Monday, 09 September 2024 00:00

ታማኝነት፤ አብሮ ለመኖር

Written by  ሙሉእመቤት ጌታቸው
Rate this item
(1 Vote)


        በሰንሰለታማ ተራራዎች በተከበበች ሰላማዊ መንደር ውስጥ የሚኖር ትንሽ ማሳ የነበረው አንድ  ድሃ  ገበሬ ነበር፡፡ ገበሬው  በነበረው ትንሽ ማሳ ላይ የተለያዩ ሰብሎችን   እያመረተ ህይወትን ከቤተሰቡ ጋር በደስታ ይመራል፡፡ ይህ ሰው  በመንደሩ  ውስጥ በጠንካራ ሠራተኝነቱ፤ በቁርጠኝነቱና በታማኝነቱ ይታወቃል፡፡ በአንድ ወቅት መንደሩ  በከባድ ድርቅ ተመታ፡፡ አዝርእት ጠፋ፡፡ አብዛኛዎቹ ገበሬዎች ያለ የሌለ አቅማቸውን አሟጠው እስከ  መጨረሻው  ቢጥሩም ችግሩን መቋቋም  አልቻሉም፡፡ ድሃው   ገበሬ ግን  ሁኔታው ቢከብደውም በጥንቃቄ በማቀድና ጠንክሮ በመስራት ጥሩ ምርት ማምረት ቻለ፡፡ አንድ ቀን  ለኑሮ  የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን  ለቤተሰቡ ለማሟላት፣ ምርቱን ወደ  ገበያ ወስዶ ለመሸጥ አሰበ፡፡ ምርቱንም ተሸክሞ ወደ ደራው ገበያ ገባ፡፡
ገበያ ገብቶ  ምርቱን  ከመዘርጋቱ አንድ  ሃብታም  ነጋዴ ተመልክቶ  ቀልቡ በሚያምረው ምርት ላይ አረፈ፡፡ ነጋዴው በምርቱ ጥራት ተመስጦ፤ “ምርትህን በሙሉ በውድ ዋጋ እገዛሃለሁ፤  አንተ ደግሞ  እኔ በምነግርህ ሃሳብ ትስማማለህ” አለው፡፡ “የምትነግረኝ ምንድንው?” ሲል ገበሬው ጠየቀ፡፡ “አሁን የገበያተኛው  ዓይን በሙሉ በአንተ  ምርት ላይ ስለሆነ  ለሚያናግርህ ሁሉ ምርቱ ከአኔ ሰፊ ማሳ ላይ  እንደተገኘ ትናገራለህ፤ ይህን ካደረግህ  በማትገምተው ትልቅ ብር እገዛሃለሁ” አለው፡፡ ምንም  እንኳ  ገንዘቡ ቤተሰቡን ከችግር የሚያሳርፍ  መሆኑን  ቢያውቅም  ገበሬው  ቁርጠኛና  ታማኝ ስለነበር፤ “እውነት ባልሆነ ነገር አልስማማም፤ የኔ ምርት የመጣው  ከኔ ትንሽ ማሳ ላይ ነው፤ ስለዚህ  መዋሸት አልፈልግም” ብሎ የሃብታሙን ትልቅ  ስጦታ ትህትና በተሞላበት አነጋገር ውድቅ አደረገው፡፡
  ሃብታሙ ነጋዴም በገበሬው  ታማኝነት ተገረመ፡፡ ቆራጥነቱም  በገበያተኛው መሃል ተሰራጨ፤ አልፎም የገበያውን ሁኔታና የሕዝቡን የኑሮ ግብግብ  በድብቅ ሊጎበኝ ከመጣ  የአካባቢው ንጉሥ ጆሮ  ደረሰ፡፡ ንጉሱም በገበሬው ታማኝነት ስለተደነቀ ወደ ቤተመንግስቱ አስጠራው፡፡ “በዚህ የችግር ጊዜ ያሳየኸው ታማኝነት የሚያስመሰግን ነው፤ እንደ አንተ አይነት ቁርጠኛ  ዜጎች ናቸው ማህበረሰባችንን የሚያስተሳስሩ እሴቶችን ጠብቀው የሚያቆዩትና ለትውልድ የሚያስተላልፉት፡፡ ሰው ሁሉ ያንተን ፈለግ እንዲከተል  እንፈልጋለን፤ ለቁርጠኝነትህና ለአርአያነትህ  ሽልማት ይገባሃል፡፡” በማለት ሰፊ ለም መሬትና እርሻውን የሚያስፋፋበት በርካታ ገንዘብ ሸለመው፡፡ ገበሬውም  ሽልማቱን  ተቀብሎ  ብዙ ምርት አመረተ፤ በችግሩ የተጎዱ የመንደሩ ገበሬዎችንም   መርዳት ጀመረ፡፡ የእርሱ ታማኝነትና ቁርጠኝነት በዙሪያው ላሉ ሁሉ ማነቃቂያና ማስተማሪያ  ሆናቸው፡፡  
ታማኝነት፡-  ከማታለል፤ ከማጭበርበር፤ ከመዋሸትና ከመስረቅ እራስን ማጽዳት ነው፡፡ በሌላ መልኩ እውነተኛነትን፤ ግልጽነትን፤ ታማኝነትን፤ ተጠያቂነትን ማዳበር፤ እውነትን መናገርና መተግበር ነው፡፡
ታማኝነት፡- ተአማኒነት የተላበሰ  ቤተሰብን፤ ማህበረሰብን፤ ኃላፊነቱን የሚወጣና ተጠያቂነትን ያዳበረ  ብቁ ዜጋን ለመፍጠር፤ አዎንታዊ ግንኙነቶችን፤ ማህበራዊ መተማመንን፤ ሃገራዊ አንድነትንና እድገትን ለማስፈንና  ፍትሐዊ  ውሳኔ ለመስጠት፤ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡
ታማኝነት፡-  የሰው ልጅ ስልጣኔ  ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ፤ ለመተማመን፤ ለጥሩ ግንኙነት፤ ለመከባበር፤ ለመተሳሰብ አብሮ ለመኖር፤ አዎንታዊ ለውጥ  ለማምጣት የሚረዳ የማህበረሰብ   እሴቶች  መርህ ሲሆን፤ ለማህበራዊና ሃገራዊ ሁለንተናዊ እድገት የሚጠቅም፤ ከልጅነት  ጀምሮ  ከታላላቆች  የሚወረስና የሚተገበር ጠንካራ  የለውጥ  መሳሪያ ነው፡፡ በታማኝነት ላይ የተመሰረተ ግላዊም ሆነ ሙያዊ መስተጋብር፡- ግልጽነትን፤ ፍትሐዊነትን ተጠያቂነትን ያዳብራል፤ለፍትሐዊና ለማህበራዊ እኩልነት መሰረት ይጥላል፡፡
-በምንኖርበት የስልጣኔ ዘመን የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ፤ አለምን የሚያስጨንቁ የፖለቲካ መከፋፈል፤የማህበራዊ  እኩልነት አለመመጣጠንና የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ፈተናዎችን ለመቋቋም የጎላ  አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡  
-ታማኝነት በሁሉም የሕይወት ዘርፍ እውነተኛነትን ያረጋግጣል፤ ጠንካራና አስተማማኝ ግንኙትን  ይገነባል፤ አዎንታዊ የሥራ አካባቢን ይፈጥራል፤  ምርታማነትን  ያሳድጋል፤ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ያሰፍናል፡፡ የጠበቀ ማህበራዊ መስተጋብሮችንና ግላዊ እውነተኛነትን ያሳድጋል፡፡ ያልታሰበና ያልተገመተ ሰላምን፤ ደስታንና ስኬትን በማጎናጸፍ የተሟላና ነጻ ሕይወት መምራት ያስችላል፡፡
-አካላዊና አእምሯዊ ጤንነትን ይጠብቃል፡፡ በተቃራኒው ታማኝ አለመሆን መድሃኒት  ለሌላቸው  ሥር ሰደድ በሽታዎች፤ እንደ  ደም ግፊት፣ ልብ፣ ስኳርና መሰል ሕመሞች መነሻ ይሆናል፡፡ ጭንቀትን፤ ውጥረትንና  ሰላም ማጣትን ያስከትላል፡፡
ታማኝነት፡- ለሌሎች እውነተኛ ሆኖ መገኘት ብቻ ሳይሆን ለእራስ ስሜት፤ ለእራስ ሃሳብና ለእራስ ፍላጎት ጭምር ታማኝ ሆኖ መገኘትን ያካትታል፡፡
-ሰዎች ታማኝ ሲሆኑ  እራሳቸውን  ያውቃሉ፤ ሃሳባቸውን ስሜታቸውንና ባህሪያቸውን በግልጽ ይረዳሉ፡፡ ድክመታቸውንና ጥንካሬያቸውን ይለያሉ፡፡ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ ማስተካከል የማይችሉትን አምነው ይቀበላሉ፡፡ ለሚጠፋውም  ለሚለማውም ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡ በራሳቸው ይተማመናሉ፡፡ እራሳቸውን  ለስኬት ያበቃሉ፡፡ በሌሎች ዘንድ ይታመናሉ፤ ከብርና  ዝናን  ይጎናጸፋሉ፡፡
-ሰዎች ታማኞች ሲሆኑ ሁኔታዎችን፤ አላማዎችን፤ እሴቶችንና ግቦችን በማገናዘብ፡ ፍርሃትን ፤ ይሉኝታን  የማህበብረሰብ ጫናን፤ እራስ ወዳድነትን አስወግደው  ትክክለኛ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ፍትሐዊነትንና እውነተኛ መተማመንን ይፈጥራሉ፡፡
-ታማኝ   ሰዎች  በንግግርም ሆነ  በድርጊት እውነትን  ይተገብራሉ ፤ እውነተኛነትን ያበረታታሉ፤ በዙሪያቸው ላሉ ተምሳሌት ይሆናሉ፤ የመደማመጥ፤ የመደጋገፍ፤ የመተማመን፤ የመከባበርና ርህራሄ የሰፈነበት፤ በተስፋ የተሞላ  አካባቢን ይፈጥራሉ፤ አዎንታዊ ለውጥ በማምጣት ሕብረተሰብን ለማሳደግ  ጠንክረው ይሠራሉ ፡፡  
-ታማኝ ሰዎች  በቅንነት፤ በመቻቻል፤ በመከባበር   ላይ የተመሰረተ  ጠንካራና  ትርጉም ያለው የግንኙነት መስመር ይዘረጋሉ፤ ጥሩ ማህበራዊ  መስተጋብሮችን  ይፈጥራሉ፤ ግላዊ ፍላጎቶችን  በማጥበብ  የጋራ መፍትሄ ያበጃሉ፤  ውህደትንና የእኔነት  ስሜትን  ያሰፍናሉ ብሎም  ማህበራዊ መተማመንን፤ መደጋገፍን፤ መተጋገዝንና ፍቅርን  ያሳድጋሉ፡፡
በአጠቃላይ   ታማኝነት   ግላዊና  ማህበራዊ  መተማመን በማሳደግ፤ በልዩነት መሃል  አንድነትን፤  መቻቻልን፤ ውህደትንና አብሮነትን በማዳበር፤ ፍቅርን  መደጋገፍንና መተባበርን፤ በጋራ መስራትን፤ በጋራ መኖርንና በጋራ ማደግን በማጎልበት፤ ሃገራዊ  ሰላምንና እድገትን እውን ለማድረግ  ጠቃሚ መሳሪያ ነው፡፡ በተለይም ጥሩና ጥሩ ያልሆኑ  ማህበራዊ መስተጋብሮች እኩል  በተስፋፉበት  በዚህ ዘመን  የሚከሰቱ ማህበራዊ ቀውሶችን ለመፍታትና ሰላምና ውህደትን ለመፍጠር ሰዎች  ለራሳቸውም  ሆነ ለሌሎች ታማኝ ሆነው  መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡



Read 330 times