“እቴ አበባ እቴ አበባዬ
አዬ እቴ አበባዬ
እቴ አበባ ስትለኝ ከርማ
አዬ እቴ አበባዬ
ጥላኝ ሔደች ባ’ምሌ ጨለማ
አዬ እቴ አበባዬ……..”
ሰላም ለኪ፤ በትዕቢት ሳይኾን በመውደድ ስጋት ለወረሳት ልብህ! እጅ ነስቻለኹ እጅግ ውብ ለኾነው ለነፍስኽ ማማር። ሰላም ይኹንለት ከሐምሌ ጭጋግ ጋር ለሚጨፈግገው ስሜትህ፣ ከነሐሴ ዝናብ ጋር ለሚፈሰው ስውር ዕንባህ። ሀዘንኽን አቁረኽ ጨዋታህን ዙርያኽ ላለው ኹሉ ያለ ስስት ላፈሰስኽው፣ የነፍስያዬን ቁር በቀረችኽ ስስ እስትንፋስ ላሞቅኽው፣ የኔ ሰው ሰላም ይኹንልኽ። ከመቅደስ እንደሚስረቀረቅ የቅዳሴ ድምጸት፤ የበደነን ስጋ እንደሚቀሰቅስ፣ ሕያው እንደሚያደርግ፣ ትንሳዔን የተነፈስኽባት ነፍሴ በመደነቅ ስለ ኣንተ ቃል አልባ ኾናለች።
“. . . እናቴን ጥሯት (ለምለም) መድሃኒቴን
(ለምለም) እሷን ካጣችሁ (ለምለም) መቀነቷን (ለምለም) አሸተዋለሁ (ለምለም) እሷን እሷን (ለምለም) አባቴን ጥሩ (ለምለም) መድሃኒቴን (ለምለም) እሱን ካጣችሁ (ለምለም) ጋሻ ጦሩን (ለምለም) አሸተዋለሁ (ለምለም) እሱን እሱን (ለምለም)”
አንተ ሆዬ ስታስጠራው ያላገኘኽውን ጋሻ እና ጦሩን ይዘኽ የቀረኸውን መድኃኒትን አሽትተኽ ጠገብኽው? በዓል እና ችጋር ሲገጥም ጉድለት በጎረቤት ይሟላል፤ አውድ ዓመት እና ሞት የገጠሙ እንደኾን፣ ማን ነፍስ ማካፈል ይችላል? ሰው ማጣት ዐይኑ ይጥፋ! አካሌ ጠፈፍ አለልኽ፣ ልብኽ በምትወደው ዕለት ውድኽን የተነጠቀው? የእናትኽ መቀነት ሀዘንኽን ሸክፎ አሰረው? ከሚለወጥ ዘመን ተኳረፍኽ? ቀን ጠፍቶ ኖሮ ነው እግዜሩስ በአደይ አበባ ላይ መቃብር የሚስለው? የአውድ ዓመትን ጥንጁት ከፍትሐት ዕጣን የሚቀላቅለው? ዓለሜ አደይ አስጠልቶኽ ቀረ?
አበባ አየኽ ወይ ፍቅሬ?
ቀን ቀንን ተክቶ፤ ሳምንታት ተባዝቶ፤ ወራት ተደምሮ፣ የዓመት አዳፋ ራሱን ሊቀይር ሲል አበባ አየኽ ወይ ፍቅሬ? ቁስልኽ ሻረልኽ ወይ? ማቃሰት እህህታህ ጋብ አለልኽ ይኾን? ሕይወት ስትነጥቅ አታስጠነቅቅም። ተክታ ስትሰጥም፣ “ይዤ መጣኹልኽ!” ብላ አታበስርኽም።
ጥቋቁሮቹን ቀናት በቀስታ አንሸራትታ፣ መልኳን ማፍካት ስትጀምር፣ አበባ አየኽ ወይ ፍቅሬ? በሀዘን የመረቀዘውን ልብኽን በዕንባ እንዲታጠብ በቀስታ ሕይወት ስትጫነው አበባ አየኽ ወይ ውዴ? ፈቀድኽላት ወይ ለሳቅ? ፈቀድኽላት ወይ ለመጽናናት ዕንባ? ልጠግንኽ ብመጥን የዓለም ደስታ የኔ ነው። ማፍቀርን አብሮ ማልቀስ፤ እኔን ይምታኝ ብሎ አባብሎ ማንሳት አድርጌ ስዕሉን ባሟላ፤ መፋቀርን ስጋ ከማፋተግ ሰርክ ከመገልፈጥ አልቄ ባከብረው ለእኔ ክብሬ ነው። ብችልማ ፍቅሬ ከቀን ጎዶሎ ጋር እንዳትገጣጠም ከስር ከስር ሔጄ እሞላልኽ ነበር። ግን ደግሞ ሰው ነኝ መንጠራራቴ የማይደርስበት ከፍታ፥ ስስቴ የማያስጥለው መከራ፥ ለጋስነቴ የማይሞላው ጉድለት አለ - አለኽ። ላልደረስኹበት ከፍታ በሸለቆ አብሬኽ እሰለፋለኹ፤ ላላስጣልኹኽ መከራ አብሬኽ እታገላለኹ፤ ላልሞላኹት ጉድለት አብሬ እታመማለኹ።
አበባ አየኽ ወይ ፍቅሬ?
አበባ አየኽ ወይ ባልንጀሮችኽ በሕይወትኽ ውስጥ በተራ ሲቆሙልኽ? እንጨት ሰብረኽ ቤት እንድትሰራ፣ ባዳውን ዘመድ ሲያደርግልኽ አበባ አየኽ ወይ ውዴ? ወንድሞችኽን ሰርክ አጥር ሲያደርግልኽ አበባ አየኽ ወይ? ኮከብ እየቆጠርኽ ደጅ እንዳታድር የባይተዋሩን ቤት ወለል ሲያደርግልኽ አበባ አየኽ ወይ ፍቅሬ? ዘመን የማይሽረው አደይ መስላ ኮለል ስትል አየኻት እናትኽን? እግዜር ለወሰደብኽ ነፍስ በዚህ ኹሉ መንገድ ለካሳ ሲለምን? አበባ አየኽ ወይ ውዴ?
አንተን በማፍቀር ውስጥ አበባ አየኹ ፍቅሬ! እውነት ይሉት አበባ፤ እምነት ይሉት ሐመልማል። በዚህ እደነቃለኹ - አማን ይኹንለት፣ በፍትወት ላልተደለቀ የአንተ ወንድነት። ማን እንደሰበረው ሳታውቅ፣ ከጉድለትኽ ሰጥተኽ ያከምኸውን ውስጠቴን እያየኹ አዱኛ ይሙላለት እላለኹ፣ ለምርቃት ቃሌን እሰጣለኹ። ቸር ይመልከት ዓይንህ ጭን ማለፍ የቻለ፤ ደህና ልብ ሲያይ ቆሞ ላስተዋለ። ሰላም እላታለኹ ያቺን ቆንጆ ልብኽን፣ በዘመን ድሪቶ ከመታፈን ተርፋ እውነትና ፍቅርን ዘወትር ለምትሰፋ። አንተዬ ምን ይሉት ቅኔ፣ ምን ይሉት ዕውቀት ከቀልብህ ቢታጀል፣ በስብርባሪ ታንኳ ማሻገር ቻልኽበት?
ከብረኽ ቆየኝ ውዴ . . .
ከብረኽ ቆየኝ የኔ ሰው። በዓመት መጽናናትኽ ሞልቶ፤ ከጭጋግ ተስማምተኽ፤ ለዝናቡ ለዝበኽ፤ ሆያ ሆዬ ሆድ ሳያስብስኽ ከአደዩ ታርቀኽ። ከብረኽ ቆየኝ ውዴ፣ ያጣኽውን ነገር መተኪያ አግኝተኽ፥ ሳቅኽን የእውነት ከአንጀትኽ አድርገኽ። ከብረኽ ቆየኝ ፍቅሬ ያሰረኽን ሀዘን፣ አንተ በተራኽ ጠፍረኽ ከብረኽ ቆየኝ ከብረኽ።
Wednesday, 04 September 2024 00:00
አበባ አየኽ ወይ?
Written by የአብሥራ አድነው
Published in
ህብረተሰብ