Saturday, 07 September 2024 11:23

የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)


       “55በመቶ ለአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ብቻ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል እንዲሁም የህክምና ባለሙያ በጤና ተቋም ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ተችሏል” በጤና ሚንስቴር የስነተዋልዶ፣ የቤተሰብ እቅድ፣ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ዴስክ ተወካይ ሞቱማ በቀለ
ጤና ሚንስትር ተደራሽነት፣ ጥራት እና ምላሽ ሰጪ የጤና ስርአት ለሁሉም አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች በሚል መሪ ቃል 5ኛውን የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ጉባኤ ነሀሴ 27 እና 28 2016 ዓ.ም አካሂዷል። ለ2 ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ላይ የጤና ሚንስቴር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የትምህርት ሚንስቴር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እና ወጣቶች ተሳትፈዋል።
የጤና ሚንስቴር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጉባኤው መድረክ ላይ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም የጤና ተደራሽነት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ ቆይቷል። ነገር ግን ተደራሽነት ብቻ በቂ ባለመሆኑ ጥራት እና ምላሽ ሰጪ የሆነ የጤና ስርአት ያስፈልጋል። ስለሆነም መንግስት፣ ባለድርሻ አካላት፣ ማህበረሰቡ እና ወጣቶች ለተፈፃሚነቱ መስራት እንደሚገባቸው ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል። ሚንስተሯ አክለውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጣቶች በተለያዩ የጤና ችግሮች(በሽታ) ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው ይህን ችግር አስቀድሞ መከላከል እና ችግሩ ሲያጋጥም ደግሞ መፍትሄ የሚሰጥ የጤና ስርአት ያስፈልጋል ብለዋል። ስለሆነም ጤና ሚንስቴር የአፍላወጣቶች፣ የስነተዋልዶ እና ሌሎች ስትራቴጂዎች ላይ እየሰራ ይገኛል።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በአስራዎቹ እና በሀያዎቹ የሚገኙ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ለተለያዩ የስነተዋልዶ ችግሮች (የጤና መጓደል) ይጋለጣሉ።  ለምሳሌ ያህል በአፍላ እድሜ የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር፣ ስለ ቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በቂ እውቀት አለመኖር፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ፣ ኤችአይቪ/ኤድስ እና ሌሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች (ኢንፌክሽኖች) ተጋላጭ መሆን እንዲሁም ያለ እድሜ ጋብቻ፣ በአፍላ እድሜ ልጅ ከመውለድ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው። ከአካላዊ በሽታ(ችግር) በተጨማሪ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም ይከሰታሉ። ለነዚህ ችግርች እንደ መንስኤ የሚጠቀሰው በቂ ግንዛቤ (እውቀት) አለመኖር፣ አገልግሎቱ ምቹ እና ተደራሽ አለመሆን እንዲሁም መሰል በአገልግሎት ሰጪ እና ተጠቃሚ መካከል ያሉ ክፍተቶች ናቸው።
“የኔ ታብ የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ(አፕሊኬሽን) ላይ ማንኛውም ሰው የስነተዋልዶ መረጃ ማግኘት ይችላል” በማለት በጤና ሚንስቴር የስነተዋልዶ፣ የቤተሰብ እቅድ፣ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ዴስክ ተወካይ የሆኑት ሞቱማ በቀለ ተናግረዋል። አቶ ሞቱማ በቀለ እንደተናገሩት አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች በጤና ዙሪያ በቂ መረጃ የላቸውም። ስለሆነም የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶችን ጉዳይ የጤና ስርአቶች ላይ በማካተት፣ ምቹ የጤና ማዕከላት በማስፋፋት፣ በሁሉም ቦታ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ውክልና (ተወካይ) እንዲሁም ተሳትፎ እንዲኖር በማድረግ መስራት ያስፈልጋል። ይህም የወጣቶችን ጥያቄ መሰረት በማድረግ እና እራሳቸውን ተሳታፊ በማድረግ የሚሰራ መሆኑን አቶ ሞቱማ በቀለ ተናግረዋል።
ወጣት ቶፊቅ ኢስማኤልሀኪም የጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል ፕሬዝደንት ነው። እንደ ቶፊቅ ንግግር ካውንስሉ በስነተዋልዶ እና በሌሎች የጤና ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት እንዲሁም ከጤና ባለሙያዎች ጋር የማገናኘት (ህክምና እንዲያገኙ) ስራ ይሰራል። በጤና ሚንስቴር ውስጥ የተቋቋመው ካውንስል አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ‘አቻ ለአቻ የሆነ ግንኙነት’ እንዲኖራቸው በማድረግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ካውንስሉ በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ወጣቶች የተውጣጣ ነው። “ካውንስሉ በክልል ደረጃ ተዋቅሯል፤ በቀጣይ በዞን እና በወረዳ ደረጃ እንዲሰራ እናደርጋለን” ብሏል የጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል ፕሬዝደንት ቶፊቅ ኢስማኤልሀኪም።
በጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት የሆነችው ቤተልሔም ዳኛቸው እንደተናገረችው ስለ ኤች አይ ቪ፣ አባላዘር፣ ያለተፈለገ እርግዝና እና ስለ ወሲባዊ ግንኙነት የምክር እና የህክምና አገልግሎት ይሰጣል። ከስነተዋልዶ ጤና በተጨማሪ በሌሎች የጤና ዘርፎችም አገልግሎት እንደሚሰጥ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ተናግራለች። ወጣት ቤተልሔም እንደተናገረች ካውንስሉ ቁጥራቸው ከፍተኛ ለሆነ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች አገልግሎት ተሰቷል። በት/ቤት እና በመኖሪያ አከባቢ አገልግሎቱን በመስጠት ለተጠቃዊች ይበልጥ ለማዳረስ እየተሰራ ይገኛል። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎቱ የተፈለገውን ያህል ተደራሽ አለመሆኑን ቤተልሔም ዳኛቸው ተናግራለች። የጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት የሆነችው ቤተልሄም ዳኛቸው የሰላም መጓደል ለአገልግሎቱ እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው ብላለች።  
“ከነበረው ሁኔታ አንፃር ዘግይተን ነበር፤ አሁን ግን 50 በመቶ ያህል ሰርተናል” ያለችው በጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል የትግራይ ክልል ፀሀፊ ሮዛ ኣባዲ ናት። እንደ ሮዛ ንግግር የወጣቶች አካላዊ እና ስነልቦናዊ ተጎድተዋል። “ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ አለ” ብላለች ሮዛ አባዲ። ስለሆነም በክልሉ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ላይ ብዙ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ፀሀፊዋ ተናግራለች። ትምህርት እና ሌላ አስፈላጊ እርዳታ በማድረግ ወጣቶች ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲሆኑ ለማድረግ በቀጣይ ዓመት እንደሚሰራ የጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል የትግራይ ክልል ፀሀፊ ሮዛ ኣባዲ ተናግራለች።
የጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት አቡበከር መሀመድ በበኩሉ በክልሉ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት እና የአደንዛዥ እፅ ተጠቂነት በወጣቶች ላይ ያለ ችግር መሆኑን ተናግሯል። እንደ ፕሬዝዳንቱ ንግግር እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከመንግስት፣ ከህክምና ባለሙያዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከወጣቶች ጋር እየተሰራ ይገኛል። እንዲሁም የወጣት ማዕከላትን ማስፋፋት እና በክልሉ አርብቶአደር ማህበረሰብ እንደመሆኑ የህክምና ባለሙያዎች (ኋልዝ ወርከር) ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ማድረግ ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሆን በጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት አቡበከር መሀመድ ተናግሯል።
ጤና ሚንስትር ባዘጋጀው የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች 5ኛ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት እና ካነጋገርናቸው ሰዎች መካከል በዩዝ ኔትዎርክ ፎር ሰስተነብል ዴቨሎፕመንት (Youth network for sustainable development) ሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚያገለግሉት ዶ/ር ረድኤት ንጉሴ ናቸው። ዶ/ር ረድኤት ንጉሴ እንደ ወጣት እንዲሁም እንደ የህክምና ባለሙያ የተናገሩት ለወጣቶች የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት መንገድ የተለየ መሆን እንዳለበት ነው። ከአቀባበል፣ ቃላት አጠቃቀም እና መሰል ሁኔታዎች አንፃር ለወጣቶች አመቺ መሆን እንደሚገባው የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። የህክምና ባለሙያዋ በወጣቶች ዘንድ አንዳንድ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች መኖራችውንም አክለው ጠቅሰዋል። “ስልጠና በምሰጥበት ወቅት የአጭር ጊዜ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የሆነው መድሃኒት (ፓስት ፒል) ከግንኙነት ከ72 ሰአታት በኋላ የሚወስድ የሚመስላቸው ወጣቶች አጋጥመውኛል። በጣም ነበር የደነገጥኩት። መድሃኒቱ መወሰድ ያለበት በ72 ሰአታት ውስጥ እንጂ በኋላ አይደለም” ብለዋል ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ረድኤት ንጉሴ።
በተመሳሳይ የጤና ሚንስቴር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል ፕሬዝደንት ቶፊቅ ኢስማኤልሀኪም በአፍላ ወጣቶች እና በወጣቶች የስነተዋልዶ ጤና ላይ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች መኖራቸውን ጠቁሟል። “እንደ ነውር ይቆጠራል፤ እኛም እኮ ተወልደን ነው” በማለት በግብረ ስጋ ግንኙነት፣ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እና መሰል ጉዳዮች ላይ ያለውን የግንዛቤ (መረጃ) ክፍተት ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ውስጥ ወደ 40 ሚሊዮን የሚሆነው የህዝብ ቁጥር የወጣቶች ነው። “አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች በተፈጥሮ የሚጎላቸው ሆርሞን አለ” ብለዋል በጤና ሚንስቴር የስነተዋልዶ፣ የቤተሰብ እቅድ፣ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ዴስክ ተወካይ የሆኑት አቶ ሞቱማ በቀለ። እንደ ባለሙያው ንግግር በሆርሞን አለመስተካከል ምክንያት በአፍላ ወጣት እድሜ ላይ ስሜታዊ ወይም ባለማገናዘብ የሚወሰን ውሳኔ ይበዛል። እንዲሁም የሚፈፀመው ተግባር (ውሳኔ) ልክ እንደሆነ የማሰብ ሁኔታ አለ። ስለሆነም ጤና ሚንስቴር ከ10 እስከ 24 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊ እና ወጣቶች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አቶ ሞቱማ በቀለ ተናግረዋል። “55በመቶ ምቹ ለአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ብቻ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል እንዲሁም የህክምና ባለሙያ በጤና ተቋም ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ተችሏል” ብለዋል አቶ ሞቱማ በቀለ። አክለውም የተለየ ህክምና መስጫ ክፍል ማመቻቸት ባይቻል እንኳን ለወጣቶች ህክምና ለመስጠት የሰለጠነ የህክምና ባለሙያ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በጤና ሚንስቴር የስነተዋልዶ፣ የቤተሰብ እቅድ፣ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ዴስክ ተወካይ የሆኑት አቶ ሞቱማ በቀለ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና እንዲጠበቅ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አድርገዋል።   



Read 207 times