“ቆሻሻ አውጡ!”
ሰፈሩ በጽዳት ሰራተኞች ድምጽ ድብልቅልቁ ወጣ። እየተነጫነጭኹ ነቃኹ። ድምጹ ተደገመ. . . . “ቆሻሻ አውጡ!” ይኼን ጥሪ ስሰማ ካለኹበት ተንቀሳቅሶ ቆሻሻ ከመፈለግ ይልቅ አእምሮዬን አውልቆ መስጠት፥ ስጋዬን በፌስታል አንጠልጥሎ መኪናቸው ላይ መዶል ያምረኝ ከጀመረ ሰንብቷል። በሬ በኃይል ተንኳኳ።
“ተነሽ! አንቺ ጅራሬ ቆሻሻ አውጪ!” ጎረቤቴ ካልዳኙ አንባረቀ።
“ዳኙ?”
“አቤት?”
“አፋፍሰኽ መኪናው ላይ ወርውረኝ?”
“ጥንብ አይቀበሉም! ተነሽ አትሟዘዥ አቦ!” ጥሎኝ ኮቴው ሲርቅ ይሰማኛል። ካልዳኙ የጠርሙስ ወዳጄ፥ ጎረቤቴ፥ የሰፈር መከታዬ፥ የስካር አቻዬ ነው፤ እወደዋለኹ። ሰዓቱ ለሁለት ሩብ ጉዳይ ይላል፤ ለካ ዳኙ ስራ ረፍዶበት ነው መጣደፉ። እልል ያለ ጠበቃ ነው፤ ኹሌም 11:30 ሳይሞላ። ከ11፡30 በኋላስ? ዳኙን ዓለም ላይ ያለ ምንም ነገር አያገባውም፡፡ ያን ጥቁር ጋዋን ቢሮው ያንጠለጥለዋል። ሕግን አንጠራርቶ ይሰቅለዋል፥ ፍትሕን ቢሮው ጥግ ያለው ልብስ መስቀያ ላይ ይቸነክረዋል፥ ጸአዳ ሸሚዙ ያንን ጥቁር መግነዝ አምልጦ ዓይን ማጥበርበር ይጀምራል። ስጋው ጽልመቱን ጋዋን ቢያወልቅም ጨለማው ወደ ውስጡ ነፍስያው ድረስ ይሰርጋል። መስሪያ ቤታችን መንገድ ተሻግሮ ፊት ለፊት ይፋጠጣል። የስራ መውጫችን ሲደርስ ከአዳኝ ወጥመድ እንዳመለጠች ወፍ ብርርርርር ብለን እንወጣለን - ወደ ገነታችን ከቤ ግሮሰሪ። ከስራ ወጥተን እዚያ ስንደርስ ‘ጥላት’ ድል አድርጎ የተመለሰ ጀግናን የሚያስንቅ አቀባበል ይደረግልናል፡፡ ከቤ? የከቤማ ይብሳል! ኒሻን ትከሻችን ላይ ሊያኖር ምንም አይቀረውም። እኔም ገና ቢጫው ወንበር ላይ ከማረፌ ዓለም፥ መከራዎቿ፥ ጉድለቷ፥ የበሽተኞቼ ፊት፥ የአባቴ እስር ቤት መክረም፥ የታናሽ ወንድሜ አእምሮ ሕመም ኹሉም እያየዃቸው ይኮስሳሉ - ሚጢጢዬ ጠጠሮች ይሆናሉ፤ ያኔ በልጅነቴ ቅልብልቦሽ የተጫወትኹባቸው።
የግዴን ተነሳኹ። ለመልበስ ማሰቡ በራሱ ደከመኝ። ምን አለ እነዚያ የተረገሙ ባልና ሚስት ያን ዕፀ-በለስ ባልበሉ! ከረበበባቸው የፈጣሪ ጸጋ የተነሳ ዕርቃን መኾናቸው አይታወቃቸውም ነበር፥ ያ ዘመን ላይ በኾንኹ ባልለበስኹ ብዬ ተመኘኹ። ግን በዚህ ዘመን ሰው እንዲህ አረመኔነት ውስጥ ተነክሮ ምንም ሳይታወቀውና ሳንተዋወቅ፣ ኃፍረታችን ሳይታይ የምንኖረው ከመጠን ያለፈ ጸጋው ረብቦብን ነው? ወይስ አመጽ ጥግ ሲደርስ ሽልማቱ የጋራ እውርነት ነው? የኾነው ኾኖ እንደነገሩ ለባብሼ ተጎትቼ ወጣኹ። ከተማዋ የነጋባት አለሌ ጨፋሪ ትመስላለች፤ ምንም ብትመስል ግድ የለኝም።
ወደምሰራበት ሰፈር የሚያደርሰኝ ታክሲ ውስጥ ገባኹ፥ ወንድሜ ትዝ አለኝ፤ የልጅነት መልኩ- ያ ደማቅ ፈገግታው። አባዬ . . . . አባዬ. . . አባቴ ሙሰኛ እጁን ያበሰበት የኔ ንጹሕ ሸማ! ሰላም አድሮ ይኾን? ድንፋታም ወጠምሻ እስረኛ አባቴን ረገጠብኝ ይኾን? ባባኹ፤ ናፈቁኝ። መድኃኒት መግዣ አጥተው ፊት ለፊቴ እንባቸው የተንዥረዥረው የራሕዋ እናት ትዝ አሉኝ. . . ኹሉም ችግሮቼ ከትናንቱ ጠጠርነት ወደ ግዙፍ ዐለትነት ተለውጠው አደሩ። ፈራኹ፤ ተላትሜ የምደቅቅ ትንሽዬ ፍጥረት መኾኔ አብሰለሰለኝ። እርጉማን ባል እና ሚስት! ተስገብግበው በለሱን ባይበሉ ኖሮ ይኼ ኹሉ ጉስቁልና አልነበረም ቱ! እና ማንን ልውቀስ? የማውቀውን ሳይኾን የማላውቀውን የሩቁን መውቀስ ተምሬ አድጌያለኹ።
እንደ ሰው ከተሳፈርኹበት ታክሲ እንደ ነተበ ጨርቅ ከቁር እንደማያስጥል፥ ገመና እንደማይሸፍን ኾኜ ወረድኹ። ቆሻሻ አውጡ ሲባልኮ ዳኙ መኪናቸው ላይ ሊወረውረኝ ይገባ ነበር፤ ይኼ ንፉግ ኤጭ! ወደ መስሪያ ቤቴ ግቢ ስገባ እሪሪሪሪሪሪሪ በይ ይለኛል- የበሽተኛ መአት። ደዌ ካደቀቀው የሕሙማን መተኛ እና ከሬሳ ክፍሉ የቱ ይሻላል? ይኼን እያሰብኹ ሞት ራሱ ስጋ ለብሶ ፊቴ ቆመ - ዶክተር ጀምበሬ እውነትም በስም እና በተሰያሚው መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት የለም። በፈጣሪ! እርሳቸውን ብሎ ጀምበር! ስማቸውን መልዓክ አላወጣውም፥ ምንአልባት ከኾነ እንኳ ሊኾን የሚችለው የወደቀው መልዓክ ነው። ባየኋቸው ቅጽበት ቀኑ ሌሊት ስምንት ሰዓት ጋኔን ልጆቹን የሚላጭበት ሰዓት ይመስለኛል፥ ላጭቷቸው ይኾን እንዴ የተመለጡት? የሆስፒታሉ የሐኪሞች ዋና ኃላፊ ናቸው፥ ስልካቸው ቶሎ ቶሎ ይጮሀል፥ ሰማያዊ ከተመረተች ዓመት ያልሞላት ከፍ ያለች መኪና አለቻቸው፥ ሽቶአቸው የትም ይኹኑ ኹሉም ደርብ ላይ ይሸታል. . . . መግደላዊት ማርያም ክርስቶስ አናት ላይ ያፈሰሰችውን በልብሳቸው እየተንከባለሉ አብሰውት ይኾን? እንጃላቸው! ሽቶአቸው ሲሸተኝ ገና ሊሞቱ የተዘጋጁ ብዙ ሰዎች ይታወሱኛል፤ እንደ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን የትንሳዔ ተስፋ የሌላቸው። መድኃኒት ከሆስፒታላችን ቶሎ ያልቃል፥ ጀምበሬ ይሽቀረቀራሉ፥ የራሕዋ እናት ያቀረቅራሉ።
እኔ ሕይወት በዝረራ የረታችኝ ተሽናፊ ነኝ። ተለጉሜ በሽተኞቼን ሳክም እውላለኹ፤ እየወደድዃቸው በተመሳሳይ ጊዜ እጠላቸዋለኹ። ለምን ጠንካራ አልኾኑም? ለምን ደህና ቦታ አልታከሙም? ለምን ይታመማሉ? ለምን ማሳከሚያ ያጣሉ? ዓለም አፈር ልሰው የሚነሱ ታጋዮች እና ተናጣቂዎች የሚያፈጓት ቅሪላ እንደኾነች እንዴት አያውቁም? እናደድባቸዋለኹ። ለምን አይዘርፉም? ለምን አይገድሉም? ለምን ቀማኞች አይኾኑም? ሐብታሙ እና ዋልጌው የጨከነውን ያኽል ድሃው እና ምስኪኑ ጨክኖ ቢኾን አንዳችን እንተርፍ ይኾን? የመኪና መንገድ እንዲሰራበት የተመደበውን ገንዘብ ‘እምጷ ቅልጥ!’ ብሎ አግበስብሶ ሰፈር መሀል ሲንጎማለል፥ አያ ንጋቱ ልጁ ምጥ መጥቶባት መንገዱ መኪና ስለማያስገባ የወሳንሳ ሲወስዷት እጃቸው ላይ ሞታ እስታሁን ያንን የወረዳ አስተዳዳሪ አያ ንጋቱ ተኩሶ አለመግደሉ የእግዜር ቸርነት አይደል? ከሚመጣላቸው ኩርማን እህል አፉ ላላዞረው አስታማሚ ሲቆርሱ እመለከታቸዋለኹ - እወዳቸዋለኹ፤ ጀምበሬ ረግጠው የሚያንፈራፍሩትን ሰብዓዊነት ከተኛበት ትር ትር ሲል በነርሱ አልፎ ይታየኛል።
ከምጽአት ቀን ይልቅ ከዚያ መቃብር ግቢ ወጥቼ እነ ዳኙን የምቀላቀልበት ሰዓት ይናፍቀኛል። ኹሌ ዳኙ እና እኔ የምንደዋወልበት ሰዓት 11፡30፥ ከራሳችን ለመለየት የቆረብንበት ሰዓት፥ የነጻነት ሰዓት፥ የሽሽት ሰዓት፥ የግርግር ሰዓት፥ የጠርሙስ ሰዓት፥ የውካታ ሰዓት. . . እከንፋለኹ፤ ይኼንን አስቀያሚ ዓለም ለመሸሽ. . . ወደ ገነታችን ከቤ ግሮሰሪ። ከዳኙ ጋር ሞቅ ያለ ሰላምታ እያስተናገድን ወደ ውስጥ ገባን። ማስቴ ለሁለታችንም ካስትል ከፈተችልን። ከጠርሙሱ ወደ ሆድ ዕቃችን መጠጥ መገልበጡን ተያያዝነው፥ ዳኙ ፈዟል።
“ እስቲ ነገ ጠዋት ቤተክርስቲያን እንሂድ? “
“ምን አልከኝ?”
“ነገ እሁድ አይደል? እንሂድ እንሳለም?”
“እሺ! “
“የምርሽን ነው?”
“አዎ ለመቀስቀስ ያብቃህ እንጂ።”
አምላክ ፊት ለመቅረብ ግን ብቁ ነን? እኛ ነን ፍለጋውን መኼድ ያለብን ወይስ እርሱ ነው ፈልጎን ሊመጣ የሚገባው? ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ወጣን። ከካፌ ስድስት የተቀቀሉ እንቁላሎች ገዝተን መሰልቀጥ ያዝን. . . አባቴ. . . . ወንድሜ. . . ትንንሽዬ ስብርባሪዎች ኾነው አእምሮዬ ውስጥ ተመሽገዋል፤ ረሳኋቸው - ራሴን ረሳኹ።
Tuesday, 10 September 2024 00:00
ትንንሽዬ ስብርባሪዎች
Written by የአብሥራ አድነው
Published in
ህብረተሰብ