Sunday, 01 September 2024 20:23

ቃልና ሙዚቃ (ገብረክርስቶስ ደስታና ተስፋዬ ገብሬ)

Written by  ትሬዛ ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 እንደ መዝለቂያ
“አስቀድሞ ቃል ነበር።” እንዲል፣ በዘፈቀደ ሳይሆን በውበት የተሰናኙ ቃላትን አስቀድመን፣ ቃላቱን ነፍስ ዘርቶ ወደ ተግባር የሚቀይረውን ሙዚቃ እናስከትልና፤ ደግሞ እርስ በእርሱ በከያንያኑ አማካኝነት እያዛመርን እንፈክራለን። የፍካሬያችን መነሻ የገብረክርስቶስ ደስታ ክትብ ቃላቱ (ግጥሞቹ) እና የተስፋዬ ገብሬ ሙዚቃ ነው። አጽመ ፍካሬያችን ስልተ-ምት (rhythm) ነው።
‘ሁለቱ ከያኒያን ለምን ተመረጡ?’ ከተባለ አንድም በተጋሩት ዘመን፣ እንዲሁም በተለዋወጡት ውብ ቃላት።  
“የገብረክርስቶስ ደስታ የግጥም መጽሐፍ ከተስፋዬ እጅ ላይ እንደማትጠፋ ሙሉጌታ ተስፋዬ ያስታውሳል። ‘የፍቅር ሰላምታ’ የተሰኘችውን የገብረክርስቶስን ግጥም ገና የአስራ አምስት ዓመት ታዳጊ ወጣት ዕድሜ ላይ እያሉ ተስፋዬ ሙሉዋን በቃሉ ይወጣት እንደነበረና በዜማም ለወ.ወ.ክ.ማ. ማኅበረሰብ ይጫወታት እንደነበር ይናገራል።” (ማርቆስ ተግይበሉ፣ 2015:102)።
ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ጥልቅ ናፍቆት በተደጋጋሚ በኪነታቸው መግለጻቸው እንዲሁም ሁለቱም አጥብቀው የወደዷትንና የናፈቋትን ሀገራቸውን እስከ አጽመ ርስት መነፈጋቸው ቢያመሳስላቸው ነው። ሆኖም ዋናው የፍካሬያችን ማጠንጠኛ ስልተ-ምት ሆኖ ሳለ ሌሎቹን ጉዳዮች እንደ ግብዓት እንጠቀማለን። ለዚህም ሁለቱ ኪነቶች የሚጋሩትን ስልተ-ምት መዝዘን በሁለት ከያኒያን ሥራዎች እያመሳከርን እናወጋለን።
“አስቀድሞ ቃል ነበር።” ባልነው መሠረት ለዚህ ጨዋታ ባለቃሉ ገብረክርስቶስ ነውና በውብ ቃላቱ በአሐዱነት ይቀድሳል። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ... በ’ኛም አደረ።” እንዲል ቃልን ሥጋ አልብሶ በአካል ወሥጋ ንቅናቄ ወደ ተግባር የሚለውጠው ተስፋዬ ገብሬ ነው።
ከሥነ ጽሑፍ ዘውጎች ሁሉ ሙዚቃ ለግጥም እጅጉን ቅርበት አላት። “እህትማማች ሙያዎች” (Sister arts) በመባል ይጠራሉ። ይህም የሆነበት ምክንያት የሙዚቃ ቅንጣት (Element of music) የሆነው ስልተ-ምት በግጥም ውስጥ መገኘቱ ነው። መገኘቱም ብቻ አይደለም፣ ሙዚቃ በግጥም ውስጥ ያለው ሚና መሰረታዊም ነው። ስንኝ ከዝርው ለመለየቱ የሙዚቃ ቅንጣት የሆነው ስልተ-ምት ትልቁን ድርሻም ይይዛል። ከስልተ-ምት የሚመነጨው እጅጉን ሥርዓታዊ ዜማ ለግጥም ተፈጥሮአዊ ባሕርዩ ነው። ግጥም በፈንታው ለሙዚቃ፣ በተለይም በሰው ድምጽ ለሚከወን ሙዚቃ እንደ ጀርባ አጥንት ይቆጠራል።
እርግጥ ይህም ብቻ አይደለም ምክንያታችን፤ ገብረክርስቶስንና ተስፋዬ ገብሬን ትይዩ አቁመን ከሥራዎቻቸው እየመዘዝን ማዛመራችን። በሁለቱ ከያኒያን ኪነቶች ውስጥ የሚገኘው ስልተ-ምት ተመሳስሎሹ ነው እንጂ። ይህ ጉዳይ በጨዋታችን ስንገፋ ግልጽ እየሆነልን ይሄዳል።
 ቃልና ሙዚቃ
ላልረጋች ተጓዥ ነፍሱ፣ ለሞገደኛ ስንኞቹም ማለፍያ የሚፈልገው ገብረ ክርስቶስ፤ የመድበሉን ርዕስ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” ሲል ሰይሞታል። መንገድ፣ ያውም ሰፊ መንገድ። ለገብረክርስቶስ ቃሎች መንገዱ ካልሰፋ ማለፊያ ይጠባቸዋል። በገብረክርስቶስ “ከበሮ” ምት የተስፈነጠረ፤ መመለሻው ከጠበበ መዝረክረኩ ነው። በ”ለቡጊ” የተወራጨ፤ ሰፊ ቦታ ካላገኘ መጦዙ ነው። ለፈጣን ተጓዥ ነው ጠብቦ ጉዞውን የማያስተጓጉል ሰፊ መንገድ የሚያስፈልግ።
“ከአንዱ ዓለም ወደ አንዱ፤
ስጓዝ እፈጥናለሁ - - -”
 (እንዳለው ገብረክርስቶስ ደስታ)
በሙዚቃ ብንመስል በፈጣን ስልቶችና በኃይለ ምቶች የታጀቡ ሙዚቃዎች፤ መንፈስን እጅግ ስለሚያነቃቁ አካልን ፈትተው የመልቀቅ ኃይል ስላላቸው መወራጫ ቦታ መፈለጋቸው አይቀርምና ሰፊ መንገድ (ማረፊያ) ያሻቸዋል። በወጣትነት ዘመኑ በፈጣን ስልት የታጀቡ ሙዚቃዎችን የሚወደው ተስፋዬ ገብሬ፤ በቀዝቃዛ ስልተ-ምት የሚሠራውን ባህላዊውን የኢትዮጵያ ሙዚቃን ሽሽት ሀገር ፍቅርን እስከ መልቀቅ ደርሷል። (ማርቆስ ተግይበሉ፣ 2015:102)
የሁለቱን ከያኒያን ሥራዎች ተጣምሮ በስልተ-ምት ተመሳስሎሽ ነውና የምንፈክረው ፤ ገብረ ክርስቶስ ለግጥሞቹ ሰፊ መንገድ እንደሚፈልግ ሁሉ ተስፋዬ ገብሬ ለሙዚቃው ለመወራጨት የማያግድ ሰፊ መንገድ የሚፈልግ ሰው ነው። ይህን ለማረጋገጥ (ማርቆስ ተግይበሉ፣ 2015:110) እንመልከት።
“ተስፋዬ ገብሬ ሲጫወት ተረከዙ መሬቱን ይቆረቁራል፣ የእግሩ ጣት መድረኩን ያጮሃል፤ ቅልጥሙ ይብረከረካል፤ ዳሌው እንደሐረግ ይመዘዛል፤ እንደላስቲክም ይሳባል፤ ወገቡ ይቅበጠበጣል፤ እጁ ይራወጣል፤ አንገቱ ለብቻው ይዘፍናል፤ ዓይኑ ፍቅር ያረፈበትን ዛፍ ለማግኘት በየቦታው ይሯሯጣል፤ ፍቅሩን ይጠራታል፤ ባልሰለቹና ባልተሰሙ ግጥሞች ፍቅሩን ያሞግሳታል፤ በዜማውና በግጥሙ የተደበቀውን የየሰውን ፍቅር ሁሉ ከየጓዳው ያወጣዋል፤ ይስበዋል፤ ያመጣዋል።”
ይህን የጳውሎስ ኞኞ ዘገባ ላነበበ ሰው መቼም ተስፋዬ ለአካሉ ማረፍያ፤ ለሙዚቃ መገለጫ ውዝዋዜ ሰፊ ማረፊያ መፈለጉን ይገነዘባል።
“ለቡጊ
በግሬ ጣራ መርገጥ፤
 ሙዚቃው ሲጋልብ መውጣት መውረድ
መፍረጥ፤
[ዓ]ይኔን ማገላበጥ፤
መርበትበት መንቀጥቀጥ
መላጋት መንገድገድ እንደሰከረ ሰው
የናፈቀኝ ይህ ነው፤
ተነስቼ ልዝለል፤
“ቡጊ ቡጊ” ልበል።”
(እንዳለው ገብረክርስቶስ ደስታ)
ከያኒያኑ ከበሮዋዊ ነው ጨዋታቸው። አካል ሥጋን ፈትቶ የሚለቅ የሚያወራጭ ግጥም እና ሙዚቃ ይሠራሉ። ለዚህም ነው በስልተ-ምት ተመሳስሎሽ ያዛመድኋቸው። ለዚህም ሳይሆን ይቀራል እነዚህ ሁለቱ ከያኒያን እጣ ፈንታን እስከመጋራት የሚደርሱት? አጥብቀው ለሚወዷት ሀገራቸው ዘወትር በቃል በሙዚቃ ሲያወድሷት፣ ሲዘምሩላት ኖረው ጭራሹን እስከ አጽመ ርስት መከልከላቸው፤ ወጥተው መቅረታቸው?
‘Dear Ethiopia’ የተሰኘውን የተስፋዬ ገብሬን ሙዚቃ ብናደምጥ፣ በግለሰብ ደረጃ የሀገሩን ፍቅር “ውድ ኢትዮጵያ በጣም ይወድሻል ተስፋዬ ገብሬ” ሲል ያዜምላታል። በዘወትር ጸሎቱ ሁሉ ያስታውሳታል። (ማርቆስ ተግይበሉ፣ 2015: 261)። ሆኖም ግን በናፍቆቷ እንደታመመ ላ’ፈሯ ሳይበቃ ተሰናበታት ምድሩን።
“ የዘወትር ጸሎት
አምላክ ሆይ! ሃገሬንና ወገኖቼን ጠብቅልኝ።
ከወራሪዎች፣ ከጎዳና ሽፍቶች... በጠራራ ፀሐይ ከሚነጥቁ፣
ሞት ከማይፈሩ፤ ሰው ገድለው ባንክ ከሚዘርፉ...
የዛሬም፣ የሁልጊዜም ጸሎቴ ይህ ነው።”
ገብረክርስቶስ ደስታ በበኩሉ፤ በስዕል ሥራውም ሆነ በግጥም ሥራው ሀገሩን ሲያወድስ፣ ሲዘምርላት ኖሮ ለሀገሩ አፈር ሳይበቃ አረፈ።
“ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ፤
እዚያ ነው አፈሩ የእማማ የአባባ።
ስሳብ እሔዳለሁ፥ ቢሰበርም እግሬ፤
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ ሀገሬ።
አለብኝ ቀጠሮ፤
ከትውልድ ሀገሬ ካሳደገኝ ጓሮ።”
ሲል በነፍስ በሥጋ ለሀገሬ መሬት ያልበቃሁ እንደሆን፣ በሞቴ ግን አርፍባታለሁ ብሎ በመተማመን በውብ ቃሉ ለቀደሳት ሀገሩ መሬት፣ የመጨረሻ እስትንፋሱን ጥልቅ ምኞት ከለከልነው። ለነፍሱ ማረፊያ ላላገኘባት ለአጽሙም ማረፊያ ነፈግነው። ተስፋዬም ሆነ ገብረ ክርስቶስ አጥበቀው የተመኙትን በጥብቅ ተነፈጉ። የፈለጉት ሰፊው መንገድ፣ በነፍስ በሥጋ አርቆ ወስዶብን፣ ሳይመልስልን ቀረ።
“ጉዞ ከጽንፍ አጽናፍ፤
ፍጥነት እንደ ብርሃን ዓለማትን ልለፍ።
ፀሐይ ልሁን ፀሐይ፤
እንደ ፅርሐ አርያም ሁሉንም የሚያሳይ።
እሳተ ገሞራ አመድ እረመጡን፤
ጎርፍ፤ የእሳት ጎርፍ ልሁን።
ከሲኦል ሚሊዮን ቢሊዮን ልቃጠል።
ከገሃነመ እሳት ሚሊዮን ነበልባል።
መንገድ ስጡኝ ሰፊ - - -”
(እንዳለው ገብረክርስቶስ ደስታ)
የሙዚቃና የግጥም መሠረታዊ መገለጫ የሆነው ስልተ-ምት በእንቅስቃሴ ይታወቃል። (Rhythm is not static.) ያም ሆኖ “የጠፈር ባይተዋር” ግጥሙ ከስልተ-ምትም ፈጣን ስልተ-ምትን ይጠቀማል። ከቃል ቃል፣ ከሃረግ ሃረግ ኃይለ ምት በተሞላበት ፍጥነት እንድንገሰግስ ያስገድዳል። ይህን ወደ ተስፋዬ ገብሬ ስናመጣው በአብዛኛው ተስፋዬ ሙዚቃ የሠራባቸውን ስልቶች እንመልከት፦ ዲስኮ፣ ፋንክ፣ ሬጌ፣ ጃዝ፣ የኢጣሊያ ባህላዊ ሙዚቃ ፣ ትዊስት። ተስፋዬ ሀገር ፍቅርን ከለቀቀባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ ባህላዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ በአብዛኛው ትዊስት ለመጫወት ስላልተመቸው እንደሆነ (ማርቆስ ተግይበሉ፣ 2015:99) በተጨማሪም “የፍቅር ሰላምታን” የሠራበት ስልት ፈጣን በመሆኑ ለኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች አመቺ እንዳልሆነ (ማርቆስ ተግይበሉ፣ 2015:102) እንዲሁም በኋላ ላይ የተጫወታቸው በፈጣን ስልቶች የተቀነበቡ ሙዚቃዎች ማሳያዎች ናቸው።
ዲስኮ፣ ፋንክ፣ ሬጌ ፣ ጃዝ ፣ ትዊስት፣ የኢጣሊያ ባህላዊ ሙዚቃ ስልት፣ እነዚህ ተስፋዬ ገብሬ ሙዚቃዎችን የሰራባቸው ስልቶች ናቸው። ዲስኮና ፋንክ ሙዚቃ ስልቶችን ብንመለከት ጠንካራ ስልተ-ምት (strong rhythmic role) ያላቸው የዳንስ ሙዚቃዎች ናቸው። የምት ሙዚቃ መሳሪያዎቻቸው (percussions) እጅጉን የሚጎላ፣ ከበሮዎቻቸው አስፈንጥሮ የሚያወራጭ ነው። እንግዲህ ተስፋዬ በእነዚህ ስልቶች ብዙ ተጫውቷል። ተቀርጸው ከተቀመጡት ውስጥ (The cross, sport, Love is life, መጋቢት ሀያ ስምንት) እንደማሳያ ይሆናሉ። ሬጌና ጃዝ ሙዚቃ ዘውጎች በአመዛኙ በፈጣን ስልትም በቀዝቃዛም መቀንበብ ቢችሉም፣ ሰውነትን ፈትተው በነጻነት መወዝወዝ የሚያስችሉ ናቸው። ቤዛቸውም (Bass) ኃይለ ምቱ (strong beat) ጎልቶ የሚደመጥ ነው። ከእነዚህ ሥራዎቹ ውስጥ ‘Dear Ethiopia’ን ማድመጥ እንችላለን። ይህም ብቻ ሳይሆን ተስፋዬ ገብሬ በትዊስት ስልት በሀገር ውስጥ እያለ በሠራቸው ሙዚቃዎች ውስጥም ከበሮ እጅግ ጎልቶ ይደመጣል። ስልቱም ከተለመደው በላይ ፈጣን ነው (ማርቆስ ተግይበሉ፣ 2015:102)።
እንግዲህ እንዳወጋነው ገብረ ክርስቶስ ደስታ በሀገራችን ዘመናዊ የግጥም ስልትን ተከትለው ከተቀኙ ገጣሚያን ውስጥ ይመደባል። እርሱ ብቻም ሳይሆን በግጥም ስብስቦቹ ውስጥ ጨርሶውኑ የወል ቤት ማግኘት ያቅታል። ግጥሞቹ ስሜትን ተከትለው የመፍሰስ ባህርይም አላቸው። በተለይም ሙዚቃዊ ግጥሞቹ ያለድምጽ ይወዘውዛል። ተስፈንጣሪ የሚባሉ ቃላትን የስንኞቹ መክፈቻና ማሰሪያ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌነት፦ ከበሮ፣ ለቡጊ፣ የሙዚቃ ድምጽ፣ ባለክራር፣ የጠፈር ባይተዋርን መመልከት እንችላለን። እነዚህ ግጥሞቹ ላይ ከተመለከትናቸው ተስፋዬ ገብሬ ሙዚቃዎቹን ከሠራባቸው ስልቶች በተለይም ዲስኮ፣ ፋንክ፣ ሬጌና ጃዝ ስልቶች ጋር የመመሳሰልና ባህሪይ የመዋረስ ነገር አላቸው። ልክ እንደ ፋንክና ዲስኮ ሙዚቃዎች (Strong rhythmic role) አላቸው። በኃይል መወዝወዝም ይችላሉ። እንደ ሬጌ ሙዚቃ (off beat) ላይ ያስፈነጥራሉ። አካልን ፈትተው በነጻነት የማውረግረግ ኃይል አላቸው። እንደ ጃዝ ሙዚቃም (percussive) ናቸው።
ተስፋዬ ገብሬ ከላይ እንዳየነው፣ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤትን የለቀቀው በወቅቱ በሀገር ፍቅር ቤት ይሠራበት በነበረው ቀዝቃዛ ስልት ባለው ባህላዊ ሙዚቃ ምክንያት ነው። (ማርቆስ ተግይበሉ፣ 2015:102)። ተስፋዬ በኃይለ ምትና በፈጣን ስልተ-ምቶች የተቀነበቡ ሙዚቃዎችን የተጫወቱ ቀደምት የሀገራችን ሙዚቀኞች ስር የሚመደብ ነው።
ሳጠቃልልም፣ ገብረክርስቶስ ደስታ እና ተስፋዬ ገብሬ መዘመንን ሽተው፣ መሻታቸውን በሥራዎቻቸው የገለጡ፤ መገለጣቸው በስልተ-ምት (ከስልተ_ምትም በፈጣን ስልተ-ምት) መፈከር የሚችል ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሥራዎቻቸው ከበሮአዊ (percussive) ነው። ኃይለ ምታቸው (strong beat) አስፈንጣሪ ነው። ለዳንስ ጋባዥም ነው።   
“ዛር ነው ውዝዋዜ
እብደት ነው ትካዜ
ያካል ንቅናቄ አገሩ ሙዚቃ
አገሩ ሙዚቃ
ሰው ያሽከረክራል መንፈስ እያነቃ።”
(እንዳለ ገብረክርስቶስ ደስታ)


Read 243 times