Saturday, 07 September 2024 11:41

ንጉስ ሳይ፤ ክሰስ - ክሰስ ይለኛል!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


        ነብሱን ይማረውና ሟቹ ገጣሚውና የሥነ-ጽሁፍ ሰው እንዲሁም የሰላው ሐያሲ አቶ ደበበ ሠይፉ ከማስተማሪያ ክፍለ-ጊዜዎቹ በአንደኛው የሚከተለውን ሙከራ ሰርቶ ነበር።
አንዲት ወፍራም ልጅ ከተማሪዎቹ መካከል ይመርጥና ወደ ሰሌዳው እንድትመጣ ይጠይቃታል። የተባለችውን ትፈጽማለች። ልጅቷ ከተማሪዎቹ ፊት እንድትቆም ያደርግና ሲያበቃ “እስቲ ይህችን ልጅ አሞግሷት” ይልና ይጠይቃል። ጥቂት ተማሪዎች እጃቸውን እያወጡ ማሞገስ ጀመሩ።
“የእኔ ድምቡሽቡሽ!” አለ አንደኛው። “የእኔ ትምቡኬ!” አለ ሁለተኛው።
“የእኔ ደልካካ!” ቀጠለ ሌላው። “የእኔ ሞንዳላ”።
“የእኔ ዱብዬ!” ወዘተ…
ተማሪዎቹ ማሞገሳቸውን ቀጠሉና ዘጠኝ ያህል ማሞገሻ ቃላት ተገኙ። ከዚያ ሙገሳው ቆመ። አቶ ደበበም በሉ እስቲ አሁን ደግሞ ስደቧት አለ። ከሞላ ጎደል የክፍሉ ተማሪ በሙሉ እጁን በሚገርም ፍጥነትና ልበ-ሙሉነት አወጣ። የስድቡ ሥነ-ስርዓት ቀጠለ።
የመጀመሪያው- “ጉርድ በርሜል!” አለ። ሁለተኛው “ግንዲሳ!” አለ። “ድብ!” አለ ሦስተኛው። “ድብዳብ!”፣ “የተነፈሰች ጎማ!”፣ “ግንድ እግር!”፣ “ግማሽ ተራራ!”፣ “ዝፍዝፍ!”፣”ድልብ!”፣ “መሲና”፣ “የጋራ ጉማጅ!”፣ “ቦክሰኛ!”፣ “ተንቀሳቃሽ ቤት!”፣ “የእኔ ሸበላ!” ወዘተ አሥራ አንድ ቃል ተገኘ።
ቀጥሉ ስደቧት አለ፡-
“ቀጫጫ!”፣ “የቆመች ፓስታ!”፣ “ወባ!”፣ “ሲምቢሮ!”፣ “ቋንጣ!”፣ “ሎሊ-ፖፕ እግር!”፣ “ደረቁቻ!”፣ “በልታ እማታስመሰግን!”፣ “ከሲታ!”፣ “ያለቀች መጥረጊያ!”፣ “ሣር!”፣ “ቆረቆንዳ!”፣ “ጎድናም!”፣ “የቆመች አፅም!”፣ “ጥላቢስ!”፣ “ስፒል!”፣ “ሹካ!”፣ “ሹል-ቴክስ!”፣ “ቀስት!”፣ “ጅማት!”፣ “ጣረ-ሞት!”፣ “ሳሙና ላይ የተሰካች ሰንደል!”፣ “ጠሟጋ!”፣… ወዘተ ባንድ ጊዜ ስድቡ ተዥጎደጎደ። ሰሌዳው ሞላ። “በቃ! በቃ!” አለ መምህሩ ጆሮውን በመዳፎቹ ውስጥ ቀብሮ።
ከዚህ በኋላ መምህሩ “ይሄውላችሁ ልጆች ማህበረሰባችን ይሄን ይመስላል።” የስድብ ቃላት ሞልተውናል። የማሞገሻ ቃላት ግን እንዳያችሁት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።
***
በየኑሯችን ውስጥም ሆነ በየስብሰባው የምናየው የዚህን ባህል አባዜ ነው። “ንጉስ ሳይ፣ ክሰስ ክሰስ ይለኛል” የሚለውም ተረት ሥረ-መሰረቱ ይኸው አባዜ ነው። ስድብ፣ ግዝት፣ ተቃውሞ፣ ማንቋሸሽ፣ እርግማን በህዝብም፣ በመንግሥትም፣ በድርጅቶችም አንደበት ነጋ ጠባ ይመላለሳሉ። ለምስጋናና ለመልካም ስም ሙገሳ መስጠት (Merit) እንደ ታላቅ ኪሳራ ተቆጥረዋል። በየስብሰባው፣ በየግምገማው፣ በየመድረኩ የሚታየው በዚሁ ሌላውን በማንኳሰስና ድክመቱን በማጋነን አባዜ ራስን ትልቅ የማድረግና አንቱ የማለት ፈሊጥ ነው። ውስብስብ የባህል ሳንካ ነው። ትላንትም ነበር። ዛሬም አለ። የወደፊቱ ሊታሰብበት የሚገባ ነው።
የፖለቲካ ድርጅቶች እርስ በርስ ደግ ስራዎቻቸውን ለማየት ጭንቃቸው ነው። ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ ይህ ጣጣ አለ። ከላይ በመምህሩ ሙከራ እንዳየነው ስድብን እንደ ክላሸንኮቭ ጥይት ማከታተል፣ ምስጋናን እንደቦኩ ፀበል በጸሎት ጠብታ በጠብታ መጠበቅ፣ ባህላችን ከሆነ ውሎ አድሯል። ወደላይ የሚወጣን ሰው እግሩን ከመጎተት ጀምሮ ኃጢያቱን በማብዛት የእርግማን መአት ማውረድ፣ የተሻለ የሰራንና አዲስ መንገድ የቀየሰን አሊያም ታላቅ እመርታ ያሳየን ሁሉ ሰንክሎ ለመጣል ሸሚዝን መጠቅለልና ቀበቶን ማጥበቅ በደምና በአጥንት የተወረሰ ልማድ ሆኗል። ይህ ባህል በየቢሮው፣ በየቴያትር ቤቱ፣ በየት/ቤቱ፣ በየስፖርት ሜዳው የሚታይ ነው። የየቢሮው ኃላፊዎችና የየተቋሙ መሪዎች የተሰራውን ደግ  ስራ አሞግሰው ሞራል ከማጎልበትና የሥራውን እድገት ለማሳየት ከመጣር ይልቅ ያልተሰራውን ጠቅሰው ሁሉን አፈር-ድሜ አስግጠው “አትረቡም፤ እናንተን ከምመራ ሞቼ ባረፍኩ” ዓይነት “ግምገማ” ያካሂዳሉ። ማመስገን ካለባቸው ሰው በሌለበት፣ መራገም ካለባቸው ደግሞ ህዝብ በተሰበሰበበት ሆኗል ፈሊጣቸው። ማናቸውም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚም ሆነ የማህበራዊ መዋቅርና መደላድል መሰረቱ ጠብቆ፣ ልስኑ አምሮ ብሩህ የእድገት አቅጣጫ ለመያዝ ገና በመፍረምረም ላይ ባለበት አገር ብቅ ያለውን ደግ ነገር ሁሉ እየኮረኮምን ዘላቂ እድገት እናመጣለን ብሎ ማሰብ “ከአባ ቁፋሮ እሸት ተቀጥፎለት” እንደሚባለው ተረት ዓይነት ነው። ምንም ይሁን ምን በሀገራችን የሚታየውን አጠቃላይ ሁኔታ ደግ ደጉን ለማየት ዓይን ሊኖረን ይገባል። የምርጫ እንቅስቃሴ ጥሩ ሆኖ ያለንቀትና ያለዛቻ ቢሆን ደግ ነገር ነው። ድርጅቶች አመራሮቻቸውን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥና መሻራቸው ያለ ዘለፋ ሲሆን ደግ ነገር ነው።
እርግጥ ሳንካና እኩይ ተግባሩ በበዛና በተወሳሰበ ቁጥር በመሀል ብቅ ጥልቅ የሚሉ እውነቶችንና ሐቀኛ ስራዎችን አንጥሮ አውጥቶ ማመስገን ይከብድ ይሆናል። ልፋት መጠየቁ አይቀርም። የባህል የልማድ ማህተም አለበትና። ያም ሆኖ ግን፣ ወደድንም ጠላንም ጥቃቅኖቹን በጎ ነገሮች በመልቀምና እንደ ችግኝ በማፍላት ነው ወደ ትላልቅ ዛፎች ልንቀይራቸው የምንችለው። የተከፈተውን በር ከማንኳኳት ገርበብ ያለውን ማስከፈት ይሻላል። ደሞ የተዘጋውን በር ለማስከፈት በጥሞና ማንኳኳት ከዚያ ይቀጥላል። እንጂ በጽንፈኝነት ኮረብታ ለኮረብታ ቆሞ ክፉ ክፉውን መደርደር ለፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ ለመንግሥትም፣ ለህዝብም የሚበጅ ልማድ አይደለም። ለመጪው አዲስ ዓመት ብዙ ደግ ነገር ለማግኘት ዓይንንም ልቡናንም መክፈት ይፈልጋል። ከሁሉም በላይ ግን ቀና መሆንን ይጠይቃል። እስከ ዛሬ  በክፉ መንገድ ሞክረነው ያጣነውን እስቲ ዛሬ ደግሞ በደግ መንገድም እንሞክረው። ደግ ደጉን ያሳየን!!
አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና፣ የብልፅግና ያድርግልን!!
አዲሱን ዓመት እርስ በርስ የምንተሳሰብበትና ለአገር የምናስብበት ያድርግልን!!
አዲሱን ዓመት ተነጋግረን-ተወያይተን  የምንግባባበት ያድርግልን!!
አዲሱን ዓመት እርስ በርስ የምንከባበርበት ያድርግልን!!
መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!!

Read 725 times