Monday, 02 September 2024 12:06

አዲሱን ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነት!

Written by  ሙሉእመቤት ጌታቸው
Rate this item
(1 Vote)


       አዲሱ ትውልድ የነገ  መሪ፤ አምራች ኃይልና ሃገር ተረካቢ ነው፡፡  ስለዚህ ትውልድን  መቅረጽ ማለት፦ የአዲሱን ትውልድ የፈጠራ ችሎታ፤ ማህበራዊና ስሜታዊ ብልሃቶች፤ ስነምግባራዊ  እሴቶች በማዳበር  ወደፊት ለሚያጋጥሙት   ፈተናዎችና  መልካም  አጋጣሚዎች  እራሱን  እንዲያዘጋጅ መርዳት  ነው፡፡ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በርሕራሄ፤ በመቻቻልና በቁርጠኝነት በመምራት  አዎንታዊ  ለውጥ ማምጣት  እንዲችል  ማዘጋጀት ነው፡፡  የሚጠበቅበትን  ትልቅ ኃላፊነት አውቆ  የሚቀበል፤ ሙሉ ኃይሉን ተጠቅሞ ግዴታውን ለመወጣት፤ ሃገራዊና  ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት እራሱን ያዘጋጀ   ብቁና ሙሉ ሰው  መፍጠር ነው፡፡  ይህ የለውጥ ኃይልና  የሃገር ተስፋ ነገውን ማሳካት እንዲችል፤ የመንከባከብ፣ የማስተማር፣ በአርአያነት የመምራት ትክክለኛ አቅጣጫ የማሳየት  ኃላፊነት የያንዳንዱ ዜጋ ተግባር  ወይም  የሁሉም ሰው የጋራ ሥራ ነው፡፡
አንድ በሥራ አጋጣሚ ያገኘኋቸው  ከሩዋንዳ  የመጡ  ትልቅ ሰው የሩዋንዳ ገጠመኛቸውን እንዲህ አጫወቱኝ ፡-
ሩዋንዳ የሄድኩት በስራ ምክንያት ነበር፡፡ ሩዋንዳ ከገባሁ ከጥቂት ቀናት በኋላ  ወደ ሥራ ቦታ መሄድ ስለነበረብኝ፣ አረፋፍጄ ኮንትራት ታክሲ ፍለጋ ወጣሁ፡፡ ካረፍኩበት ሆቴል ወጥቼ  መንገድ  ላይ ቆም ከማለቴ አንድ በፍጥነት  የሚሽከረከር ታክሲ ሲያልፍ  አስቆምኩት፡፡ ጠጋ ብዬም  የምሄድበትን ነግሬ እንዲያደርሰኝ  ጠየቅሁት፡፡ የእጅ ሰዓቱን ተመልክቶ፣ ጥቂት ካመነታ  በኋላ  ግባ  አለኝ፡፡ ”ምነው ችግር አለ?“ አልኩት፣ ሲያመነታ ስላየሁት፡፡ ”አይ ችግር የለም ግን  የምቸኩልበት ጉዳይ ስላለኝ  አልደርስ ይሆን? ብዬ ነው“ አለኝና ጉዞ  ጀመርን፡፡  
በመንገዳችን ላይ  ለሃገሩ እንግዳ  መሆኔን  ነግሬው፣ ስለ ሃገሩም ስለ እራሴም   እየተጨዋወትን አንዳንድ ጊዜ ፍጥነት ሲጨምር ቀስ በል እያልኩት ስንጓዝ፣ በቅጽበት  የመኪናውን  ፍጥነት ቀንሶ  ከመንገዳችን  በስተግራ  በኩል ወዳለው  መንገድ በትኩረት  ሲመለከት፣ አንዳች የሚያስደነግጥ ነገር እንዳየ ስለገባኝ፣ እኔም ትኩረቴን ወደዚያው አደረግሁ፡፡ የሚታየኝ ነገር አልነበረም፡፡አሽከርካሪው በፍጥነት መሪውን አዙሮ ትኩረቱን ወደሳበው አቅጣጫ ማሽከርከር ጀመረ፤ ፊቱ ላይ የግርምትና የብስጭት ስሜት ይነበባል፡፡ ምን  እንደተፈጠረ ጠየቅሁት፤ አልመለሰልኝም፡፡
አንድ ሌላ መንገድ ላይ ደረስን፡፡ በመንገዱ ዳር እድሜው  በግምት 11 ዓመት የሚሆን ታዳጊ በእግሩ ጠጠር እየመታ ይጓዛል፡፡ ታክሲው አጠገቡ ደርሶ በድንገት ቆመ፡፡ ልጁ ደንግጦ ዞር አለ፡፡ አሽከርካሪው በፍጥነት በሩን ከፍቶ ወጣና የልጁን ክንድ ጨምድዶ ይጠይቀዋል፤ ልጁም በድንጋጤ ይመልሳል፡፡ ጥቂት ተጨቃጨቁ፡፡ የሚነጋገሩት በአካባቢው ቋንቋ ስለነበር ምን እንደተባባሉ አልሰማሁም፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁለቱም ተያይዘው ታክሲው ውስጥ ገቡ፤ አሁንም  አልገባኝም፡፡
ታክሲዋ አቅጣጫዋን ቀይራ በፍጥነት መጓዝ ጀመረች፡፡ ለደቂቃዎች ዝምታ ሰፈነ፡፡ “ወዴት  እየሄድን ነው?” አልኩ፤ ግራ በተጋባ ስሜት፡፡ አሽከርካሪው ዞር ብሎ “በጣም ስለተበሳጨሁ ነው ይቅርታ፤ ከመጀመሪያው መንገር ነበረብኝ”  በማለት ታሪኩን ይነግረኝ  ጀመር፡፡ “ይህ ልጅ ተማሪ ነው፤ በትምህርት ሰዓት   መንገድ ላይ መገኘት አልነበረበትምና  ለምን? ስለው  ወላጆቹ እንዳስቀሩት ነገረኝ  እናም ለማረጋገጥ ወደ ቤተሰቦቹ እየሄድኩ ነው” አለኝ ፡፡
“የቅርብ ዘመድህ ነው?” አልኩት፤ “አይ ዜጋ ነው” ሲል መለሰልኝ ፡፡ ምን ማለቱ እንደሆነ ስላልገባኝ ዝም አልኩ፡፡ እርሱም እንዳልገባኝ ገብቶት ነው መሰል፣ ንግግሩን በመቀጠል፤ “አየህ፤ እኛ ሩዋንዳውያን በ1994ቱ የዘር ግጭት ብዙ ወገኖቻችንን፣ ንብረቶቻችንን፣ አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነታችንን፣ ሞራላችንን፣ማንነታችንን  አጥተናል፡፡ በአጠቃላይ ተነግሮ የማያልቅ ችግር አሳልፈናል፡፡
”ከዚህ በኋላ ያንን  ችግር  መድገም አንፈልግም፤ ስለዚህ  ሁሉም ሰው ችግሮችን  ቀድሞ ለመከላከል በንቃት የመጠበቅ፣ በተሰጠው ኃላፊነት ላይ ጠንክሮ የመሥራት፣ ኃላፊነቱን የመወጣት፣ ሕግ የማክበርና የማስከበር፣ ትውልድን የመቅረጽና ብቁ ዜጋ የማፍራት ሃገራዊ ግዴታ አለበት፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ዜጋ ከሥርዓት የወጣ ነገር ሲያይ፣ በተለይ  ደግሞ ሃገር ተረካቢው ትውልድ ላይ  ከቻለ ማስተካከል አሊያም ለሕግ ማቅረብ ግዴታው ነው፡፡  ለዚህ ነው ወላጆቹን ማግኘት የፈለግሁት፡፡ ጥፋቱ  የእርሱ ከሆነ እራሱ አሊያም  ቤተሰቡ በሕግ  ይቀጣሉ፡፡” ብሎ ሳይጨርስ ልጁ የሆነ ነገር ተናገረ፡፡ ታክሲዋ ወደ ቀኝ ታጥፋ  መንደር  ውስጥ ገባን፡፡
ብዙም ሳንጓዝ በአንድ ጎን ያዘመመ ጎስቋላ ቤት አገኘን፡፡ ታክሲዋ ቆመችና ሁለቱም ተያይዘው ወረዱ፡፡ የታክሲዋን  ድምጽ ሲሰሙ አንድ በእድሜ የገፉ አዛውንት አንዲት እመበለት አስከትለው፣ ከቤት ወጡና፣ ከታክሲ አሽከርካሪው ጋር ንግግር ጀመሩ፡፡ ንግግሩ በቀላል የሚቋጭ አልነበረምና ቀስ በቀስ እየጋለ መጣ፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ተሰበሰበ፤ ጫጫታው እየጨመረ መጣ፡፡ የተሰበሰቡት ሰዎች አሽከርካሪውን ይማጸናሉ፡፡ አሽከርካሪው እንቢታውን  ለመግለጽ  ንግግር ብቻ ሳይሆን፣ እጆቹንና ጭንቅላቱን ያወራጫል፡፡ ፍሬ ሃሳቡ ባይገባኝም  በሃሳባቸው  እንዳልተስማማ ተረዳሁ፡፡ በመጨረሻ  እንደምንም አሳምነውት  ወደ ታክሲው ተመልሶ ጉዞ ጀመርን፡፡
“የአንዳንድ ቀን ገጠመኝ ይገርማል፡፡ አንተንም  አስረፈድኩህ፤ የኔም ጉዳይ ቀረ” አለና በረጅሙ ተንፍሶ፣ “እነዚህ ሰዎች  ሕግ ፊት መቅረብ ነበረባቸው፤መቀጣት ነበረባቸው” እያለ ሲቆጭ፤ “ለምን?” አልኩት  በመገረም፤ “ልጁን  ትምህርት ቤት አስቀርተው ሌላ ሥራ ማዘዝ አልነበረባቸውም” አለኝ፤ ብስጭቱ እንደገና እያገረሸበት፡፡ ከጥቂት ዝምታ በኋላ በጎን አይኑ እያየኝ፤ “እንደነገርኩህ ነው”  አለኝ፤ ለመረጋጋት  እየሞከረ፡፡
“ያሳለፍነውን ችግር መድገም አንፈልግም፡፡ በዛ ላይ ያጣናቸውን ነገሮች ለመመለስ እራሱን የቻለ ስራ ይጠይቃል፤ የሁሉንም  ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት የሚፈልግ ሥራ፤” አለና  አይኖቹን  ጠበብ አድርጎ፣ ከፊት ለፊቱ  ያለውን ረጀም  መንገድ በርቀት እያስተዋለ፣  በዝምታ  ማሽከርከር ጀመረ፡፡
“የምትገርም ሰው ነህ፤ ልጅህ አይደል፤ የቅርብ ቤተሰብህ አይደል፤ለማታውቀው ሰው ይህን ያህል ዋጋ መክፈል አይከብድም?” አልኩት፡፡ ዝምታውን ለመስበር፤ “ይሄ’ኮ ግዴታ ነው”  አለኝ  ፈገግ ለማለት እየሞከረ፡፡ “እንዴት?” ስል ጠየቅሁ፤ “ያኔ እኮ የማንወጣው ችግር ውስጥ የገባነውና  ያን ያህል ዋጋ የከፈልነው፡  እንዲህ እያሰብን  ነው፤ ልክ አሁን አንተ እንዳሰብከው፡፡ እዛኛው መንደር እሳት  ሲነድ እኛ መንደር የማይደርስ መስሎን ችላ ስንል፤ ያኛው ቤት ሲፈርሰ የኛ  ቤት የማይፈርስ መስሎን ችላ ስንል፤ የጎረቤት ልጅ ሲበላሽ የኛ ልጅ የማይበላሽ መስሎን ችላ  ስንል፤የሌላ መንደር ልጆች በመጫወቻ ቦታ ሲጣሉ ነገ የኛ መንደር ልጆች  የማይደግሙት  መስሎን ችላ ስንል፤ ሁሉም አድጎ አድጎ መጨረሻ  ዘርና ሃገር ለማጥፋት በቃን፤ የማይሽር ጠባሳ ታቀፍን፡፡
“እናም ጠባሳችንን ለማከም፣ ትውልዱን ጠብቆ ወደ ትክክለኛ መንገድ በመምራትና ብቁ ዜጋ በመፍጠር  ሰላምን  ማስፈን፤ ረሃብን   ችግርን  ማጥፋት፤ የሕዝብን  የአኗኗር ዘይቤን ማሻሻል ብሎም ሃገርን  መቀየር  የእያንዳንዱ  ሩዋንዳዊ   ኃላፊነትም ግዴታም  ነው”  ካለ በኋላ፤ “የአንድ ሃገር ሕዝብ እድገቱም፣ ሰላሙም፣ ችግሩም የጋራ መሆኑን አውቆ ሁሉም ሰው  የየራሱን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ሰው አካባቢውን መጠበቅና አርአያ ሆኖ ትውልዱን ጥሩ ነገር ማስተማር  ያለበት በመጀመሪያ ለራሱ ሲል፣  ከዛም ለቤተሰቡ፣ አለፍ ሲል  ለማህበረሰብና  ለሃገር ነው፡፡ ይህ ልጅ ትምህርቱን አቋርጦ  ዱርዬ ቢሆን ነገ ሰርቼ ስመጣ ገንዘቤን መንገድ ላይ ይቀበለኛል፤ ስለዚህ ችግሩ ወደ ራሴ ይመለሳል ማለት ነው” አለኝ፡፡
 እንዲህ እየተጨዋወትን ተጉዘን መሥሪያ ቤት ደረስን፡፡  የያዝኩት  ገንዘብ ዶላር ነበር፡፡ ወደ ሩዋንዳ ፍራንክ ለመቀየር ባንክ እንደምሄድ ቀደም ብዬ የነገርኩት ቢሆንም፣ በነበረው ግርግር ምክንያት ረስቶታል፡፡ እኔም  የሰውየውን ሁኔታ አስቤ   ዶላሩን ብሰጠው ይጠቅመዋል   ብዬ ዝም አልኩ፡፡
ጉዞዬን አጠናቅቄ  ከታክሲው ልወርድ ስል፤ ስለነበረን ጊዜና ስለመልካምነቱ አመስግኜው ዶላር አውጥቼ ስሰጠው፣ ቀና ብሎ አየኝና፤ “ፍራንክ  ነው የምፈልገው” አለኝ፡፡ “አልዘረዘርኩም፤ ብዙ ስለደከምክ እንድትጠቀም  ፈልጌ ነው”  አልኩት፡፡  “አይሆንም፤ ዘርዝረህ ስጠኝ” አለኝ፡፡ “አንተ ብትዘረዝረው ምን ችግር አለው?” አልኩት፡፡ “ችግርማ አለው፤ ወንጀል እኮ ነው፤ዶላር ሕጋዊ ገንዘባችን አይደለም፡፡ በሕግ ያልተፈቀደ  ገንዘብ  መቀበል  ሙስና ነው፤ ሙስና ደግሞ ወንጀል ነው፤ ወንጀል ልታሰራኝ ትፈልጋለህ?” አለኝ  ብስጭት ብሎ፡፡ “አሁን ባንክ ለመሄድም ሰዓቱ ረፍዷና እባክህ ተቀበለኝ” ስለው፤ በጣም ተበሳጭቶ፤ “ትሰማኛለህ እኔ ወንጀል መስራት አልፈልግም፤ ግባና እንሂድ” አለኝና እንደገና ተያይዘን ወደ ባንክ ተመለስን፡፡ ሂሳቡን ዘርዝሬ ሰጥቸው እሱም ወደ ሥራው እኔም ይህን መልካም ሰው በማሳዘኔ እራሴን እየወቀስኩና በድርጊቱ እየተገረምኩ ወደ ሥራ ቦታዬ ተመለስኩ” አሉኝ፡፡
 እኝህ ሰው ይህንን ሲያጫውቱኝ  ረጅም ዘመን  ወደ ኋላ ተጉዤ የልጅነት ዘመኔን  እንዳስብ አደረጉኝ፡፡ የሰፈራችንን  እማማ በቀሉን  አስታወሱኝ፡፡ በርግጥ ሁሉም ትልቅ ሰው ልጆች ትክክል ያልሆነ ነገር  ሲሠሩ  እንደ ጥፋቱ ክብደትና ቅለት   ይገስጻሉ፤ ይገርፋሉ፡፡ በእድሜ ከፍ ያሉ  የሰፈር ልጆችም  ከታች  ያሉትን ይቀጣሉ፤  ለማስተካከል  ይሞክራሉ፡፡ የእማማ በቀሉ ግን ይለያል፤  ጥፋት ያጠፋ ልጅ ከተገኘ ያጠፋው ልጅ ካልተቀጣ፡ እንደ  ጥፋቱ መጠን ሰውነቱ  እስከሚንደበደብ  በሳማ  ካልተገረፈ፤ ጆሮውን ካልተቆነጠጠ የቀረው ይቀራል እንጂ ወደ ጉዳያቸው አይሄዱም ነበር፡፡  ልጅን መቅጣት በትኩሱ፤ ጥፋቱን ሳይረሳ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ሲሆን ማንም ልጅ አያጉረመርምም፤ ማንም ወላጅ አይከፋውም ነበር፡፡
ዛሬስ እኛ እንዲህ አይነቱ ተቆርቋሪነት ይኖረን ይሆን? ትውልድን  የመንከባከብ የማስተማር፤የማብቃት፤ ትውልድን  የማዳንና ብቁ ዜጋ የመፍጠር  ኃላፊነትስ  የሁላችን  የጋራ  ሥራ መሆኑን ተረድተነው ይሆን?  እያንዳንዳችን  የየራሳችንን ድርሻ ባለመወጣታችን የችግሩ ገፈት ቀማቀሾች መሆናችንንስ አስተውለነው ይሆን?  ይህንን ነው እንግዲህ  ባለታሪካችን ያስተማረን ፡፡

Read 409 times