ጳጉሜ 1 “የመሻገር ቀን” ነው። መሻገር? ደግሞ ወዴት ነው የምንሻገረው? እየተሻገርን ዕድሜ መጨመር ብቻ ምን ዋጋ አለው? በቅንነት እንየው ከተባለ ማለቴ ነው።
ጳጉሜ 2 “የሪፎርም ቀን” ሆኗል። “ፎርም” በመቀየር ብቻ የት ይደረሳል? ቅርጹ ሌላ፣ ውስጡ ሌላ! እንዲህ ሲባል ግን በቅንነት እንጂ “ነገር ለማጣመም” አይደለም። በጎ በጎውን ነው ማየት። ቢሆንም ግን፣ ሪፎርም ማለት ፊርማ እንደመለወጥ ይመስላል። “በአዲስ ፊርማ መጥተናል” ብንባባል ትርጉም የለውም። የማይቀየር የጣት አሻራ አይሻለንም?
ጳጉሜ 3 የሉዓላዊነት ቀን? ይሄ ነገር የመንግሥት ጉዳይ ነው አይደለም? ደግሞም የዕለት ተዕለት ሥራ እንጂ፣ በዓመት አንድ ቀን ትዝ ሲለን ብናነሣሣው ምን ጥቅም አለው? የደስታ ቀን ስለተባለኮ ደስታ አይገኝም - በቅንነት እንነጋገር ከተባለ። ቢሆንም በሉዓላዊነት ላይ ቀልድ የለም። ዘራፍ!
ጳጉሜ 4 የኅብር ቀን? መጀመሪያ የትኛው “ኅብር” ማለታችን እንደሆነ ብንመካከርበት አይሻልም? ማኅበር፣ ኅብረት ለማለት ነው? ብዙ ሆኖ በአንድ ቦታ መገኘት ወይም አብሮ መሆን ማለት ነው? ኅብረ-ቀለማት እንደሚባለው። በዚህ ጉዳይ ላይ ተመካክረን የተግባባን አልመሰለኝም። ነገር ለማሳጠር ከፈለግን፣ መዝገበ ቃላት ላይ አይተን እዚሁ ልንጨርሰው እንችላለን። ግን በምክክር ይሻላል? እስከዚያው… የኅብር ቀን ነው ብለን ለመናገር ይከብደናል - ቀና ቀናው እንይ ካልን።
ጳጉሜ 5 የነገ ቀን? ነገማ ሌላ ቀን ነው። የዛሬውን ተነጋግረን ሳንጨርስ? ደግሞስ ዛሬ ስለ ነገ ምን አስጨነቀን? ራሱ ይጭነቀው እንጂ። አይደለም እንዴ? በቀና ስሜት ስናያቸው እንዲህ ይመስላሉ።
የመሻገር ቀንን ለጊዜው እናቆየው። በኋላ እንመለስበታለን። አሁን ወደ ፊት በመሻገር፣ በሉዓላዊነት ቀን እንጀምር።
የሉዓላዊነት ቀን? ጥሩ ነው። መጥፎ አይደለም። ግን፣ የሉዓላዊነት ጉዳይ በጳጉሜ 3 ላይ ተገድቦ መቅረት አለበት ወይ የሚለው ጥያቄስ?
ቁምነገሩ ላይ እናተኩር ከተባለማ፣ ትክክለኛው አጻጻፍ “ልዑላዊነት” ሳይሆን አይቀርም መሰለኝ። ልዑል ማለት፣ የበላይ ወይም ከፍተኛ ማለት አይደለም? super እንዲሉ ነው። ለነገሩ sovereignty… super እና reign ከሚሉ ቃላት የመጣ ነው አሉ። የበላይ ሥርዓት፣ ዋና የሥልጣን ባለቤት፣ ከፍተኛ ገዢ… እንደማለት ነው። የመንግሥት ሥልጣንን ወይም የአገር ነጻ ሕልውናን የሚያመለክቱ ትርጉሞችም አሉት።
ለማንኛውም ግን፣ ሉዓላዊነት የሚል ቃል ስንሰማ፣ ፉከራ ወይም ኩራት፣ ቁጣ ወይም ፍቅር… በየተራ ሊፈራረቁብን ይችላሉ። አንዳንዴም ይደበላለቁብናል።
ራሳችሁን ታዝባችሁ ከሆነ፣ ሉዓላዊነት የሚለውን ቃል አንዳንዴ… እርስ በርስ ለመጣላት፣ ወይም ደግሞ አንዳችን ሌላችንን ለማስፈራራት እንጠቀምበታለን። ቢሆንም ግን የሚያስማማ ነገር አይጠፋም። “የፋሺስት የእብሪት ወረራ፣ የግብፅ መንግሥት ሤራ”… ብለን ስንናገር፣ ጉዳዩ የሕልውናና የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑ አይጠፋንም። ዘራፍ!
“የምዕራባዊያን ግፊት፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት ጫና”… ብለንም እንናገራለን። ይሄ ይሄ እንኳ እንደ ሁኔታው ነው። ሥልጣን የያዘውን መንግሥት ከጠመድነው፣ “አውሮፓና አሜሪካ መንግሥት ላይ ጫና ማሳደር አለባቸው፤ ማዕቀብ መጣል ይገባቸዋል” ብለን በአቤቱታ ልናጨናንቃቸው እንችላለን። ከመንግሥት ጋር ከተመቻቸን ደግሞ “አያገባችሁም፤ እናንተ ምን ቤት ናችሁ?” እንላለን።
በአገር ጉዳይ የመጡብን ከመሰለን ግን፣ “የማናውቃችሁ መሰላችሁ እንዴ? አፍሪካን እንደወረራችሁ በቅኝ ግዛት እንደተቀራመታችሁ የምንረሳ መሰላችሁ?” ብለን ልክ ልካቸውን እንነግራቸዋለን።
ሉዓላዊነት… ሌላ ትርጉምም አለው። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ሕይወት ላይ ንጉሥ ነው የሚል ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን። እንዲያውም፣ ከሌሎቹ ትርጉሞች የተሻለ ሥልጡን ትርጉም ነው። በዚህ ካልተስማማችሁ ግን… ወደ ጸብ መግባታችን ነው። የሉዓላዊነትን ትርጉም ምንም አታውቁም ማለት ነው… አንተ ነህ የማታውቀው… እናንተ ናችሁ የዞረባችሁ… አንተ ነህ የተጋረደብህ! ዘራፍ! ሉዓላዊነታችሁ ተደፈረ?
ግን ከምር ዛሬ ዛሬ ነባሩ የሉዓላዊነት ትርጉም ድንግዝግዝ ሆኗል። ድሮኮ… የአገር ድንበር፣ ወሰንና ዐጥር… አትድረስብኝ አልደርስብህ ማለት ይቻል ነበር። ዛሬ ግን ድንበር የማይከልላቸው ነገር በዝተዋል። በቴሌቪዥን ዲሽ ተጀመረ። ከዚያ በኢንተርኔት ዓለም ሁሉ ተደበላለቀ።
ምን ይሄ ብቻ!
እልፍ ድሮኖችን በመንጋ ማሰማራት እየተቻለ፣ የአገር ድንበር እንዴት ነው የሚጠበቀው?
በዚያ ላይ እልፍ አእላፍ ሳተላይቶች ሰማይ ላይ እየተሽከረከሩ እያንዳንዷን ካሬሜትር ይቆጣጠራሉ - በማያንቀላፉ ዐይኖቻቸው። ይህም ብቻ አይደለም። እንደ ሳተላይት ቴሌቪዥን፣ አሁን ደግሞ ድንበር የማያግደው የሳተላይት ኢንተርኔት እየተስፋፋ ነው። እና፣ ሉዓላዊነት አለቀለት ማለት ነው? ሉዓላዊነት ማለት ዐጥር ግንብ ማለት ከሆነ ችግር አለ።
ሉዓላዊነት ማለት፣ ጥቃትን የማይቀበል፣ የዜጎችን ነጻነት የሚያስከብር አገርና ሥርዓት ማለት ከሆነ ግን ችግር የለውም። አንድ የጳጉሜ ቀን ቢመደብለት አይበዛበትም። ሉዓላዊነትን የማስከበር ሥራ የዕለት ተዕለት ሥራ እንደሆነ ስታስቡት፣ አንድ ቀን ቢሰየምለት እንዴት ይበዛበታል? ግን እኛ ምናገባን? የመንግሥት እንጂ የኛ ሥራ አይደለም - በቅንነት እንነጋገር ከተባለ።
የኅብር ቀን? ኅብረት ለማለት ነው? መተባበር፣ ማኅበር ከሚሉ ቃላት ነው ዝምድናው? ወይስ ከብዝኃነት ጋር? ኅብረ-ቀለማት እንዲሉ። ብዙ የቀለም ዐይነቶችን ያካተተ ወይም የያዘ እንደማለት ነው።
ኅብረ-ዝማሬ የሚለው አገላለጽ ሁለቱንም ትርጉሞች ሳያጠቃልል አይቀርም። በኅብረት መዘመር ወይም ተባብሮ መዝፈን ነው - አንድ ትርጉሙ። ብዙ ሰዎች ተባብረው በአንድ ድምጽ ይዘፍናሉ። በሌላ በኩል ግን፣ የተለያዩ ተዛማጅ የድምጽ ዐይነቶችን ያጣመረ ሙዚቃና ዜማም፣ ኅብረ ዝማሬ ይባላል። ስለዚህ ኅብረትም ብዝኃነትም ሊሆን ይችላል። “ኅብራችን ለሰላማችን” የሚለው አገላለጽ ወደየትኛው ይቀርባል? ለሰላም እስከጠቀመ ድረስ ግን ጥሩ ሳይሆን አይቀርም።
የነገ ቀን?
የዛሬውን ሳንጨርስ? ለነገማ ነገ አለለት። ለነገ አታስቡ የሚል ብሂል አስታወሳችሁ? ወይስ “ስለ ነገ አትጨናነቁ” ነው የተባለው? በእርግጥም፣ ስለ ነገ አለማሰብ አይቻልም። መቼም የምንሰራው ነገር ሁሉ፣ ለነገ ነው፤ ለበኋላ ነው። አለበለዚያ “ነገ” የተባለው ጊዜ ከች ሲል በባዶ እጅ ይሆናል።
የመሻገር ቀን?
ወዴት ነው የምንሻገረው? ወደ ጳጉሜ 2፣ ወደ አዲስ ዓመት? ከቤት ወደ መሬት? ወይስ ከጎዳና ወደ ብልጽግና? ደግሞ ስንት ዓመት ተሸጋገርን? ዕድሜ ብቻ የሚጨምር ከሆነ ምን ዋጋ አለው? ለነገሩ ተመስጌን ነው። ዕድሜ ያልሰጣቸውም አሉ። ግን “ተሸጋግሯል!”… “ተሸጋግራለች” የሚሉ ቃላት በጣም አስደሳች ቃላት እንደነበሩ አትርሱ። ከአንድ እርከን ወይም ደረጃ፣ ወደ ከፍተኛ እርከንና ደረጃ… ተሸጋግሯል ተብሎ ማኅተም ሲያርፍበት፣ ደስ የሚል ነገር አለው።
በነገራችን ላይ መሻገር፣ ገደሉን ለመዝለልም፣ በድልድይ ላይ ለማለፍም ሊሆን ይችላል። ከአንድ ቦታ ወደ ማዶ ማለፍም መሻገር ነው። ነገር ግን መጓዝ ማለት እንደሆነም በመዝገበ ቃላት ተጠቅሷል። ሠገረ… ከሚለው ቃል ጋር የተዛመደ ስለሆነ፣ መሻገር ማለት፣ መራመድ፣ መሄድ፣ መጓዝ ማለትም ነው። ተሻግሮ መቆም ብቻ አይደለም ለማለት ፈልጌ ነው።
የሪፎርም ቀን?
አስቸጋሪው ቀን ይሄ ነው። የሪፎርም ቀን? ለመንግሥት ሠራተኞች ትርጉም ይኖረው ይሆናል። ለሌሎቻችን ግን፣ ጉዳይ ካልገጠመን በስተቀር፣ ሄደንም ካልተጉላላንና ካልተንገላታን በቀር፣ “ሪፎርም” ምንም ስሜት የሚሰጠን አይመስለኝም። ጉዳያችን ከተስተጓጎለና ከተጓተተ፣ ያኔ… ያኔ… እንነጋገራለን። እስከዚያው ግን… ማለት… ምንድነው ሪፎርም?
“ፎርም” ብቻ? ፎርም መቀየር ምን ያመጣል? ቅርጽ ብቻ?
በነገራችን ላይ፣ form የሚለው ቃል ፈረመ ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሳይኖረው አይቀርም። ፊርማ፣ የሰውዬውን ሀሳብና ፈቃድ፣ ውሳኔና ስምምነት የሚያሳይ ቅርጽና ምልክት ነው። ፊርማ ብቻውን ግን ዋጋ የለውም። “ሪፎርም” ማለትኮ ፊርማ እንደመቀየር ነው። ለአዲስ ዓመት በአዲስ ፊርማ መጥተናል! እንደማለት ነው።
ለነገሩ፣ ዛሬ ዛሬ ፊርማ እየቀረ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊትኮ፣ ፊርማ መለማመድ እንደ መዝናኛ ነበር የሚቆጠረው። ፊደል ተምሮ መጻፍ የተለማመደ ልጅ፣ ያገኘው ነገር ላይ ስሙን ሲጽፍ ውሎ ሲጽፍ ቢያድር እንደማይሰለቸው ማለት ነው። ፊርማ መለማመድም እንደዚያ ነበር። የማደግ ምልክት ነበር። ወይም የማደግ ምኞት!
በጣት አሻራ ከመፈረም፣ በስክርቢቶ መፈረም ተብሎ የተዘፈነበት ጊዜ ሳይኖር አይቀርም። ሥልጣኔ መሆኑ ነው። ዛሬ፣ ባዮሜትሪክስ ተብሎ በፊርማ ምትክ የጣት አሻራ ተመልሶ መጥቷል። ሥልጣኔ መሆኑ ነው - ወይም ቴክኖሎጂ!
የሆነ ሆኖ… ሪፎርም ከማለታችን በፊት ፎርም በሚለው ቃል ላይ በቂ ጊዜ ሰጥተን ብናስብበት መልካም የአእምሮ አክሮባት ሊሆንልን ይችላል። ተፈጥሯዊ ነገሮች ላይ ቅርጽ ይዘትን ይከተላል። የሰው ፈጠራ የሆኑ ነገሮች ላይ ደግሞ፣ ቅርጽ አገልግሎትን ይከተላል ይባላል። ሪፎርም የሚለው ቃል የሚመጣው እዚህ ላይ ሳይሆን አይቀርም።
በሰው የተፈጠሩ ነገሮች፣ ወይም ሰው ያዋቀራቸው ተቋማት፣ አገልግሎታቸውንና ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወንና ለማሟላት የሚችል ቅርጽ ሊኖራቸው ይገባል ለማለት ነው - ቅርጽ ለአገልግሎት ተገዢ መሆን አለበት ሲባል። ካልሆነ ግን፣ ቅርጹን ማስተካከል ነዋ - “ሪ-ፎርም” ማድረግ?
Saturday, 07 September 2024 11:15
ለጳጉሜ ቀናት የተሰጡ “ስሞች”ን በ”ቀና” ስሜት እንያቸው!
Written by ዮሐንስ ሰ.
Published in
ነፃ አስተያየት