አዳም ረታ በተለይ ኋላ ላይ ባሳተማቸው ‘እቴሜቴ የሎሚ ሽታ’፣ ‘ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’ እና ‘የስንብት ቀለማት’ ኪናዊ ድርሰቶቹ ውስጥ የተለያዩ ፍልስፍናዊ እሳቤዎች ጎልቶ ይንጸባረቅባቸዋል፡፡ ለአብነትም የድህረ-ቅኝ ግዛታዊነት (postcolonialism) ፍልስፍናዊ እሳቤዎች በእነዚህ ድርሰቶች ውስጥ በስፋት ይነበባል፡፡
ይሄ ማለት ግን እነዚህ የአዳም ኪናዊ ስራዎች በዚህ የድህረ-ቅኝ ግዛታዊነት ፍልስፍናዊ እሳቤ አውድ ውስጥ ብቻ የሚነበቡና የሚፈከሩ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ከእነዚህ ድርሰቶች ውስጥ ቴክስቶችን ወስደን በተለያየ አውድ ሊፈከሩ የሚችሉ አምሳለ-ብዙ እሳቤዎች አሉ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ላይ ግን በዋናነት የአዳም ረታ ድርሰቶች ውስጥ እንዴት የድህረ-ቅኝግዛታዊነት እሳቤዎች እንደተንጸባረቁ በወፍ በረር ለማስቃኘት እሞክራለሁ፡፡
ድህረ-ቅኝግዛታዊነትን
(postcolonialism) በጨረፍታ
ድህረ-ቅኝግዛታዊነት የቁም ፍቺው እንደሚያመለክተው ከቅኝግዛታዊነት (Colonialism) ቀጥሎ የሚመጣ ሥርዓት ማለት አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ የቅኝግዛታዊነት እሳቤዎችና ሌጋሲዎች በተዘዋዋሪ መንገድ በድህረ-ቅኝግዛታዊ ዘመን እንዴት እንደቀጠሉ የሚያትት እሳቤ ነው፡፡ ምንም እንኳን በቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩ ሃገራት ዜጎች ጦር አንስተው ቅኝገዢዎችን ከሃገራቸው ማስወጣት ቢችሉም፣ የቅኝግዛታዊ ሌጋሲዎቻቸውን ግን ማስወገድ አለመቻላቸውን ያትታል፡፡ ይሄ የቅኝግዛታዊነት ውርስ ደግሞ፣ በድህረ-ቅኝግዛት ዘመንም በቅኝተገዢው ማህበረሰብ ነባር ባህል፣ ዕውቀት፣ እሴት፣ ማህበራዊ መስተጋብር…ላይ ከፍተኛ ተቃርኖ እንደፈጠረ የሚያብራራ ዕሳቤ ጭምር ነው፤ድህረ-ቅኝግዛታዊነት፡፡
ድህረ-ቅኝግዛታዊነትን ይበልጥ ለመረዳት ቅኝግዛታዊነትን (Colonialism) በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አፍሪካዊው ፈላስፋ ቫሌንቲን ሙድምቤ (Valentin Mudimbe) ‘The Invention of Africa’ በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ እንዳሰፈረው፣ በአንድ በኩል ቅኝግዛታዊነት ማለት ቅኝገዥዎች የቅኝ ተገዥውን ሃገርና ማህበረሰብ በሃይል በመቆጣጠር፤ የተፈጥሮ ሃብቱን አሟጦ ወደ ምዕራቡ ዓለም የመላክ ሂደት ነው፡፡ የቅኝገዢዎች ብዝበዛ ቀጣይነት እንዲኖረው ደግሞ፣ የቅኝተገዥው ማህበረሰብ ማንነታዊ መሰረትን እንደገና የማዋቀር፣ የመቅረጽና የመበየን ስራ ይሰራል፡፡ እንዲሁም ማንነትን እንደገና የመበየንና የመቅረጽ ሥራ በቅኝገዢዎች ከተሰራ በኋላ፣ የስልጣን ተዋረዱ ሳይዛነፍ እንዲቀጥል የሚያስችሉ የፈጠራ ተረኮችን ሰርተው ያሰርጻሉ፡፡ ይሄ ማለት ቅኝተገዥዎች በዚህ የሃይል ተዋረድ ውስጥ ቦታቸው የተገዥነትና ጥገኝነት መሆኑን በሃቲት (discourse)፣በሥነ-ዕውቀት፣ በተረክና በሌሎችም ይስሙላ ሳይንሳዊ ምርምሮቻቸው አማካይነት ተፈጥሮኣዊ ዕውነታ አድርገው በማህበረሰቡ ውስጥ እንደሚያሰርጹ ሙድምቤ በመጽሐፉ አስፍሯል፡፡
ህንዳዊቷ የድህረ-ቅኝግዛታዊነት ፈላስፋ አኒያ ሉምባ (Ania Loomba) ‘Colonialism/ Postcolonialism’ በተሰኘ መጽሐፏ ደግሞ፣ ይህንን የቅኝግዛታዊ ሃቲት (colonial discourse) እና ተረክ ከስር መሰረቱ መረዳትና ይኸ ተረክ በድህረ-ቅኝግዛት ዘመንም እንዴት እንደቀጠለ ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው ትላለች፡፡ ቀጠል አድርጋ፣ “ቅኝአገዛዝ በታሪክ ሂደት ውስጥ ሁለትዮሻዊ ተቃርኖ (binary opposition) በመፍጠር አደገኛና ውስብስብ ተረኮችን ፈጥሯል፡፡ አውሮፓን ወይም የምዕራቡን ዓለም ‘እኛ’ በሚለው ጎራ ውስጥ በማስገባት ከምዕራቡ ዓለም ውጪ ያለውን ማህበረሰብ ደግሞ ‘ሌሎች’ (Others) በሚለው ጎራ መድቧቸዋል፡፡ ይህን የሁለትዮሻዊ ዓለም (west-east) ተረክ አውሮፓውያን ለራሳቸው ያላቸውን ምስልና ከአውሮፓ ውጭ ባሉ ሕዝቦች መካከል አለ የሚሉትን የልዩነት መስመር ለማስመር ጉልህ ሚና ተጫውቷል” ትላለች፤ አኒያ ሉምባ፡፡
ለአብነትም አውሮፓውያንን፤ “የሰለጠኑ”፣ በ”አመክንዮ ታግዘው ማሰብ የሚችሉ” እና ዕውቀታቸው ለሌሎችም “አርዓያ መሆን የሚችል” አድርገው ሲበይኑት፤ በአንጻሩ ከአውሮፓ ውጪ ያለው ማህበረሰብ ደግሞ “ያልሰለጠነ”፣ ስሜቱን “መግራት ያልቻለ” አድርገው ፈርጀውታል፡፡ እንዲሁም የቅኝተገዢው ማህበረሰብ ነባር እሴቶችን ለመዘመንና አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት የ”ማያስችል” አድርገው በይስሙላ ሳይንሳዊ ጥናቶቻቸው ጭምር አስደግፈው ማሳመን ችለዋል፡፡ ስለዚህ የቅኝተገዢው ማህበረሰብ ‘እንዲዘምንና እንዲያድግ አውሮፓዊ ዕሴቶችን እንደወረደ መቀበል ይኖርበታል’ የሚለው የቅኝግዛታዊ ሃቲት፣ በቅኝተገዢው ማህበረሰብ ልሂቃን ጭምር ተቀባይነት ማግኘቱን አኒያ ሉምባ በመጽሐፏ ታብራራለች፡፡
ሌላኛው ዕውቁ የድህረ-ቅኝግዛታዊነት ፈላስፋ ኤድዋርድ ሰይድ ‘Orientalism’ በተሰኘ ዝነኛ መጽሐፉ፣ ምዕራባውያን አሁን የምንኖርበትን ዓለም፣ የእነሱን ሁለንተናዊ የበላይነት መሰረቱ ሳይናወጽ እንዲቀጥል ማድረግ ችለዋል፡፡ አውሮፓ የሁሉም ነገር ማዕከልና መነሻ ተደርጋ እንድትወሰድ ማድረግ የቻሉት ስልጣን-ወ-ሃይል (power) እና ዕውቀት በፈጠሩት ትግግዝ አማካይነት ነው ይለናል፡፡ ይህም ማለት አውሮፓ-መር ( Eurocentric) የሆነውና በዓለም ላይ የተሰራጨው እውቀት ሥረ-መሰረቱ፣ ከአውሮፓውያን ግኝግዛታዊ ሃቲትና ተረክ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው የመካከለኛ ምስራቅ ታሪካዊ ሁኔታን እንደማሳያ በማቅረብ አብራርቷል፡፡
ከዚህ አንጻር፣ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ እየኖርንባት ያለችው ይህች ዓለም፣ በዚህ ቅኝግዛታዊ ሃቲትና ተረክ ነው የተበጃጀችው፡፡ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አንስቶ ቅኝአገዛዝ “አበቃ” ቢባልም፣ መልኩን በመቀየር ከአውሮፓ ውጭ ባሉ ሃገራት የትምህርት ስርዓት፣ የመንግስት አወቃቀር፣ የባህል ዘርፍ…ውስጥ ሰርጾ በመግባት ህልውናውን ማስቀጠል ችሏል፡፡
የድህረ-ቅኝግዛታዊ አሳብያንና ስራዎቻቸውም ከትናንት የተሻገሩ የቅኝገዥዎች ሌጋሲዎቻቸውን በዛሬው አስተሳሰባችን፣ የህይወት ዘይቤያችንና ሃገራዊ ተቋሞቻችን ውስጥ እንዴት እየተተገበሩ እንዳለ ያሳዩናል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት የአዳም ረታ ኪናዊ ድርሰቶችም ውስጥ እንዴት የቅኝግዛታዊ ሃቲቶችና ተረኮች በትውልዱ ውስጥ ሰርገው እንደገቡና እውነት ተደርገው እንደተወሰዱ በገጻባህርያቱ አማካኝነት አጉልቶ ያሳየናል፡፡
አዳም ረታን እንደ ማህበረሰባዊ ሃያሲና ፈላስፋ
አዳም በድርሰቶቹ፣ ‘አድዋ ላይ ቅኝ ገዥዎችን ድል አድርገን መልሰናል’ የሚለው ኩራታችን አፋዊ እንጂ ከልብ የመነጨ እንዳልሆነ በላቀ ኪናዊ ውበትና ጥልቅ መረዳት ውስጥ ሆኖ ገልጦ ያስነብበናል፡፡ ከ’የስንብት ቀለማት’ (ገጽ፣24) አንድ ሰበዝ እነሆ፤ “…ቅኝ አልተገዛንም ብለው ጉራ እየነፉ በየቀኑ ግን የተገዥነት አገልግሎት ይሰጣሉ” ይላል፤በማህበራዊ ሃያሲነት የታጨው ገጸ-ባህሪ ዮሃንስ ወላይሶ፡፡ ትውልዱን በሰላ ብዕሩ ይሄሳል፡፡ ማህበረሰባዊ ነጻነታችንን እና የስልጣኔ አሻራዎቻችንን እንደ ልቃቂት አውጥተን ጥለን ፈረንጅ ለመምሰል የተጓዝንባቸው የሕማም ዓመታትን እንደገና እንድናጤናቸው አዳም በተለያዩ ገጸ-ባህሪያት በኩል አድርጎ ይገስጸናል፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት ከራሳችን ጋር እንታረቅ ዘንድም ይወተውታል፡፡
እንደሚታወሰው ከድህረ-አድዋ በኋላ በመንግስት ደረጃ ከተያዙ ግዙፍ ዕቅዶች መካከል አንዱ የዝመና (moderenization) ፕሮጀክት ነው፡፡ የዝመና ፕሮጀክቱ ዋነኛ ማጠንጠኛው እንደ አውሮፓውያኑ “መሰልጠን” የሚል ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ የአውሮፓውያንን ፈለግ በመከተል ኢትዮጵያን አውሮፓ እንድትመስል ማስቻል በሚል ተረክ ነበር የታጀበው፡፡ የአውሮፓን “መንገድ እንከተል” በሚለው የኢትዮጵያ የዝመና ፕሮጀክት ውስጥ ጎልቶ የተንጸባረቀው የኢትዮጵያ ‘ነባር እሴቶች ሀገር ለማዘመን ወይም ለማሳደግ ብዙም ፋይዳ እንደሌላቸው፤ በአንጻሩ እንደ አውሮፓውያኑ ለመዘመን የእነሱ የሆነው ነገር ሁሉ እንደወረደ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል’ በሚል እሳቤ የተቃኘ ነበር፡፡
ይህ ታሪካዊ የዝመና ፕሮጀክት በ’የስንብት ቀለማት’ ውስጥ የባህል ሃያሲ በሆነው ገጸ-ባህሪ ዮሃንስ ወላይሶ እንዲህ ይተቻል፤ “የኢትዮጵያ ምሁራን ሲሰለጥኑና ዘሮቻቸውን ሊያሰለጥኑ ሲፈልጉ መጽሐፎች ይጽፋሉ፡፡ በነዚህ መጽሐፎች ውስጥ የሚጠይቁት አንድ ዋነኛ ጥያቄ ‘እኔ ምን አለኝ?’ ሳይሆን እነሱ ምን አላቸው? ነው አሉ፡፡ …ካላመናችሁ ‘ጃፓን እንደምን ሰለጠነችን’ አንብቡ…” (የስ.ቀ፣ 785)፡፡
በእርግጥ የባህል ሃያሲው ትችት ስላቅ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ደረቅ ሃቅ ነው፡፡ ሳናላምጥ የዋጥናቸው የቅኝግዛታዊ ሃቲቶችና ተረኮች የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ታዲያ እንደወረደ ተቀብለን ከተጋትናቸው እሳቤዎች መካከል “እውቀት”፣ “ስልጣኔ”፣ የተቋማት ግንባታ፣ ቁሳዊ ልማት፣ ርዕዮታዊ መረዳት…ከአውሮፓውያኑ እንደሸቀጥ ወደ ሃገር ውስጥ አስገብቶ በየቦታው የሚከፋፈል አድርጎ የመረዳት ሥሁት አረዳድ አንዱ ነው፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ እውቀት በተውሶ ለማምጣት ከአንዱ ሃገር ወደ ሌላ ሀገር ስንባጅ አንድ ክፍለ ዘመን መሻገራችን ጥሩ አብነት ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ጣሊያን በ1928 ዓ.ም እንደገና ተመልሶ መጥቶ ኢትዮጵያን ለአምስት አመት በሃይል ይዞ ሲቆይ ያደረገው ዋነኛ ነገር፣ የምዕራቡን ዓለም ሃያልነት ከፍ ከፍ በማድረግ፣ የኢትዮጵያን ኋላቀርነት ማጉላት ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት የሚያስተሳስሯቸው እሴቶች እንዲላሉና እንዲበጠሱ በመስራት፣ በምትኩ ከፋፋይ ፖሊሲዎችን የማንበር ሥራ ነው የሰራው፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ የጣሊያን ቅዥግዛታዊ ሃቲት፣ ከ”ነጻነት’’ በኋላም መቀጠሉ ነው፡፡ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ‘Slaves of State, Intellectuals of development in Ethiopia…’ በተሰኘው መጽሐፉ፣ ይህንኑ የጣሊያን ቅኝግዛታዊ ሃቲት እንዴት እንደቀጠለ (በገጽ፣209) እንዲህ ይገልጿል፤…በድህረ ጣሊያን “የቀጠለው የአምስት አመቱ የጣሊያን ሌጋሲ ዘመናዊ ተቋማትና ግብዓቶች፣ እጅግ የጠበቀ ማዕከላዊ አስተዳደር ለመመስረት ውለዋል፡፡ ንጉሱን (አጼ ኃይለ ሥላሴን) ማዕከል ያደረገ ከላይ ወደ ታች የተዘረጋና ብዙሃኑን የሚቆጣጠር ስልት ከጣሊያን ፖሊስ በመዋስ ዘርግተዋል፡፡ በአጠቃላይ የጣሊያን አገዛዝ ሌጋሲ፣ የመንግስት መር ልማታዊነት እና ፖለቲካዊ ነክ ፖሊሲን ቅርጽ በማስያዝ ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳለው” አስረጆችን ጠቅሶ አብራርቷል፡፡
ብቻ “የአውሮፓ የስልጣኔ መንገድ”ን በመከተል ካለንበት ‘ጨለማ ወጥተን’ ልክ እንደ’ሰለጠኑት’ ሃገራት በ’ብርሃን’ መንገድ ለመጓዝ በሚል እዚህም እዚያም ባጀን፡፡ ሙከራው ግን ከቀውስ ወደ ቀውስ ከመሸጋገር ያለፈ አንድ ስንዝር እንኳ ፈቅ እንድንል አላገዘንም፡፡ ለምን?...
አዳም ረታ ይህንን የህማም ጉዟችንን እንደ ከያኒ ሥነውበታዊ ፍኖቱን ሳይለቅ፤ እንደ አሳቢ ደግሞ ከሥነ-ዕውቀታዊ ከፍታው ሳይወርድ ገልጦ ያስነብበናል፡፡ ታመን እንዳልታመምን በማስመሰል፣ የመጣንበትን ሥሁት መንገድ ዳግም እንድናጤነው ይወተውታል፡፡ ከህማማችን የምንፈወስበት መውጫ መንገዱን ጭምር በድርሰቶቹ ውስጥ ያሳየናል፡፡
አዳም ልክ እንደ ድህረቅኝግዛታዊ ፈላስፎች፣ ቅኝገዥዎች ኢትዮጵያን በሃይል ወርረው በመያዝ ለብዙ ዓመታት ባይቆዩም፣ ቅኝግዛታዊ ሃቲቶቻቸው ግን በትውልዱ ልብ ውስጥ ሰርጾ መግባቱን በድርሰቶቹ ይተርካል፡፡ የቅኝገዢዎች የህይወት ዘይቤያቸውን፣ የአገዛዝ ስልታቸውንና ዕቅዳቸውን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ተቀብለን እየተገበርነውና እየኖርነው እንዳለ ከመጣንበት የትናንትናው መንገድ ሰበዞችን እየመዘዘ ይወቅሰናል፡፡
“ባዴ [ፈረንጅ] የተለየ ብሩህ አይደለም ብለው የነዘነዙኝ፣ በባዴ ቅኝ ገዥዎች ራሳቸውን እንዲጠሉ ጥልቅ ትምህርት የወሰዱና ዛሬም ከእነሱ እግር ስር የማይጠፉ፣ ወገናቸውን ባዴ በቀደደላቸው መንገድ የሚቀረቅቡ ነጋዴዎች ናቸው፤” ይላል (የስንብት ቀለማት፣ ገጽ-23)፡፡ …ይህቺ ራሳቸውን የ”ወርቃማው ትውልድ” ወይም የ”ያ ትውልድ” አባላት ነን ለሚሉት አብዮተኞች የተሰነዘረች ትችት ነች፡፡ ትችቷ ለዚህኛውም ትውልድ በሚገባ ትሰራለች፡፡ እስኪ ይህቺን ትችት ከሌላ ማዕዘን እንመልከታት…
ትልቁ አሳቢና ሳይካትሪስት ፍራንዝ ፋኖን ‘Black Skin, White Masks’ በተሰኘው መጽሐፉ፣ የቅኝተገዢዎች (የጥቁሮች) የታህታይ ቀውስ (Inferiority complex) ምንጩ የ”ቅኝግዛታዊ ሃቲት” ነው ይላል፡፡ የቅኝግዛታዊነት ባህሪይ በራሱ አገላለጽ እነሆ፤ “…colonialism not only exploits but dehumanize and objectifies the colonized subject.”…ፋኖን፤ የቅኝግዛታዊ ሃቲት በቅኝ ተገዢው ግለሰብ ሥነ-ልቦና ውስጥ እንዲሰርጽ ያደረገበት መንገድ ደግሞ ግለሰቡ የወጣበትን ማህበረሰብ ታሪኩን፣ ማህበራዊ እሴቱን ዋጋ በማሳጣትና በማጥፋት ከትውስታው ማህደር እንዲፋቅ በማድረግ፣ በምትኩ የነጭ የበላይነትን ተፈጥሮኣዊ አድርጎ የሚቀበልና እሱን ለመምሰል የሚሞክር ግለሰብ ሆኗል ይላል፡፡ ከላይ ከ’የስንብት ቀለማት’ የመዘዝናት ሂስም ይህንን ዕሳቤ መነሻ ያደረገች ይመስላል፡፡
የባህል ሃያሲው ዮሃንስ ወላይሶ ይቀጥላል፤”…የአገራችንን መልካም ታሪክ እንጥቀስ ስንል ዐይኖቻቸው ቀልተው ‘the past is a foreign country’ (ያለፈው ዘመን ባዕድ አገር ነው) ይሉናል፡፡…የነጭና የጥቁር ተራቾች ግን ታሪክ አስፈላጊ አይደለም……ያውም ደብተራ የዘባረቀው ብለው ለምን የታሪክ ምሁር እንደሆኑ ግን አይነግሩንም፡፡…የባዕድ ደብተራ የጻፈውን ግን ያምኑታል” ይላል፤’የስንብት ቀለማት’ (ገጽ፣23)፡፡
እዚህ’ጋ ያለፈውን ታሪክ፣ የማህበረሰቡን ዕሴትና ዕውቀት በጭፍን ማጥላላትና መናቅን የመሰልጠን መንገድ አድርገን፣ እዚህ ለመድረሳችን በርካታ አስረጆችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሳዛኙ ነገር እየሄድንበት ያለውን ይኸው ስሁት መንገድን ቆም ብለን ለመረዳት እንኳ ጊዜ የሌለን መሆኑ ነው፡፡ የማጥላላት ዘመቻውንም የሚያጋፍረው፣ መድረኩን የያዘው ‘ሰለጠንኩ’ ወይም ‘ተማርኩ’ ባዩ መሆኑ ደግሞ ነገሩ ይበልጥ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡
አፍሪካዊው ፈላስፋ ሙድምቤ ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፉ እንዳሰፈረው፣ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ቢያንስ ነጭ ቅኝገዥዎች የአፍሪካን መሬት ለቀው ቢወጡም በእነሱ ቦታ “ጥቁር ቅኝገዥዎች” ወይም ልሂቃን ተተክተዋል ይላል፡፡ በምዕራቡ ዓለም የቅኝግዛታዊ ሃቲትና ዕውቀት ተኮትኩተው ያደጉት አፍሪካውያን፣ ቀድሞ ቅኝገዢዎች ሲከውኑት የነበረውን ነገር በአንድም ሆነ በሌላ አቅጣጫ አስቀጠሉት እንጂ ውርሱን ለማስቀረት አልጣሩም ሲል ይተቻል፡፡ “ነጭ ቅኝገዥዎችን የተኩት አፍሪካውያን የፖለቲካ ልሂቃን፣ ከምዕራቡ ዓለም ሥርዓት ወይም ተቋማት ጋር ያላቸው ግንኙነት የጌታና የሎሌ ወይም የጥገኝነት እንዲሆን ያደረገውም ይኸው የቅኝአገዛዝ ሌጋሲ ነው” ይላል፡፡ በራሱ አገላለጽ፤ “…colonialism should have produced a body of knowledge on the means of exploting dependencies…”እንዲል፤ሙድምቤ፡፡
በሃገራችን ኢትዮጵያም የሆነውና እየሆነ ያለው ይኸው የቅኝ አገዛዝ ማዕከላዊ እሳቤ፣ ከትምህርት ስርዓታችን አንስቶ እስከ ፖለቲካዊ መድረኮች ሞልቶታል፡፡ እውቀት ከሌሎች ሃገራት ተፈልጎ የሚመጣ እንጂ ከራሳችን አንጥረን ማውጣት እንደምንችል ሊገለጥልን እንዳልቻለ የምዕተ-ዓመቱ ጉዟችን ጥሩ ምስክር ነው፡፡ አዳምም በድርሰቶቹ ይህንን በደመነፍስ የሚደረግ ጉዞ ነው፣ በኪናዊ ድርሰቶቹ አጥብቆ ለመሄስ የጣረው፡፡
በ’እቴሜቴ ሎሚ ሽታ’ ሰዓሊና ሃያሲ መስኮት ገረሱን፣ የዘመኑን ሁኔታ እንዲተነትን፣ እንዲሄስና እንዲፈክር አዳም ረታ ያጨው ይመስላል፡፡ መስኮት በተለይ ፈረንጅ ያልነካውን ወይም ‘ያልባረከው’ ነገር ፋይዳ ቢስ ለሚያደርጉና የፈረንጅ እውቀት የሁሉም ነገር መመዘኛ አድርገው ለተቀበሉ የዘመኑ ወጣቶች፣ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በሚጽፋቸው ጽሁፎችና በሚሰጣቸው ቃለ-መጠይቆች ላይ ትችቱን ይወረውራል፡፡ እንዲህ ይላል፤”እዚህ አዲስአባ ውስጥ አንዳንድ ቦታ እንጀራ በቢላ ሲቆረስ እናያለን፡፡ ይኼን በቢላ የመቁረስ ባህል የጀመረው ማን ነው? ለምን ጀመሩ? እንጀራን በቢላ መቁረስ እንጀራን ወደ ዳቦ ለማውረድ መጣር እንደሆነ አልተረዱም? የእኛ ትልቁ ችግራችን ዕውር ኮፒ አድራጊዎች መሆናችን ነው፡፡ ፈረንጅ ዳቦ ሲቆርስ ዐይተን ከዛ ያን በጭፍን ያለ ጥየቃ ያለ ትንታኔ ተበደርን፡፡ የዚህ ችግር መነሻው በራሳችን ማመን አለመቻላችን ነው፡፡ በራሱ የማያምን ሕዝብ ወደ ባርነት የሚጓዝ ነው…” (እቴሜቴ፣ 16)፡፡
ከላይ ከ’እቴሜቴ’ የወሰድኩት የመስኮት ሃሳብ ከማዕምር ጥናት ጋር በትይዩነት ትንሽ እናፍታታው፡፡ ማዕምር መናሰማይ (ዶ/ር) “A Critical Dialogue between Fifteen and Twenty first Century Ethiopia” በተሰኘው ጥናቱ፣ ያለፉት ሦስት የመንግስት ስርዓቶችን (አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ ደርግና ኢህአዴግ) ኢትዮጵያን ለማዘመን የሄዱበትን መንገድና ዘይቤ “ፍዝ ዝመና” (passive modernization) በማለት ሰይሞታል፡፡ ይህም ማለት በልማት ስም ምዕራባዊ ለመምሰል በመሞከር፣ በምዕራቡ ዕውቀትና ሥነ-ዘዴ ላይ በመመስረት ልማት ለማምጣት ያደረጉትን ያልተሳካ ሙከራ ነው፣ “ፍዝ ዝመና” ሲል የጠራው፡፡ ይህ ፍዝ ዝመና ሃገር በቀል ዕውቀቶችን፣ እሴቶችን፣ እይታዎችን፣ ባህሎችንና ተቋማትን አፈራርሶ በምዕራቡ እሳቤ የመተካት ሙከራ ነው ሲል ይተቻል። የዚህ ውጤትም በሃገሪቱ ውስጥ መልከ-ብዙ ቀውስና ምስቅልቅሎሾችን አስከትሏል፡፡ በራሱ አገላለጽ፤ “…the failure of modernization in Ethiopia is also the failure of knowledge: of Ethiopia and of modernization…” ይላል፡፡
ታዲያ የ’እቴሜቴ ሎሚ ሽታ’ው መስኮት ገረሱ በጭፍን እየሄድንበት ካለው መንገድ ለአንዳፍታ ቆመን እንድናስብ ድምጽ አውጥቶ ይጣራል፡፡ ለዚህ መድሃኒቱ የተገፉትን ሃገር በቀል እሴቶች ወደ መድረኩ መመለስ ነው ይላል፡፡ መስኮት በስዕል ስራዎቹና ለጋዜጦች በሚሰጣቸው ቃለመጠይቆች አማካኝነት ይህንን ሃሳቡን ያስተጋባል፡፡ ለአብነትም መስኮት አስቀድሞ ይከተለው የነበረውን የ”አብስትራክት ኤክስፕረሽኒዝም” (Abstract expressionism) የአሳሳል ዘይቤ በመተው፣ የሃገር በቀል ዕውቀትና ልምድን መሰረት ያደረገ “ተነካናኪ” ወይም “ቅርባዊነት” የተሰኘ የአሳሳል ዘይቤ ፈጥሯል፡፡
ቅርባዊነትን (እቴሜቴ፣15) መስኮት ሲያብራራው፤ “በአገራችን የባህል አሳሳል የበላይነት ቦታ ያላቸውን ዐይንና ፊትን በተለይ ዐይንን በሌሎች የስሜት ሕዋሳትና ብልቶች ቀስ በቀስ መተካትና ቢቻል እኩል ለማድረግ የሚሞክር የአሳሳል ዘይቤ ነው፡፡ በባህል ስዕሎቻችን ዐይን ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ዐይን ማለት ርቀትና ሃሳባዊነት ሲሆን፣ የየቀኑ ኑሮአችን ግን የቅርብ፣ አፋኣዊና ተነካናኪ ነው፤” በማለት ይቀጥላል፡፡ ከዚህ በመነሳት ክፍለ ዘመን የተሻገረው የተቃወሰ ጉዟችን ዳግም መታደስ የሚችለው፤ ከራሳችን ጋር እርቅ ማውረድ ስንችል፤ ወደ ራሳችን አተኩረን መመልከት ስንደፍር እንደሆነም አዳም በመስኮት ገረሱ በኩል ይነግረናል፡፡ የድህረ-ቅኝግዛታዊነት ፈላስፎችም ከቀውስ መውጫ አንዱ መፍትሄ ይሄው መንገድ እንደሆነ ነው የሚያትቱት፡፡
መዓምር ከላይ በተጠቀሰው ጥናቱ አጽንኦት ሰጥቶ እንዳሰፈረው፣ “የኢትዮጵያ የዝመና ፕሮጀክት ሂደት ነው መሆን ያለበት፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ዋነኛ የዝመና ፕሮጀክት መሰረትና መመዘኛ መሆን ያለበትም ከቁሳዊ እድገት ይልቅ የራሳችን የሆነውን ዕውቀትና ሥነዘዴ የማሰስ ሂደት ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ የዝመና ፕሮጀክት ዋነኛ መሰረቱና ማጠንጠኛው ራስን ከማወቅ ጋር መያያዝ ይኖርበታል፡፡ ታሪክን፣ ባህልን፣ ሃገር በቀል ተቋማትንና ዕውቀትን… በጥልቀት ማጥናት፣ መተንተንና መሄስ ሥለራሳችን ይበልጥ ለማወቅ ያስችለናል፡፡ ከራሱ ማንነትና የኋላ ታሪክ ጋር የታረቀ ሃገር፣ ዛሬና ነገውን የተሻለ ማድረግ የሚችለውም በዚህ ሂደት ነው” ይላል፡፡
አዳም ረታም ልክ እንደ ድህረ-ቅኝግዛታዊ ፈላስፎች ራስን መመርመር፣ ማጥናትና መሄስ ከገባንበት የተቃርኖ ቀውስ መውጫ መንገድ መሆኑ በድርሰቶቹ ደጋግሞ ያትታል፡፡ በኪናዊ ድርሰቶቹ ውስጥ ልክ እንደ ድህረ-ቅኝግዛታዊ ፈላስፎች በታሪክ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙንን ስብራቶች ገልጦ ያሳየናል፡፡ እነዚህን ስብራቶች ለመጠገን የሄድንባቸው ስሁት መንገዶችን ይሄሳል፡፡ ከምንም ነገር በላይ ራስን ማወቅ፣ መመርመርና መሄስ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመድረስ አማራጭ መንገድ አድርጎ ያቀርባል፡፡ አዳም ረታ ልክ እንደ ድህረ-ቅኝግዛታዊ ፈላስፎች ሁሉ ጥልቅ የሆኑ ማህበራዊ ሂሶችን ከላይ በተጠቀሱት ስራዎቹ ሰንዝሯል፡፡
Sunday, 01 September 2024 20:40
አዳም ረታን እንደ ፈላስፋ
Written by አብርሃም ገብሬ ደቢ
Published in
ጥበብ