመሃል ከተማ ትርምስ በመፍጠር ማእከላዊ መንግስቱን ጠምዶ እንዲይዝለት፤ ህውሓት ደግሞ በሰሜኑ ግንባር ጋሻ ሆኖ ማእከላዊ መንግስቱን እንዲመክትለት ነበር፡፡ ኦነግ እስከ 1983 የሰላም ኮንፈረንስ አላስፈለገም ነበር፡፡ ኢህአፓ ህውሓት እና ኦነግ በቅኝ ግዛት ትረካ ውስጥ ምንም ሳይሆኑ የሻእቢያ የመጫወቻ ካርዶች ነበሩ፡፡ ኢህአፓ የሻእቢያን እርዳታ ለማግኘት ሲል ብቻ እጁን ተጠምዝዞ፣ የኤርትራ ትግል የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው የሚለውን ተገዶ ተቀበለ፡፡ ኢህአፓ ይህን አቋም በይፋ ለሻእቢያ እስኪያሳውቅ ድረስ በኤርትራ በርሀ ለ1 አመት በቁም እስር መልክ ቆየ፡፡ ምስክራችን የዚህ የቁም እስር ሰለባ የነበረው ተስፋዬ መኮንን ነው፡፡ መፅሐፉም (ይድረስ ለባለታሪኩ)፤ የሻእቢያን መልክ፣ አላማና የታሪክ አጥፊነት ተልእኮ ያሳያል፡፡ ህወሓትም እንደዛው በሻእቢያ የቅኝ ግዛት አስተምህሮ የተጠመቀ ሎሌ ደቀመዝሙር ነው፡፡ ይህን ከተቀበሉ በኋላ ሁለቱ ድርጅቶች ሊንቀሳቀሱ የቻሉት የኢትዮጵያ አካል በሆነው ከመረብ በስተደቡብ እንጂ በኤርትራ ክፍል አልነበረም፡፡ ኤርትራ የውጭ ሃገር መሆኗ ነው፡፡ በዚህ መልክ ኢህአፓን የመሰለ ተራማጅ ፓርቲ፣ የሻእቢያ ባርያ ሆነ፡፡
የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ከሆነ፣ ኤርትራ የማን ቅኝ ነበረች? ከማንስ ነው ነፃ የምትወጣው? የሚለውን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ቢሆን ኖሮ፣ እንደ ማንኛውም በቅኝ ግዛት ስር እንደነበረ ህዝብ ነፃነቱን ይቀዳጅ ነበር፡፡ በኤርትራ ሁኔታ ግን ይህ አልሆነም፡፡ ምክንያቱም ኤርትራ የሚባለው ክፍል ከቅኝ ግዛቱ በፊት ራሱን ችሎ ቆሞ የነበረ ስላልሆነ ነው፡፡ በዚህ ስም የሚታወቅ ህዝብ፤ ቦታ ወይም ባህል አልነበረም፡፡ የጣልያን ቅኝ አገዛዝ ማብቃትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለተመድ ያስገባችውን የይገባኛል ጥያቄ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ተመድ በውሳኔ ቁጥር 390፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትዋሀድ ወሰነ፡፡ በጣልያን ወረራ ምክንያት ከግዛቷና ከተፈጥሮ የባህር በሯ ጋር ተቆራርጣ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ በ1950 የተመድ ውሳኔ መልሳ ማግኘት ችላ ነበር፡፡ በዚህ ምላሽ ለጊዜውም ቢሆን እፎይ አለች፡፡ ይህ ውሳኔ ህጋዊና የቅኝ ግዛት ጥያቄን እስከ ወዲያኛው ያስወገደ ነው፡፡ ኤርትራውያንም ይህ እንዲመጣ ብዙ ታግለዋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በህግ ያገኘችውን ግዛት፣ ከውስጧ በወጣው ህወሓት/ኢህአዴግ አጣችው፡፡ ከቅድመ ፌደሬሽን በፊትም ሆነ በኋላ በምንም አይነት ሁኔታ ኤርትራ የሚባለው ክፍል በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ስር ነበር የሚለውን ሀሳብ የሚያረጋግጡ የህግም ሆነ የታሪክ ሰነዶች ማቅረብ አልተቻለም፡፡ ይህ የፌደሬሽን ውሳኔ በአብዛኛው የኤርትራ ህዝብና የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ አልነበረውም፡፡ የፌደሬሽኑ ውሳኔ በደንብ ሲነበብ፣ ፌደሬሽን በራሱ የመጨረሻ ግብ አልነበረም፡፡ አላማው ውህደት ነበር፡፡ እዚህ ጋ ማንሳት የሚገባን፣ ፌደሬሽኑን በማፍረስ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በማዋሀዱ ሂደት፣ የኤርትራውያን ሚና የጎላ መሆኑን ነው፡፡ ብዙ ጠመዝማዛ የሃሳብ ፍጭቶችን አልፎ የኤርትራ ፓርላማ ፌደሬሽኑን አፍርሶ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር አዋሃደ፡፡
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጣልያን ድል በመደረጓ፣ በሰሜን አፍሪካና በምስራቅ አፍሪካ የነበራትን ግዛቶች እንድታስረክብ ተደርጎ ነበር፡፡ ጣልያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፍሪካ የነበሯትን ግዛቶች ለሃያላኑ አስረከበች፡፡ ይህን ተከትሎ ኤርትራ ለ10 አመታት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ድላ አድራጊ በነበረችው እንግሊዝ ስር ወደቀች፡፡ የሁለተኛውን የአለም ጦርነት ማብቃት ተከትሎ፣ የአራቱ ሃያላን ኮሚሽን፣ በኤርትራ ባደረገው የህዝብ ምክክር፣ ግማሽ የሚሆነው የኤርትራ ክፍል ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር መዋሀድን ሲደግፍ፣ የተቀረው ዳግም በባርነት ስር መኖር እንደማይፈልጉና ነፃነትን እንደሚሹ አስገንዝበዋል፡፡ የህዝቡ ውሳኔ ይህ ቢሆንም አራቱ ሃያላን የራሳቸውን የግል ፍላጎት ስላስቀደሙ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ ባልተቻለ ጊዜ አሜሪካና እንግሊዝ የነበራቸው አቋም ምእራባዊው ክፍልና አብዛኛው ሙስሊም የሆነው የኤርትራ ግዛት ወደ ሱዳን እንዲጠቃለል፤ የቀረው ክርስቲያኑ ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲካለል የሚል ነበር፡፡
ማሳረጊያ
ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ.ም፣ የሽግግር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዶ ነበር፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ህወሓት/ኢህአዴግ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂም በታዛቢነት ተገኝቶ ነበር፡፡ ይህ ጉባኤ እውቅና ሳይኖረው የኢትዮጵያንና የኤርትራን የወደፊት እጣ-ፋንታ የወሰነ ነበር፡፡ የጉባኤውን ህገወጥነትና ኢህአዴግም በኢትዮጵያ እጣ-ፋንታ ላይ የመወሰን ስልጣን የለውም ብለው ብቻቸውን ሲሟገቱ የነበሩት ፕሮፌሰር አስራት ብቻ ነበሩ፡፡ ሌላው እጅ ለማውጣትና ለማጨብጨብ ብቻ የተሰበሰበ ነበር፡፡ በዚህ ጉባኤ ውሳኔ መሰረት በኤርትራ ከሁለት አመት በኋላ በተመድ ታዛቢነት ህዝበ-ውሳኔ ይካሄዳል፡፡ የህዝበ ውሳኔው አስፈላጊነት ለኤርትራ ህዝብ የሚቀርበውን ነፃነት ወይስ አንድነት የሚለውን ለመወሰን ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ኢትዮጵያ እንዳትድን ሆና የቆሰለችው በዚህ ጉባኤ ውሳኔ ነው፡፡ ህወሓት/ኢህኣዴግ ከሁሉ ቀድሞ የኤርትራን ነፃ ሀገርነት እውቅና ሰጠ፡፡ የኤርትራ ነፃ ሀገር ሆና መውጣት ኢትዮጵያ ላይ ከባድ ጉዳት አሳድሯል፡፡ የጠላት ኢትዮጵያን ከባህር በር የመነጠል እኩይ አላማ፣ በህወሓት/ኢህአዴግ ፍፃሜውን አገኘ፡፡ ህወሓት ባለማወቅ ወይም በውስጡ ይዞት የነበረው እኩይ አላማ እዚህ ይቅር የማይባል ስህተት ላይ ጣለው፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ መንግስታት ካለፈ ታሪክ ጋር ያላቸውን ፀብ በሚገባ ታዝቦታል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያጋጠመውን ሲያጫውተን እንዲህ ይለናል፤ “አብዮታዊ መንግስታት መጀመሪያ ታሪክን እንዴት እንደሚጠሉና የኋላ ኋላ ግን እንዴት እሱኑ የሙጥኝ እንደሚሉ ነው፡፡ ደርግ እንደመጣ አንዳንድ ባለስልጣኖች የታሪክ ሰነዶችን እስከማቃጠል ሁሉ ተጋብዘዋል፡፡ የአብዮቱ አስረኛ አመት ሲከበር ብሎም ከሻእቢያ ጋር ትንቅንቁ ሲግም ታሪክ መድህናቸው ሆኖ ታያቸው፡፡ በዘመነ ኢህአዴግም የሆነው ይህ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ታሪክ አለርጂክ የሆነ ስርአት ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ በባድመ ጊዜ ግን የታሪክ ባለሙያዎችን ድጋፍ ፈለገ” ይለናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግማሽ ኤርትራዊ የሆነው በረከት ስምኦን የኢትዮጵያን ታሪክ ሊያስተምረን በመድረክ ተቀመጠ ይለናል፡፡ በረከት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መድረክ መቀመጡ ሳያሳፍረው፣ “ኢትዮጵያና ኤርትራ ጎረቤታም ሀገሮች እንጂ አንድ አገር ስላልሆኑ እርማችሁን አውጡ” አለን ሲሉ ቁጭታቸውን የህይወት ታሪካቸውን በከተቡበት መፅሐፋቸው (ህብር ህይወቴ፡-ግለ ታሪክ) ላይ አስፍረውታል፡፡ ሁለቱ ሀገሮች አሁን ብቻ ሳይሆን ቀድሞም በታሪክ ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም በማለት፣ የሰለቸንን የሻእቢያ የተፋለሰ የታሪክ ትንታኔ አነበነበልን ሲሉ ያክላሉ፡፡ የሚገርመው በረከትን አጅቦ በመድረኩ ላይ ተቀምጦ የነበረው አንዳርጋቸው ፅጌ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ጭቃ ሲለጠፍ አንዳርጋቸው ጭቃ አቀባይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ፍፁም ፀረ- ኢትዮጵያ አቋም ሲያራምዱ በነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ስር ማለፏ ያሳዝናል፡፡ ከውስጥ የወጓትም እነሱ ናቸው፡፡ የጡት ነካሽ ይላል፤ የሃገራችን ሰው፡፡
መውጫ
በኢትዮጵያ በኩል የኤርትራን ነፃነት ለማወጅና ከባድመ ጦርነት በኋላ ለመጣው የአልጀርስ ስምምነት አስረጅ ሆነው የቀረቡት የ1900ዎቹ ሙት ውሎች ናቸው፡፡ ጣልያን ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም ስትወር በቬና የውል ስምምነት ድንጋጌ መሰረት እነዚህ ውሎች ሙትና ከጨዋታ ውጪ ሆነዋል፡፡ በነዚህ ሙት በሆኑ ውሎች ኤርትራ ምንም እንደማታጣ፣ ኢትዮጵያ ግን ጉሮሮዋ እንደሚዘጋ እየታወቀ ነው አልጀርስ ላይ ህወሓት/ኢህአዴግ ስምምነቱን የፈረመው፡፡ ኢትዮጵያ በጦር ሜዳ ያገኘችውን ድል በጠረጴዛ ላይ አጣችው፡፡ በድጋሚ አልጀርስ ላይ የተቀመጠውን ጋሪ ሲጎትት የነበረው የኤርትራ ፈረስ ነው፡፡
ኢህአዴግ፣ ኤርትራን በቅኝ ግዛትነት አውቆ ነጻነት ይገባታል የሚል አቋም መውሰዱን ከላይ አይተናል፡፡ ይህ አቋም ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት አልነበረውም፡፡ እንዲያውም ህውሓት/ኢህአዴግ ውሳኔ የመስጠት ህጋዊ ውክልናም አልነበረውም፡፡ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል የትዳር ፍቺን ያህል እንኳን ክብደት አልተሰጠውም ነበር፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያን ህዝብ ከልክ በላይ ስለናቁት ይሆናል፡፡ በኤርትራ መገንጠል ኢትዮጵያ የነበራት ህጋዊ የባህር በር ባለቤትነት ለኤርትራ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ በዚህ ውሳኔው ህወሓት/ኢህአዴግ፣ ኤርትራን ጠቀመ፤ ኢትዮጵያን ጎዳ፡፡ ከዚህም በላይ ኤርትራ ለኢትዮጵያ ቋሚ ስጋት ሆነች፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው፣ ከሻእቢያ በላይ ለኤርትራ ጉዳይ የታገለው ህወሓት ነው፡፡ በህወሓት/ኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ኤርትራ የኢትዮጵያ የግዛት አካል ናት የሚለውን የታሪክ እውነት መቃወም ቀርቶ ማንሳት አይፈቀድም ነበር፡፡ በታሪክ አጋጣሚ እንኳን “አብረው ኖረው ነበር” የሚለውን ሀቅ ለመቀበል ህወሓት አቃተው፡፡ እብሪትና ትዕቢት ወጥሮ ይዞት ነበር፡፡ ከእብሪትና ትዕቢት ፈጣሪ ይጠብቀን፡፡
Tuesday, 03 September 2024 00:00
Published in
ነፃ አስተያየት