“የመጨረሻው ፈተና” - ሂሳዊ ዳሰሳ
ርእስ: የመጨረሻው ፈተና
ደራሲ: ኒኮስ ካዛንታኪስ
ትርጉም: ማይንጌ
ዳሰሳ: ፍጹም ሰለሞን
ክፍል 2~ የታችኛው ቅርፊት
ኢየሱስም ከተቸነከረበት መስቀል ወርዷል። የመላ ዓለሙን መዳኛ የመስቀል ቀንበር አሽቀንጥሮ ጥሎ ከጎሎጎታ መልስ ተለምዷዊ ኑሮውን የሚኖር አንድ ግለሰብ እናገኛለን። ይህ የዳቦው የስረኛ ጠርዥ ነው ላልነው የመጽሐፉ መቋጫ፣ ከ55 ገጽ ያልበለጠው ንባባችን ነው። ደራሲው በብልሃቱ የትርክት እጥፋቱን ከቀለበሰ በኋላ፣ በስሜት እየወዘወዘን አዲስ ትረካ ውስጥ ይዘፍቀናል። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ልብወለድ መጽሐፍ የመጻፉ አስቸጋሪው ነገር፣ ሁላችንም በምድር ሳለ የመጨረሻው የሕይወቱ ምእራፍ ላይ፣ ምን እንደተከሰተ በደንብ ማወቃችን ነው። መጨረሻው ይታወቃል። ስለዚህ “የመጨረሻ ፈተና” ሁነቶች የሚተረኩበት ሴራ ሳይሆን፣ አንባቢውን በተዋበ ዓለማዊ ቋንቋ በስሜት ሰቅዞ መያዝ መቻሉ፣ የመጽሐፉ ትልቅ ወጥመድ መሆን ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ። ተሰቀለ ብለን ሞቱን እና ትንሳኤውን ስንጠብቅ፣ ንባቡ አስገራሚ የተረክ እጥፋት ያደርግና፣ ጊዜን ከምንመለከትበት የቀጥታ ፍሰት በመቀልበስ ወደ ኋላ ተመላሽ ትረካ ይፈጥራል።
ልክ መካከለኛ ዘመን ጽኁፎች ላይ የምናገኛቸውን ምስላዊ ምልክቶች፣ በተራኪው አንደበት ተፈጥረው በመወከያነት አልፎ አልፎ መጠቀም፣ የዚህም መጽሐፍ ሌላ መልክ ነው። መስቀሉ ወደ አበባ ዛፍ ይለወጣል፣ ጎሎጎታን ወደ ገነት፣ ሕመም ወደ ፈውስ፦ “ሩህሩሁ ዛፍ ግን አበቦቹን፣ አንድ በአንድ በእሾህ የተያያዘው ፀጉሩና በደም የተጨማለቁ እጆቹ ላይ ይረግፋል።” (ገጽ 428)
በዚህ የዳቦው ታች ቅርፊት ንባብ ውስጥ ልብ ብለን አትኩሮት ካልሰጠናቸው መደናገር መፍጠሩ አይቀርም። ምክንያቱም ሞቷል ብለን ያሰብነው ኢየሱስ በሆነ የትንሣኤ ሁነት ውስጥ እንዳለ እንዲመስል፣ ከጠባቂ መላእክ ጋር ሆኖ ሁኔታውን ወክሎ አብሮት ይታያል። መልአኩ ግርታን ለብሶ ከፈጣሪ እንደተላከ አድርጎ ኢየሱስን ይተዋወቀዋል። መልአኩ በሕልሙ ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ሳይለይ ያጅበዋል። እንዲህ አድርግ፣ አይዞህ በርታ እያለ እየገፋፋው ሁሌም ካጠገቡ አናጣውም። በጥርጣሬ የሚታይ ሰው የሚመስል ስልምልም ውብ ዓይኖች ያሉት መልከኛ መልአክ ነው። “ፈጣሪ መልካም ነገርን ወደ ከንፈሮች እንዲደርስ ነው የላከኝ” ይለዋል። ሰዎች የበዛ መራራ እንድትጠጣ ሰጥተውሃል፣ ከሰማይም ተመሳሳይ ነገር ገጥሞሃል። ተሰቃይተኻል፣ ታግለሃል። በእድሜህ ሙሉ የአንድ ቀን እንኳን ደስታ አላየህም። እናትህ፣ ወንድሞችህ፣ ደቀመዛሙርትህ፣ ድሆቹ፣ አካለ-ስንኩላኑ፣ የተጨቆኑት በሙሉ፣ ሁሉም በመጨረሻዋ አሰቃቂ የቁርጥ ቀን ትተውሃል።” ሲለው መሲሑ በጣም ይደናገራል።
“ጠባቂ መላዕክ፣ እኔ ግራ ገብቶኛል አልተሰቀልኩም እንዴ?” እየሱስ ይጠይቃል።
“ውዴ ሆይ ጸጥ በል፣ አትረበሽ” በፍጹም እንዳልተሰቀለ መልአኩ እያባበለ ያስረዳዋል።
በገጾቹ ስጋጃ ላይ ኢየሱስ እና መልአኩ ወጋቸውን ይመላለሳሉ።
“ሁሉንም ስሜቶችህን የኖርከው በሕልም ነው” ለኢየሱስ ይነግረዋል። እውነታ እና ሕልም የተገለባበጡ ናቸው። እየሱስ ለሕልም እውነታን ይስታል። ለእውነታ ሕልምን ይገድፋል። ሕልሙ ምድራዊ ደስታን ያቀርብለታል፦ “የወይን ጠጅ፣ ሳቅ፣ የሴት ከንፈር፣ የመጀመሪያው ወንድ ልጅህ ጉልበትህ ላይ መቦረቅ” (ገጽ 430)
በፈተናና ስቃይ ያንከራተተችው ምድር፣ በድንገት ወደ ገነትነት የተቀየረች ትመስላለች፣ ምድር በቅጽበት ለኢየሱስ መልካም ትሆንለታለች። ናዝራዊው ግር ይለዋል። ብዙ ነገሮች እንዴት እንደዚህ ተለዋወጡ ብሎ ሸሪኩን መልአክ ይጠይቀዋል። “ምድር አልተለወጠችም - አንተ እንጂ። ከእለታት በአንድ ቀን፣ ያንተ ምድር አይፈለግም ነበር። ከእርሷ ፍቃድ ውጪ ይሄድ ነበር። አሁን ይፈልጉታል - ያ ነው ሚስጥሩ። የምድርና የልብ ህብር መፍጠር፣ ያ! ነው የእግዚአብሔር መንግሥት” ያብራራለታል።
እንዲያም ሆኖ ከመስቀሉ አምልጦ ወደ ሌላ አዲስ ዓለሙ የገባው ክርስቶስ ሞትን እየሸሸ አለመኖርን ይጠላል። በቤዛነት ለዓለሙ ከመሰዋት ይልቅ መኖርን እየቀደሰ በራሱ ዓለም መሻት ውስጥ ሰው መሆንን ይመርጣል። እንደሰው ወዶ እና ወልዶ ከብዶ መኖር ይመኛል። ሰው ብቻ ስለመሆን ያልማል። _ _በማይገመት መልኩ መግደላዊት ማርያም ወደ ትረካው ትመጣለች። በደራሲው ደግነት ሴራውን ጠምዝዞ፣ ከብዙ ምእራፎች በኋላ ወደ መጽሐፉ መቋጫ መልሶ ከመስቀሉ ከወረደው ኢየሱስ ጋር በፍቅር ያገናኛቸዋል። የካዛንታኪስ ወንጌል ነባሩን ትርክት ደርምሶ፣ ምናቡ በሚሰግራቸው ውድ ቃላት ትርክት እያበጀ፣ ስሙር ሴራ አቋልፎ ሀዲስ የክርስቶስን ገድል ያስነብበናል። ተፋቅሮ ትእይንቱ የሚተረክበት ውብ ምልልስ ምናልባት መጽሐፉ ካሉት መሳጭ ውበታም፣ የቋንቋ ለዛ መጣፈጥ ካላቸው ምልልሶች ውስጥ ይታያሉ።
ይች ማርያም (መቅደላዊት) ከሕልም ጋር የተቆራኘች የማታለያ መሳሪያ የሆነች ትመስላለች። መግደላዊት ኢየሱስን ከመከረኛ ሕይወት ወደ አዲሱ ምድራዊ እና የስጋ ደስታ “እምነት” ትጎትተዋለች። በፍቅሯ ዮርዳኖስ አጥምቃ ታስገባዋለች፣ ከፈተናና ስቃይ ባርነት አውጥታው ገላዋን ባርካ ትሰጠዋለች፣ ከፍቅሯ ምንጭ አጠጥታው በፍቅር አቁርባ ምድራዊ ደስታ ትሰጠዋለች። “እየሱስ ያዛትና ጭንቅላቷን አንጋሎ አፏ ላይ ሳማት። ሁለቱም ጣዕረ-ሞት መሰሉ። ጉልበታቸው ከዳቸው።” (ገጽ 434)
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሁሉም ቦታ ላይ ተደባች መንፈስ ውስጥ ያለውና የስነልቦና ውጥንቅጥ ያቆራመዱት እየሱስ፣ እዚህ የመጽሐፉ ምልሰታዊ ትርክት ላይ ስናገኘው በፍካት ያበበ ደስተኛ ሰው ይሆናል። የአካል እና የርዕይ መነጠቅ ሲያሰቃዩት እምናውቀው ጸሊሙ እየሱስ በፍሠሃ ኑሮውን በፍቅር ሲቀድስ እናገኘዋለን። የሴት ገላ አማልእክትንም ያንበረክካል።
… “ውዷ ሚስት! ዓለም ውብ መሆኗን ስጋም የተቀደሰ መሆኑን አላውቅም ነበር- እርሷም ለካ የእግዚአብሔር ልጅ ነች፣ የተከበረች የነፍስ እህት። የስጋ ደስታ ኃጢያት እንዳልሆነ አላውቅም ነበር” (ገጽ 434)
ቢሆንም በፍቅራቸው ያፈሰሱት ላቦት ሳይደርቅ፣ ያ አፍታ መዋወድ ወዲያው ወደ ትራጄዲ እዝን ይለወጣል። እራሷን ሕልም ከሆነው ገነት ውጭ “ድንጋይ፣ ባልጩት፣ ጥቂት ቋጥኞች” ባሉት እንግዳ ስፍራ ታገኘዋለች። እግዚአብሔር ነኝ ያለ ዳኛ፣ ርህራሄ የሌላቸው ደቦኞቹን አሰባስቦ መቅደላዊት ማርያምን በድንጋይ ወገራ ያስገድላታል። እራሷን ከገዳዮቹ ለማስጣል የምታደርጋቸው ልመናና ልምምጦች ልብ ይሰብራሉ። በነቀዘ የብሉይ ማኅበራዊ ስምምነት ውስጥ ሴትነቷ ብቻውን ገፍትሮ ለሞት ሲያበቃት ማንበቡ በራሱ ሀዘን ያዋርሳል። ደራሲው መሳል የቻለው መጠቆምን ታልፈው የመጡ ፍጽምና የጎደላቸው የዘመነ ብሉይ ማኅበረሰባዊ ንቅዘት ማሳያዎች ይገለጣሉ። ጊዜ ተሸፍኗቸው ባለመጠየቅ ተላምደን ችላ ብለን በማድበስበስ፣ መሸፋፈን ውስጥ ያሉ ተሻጋሪ ኋላ ቀር እሳቤዎችን መልሰን እንድንመረምር በነጠላ ገጽ የተወው የዛኛው ዘመን አዳፋ ይመስለኛል። የኪነትስ ግብሯ መጠቆምም አይደል። እየሱሰም ሞቷን በሰማ ጊዜ ያዝናል።
“ውሾች ብቻ ናቸው ዝም ብለው የመቀበል ተፈጥሮ ያላቸው። ውሾችና መላዕክት! እኔ ውሻም መላእክትም አይደለሁም። እኔ ሰው ነኝ። እናም እጮኻለሁ፣ ኢ-ኢፍትሃዊ! ኢ-ኢፍትሃዊ! ነው። ሁሉን ቻይ አምላክ እርሷን መግደል ትክክለኛ ፍርድ አይደለም።” እያለ ፈጣሪውን ይኮንናል፡፡ ስለወደዳት አንድ ሴት ሙሾ ያወርዳል። በርግጥ ቀደም ባለው የመጽሐፉ ንባብ ከበረሃ ንስሃ ገዞው የተመለሰው ኢየሱስ፤ ባጋጣሚ የደቦ ፍርደኛ በድንጋይ ወግረው ሊገድሏት ሲል ከሞት አስጥሏታል።
መለኮታዊ ጣልቃ ገብ ረድኤት የመሰለው የያኔው ማዳን፣ ሞትን ፈቀቅ አደረገው እንጂ ርቆ እንዲሄድ አላደረገውም ነበር። ትረካው እዚህ ቦታ ላይ የሚያስረዳው ሁነት አለ። ይሄ አዲስ አማራጭ እውነታን እንደገና በሌላ መልኩ ማደራጀት ይመስላል፣ የአማራጭ ታሪኩ መከሰት የመሲሑ ጣልቃ ገብ የማዳን ኃይል፣ በዚህኛው ልውጥ ተረክ እውነታ ውስጥ ፈጽሞ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ያስረዳል። መግደላዊት ማርያም ለተላለፈችው ሕገ ሙሴ ሙሉ ቅጣቷን የምትከፍልበት አማራጭ እውነታን አሳይቷል። እንዲህም ሲሆን የኢየሱስ አእምሮ ከአካሉ ወጥቶ በጭልፊት መልክ ይከተላታል። ምናልባት ይህ ቅርፊት ከፈተናዎች ሁሉ “የመጨረሻው ፈተና” ውስብስብ እንድምታ “ምንነትን” ይጠቁማል። ዓለም በእርግጥም ኃጢአተኛ እንደሆነች እንረዳለን፤ ለኃጢአት ይቅርታ እንደሌለው እናያለን፤ አሮጌው የኦሪት ሕግ ሳይሻር ተግባራዊ ሲደረግ እንመለከታለን፤ በተጨማሪም የሰው ዘር ያልዳነ ፍጥረት መሆኑን ግልጽ ለማድረግ ይሞክራል።
በመግደላዊት ሞት ሀዘኑን ያልጨረሰው ኢየሱስ፤ በድንገት በሌላ ሴት እንጉርጉሮ የበለጠ ይማልላል። ረገብ ያለ ዘለሰኛ ታንቋርራለች። “ድምጿ መረዋና ቅሬታ የተሞላበት ነው” የአላዛር እህት ማርያም ነበረች። መልአኩ ከዚህች ሴት ጋር እንዲተኛ እየደለለ ያግባባዋል።
“መግደላዊትስ?” ብሎ ይጮሃል ኢየሱስ። “አንዲት ሴት ብቻ ነች በዓለም ላይ የምትኖረው፣ አንዲት ሴት በእልፍ አእላፍ ፊቶች። አንዷ ስትወድቅ አንዷ ትነሳለች። መግደላዊት ማርያም ሞተች፣ ሌላኛዋ የአልዓዛር እህት ትኖራለች፣ ትጠብቀናለች። ትጠብቅሃለች። እርሷም መግደላዊት ራሷ ነች ግን በሌላ ፊት።” (ገጽ 442)
ኢየሱስም እንደ ነብያት ቀደምት አባቶቹ ሴሰኛ፣ ሴት አውል ግብር፣ ከአንድ ሴት ወደ ብዙ ሴቶች፣ አያሌ ጋብቻዎች ውስጥ ይንሸራተታል። በመልአኩ አማላይ ምክር እየተገፋ ሁለቱን የአላዛር እህቶች፣ ማርያም እና ማርታን ሁለቱንም ሚስቶቹ ያደርጋቸዋል። ነገር ግን ኢየሱስ እዚሁ ስጋዊ ተድላ ውስጥ እንዳለ አረመኔው ሳኦል በአዲስ የክርስትና ስም ተጠምቆ ጳውሎስን ሆኖ ኢየሱስ ወዳለበት ቤት ይመጣል። “መልካሙን ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ” ጳውሎስ የአዲሱ ክርስትና ወንጌል አርበኛ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ድነት እንዴት መሆን እንዳለበት ለአዳኙ ለእራሱ ለኢየሱስ፣ ጳውሎስ ለማስረዳት ሲጥር ስንመለከት አንዳች ትልቅ ምጸት ይፈጥራል። በሁለቱ መሀል ያለው ጡጫ ቀረሽ እንኪያ ስላንቲያ ትኩረት ይስባል። “ውሸታም!” “ውሸታም!”...”እኔ የናዝሬቱ እየሱስ ነኝ፣ አልተሰቀልኩም። ከሞትም አልተነሳሁም።” ይለዋል ኢየሱስ። ምናልባት ደራሲው እየሱስን ከጳውሎስ ጋር መልሶ ማገናኘት ታሳቢ እንዲሆን ሊያደርግ የሚችለው ሁነት ክርስቶስ በቤዛነት ያልሞተበት ዓለም፣ ምናባዊ እውነታን ምንነት እንዲያመላክት ለማሳየት የፈለገ ይመስላል። የሆነ ሆኖ ጳውሎስ የነብዩን ይሁንታን ባያገኝም፣ የኢየሱስን ሞትና ትንሳኤ የሚገልጽ ልብ ወለድ ፈጥሮ ከመሥራት ውጭ ምርጫ አልነበረውም፦ “በዚህ በበሰበሰ ኢ-ፍታዊነትና ድህነት በተንሰራፋበት ዓለም፣ የተሰቀለውና ከሞት የተነሳው ኢየሱስ፤ ለምስኪኑ፣ ለየዋሁና ለተጨቆነው ሰው በጣም ውድ የሆነ መጽናኛ ነው። እውነት ወይም ውሸት ስለመሆኑ ግድ አለኝ መሰለህ?! ዓለም ከዳነ በቂ ነው!” ጳውሎስ እያስተማረ ያለው እምነት ታሪካዊ የእውነታ መሠረት እንደሌለው ከተገነዘበ በኋላም ከተልዕኮው አይዛነፍም። “እውነትን” እራሴ ፈጥሬያታለኹ ብሎ ይሟገታል። ኢየሱስ የጳውሎስን የሃይማኖት አስተምህሮ ያጣጥለዋል፤ ነገር ግን ሰውየው ያለውን ጹኑ ሀዋርያዊ እምነቱን አያናውጠውም። በምልልሳቸው አንዱ ሲግል ሌላው በርዶ ያዳምጣል። “እሱን ማን ጠየቀህ፤ ያንተን ፍቃድ አልፈልግም? በኔ ጉዳይ ለምን ትገባለህ?” እየሱስን ያፋጥጠዋል።
በእየሱስ አና በጳውሎስ መሀል ያለውን አተካራ ጋብ ያደርገውና፣ ካዛንታኪስ ወደ ሌላ ትረካ ይዞን ይገባል። የደቀመዛሙርቱ ወደ ትረካው መምጣት ሌላ ሁነት ይገልጣል። ጠባቂ መልአክ ተብዬው እራሱ ሰይጣን እንደነበር እናውቃለን። መልአኩ ሲተውነው የነበረ ድግምት መሰበሩን ይጠቁመናል። አስማቱ ይሟሟል፣ ቅዠቱም ይገለጣል። ሁሉም ሕልምና ቅዠት ነበር።
የዚህ መጽሐፍ ዋና ምልክት እና እጅግ ድንቅ ነገር - ደራሲው በድንቅ ምናብን ማቆላለፍ ብልሃቱ፣ በአታላይ ውስብስብ ሕልም እና ራእይ መሰል ቅዠት በኩል “አማራጭ እውነታን” መተረኩ ነው። ኢየሱስ ለድቃቂት የቆይታ እድሜ ከቆየበት ተምኔታዊ ደስታው እልፍኝ ወጥቶ ወደ ጽልመት እውነታው ይገባል። ከቅዠታዊ ደስታ ወደ ተቸነከረበት ጣር ይመለሳል። የመጨረሻውን ሲቃ በመስቀል ላይ ተንፍሶ እስከ መሞት ድረስ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል። “የመጨረሻው ፈተናም” የካንታኪስ ወንጌልም “ተፈጸመ”፡፡
Published in
ህብረተሰብ