እንደ መጽሐሃፍ- ቅዱሷ ቤርሳቤህ (260) ታሪካቸው ያልተጻፈ፣ ወይም ተነክቶ የተተወ ሰዎች፣ ስለ ‹ያልተቀበልናቸው› ማህበረሰቦች፣ ‹ማዕቀብ› ስለተጣለባቸው ህዝቦች፣ ታሪካቸው ተድበስብሶ በስርዓት ፍትህና ፍርድ ላላገኙ ሰዎች፣ ከመጽሃፉ መታሰቢያ ጀምሮ የት እንደገቡና፣ ‹‹የት እንደወደቁ ያልታወቁ››(129) (በአሉ ግርማ’ን ጨምሮ) ያልታወቁ ግለሰቦች፣ ለህዝብና ለሃገር የሚኾን ሥራ ሰርተው፤ ሥራቸውን በቅጡ የሚገነዘቡላቸው አጥተው በማዕቀብ ላሉ ‹እስረኞች›፣ ‹‹የሳሎኑ መብራት በርቶ የጨለመባቸው፣ በራቸው ተከፍቶ ዝግ የመሰለባቸው፣ ፍም ተንተርክኮ ብርድ ለሰፈነባቸው››(62)፣ ልክ እንደ አቶ ሥዩም ‹‹ለግፉዓንና ምንዱባን››(20) ተቆርቋሪ፣ ተከራካሪ፣ ዘብ ቋሚና ‘አለሁ’ ባይ የኾነው የዶክተር እንዳለጌታ ከበደ ብዕር በ16ኛ መጽሐፉ (አንዱ የአርትዖት ነው) በሐምሌ መጨረሻ 2016፤ ‹ሲጥል› በሚል ረዥም ልብወለድ መጥቶልናል።
፨ ከመጀመሪያው ‹ከጥቁር ሰማይ ስር› ጀምሮ እስካሁኑ ‹ሲጥል› መጽሐፎቹ በተገፉ፣ ትኩረት ባልተሰጣቸውና ባልተቀበልናቸው ማህበረሰቦች ጓዳ እየገባ በተባ ብዕሩ አንባቢን በሃዘን እየለወሰ ወስዶ ከጥቁር ሰማይ ስር እንድናስተውል ይጥለናል።
(ስለዚህ ጉዳይ በሌላ ጽሁፍ እንመለስበታለን)
፨ በ‹ዛጎል› የደብረ ሰምራ፣ በ‹ምሳሌ› የለገ ኦነሲሞስ ነዋሪ ያደረገን እንዳለጌታ፤ በሲጥል የ’ዐሊይ’ መንደር ማህበረሰብ ያደርገናል። ቦለቄና ባቄላ ተመጋቢ፣ የቦለቄ ሾርባ እንጂ ሌላ አልፈልግም ባይ ያደርገናል። ያየናትን ኮረዳ “አንቺ የቦለቄ ሾርባ፣
ተሰርተሽ ሹሩባ” ብለን እናዳንቃለን። መልከመልካም ጎረምሳ ያየች እንስትም “ቡልቅልቅ እንደ ቦለቄ
ብቅልቅል እንደ ባቄላ
ዐየን የወንድ ዛላ!” እንዲሉ ያደርጋል።
፨ ‹ሲጥል› ሃገራዊ ኹነቶችን እያነሳ፣ በ‹ያልተቀበልናቸው› ላይ በስፋት የተዳሰሱትን ጉዳዮች እየመለሰ፣ ማህበረሰብን እየሄሰ፣ በሱራፌል አንደበት ‹‹እንደ ተረት ተሰርታ፣ ረጅም ተረት ተርታ፣ በጊዜ ብዛት ተረታም ትውልድ መፍጠር የቻለች ሃገር!››(90) እያለ ሃገራችን ለገባችበት ማጥ፣ ህዝቦቿ ለደረሱበት መከፋፈል እያዘነ፣ በገጸ-ባህሪያቶቹ በኩል ችግራችንን እየነቀሰ፣ መፍትሄ ያለውንም እየነገረ ሲተርክ “ኋላ እመለስበታለሁ” ብለን የምናስቀምጠው አይደለም፤ በለመድነው ግሩም አተራረክ፣ ቴአትራዊ መልክ ባለው ቃና ሳናስበው አንድ ብለን ሁለት መቶ ሰማንያ እንላለን።
፨ መጽሐፉ ውስጥ ከምናስተውላቸውና ደጋግመን ከምንሰማቸው ድምጾች አንዱ ‹መለየት› እና ‹መለያየት› ነው።
- ሲጀምር <ሀ:ጎህ ሲቀድ>...‹‹አንድ ቀን ትቶኝ ይሄዳል›› የሚል የመለየት ስጋት ባላት ቤርሳቤህ ነው። ሲጨርስ <ኖ: ስንብት> በመለያየት ነው። መጽሐፉ ውስጥ በአንድም ኾነ በሌላም ተደጋጋሚ መለያየት’ን እናያለን። ለምሳሌ፦ የምንተስኖት እናት በሞት መለየት፤ ከቃሏ፣ ከዕምነቷ (ተገዳም ቢኾን) ከሌላ ሰው ጋር በመተኛት (በመጸነስ) መለየት(58-70)፣ የቤርሳቤህ እናት በጫት ሱስ ምክንያት ባሏንና ሁለት ልጆቿን ጥላ መለየት፣ የቤርሳቤህ (የቀድሞ) ባል ለስድስት ወራት አግብቷት በአራተኛው ወር መለየት፣ በኢዩኤል አባት የኔታ እና በወንድማቸው መሪጌታ ‹‹የሚያድናቸው እና የሚታደጋቸውን በመምረጥ››(137) በአስተሳሰብ፣ ዕምነት መለያየት፣ ኢዩኤልም አባቱ የኔታ ‹‹ውጉዝ ከመ አርዮስ›› ብለው የረገሙትን (215) የአጎቱን መንገድ በመከተል ከወላጆቹ (በኑሮም፣ በአስተሳሰብም) መለየት፣ የሱራፌል እና የፍቅረኛው መለያየት (144)፣ ከባለቤቱ ጋር ፍቺ እንዳይፈጽም በ ቢ.አ.ን (ቢገድሉንም አንሞትላቸውም ንቅናቄ) ፓርቲ በመከልከሉ፤ በመጨረሻም ከሚስቱም፣ ከውሽማውም፣ ከፓርቲውም የተለያየው ፍቺ ናፋቂ የፖለቲካ አመራር (154)፣ በገዢው ፓርቲ (በልብወለዱ) ማስፈራሪያ ኋላ ‹‹ይቅርታ አድርጌላታለሁ›› ቢልም እሷ በሰራቸው ስህተት ተለያይተው የነበሩት የአቶ ሥዩም ልጅ መኩሪያ እና ፍቅረኛው(158)፣ ኤች አይቪ ወላጆቿን ከሷ የለየባት የ’ዐሊይ’ ከተማ የስምንተኛ ቢ ክፍል ተማሪ(210)፣ የምንተስኖት በራሱ እጅ ራሱን በማጥፋት መለየት(242)፣ የረዳቱ ሚስቱ ትታው መሄድ መለየት(247)፣ የመሪጌታ በድንገት በመሰወር መለየት(247)፣... በመለያየት ስጋት ጀምሮ በመለያየት የሚያልቅ - ልብን ሃዘን ውስጥ ነክሮ፣ እንደ ገጸባህሪያቶቹ ሁሉ አንባቢውን ‘ዐሊይ’ን መልቀቅ ሳይፈልግ ራሱን መጨረሻ ገጽ ላይ እንዲያገኝ የሚያደርግ ነው።
፨ ሌላው አባትነት ሰፊ ገጽ የተሰጠው ጉዳይ ነው። አባትነትን አጽንዖት ሰጥቶ ያብራራል። ገጸባህሪያቶቹ ከአባታቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት እየተነሳ ታሪኮቹን ያዳውራል። አቶ ሥዩም ‹‹እናትነት በደንብ አልተገለጸም››(56) ቢሉም፤ ደራሲው ግን ስለ አባትነት እንጂ ስለ እናትነት ብዙ ተብሏል የሚል ይመስላል።
፨ ሱራፌል አባቱ ትቶት የሄደና በዚህ ያዘነ የተጎዳ፣ ለእናቱ ልዩ ፍቅር ያለው ነው። በቴአትር ድርሰቱ ገጸባህሪያቶቹ እንደሚነግሩን፣ በህጻንነታቸው አባታቸው ሲመታቸውና ሲቆጣቸው ‹‹ምነው በሞተ!›› ብለው የሚጸልዩ ነበሩ። በሱራፌል እናት በኩል ሰው የሌላቸውን፣ ሰው ያጡ ሰዎችን ያስታውሰናል። ያለ
‹አለሁ› ባይ የሚኖሩትን በማስታወስ ያስተክዘናል።
‹‹ሰው ራበኝ፤ ወንድም ራበኝ፤ የሚጠብቀኝ መጎዳቴንና መጎሳቆሌን የሚያውቅ ወንድም ፈለግኩ።›› (86) ትላለች። ለራሷ ወርቅና ልብስ እየገዛች ጎረቤቶቿን ‹‹ወንድሜ ገዛልኝ! ወንድም መከታ!›› እያለች ‹‹ብቻዬን አይደለሁም!››ን ሰፈርተኛ እንዲያውቅላት ትሻለች። ልጇንም ‹‹ሰው አይራብህ! ወንድም እህት አትጣ!›› (87) ትለዋለች።
፨ በቤርሳቤህ አባት ንጉሡ ያለ እናት ምንም ሳይጎድልባቸው እንዴት እንዳሳደጋቸው አባትነትን በጥቂቱ ያሳየናል። ለአባቷ ህክምና ስትልም የደህንነቱን ሰው በኮንትራት ጋብቻ ታገባዋለች። በዚህም ህይወቷ ላይ አባቷ ያለውን አሻራ ታሳየናለች።
፨ በምንተስኖት ‘አባት’ ተመስገን ደግሞ አባትነት’ን ፍንትው አድርጎ ይገልጻል። አቶ ተመስገን እንደማይወልዱ እያወቁ ‹‹..ተመትቻለሁ፤ ድሮ ወታደር ቤት ሳለሁ የደረሰብኝ ጉዳት አለ፤ አጉል ቦታ ተጎድቻለሁ፣ ግን ለማንም አላወራሁት፤ እናትህም አታውቅ። ማስረገዝ አይኾንልኝም፤ አልወልድም ልጄ! ይህን አውቃለሁ። ሃኪም ነግሮኛል።››(242) ብለው ግን ሚስታቸው አርግዛ ስትወልድ ‹‹ልጁም የእርስዎ ነው›› ብላ ‹‹የምንተስኖት አባት›› እያለቻቸው ምንም ሳይመስላቸው በንጹህ ፍቅር፣ በጥልቅ አባትነት ‘ልጃቸውን’ አሳደጉ። ‹‹ከማን ጋር ወስልተሽ? ከየት ይዘሽ መጣሽ?!›› አላሏትም - ምክንያቱም ‹‹ምስጢሬ ታወቀብኝ›› ብላ ‘ልጄን’ ይዛ እንዳትጠፋብኝ ብለው ፈርተው። ከድህነት ጋር፣ ከማጣት ጋር፣ ከችግር ጋር፤ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እስኪኾን አቅፈውት እየተኙ፣ ትልቅ ልጅም ኾኖ እጁን ይዘው አስፓልት እያሻገሩ አሳደጉት።
አባትነት ረቂቅ ነው
ተዓምር የወጠነው
የዘጠኝ ወር አይደለም
የዘላለም ምጥ ነው።
አባ በቃላቴ ድካምህን ላክም
ሽበት እስኪውጠው የጸጉርህን ክርክም
ገንዘብ አጣህ እንጂ ደሃ አልነበርክም!
ውሽንፍሩ አልፏል...
በእልፍኝ በሳሎንህ፣
ብዙ እንባ ጎርፏል...
ከተከታይ አይንህ።
መብረቁም ስቶናል ትከሻህን ታክኮ
ካንተ ጋር መደህየት ጸጋ ነበር እኮ!
የሚለውን የፈይሰል አሚን ግጥም የሚገልጽ ታሪክ፤ ደራሲው በአቶ ተመስገን ህይወት አሳይቶናል።
፨ በአጠቃላይ መጽሐፉ ብዙ፣ ብዙ የሚብራሩ ጉዳዮችን ያቀፈ ነው። በደንብ ተጠንቶ ሂስ’ም ዳሰሳ’ም ሊቀርብበት የሚገባ ነው፡፡
Sunday, 01 September 2024 20:38
የእንዳለጌታ ሃዘንተኛ ብዕር
Written by ነቢል አዱኛ
Published in
ጥበብ