Monday, 09 September 2024 00:00

በዓለም መድረክ ወርቅ ላገኙ አትሌቶች40 ሺ ብር?

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(0 votes)

  • 350 ዶላር ማለትኮ ነው። “የውሎ አበል” ክፍያ ይመስላል።
                               

          በፔሩ በተካሄደው ዩ20 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ አትሌቶች ያገኙት ድል አስደናቂ ነው። 6 ወርቅ፣ 2 ብር፣ 2 ነሐስ ሜዳሊያዎችን ተቀዳጅተዋል። ከዓለም በ2ኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ስም በማዕረግ ለመቀመጥ በቅቷል። ከአሜሪካ በመቀጠል ማለት ነው። ቻይና ሦስተኛ ሆናለች። ጃማይካና ኬንያ ደግሞ አራተኛና አምስተኛ።
ለሀያኛ ጊዜ ነው የተካሄደው። ኢትዮጵያ 2ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ የቻለችው ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። 6 የወርቅ ሜዳሊያ? ድንቅ ነው። በውድድሩ ከተሳተፉ 21 አትሌቶች መካከል ዘጠኙ የሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል። የአሜሪካ አትሌቶች 8 የወርቅ ሜዳሊያ፣ የቻይና አትሌቶች 4 የወርቅ ሜዳሊያ። የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤት ቀላል አይደለም።
በዓለም መድረክ እንደዚህ ዐይነት አስደናቂ ገድል የፈጸሙ ወጣት አትሌቶች ናቸው የ40 ሺ፣ የ30 ሺ እና የ20 ሺ ብር ሽልማት የተሰጣቸው። ከዐሥር ዓመት በፊት ቢሆን እሺ። ዛሬ የብር ዋጋ በረከሰበት ዘመን… አንድ ጫማ… ቢበዛ ሁለት ጫማ እንደመሸለም ቁጠሩት። በጣም ያሸማቅቃል።
በፓሪስ ኦሊምፒክ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ያሸነፉ አትሌቶች፣ የ7 ሚሊዮን እና የ4 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆነዋል። በቂ ባይሆንም ጥሩ ነው። አንድ ደህና መኪና ለመግዛት ይበቃል መቼም። ወደ ዶላር ብንመነዝረው፣ 60ሺ እና 35ሺ ገደማ ሊሆን ይችላል። ለኦሎምፒክ ያንስ እንደሆነ እንጂ አይበዛበትም። የስፖርቶች ሁሉ ጉልላት ነው ኦሊምፒክ።
በዩ20 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ያሸነፉ ወጣት አትሌቶች፣ ተመሳሳይ ሽልማት ማግኘት ነበረባቸው አይባልም። ቢሆንም ግን፣ 40 ሺ ብር? 350 ዶላር ሽልማት?
ከኦሊምፒክ ጋር ባይነጻጸርም፣ “የዓለም ሻምፒዮና” ነው። ከ20 ዓመት በታች የወጣት አትሌቶች ሻምፒዮና ነው በሚል ምክንያት ንቀነው ይሆን እንዴ? ከኦሎምፒክ ጋር ምን ያህል እንደሚቀራረብ አላወቅንም ማለት ነው።
የማራቶን ውድድር ባይኖረውም፣ በሌሎቹ ውድድሮች ከኦሎምፒክ ጋር በጣም ተቀራራቢ ነው። ይመሳሰላል ለማለት ብቻ አይደለም።
ታሪከኞቹ የኦሎምፒክ ጀግኖችን አንድ ሁለት ብላችሁ አስታውሱ። ፈር ቀዳጆቹ ኃይሌ ገብረሥላሴና ደራርቱ ቱሉ፣ በኦሎምፒክ ወርቅ የደመቁት ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር… እነዚህ ሁሉ፣ ከኦሎምፒክ በፊት በወጣቶች የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ያገኙ አትሌቶች ናቸው።
የጊዜ ልዩነቱ ጨምር ተቀራራቢ ነው። በሁለትና በአራት ዓመት ልዩነት ነው ወደ ኦሊምፒክ የሚሸጋገሩት። በሌላ አነጋገር፣ የዛሬዎቹ ወጣት ሻምፒዮኖች ናቸው ለቀጣዩ ኦሎምፒክ የሚጠበቁት።
በኦሎምፒክ መድረክ የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን የበቁ ጀግና አትሌቶች… ከአራቱ ውስጥ ሦስቱ፣ በወጣት የዓለም ሻምፒዮን ድል በማስመዝገብ የመጡ አትሌቶች ናቸው።
ደራርቱ ቱሉ በ1990 የወጣቶች ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች። ለኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ባለ ሜዳሊያ ሴት አትሌት ሆነች።
በሁለት ዓመት ልዩነት በ1992 የባርሴሎና ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ተቀዳጀች። የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት የኦሎምፒክ ጀግና በመሆን በአርአያነት ለበርካታ ታዳጊ አትሌቶች የመንፈስ ብርታት ሰጠች።
ኃይሌ ገብረሥላሴና ጌጤ ዋሚ በ1992 የወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ነበር የተሳተፉት። ኃይሌ ሁለት ወርቅ አግኝቷል። ጌጤ ደግሞ የብር ሜዳሊያ። ከዚያስ? በቀጣዩ ኦሎምፒክ በ1996 የኦሎምፒክ ባለሜዳሊያ ሆነዋል።
ከማራቶን ውጭ ያሉትን ውድድሮችን ካነጻጸርን፣ በ2000 የሲድኒ ኦሊምፒክ ላይ አምስት አትሌቶች ስድስት ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል - 3 ወርቅ፣ 1 ብር፣ 2 ነሐስ። አምስቱም አትሌቶች፣ ቀደም ሲል በወጣቶች የዓለም ሻምፒዮና ላይ ድል የተቀዳጁ አትሌቶች ናቸው።
ከዚያ በኋላም ታሪከኞቹ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር ይመጣሉ። ከኢትዮጵያ አትሌቶች ሁሉ፣ በኦሎምፒክ መድረክ በሜዳሊያዎች የደመቁ ወደር የለሽ አትሌቶች ናቸው - ሦስቱም።
ወደ ኦሎምፒክ ያመሩት ግን፣ በቅድሚያ በወጣቶች የዓለም ሻምፒዮና ላይ ድል በመቀዳጀት ነው።
ምናለፋችሁ፣ ባለፉት አርባ ዓመታት በዐውደ ኦሎምፒክ የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን የቻሉ አትሌቶች ቢቆጠሩ፣ ከአራቱ ውስጥ ሦስቱ በወጣቶች የዓለም ሻምፒዮና ላይ ድል በማጣጣም ያለፉ ናቸው።
በዓጭሩ፣ የወጣቶች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከኦሎምፒክ የአትሌቲክስ ፉክክር ጋር በቅርብ የተቆራኘ የብቃት ማስመስከሪያ መድረክ ነው።
እና በዚህ የዓለም መድረክ ላይ የወርቅ ሜዳሊያ የተቀዳጁ አትሌቶችን 350 ዶላር ሽልማት መስጠት ምን ይባላል? ሽልማት ከሰጡ አይቀር፣ የማያሸማቅቅ ሽልማት መስጠት ነው እንጂ፣ የአንድ ቀን የጉዞ ወጪ (ፐርዳይም) መስጠት ምንድነው?
በእርግጥ፣ መንግሥት እንዳሻው ገንዘብ እያፈሰ መስጠት አለበት ማለቴ አይደለም። እንዲያውም ከመንግሥት ጋር ባይነካካ ጥሩ ነበር። የብቃት ልሕቀትን የሚያደንቁና የሚያበረታቱ ግለሰቦች የሉም እዚህ አገር? እንደ መንፈሳዊ ኀላፊነት በመቁጠር ለጀግና ሰዎች የብቃት ደህና ሽልማት ለማዘጋጀት አስተማማኝ ዐቅም ያላቸው ኩባንያዎች የሉም? ሞልተዋል።
በዓለም መድረክ የብቃት ልሕቀትን ለሚያሳዩ ጀግኖች ከ350 ዶላር የተሻለ ሽልማት ማቅረብ አያቅታቸውም። የሰዎችን ድንቅ ብቃት ማክበር… የቀና ሰዎች ሁሉ የተቀደሰ መንፈስ ነው። አይደለም እንዴ?


Read 502 times