የዋጋ ንረት፣ የክረምቱ ዝናብና የምንዛሬ ለውጥ
ሕዳሴ ግድብና የአባይ ውኃ፣ የግብፅ መንግሥትና የሶማሊያ ስኬት
የተራቆተ ትምህርት-የ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት ከዐሥር ዓመት በፊት በአማካይ 30 በመቶ ነበር። የዘንድሮው እንደዚያው፣ ካቻምናም እንደዚያው ወይስ የዘንድሮው ትንሽ ይሻላል?
ዘንድሮ መቼም ካምናና ካቻምና የሚሻል ይመስላል። የክረምቱ ዝናብ ጥሩ ነው። በትክክል ከቀጠለና በጊዜው የሚያበቃ ከሆነ፣ ደህና የእህል ምርት መገኘቱ አይቀርም። የማዳበሪያ አቅርቦት ከዓምናው በጣም የተሻለ ስለሆነ፣ ለዘንድሮው አዝመራ መልካም አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እውነትም ዘንድሮ ተስፋ አለን።
በእርግጥ፣ ከባዱ የዋጋ ንረት ዘንድሮም አይለቀንም። እደተለመደው የኢትዮጵያውያንን ኑሮ ማናጋቱ አይቀርም። ከዓመት ዓመት በለያችን ላይ እየጋለበ ተጫውቶብናል። ዓምና ትንሽ የግለቱ የሚበርድ መስሎ ነበር። የመንግሥት የገንዘብ ኅትመት ረገብ ሲል የዋጋ ንረትም ቀስ በቀስ መብረዱ አይገርምም። ደግሞም፣ ዘንድሮ መንግሥት ከተለመደው የገንዘብ ኅትመት ቆጠብ ለማለት ቃል እንደገባ የአይኤምኤፍ ሰነድ ይገልጻል።
ቢሆንም ግን፣ ቀድሞውኑ የታተመው ገንዘብ ቀላል አይደለም። በዚያ ላይ ክፉኛ ተዛብቶ የነበረውን የምንዛሬ ዋጋ በአንድ ጊዜ ለማስተካከል የተካሄደው ለውጥ፣ ለተወሰኑ ወራት የዋጋ ንረትን እንደሚያባብስ ይታወቃል። እንደ አይኤምኤፍ ግምት ከሆነ፣ 25 በመቶ የነበረው የዋጋ ንረት፣ ዘንድሮ ወደ 30 መቶ ሊያሻቅብ ይችላል።
እንግዲህ የዋጋ ንረት የሚበርድለት ከሆነም ከዓመቱ አጋማሽ በኋላ ለከርሞ ነው። ያንን ለማየት ያብቃን።
ደግሞም የምርጫ ሲቃረብ የዋጋ ንረትን ለማብረድ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆንልን ይችላል። በእርግጥ የመንግሥትን አዝማሚያ ታዝባችሁ ከሆነ “የምርጫ ጊዜ እየመጣብኝ ነው” ብሎ ብዙም የሚጨንቀው አይመስልም። ባይጨንቀው እንኳ ትንሽ የሚያሳስበው ከሆነ፣ ጨከን ብሎ የዋጋ ንረቱን ቶሎ ለማርገብ ሊወስን ይችላል። ካደረገው ዕሠዬው ነው። አንድ ተስፋ ነው። መቼስ ስለ “ተስፋ” አይደል የምናወራው?
የዋጋ ንረት መረገብ ቢጀምር ትንሽ ትንፋሽ እናገኛለን። እንዲያ ቢሆንልን እንኳ፣ የኑሮና የኢኮኖሚ ችግሮች ሁሉ ይቃለላሉ ማለት አይደለም። የምኞትና የፍላጎት ጉዳይ ብቻ አይደለም። በአንድ አመት ይቅርና፣ ወይም በአምስትና በዐሥር ዓመት፣ ከድህነት ወደ ብልጽግና እመር ብሎ የሚገባ አገር የለም። ሰላምን እያሠፈኑ፣ ሕግና ሥርዓትን እያደላደሉ፣ በጥበብና በትጋት ለበርካታ ዓመታት በጽናት መሥራትና መገሥገሥ ያስፈልጋል - ከድኽነት ለመውጣት፣ ወደ ብልጽግና ለመጠጋት።
ይህ የዓምና ብቻ ወይም የዘንድሮ ብቻ ፈተና አይደለም። የድኽነትና የብልጽግና ጉዳይ፣ የመጪው ዓመት፣ ከዚያም የዐሥርና የኻያ ዓመታት ፈተና ይሆናል። ከዚህ አንጻር ሲታይ፣ ዘንድሮ ከዓምና እንዲሁም ከሚቀጥለው ዓመት ጋር ተመሳሳይ ነው።
እናም፣ ዘንድሮ ከዓምና የተሻለ እንዲሆን ተስፋ እናድርግ። ዘንድሮ ከዓምና ጋር ተመሳሳይ ዓመት እንደሚሆን ደግሞ እንወቅ።
የሚቀጥለው ዓመት ከዘንድሮ የተሻለ እንዲሆን እንመኝ። ግን ደግሞ ከዘንድሮ ጋር ተመሳሳይ ዓመት እንደሚሆንም አንርሳ።
ሌላው ይቅርና፣ የሕዳሴ ግድብ ስኬትም እንኳ ከዚህ የተለየ አይደለም። በየዓመቱ ግንባታው እየተመነደገ፣ በየዓመቱ ውኃው እየበረከተ፣ ሐይቁ እየሰፋ ሲሄድ ማየት ያስደስታል። በየዓመቱ ተመሳሳይ ስኬት ማየት መታደል ነው። ተመሳሳይ ነው፤ ግን እየተሻሻለና እያደገ።
ዘንድሮ እና በሚቀጥለው ዓመት የግድቡና የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ድንቅ ታሪክ ነው።
ግን፣ የማይጠናቀቁ ነገሮችም አሉ። ከዓመት ዓመት ያላባራው የግብፅ መንግሥት ተቃውሞና መሰናክል፣ ከእንግዲህ ብዙም ትርጉም አይኖረውም ብለን እናስብ ይሆናል። በሕዳሴ ግድብ ላይ ብዙም የሚያመጣው ለውጥ ላይኖር ይችላል። ነገር ግን፣ የግብፅ ተቃውሞና መሰናክል፣ ገና ተጀመረ እንጂ አልተጋመሰም።
ለምን?
ከሕዳሴ ግድብ በኋላ ገና ሌሎች ግድቦች እንደሚመጡ ያውቃል።
ኢትዮጵያውያን ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ብቻ ሳይሆን፣ ለመስኖ እርሻ የሚያገለግል ውኃ ያስፈልጋቸዋል። የግብፅ መንግሥት ይህን ያውቃል። ተቃውሞና መሰናክል መደርደሩም የበርካታ ዓመታት ዕቅድ እንደሚሆን አትጠራጠሩ። ሱዳን ውስጥ የጦር ሰፈር ለመሥራት ብዙ ሞክሯል። አሁን ደግሞ በሶማሊያ በኩል ለመምጣት መግቢያ መንገዶችን እያመቻቸ ነው።
ፊት ለፊት ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ለማካሄድ ላይደፍር ይችላል። በቀጥታ ባይሆንም ግን፣ ኢትዮጵያን ሰላም ለመንሣት፣ በግራና በቀኝ ኢትዮጵያን የሚያዋክቡ የጎን ውጋቶችን መፍጠር፣ የውስጥ ቅራኔዎችን ለማቀጣጠል ለመሞከሩ ግን አይቀርም - ከአጠገባችን ሶማሊያ ውስጥ ሆኖ።
በሌላ አነጋገር፣ የግብፅ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የሚዘረጋቸው መሰናክሎች… በአንድ በኩል አዲስ አይደሉም። ካለፉት ዓመታት ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ካሁን በፊትም ነበሩ፤ ወደ ፊትም ይኖራሉ። ዓምናም፣ ዘንድሮም፣ የሚቀጥለው ዓመትም… ተመሳሳይ ናቸው። በሌላ በኩል ግን፣ መሰናክሎቹ እየበረከቱና እየበረቱ የሚመጡ ይመስላሉ።
በሶማሊያ በኩል ኢትዮጵያን ለማሰናከል ምን ዐይነት ወጥመዶችን ለመጠቀም እንደሚሞክር መገመት ይቻላል። ታጣቂ ቡድኖችን ለማሠልጠንና ማስታጠቅ፣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን ማቀናበርና ዐመጾችን ለማበረታታት ሲሞክር እስከዛሬ ያልሞከራቸውንም ዘዴዎች ሊጠቀም ይችላል።
ከዚህ አንጻር ሲታይ፣ የግብፅ መንግስት አዝማሚያ አዲስ ቅርጽና ቅኝት ይዞ መጥቷል ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያ ላይም አዲስ ዐይነት ፈተና ተንጣጥሮባታል ብለን ብንናገር አልተሳሳትንም።
በዓመት በሁለት ዓመት አንገላገለውም።
የትምህርት መራቆትም እንደዚያው በዐጭር ጊዜ የሚስተካከል አይመስልም።
የተማሪዎች አማካይ የፈተና ውጤት ከዐሥር ዓመት በፊት 30 በመቶ ገደማ ነበር። ከዓመት በፊትም እንደዚያው ሆኗል። ዘንድሮም ያው ነው።
ዓካቻምና እንደሰማችሁት ከ1000 የ12ኝ ክፍል ተፈታኞች መካከል የማለፊያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች 35 ያህሉ ብቻ ነበሩ። ዘንድሮስ? 54 ያህሉ። የተሻለ ውጤት ነው ልንል እንችላለን። ነገር ግን፣ ከቁጥር የሚገባ ነው ለማለት ያስቸግራል።
በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የፈተና ውጤት በአማካይ ከ30 በመቶ በታች ነበር (29.3%)።
በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የፈተና ውጤትም በአማካይ ከ30 በመቶ በታች ነው(29.8%)።
ከቁጥር የሚገባ ልዩነት የለውም። የተማሪዎች ብቃት ስለተሻሻለ ሳይሆን፣ በአጋጣሚ የሚፈጠር ልዩነት ነው ማለት ይቻላል። የፈተና ጥያቄዎች “የምርጫ ጥያቄዎች” መሆናቸውን አትርሱ። በአጋጣሚ ብቻ፣ ያለ አንዳች ዕውቀት ፈተናውን የሚወስዱ ሰዎች፣ በአማካይ ከ20% እስከ 25% ውጤት ያመጣሉ። የዘንድሮና የካቻምና የተማሪዎች ውጤት ከዚህ ምን ያህል ይሻላል? የዘንድሮና የካቻምናስ ምን ያህል ይለያያል? ተመሳሳይ ናቸው። የተማሪዎች አማካይ ውጤት 30% እንኳ አልሞላም።
ለምን?
ካሁን በፊት በአዲስ አድማስ የወጡ ጽሑፎችን መጥቀስ ይቻላል። የአገራችን ትምህርት ስለተራቆተ ነው፤ የተማሪዎች ውጤት አፈር የበላው። የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ዕጥረት አይደለም። የፈተና አሰጣጥ ጉዳይ አይደለም። የአስተማሪዎች ዕጥረት አይደለም። የትምህርቱ ይዘት ስለተራቆተ ነው፣ ተማሪዎች የሚወድቁት። የመማሪያ መጻሕፍት የዚህ ምስክር ናቸው።
አዲስ የትምህት ፍኖተካርታ መጣ፤ ከድሮው የባሰ። አዲስ ሥርዓተ ትምህርትና የመማሪያ መጻሕፍት መጡ። ከድሮ ያልተሻሉ። ለዚህም ነው፤ ለሚቀጥሉት አምስትና ዐሥር ዓመታት የተማሪዎች ውጤት እንደማይሻሻል በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው። በሚቀጥሉት አምስትና ዐሥር ዓመታት ውስጥ፣ የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርትና የመማሪያ መጻሕፍት የመቀየር ዕድል የለም። ሐሳብም የለም እንጂ።
እናም፣ ከዓመት ዓመት የአገራችን የትምህርት ችግር ተመሳሳይ ነው። ግን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አዳዲስ ልጆችና ተማሪዎች ናቸው ሰለባ የሚሆኑት።
በአጠቃላይ፣ እንደ ዓምና እንደ ካቻምና፣ ዘንድሮም በብዙ ገጽታው ከባድ ዓመት እንደሚሆንብን አያጠራጥርም። የሰላም ዕጦትና የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነትና ድኽነት፣ የግብፅ መንግሥት መሰናክልና የቀይ ባሕር ግርግር፣ የትምህርት ውድቀትና የሥራ ዕጦት፣ እንደ ዓምና ዘንድሮም የአገር ችግሮች ናቸው። ነገር ግን እየተሸሻሻሉ የመጡ ነገሮች መኖራቸውንም አንርሳ።
ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የጦርነትና የግጭት ብዛት መቀነሱ ጥሩ ነው። በዚያው ልክ የሰላም ተስፋ ተሻሽሏል። ቢሆንም ግን፣ የዓምና ችግሮች ዘንድሮም ይኖራሉ።
ቢኖሩም ግን፣ ችግሮች ትንሽ ቀለል ቀለል፤ ተስፋዎችም ትንሽ ፈካ ፈካ ማለታቸውን ግን በንቀት አትዩ። ይህን እንደ ጥሩ መነሻ እየያዝን፣ ችግሮች ይበልጥ እንዲቃለሉ፣ ተስፋዎችም ይበልጥ እንዲፈኩ መትጋት ነው የሚኖርብን።
Saturday, 14 September 2024 12:29
አዲሱ ዓመት… እንደ ሌሎቹ “ዓመታት” ነው። ግን አዲስ!
Written by ዮሐንስ ሰ.
Published in
ነፃ አስተያየት