Sunday, 01 September 2024 20:34

ዕድለኛው ወር - ነሐሴ!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

   ‹‹ካገኘሻቸው - ለቃቅሚያቸው፤
ካገኘሃቸው - ለቃቅማቸው፤››
     (‹‹ስርቅታዬ››፣ ሰለሞን ደነቀ)
ነሐሴ ዕድለኛ ወር ነው፤ ሐምሌ ወር ላይ ጆሮአችንን ሰቅዞ የያዘው የዝናብ፣ የመብረቅ እና የወራጅ ወንዝ ድምጽ ለአፍታ ገለል ይልና በነሐሴ ጅራፍ ይረታል። አድባር የሚሰነጥቅ፣ አውጋር የሚያሸብር ብልጭታ መብረቁ ገሸሸ ይልና ጅራፍ በቦታው ይተካል፤ ድምጽ ወለል ብሎ የሚታለብበት ወር ነው ነሐሴ፤ መሰማማት ይገንናል…
…ነሐሴ ላይ የተገረፈ ጅራፍ ጥራትን፣ መልዕክትን፣ ተግባቦትን አንከብክቦ ካለንበት ያደርሳል። እንዳልኳችሁ ነሐሴ የመሰማማት ወር ነው። በነሐሴ፣ ጅራፍ እየቆላ ተስፋን እና ብርሃንን የሚጠባበቅ ማቲ አለ። ማቲው ቆፈንን ነው የሚገርፈው፤ በጅራፉ ያበራያል፤ እንደ መጋኛ የሠራ ጅስማችንን የጠረነፈው ብርድ መድረሻ ይጠፋዋል፤ ሙቀትን ያድለን ዘንድ ነሐሴ የተሰኘ ወር በቀመር ተካተተ ማለትም ያግባባናል።
ገላችን ከብርድ ይላቀቃል፤ በአብዛኛው የአገራችን አካባቢዎች በሬዎችም መጠነኛ ፋታ ያገኛሉ፤ እርፍ ይወርድና ማረፍ ይሆናል፤ ተሰቅስቆ ሲታረስ የከረመው መሬት እህል ማብቀል፣ ቀንበጥ ማጎንቆል ይይዛል፤ ነሐሴ ፍሬ የሚገመትበት ወር ነው፤ ስለ ጎተራችን ሙላት፣ ስለ ቀዬአችን ፍካት፣ ስለ ልጆቻችን ዕድገት፣ ስለ አዲስ ኩነት፣ ስለ መባት እርምጃችን የሚሰፈረው ነሐሴ ላይ ነው፤ ነሐሴ የትልም ወርም ጭምር ነው።      
ነሐሴ ወር ላይ ትላንታችን ሐምሌ ነው፤ ነገአችን ደግሞ መስከረም፤ ከትላንታችን ይልቅ ለነገአችን መጓጓታችን ተፈጥሮአዊ ጠባይ ነው፤ ሐምሌን አልፈን፣ መስከረማችን እንዲጠባ ተስፋ የምናደርገው የነሐሴ ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠን እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ሰናይ ነገን እንቋምጣለንና ነሐሴ መስኩ ሁሉ ለምለም የሆነ ነገን እንካችሁ ይለናል፤ ብርሃን እና ሽቱ የጽድቅ ምሳሌዎች ናቸውና ነሐሴ ከፊታችን ብርሃን እና መዓዛን ሊያድለን የተሰየመ ታላቅ ወር ነው…
‹‹አረቄ ዳቦ - ዕኩል ላክፋይ፤
የየአቅሙን ይዞ - ወዳጅ ቤት ሲታይ፤››
እንዲል ጥላሁን ገሠሠ በ‹‹የአሥራ ሦስት ወር ጸጋ›› ዘፈኑ፣ ነሐሴ የማክፈል ወርም ነው፤ ዝየራው ልዩ ነው፤ አክፋይ ሸክፈው የሚውተረተሩ ሰዎች ለዓይን ምልዐትን ያድላሉ። የምናከፍለው ሌሎች ስለሌላቸው አይደለም፤ አለኝታን ለማሳየት ነው፤ ልጅህ፣ ልጄ፤ እኔ አንተ ነን ለማለት ያህል ነው፤ ማካፈል ነሐሴ ላይ ይደራል።
ነሐሴ ጸጋው እልፍ ነው፤ የነሐሴ ጫንቃ ላይ ቆመን የመስከረምን ብራ፣ የጥቅምትን አበባ እንጠባበቃለን። አዎ ነሐሴ ጸጋው ብዙ ነው፤ ጸጋዬ ገብረመድኅንን ያገኘነው በነሐሴ ወር እንደሆነ ልብ ይሏል! ምድራችን ጸጋዬ በተባለ የኪነ-ጥበብ ቀንዲል ጸጋን ተቀዳጀች!
ጸጋዬ የአገራችንን ጸጋ አውስቶ አይጠረቃም፤ ልጅነቱ ስቦ ትዝታ ውስጥ ሲዶለው፣ ልቡናው ሠርክ ሲንቀጨቀጭ በ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት›› ግጥሙ ውስጥ እናስተውላለን፤ ልጅ ሆኖ ድክ፣ ድክ ካለበት ተንደርድሮ፣ የንታ ጋር ተከትቶ ፊደል ቆጥሮ፣ መስክ ዘልቆ ከብት አግዶ፣ ገሳ ተከናንቦ አውሬ ከእህል ላይ አስጥሎ፣ ለጥማድ በሬዎቹ ሣር አጭዶ፣ ለቤተሰቦቹ ጭራሮ ሰብሮ፣ ቀፎ ሰቅሎ ማር አጣጥሞ፣ ማሕሌት ቆሞ፣ መቅደስ አጥኖ… ያለፈበትን ሁሉ ነው ‹‹ኢትዮጵያ›› ብሎ የሚጠራት፤ ማጣጣም፣ መንካት፣ መሆን የቻለውን ነው አገሩ ብሎ በልቡ የመዘገበው፤ እኛም ተቀብለን መዝግበናል።  
‹‹…ከእናቴ ማኀጼን አልፌ፣ በኢትዮጵያ ማኅጸን አርፌ፤
ከአፈሯ አጥንቴን ቀፍፌ፣ ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ፤
ከወዟ ወዘን ቀፍፌ፣ በሕጻን እግሬ ድኬባት፤
በሕልም አክናፌ ከንፌ፤
እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ፤
ከጫጩትና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ፤
በገጠር ደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ፤
ከቆቅና ከምዳቋ፣ ከጅግራ ጠረን ስተሻሽ፤
በወንዝ አፋፍ፣ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል፣ ጥሎሽ፤….››
       (‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን፤ ‹‹እሣት ወይ አበባ››)
የጸጋዬ ኢትዮጵያ የተኖረች ነች፤ ጸጋዬ ያለፈውን፣ የነካውን፣ የተነካበትን፣ ያደረገውን፣ ያከናወነውን… ነው ኢትዮጵያ ብሎ የተቀበለው።
ሙሉጌታ ተስፋዬም የነሐሴ ገጸ-በረከት እንደሆነ ልብ ይሏል! በርካታ የዘፈን ግጥሞችን ደርሷል፤ በሙሉጌታ ድርሰት ከደመቁ ድምጻዊያን መካከል አበበ ተካ፣ ታምራት ደስታ፣ ይርዳው ጤናው፣ ሐና ሸንቁጤ፣ ብጽዐት ሥዩም እና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው፤ ሙሉጌታ በግጥሞቹ ውስጥ ሲሻው ውበትን አድንቆ፣ ሲሻው መዓት ይጠራል፤ ለፈጣሪ መዋቀሻ ሰድዶ፣ ለአገሩ መናን ይማጠናል፤ ጣዕርና ጋዕር የተነፈሰ አንደበቱ በቅጽበት የእንቁጣጣሽ መስክ ላይ ሰፍሮ ውበት ሲያልብ ታገኘዋለህ፤ ለያዥ ለገናዥ አዳጋች ነው፤ አይያዝ፣ አይጨበጥ፤ መልኩ ብዙ ነው፤ በአንዱ ግጥም ቆዝሞ ያስቆዝምህና፣ መልሶ ወደ ሽለላ ይከትሃል…
…ግጥሞቹ ሲነበቡ የሚሰጡት ሥሜት፣ በተለያዩ የጽንሰ-ሀሳቦች መስክ ውስጥ የመገማሸር ያህል ነው፤ ቋንቋ ምን ያህል ክቡድ እንደሆነ የሙሉጌታን ግጥሞች ስትኮመኩም መገንዘብ ይቻላል፤ በሰውነታችን ውስጥ ደም ትልቁን የቤት ሥራ በመወጣት ቆመን እንድንሄድ ያደርገናል፤ በአንጻሩ ደግሞ በ‹‹የባለቅኔው ምሕላ›› የግጥም መድበል ውስጥ ቋንቋ ትልቁን ሥራ ሲከውን እናስተውላለን፤ ሙሉጌታ መግለጽና መገለጥን በወጉ ያውቅበታል። ሀሳቡም ቋንቋውም ዕኩል ይናደፋሉ።
ሙሉጌታ በቋንቋ መርቀቅና በአንኳር ሀሳብ አመንጪነት ብቻ ሳይሆን፣ በርዕስ አሰጣጥም ክቡድ ነው፤ ይኼ የርዕስ አሠያየም ጠባዩ ይደንቀኛል፤ ‹‹እውነት ከመንበርህ የለህማ››፣ ከወሎ ልጅ ውሎ››፣ ‹‹አክሱም የብቃት ሥም››፣ ‹‹የጎራው ወይራ ዝየራ››፣ እና ‹‹ኩኩሉ አለ ዲበኩሉ›› የሚሉ ርዕሶችን መጥቀስ ይቻላል፤ ገና ዋናው ግጥም ሳይጀመር ርዕሶቹ የግጥም ይዘት ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን…
…በዚህ ልክ ረቅቆ ነው ግጥምን ለአንባቢ ያደረሰው፤ ረፍትህን ዕክል አይጎብኘው፣ እቴ! ሙሉጌታ ግጥምን አስመልክቶ ይሞግታል፤ ሳይኖሩ፣ ሳይነኩ፣ ሳያጣጥሙ መግጠም ብሎ ነገር ልፋት እንደሆነ ያምናል፤ ገጣሚ ተጨባጭ የሆነ ነገር ለማቅረብ የኖረውን መሰናኘት አለበት ባይ ነው፤ ተቆርቋሪ ነው፤ ኪነ-ጥበብ የደነበሸው ተቆርቋሪ ስላጣ ነው፤ ተቆጭ አያሳጣን!
ከዚህ በዘለለ፣ ሰብዐዊ ክብር ላይ ሙጥኝ ያሉ ግጥሞችን ነው የለገሰን፤ ሰው መሆን ይቀድማልና ነው ዕውነቱ፤ ለማመንም፣ ለመማርም፣ ለመሥራትም የሰው ቁመናን መቀዳጀት አለብን፤ ሰዋዊ ባሕሪያትን የተላበሱ ናቸው የሙሉጌታ ግጥሞች፤ ክቡሩን የሰው ልጅ በግጥሞቹ አክብሯል፤ ለሰው ልጆች ነበር ሲሰናኝ የነበረው፤ ገጣሚ ማሕበረሰብ ውስጥ ዘልቆ ሚና ሲያኖር ነው ሥራው ይሁንታን የሚያገኘው፤ ሠርቶ ማለፍን የመሰለ ክብር የለም፤ ያገለገሉንን እናክብር።
ወደ ነሐሴ እንመለስና፣ ‹‹ለመሆኑ በሌላ አገር ቡኼ አለ ይሆን?›› እላለሁ፤ ‹‹አለ›› እንበል፤ ግን ሰለሞን ደነቀ የማይዘፍንበት ቡኼ ምን ይፈይዳል?!
ቡኼ ከትውፊት ዕኩል የማይረሱ ዘፈኖች የሚስተዋሉበት ወቅት ነው።
ከቡኼ ዕኩል የሰለሞን ደነቀ ‹‹ስርቅታዬ›› ትዝታችን ነው፤ ሰለሞን በወፍራም ድምፁ ከትምህርት ቤት፣ ከሰኔ መሰነባበት፣ ጉብል ከመሸኘት፣ ቡኼ ደርሶ ጥቢኛ እስከመብላት፣ ካገኘሻቸው ለቃቅሚያቸው እስከማለት የሚደርስበት ዘፈን አለው፤ የሺእመቤት ዱባለ ታጅበዋለች።
በኢትዮጵያ ራዲዮ የቴክኒክ ክፍል ይሰራ የነበረው ሰለሞን ደነቀ፣ የግጥም እና ዜማ ደራሲ ብሎም ድምጻዊ ነበር፤ በአማርኛ እና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች ሙዚቃን ይጫወት ነበር። ተወዳጅነትን ካተረፈበት ሙዚቃዎች መካከል፡- ‹‹ስርቅታዬ››፣ ‹‹አይሆንም እደሪ››፣ ‹‹ሳብዬ››፣ ‹‹ያ ዳባሌ ዚማሙ (በኦሮሚኛ)››፣ ‹‹ባቡሬ (በኦሮሚኛ)››፣ ‹‹እያጉረመረመ››፣ ‹‹ሐገር›› እና ሌሎች ዘፈኖችም ተጠቃሽ ናቸው።    
ከ‹‹ስርቅታዬ›› ትንሽ ግጥሞችን እንኮምኩም፡
‹‹በልጅነቴ በልጅነትሽ፣
ያ‘ረግነው ሁሉ ትዝ ይበልሽ፤
ወይ ከመንገድ ዳር፣ ደብተር ይዘሽ፤
እስከቤት ድረስ - የምሸኝሽ፤
ጸባይ ቁንጅና - የተላበስሽ፤
ከ‘ቶ ያየሽ፤
መች ጠገበሽ፤
እኔም ባይሽ፣ ብመኝሽ፣ ብቃኝሽ፤
መች አገኘሁሽ?!
ጊዜው ቆይቷል - ከተለየሁሽ፤
ግን ከልቤ አትጠፊም ወይ ማንጠግቦሽ፤
ጊዜው ቆይቷል - ከተለየሁሽ፤
ግን ከልቤ አትጠፊም፣ ወይ ስመኝሽ፤
ካገኘሻቸው ለቃቅሚያቸው፤
ካገኘሃቸው ለቃቅማቸው፤...››
ሰለሞን ደነቀ በዚህ ዘፈን ውስጥ ያሳለፈው ትውስ እያለው ይተዝታል፤ ዘፈን የማስታወስ አቅማችንን እንደሚጨምር ይታመናል፤ ከትምህርት ቤት ጀምሮ፣ ቡኼ ሲደርስ የጨፈሩትን፣ ያጣጣሙትን ጥቢኛ፣ የልጅነት ጊዜ ጨዋታ እና ሌሎችን አስታውሶ በሚያምር ድምጹ ሲወርድ እንሰማዋለን፤ ከዚያ እናስታውሳለን፤ ለእኛ እና ለአገራችን ማማርን ተመኘሁ!  
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።


Read 149 times