Saturday, 14 September 2024 12:34

የጃፓን ትዝታዎቼ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በ1984 ዓ.ም አስራ አንድ ወራት ያህል ለሚፈጅ ስልጠና  ጃፓን ሀገር ሄጄ ነበር፡፡ በጃፓን ሀገር ቆይታዬ ከማይረሱኝ ትዝታዎቼ መሀከል የተወሰኑትን እነሆ፡፡
ስልጣኔ፡  ሁላችንም እንደምናውቀው ጃፓን፣ የስልጣኔ ማማ ላይ ከደረሱ ጥቂት የአለማችን ሀገሮች አንዷ ናት፡፡ ካስደነቁኝ ነገሮች መሀከል ለማሳያነት ሁለቱን እዚህ ላይ እጠቅሳለሁ፡፡
ትራንስፖርት፡ ከትራንስፖርት ሥርዓታቸው ውስጥ የማነሳው የባቡር ትራንስፖርትን ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ሥርዓታቸው እጅግ በጣም የተደራጀና የተሳለጠ ነው፡፡ እኔ የተማርኩት የጃፓን ሁለተኛ ከተማ በሆነችው ኦሳካ ነው፡፡ ጧት ከምኖርበት አፓርታማ በብስክሌት ባቡር ጣቢያ ድረስ እሄዳለሁ፥ ብስክሌቴን እዚያው ባቡር ጣቢያ ውስጥ በሚገኝ የብስክሌት ማቆሚያ ቦታ አቆማትና በባቡር ት/ቤቴ ወደሚገኝበት ኪዮቶ ከተማ እሄዳለሁ፡፡ ብስክሌት በማቆምበት ቦታ ምንም ጠባቂ የለውም፥ በመሆኑም የህዝቡን የታማኝነት ባህል ልብ እንበል፡፡ ባቡር የምይዝበት ሰአት የተወሰነ ነው፡፡ ከዚያ ባቡሩ ምን ያህል ሰአት እንደሚያከብር ለማወቅ አሰብኩኝና ማጥናት ጀመርኩኝ፡፡ በወቅቱ የነበረችኝ ሰአት በጣም ትክክለኛ(very accurate) ነበረች፡፡ ከዚያ አንድ ቀን በስንት ሰአት እኔ ባቡር የምይዝበት ጣቢያ እንደደረሰ መዘገብኩ፥ የመዘገብኩት ሰአቱን፥ ደቂቃውንና ሰከንዱን ነበር፡፡ በመቀጠልም በተከታታይ ቀናት ባቡሩ በጣቢያው ስንት ሰአት እንደደረሰ መዝግቤ መጀመሪያ ከመዘገብኩት ጋር ሳወዳድረው የጥቂት ሰኮንዶች ልዩነት እንኳን አላገኘሁበትም፡፡ ባቡሩ ደግሞ በየ20 ደቂቃው ይመጣል፡፡ በመሆኑም የባቡር አገልግሎት የጊዜ አጠባበቃቸው(time accuracy) በጥቂት ሰኮንዶች የሚለካ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ይህ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ውጤታማነታቸውን ከሀገራችን ሁኔታ ጋር አወዳድሬ ስላየሁት ነው መሰለኝ እጅግ በጣም አደነቅሁት፡፡ ጃፓን ለሚኖር ግለሰብ ለቅንጦት ካልሆነ በስተቀር የግል መኪና መጠቀም አስፈላጊነቱ ብዙም አልታየኝም ያስባለኝን አገልግሎት ነው ያየሁት። ከሀብታቸው፥ ከከተማቸው ዘመናዊነትና ከቁሳዊ ብልፅግናቸው የበለጠ የገረመኝ ለስራ ያላቸው አክብሮትና ለጊዜ የሚሰጡት ዋጋ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ለነኚህ ሁለት ትልልቅ እሴቶች ያላቸው አክብሮት በባቡር ትራንስፖርት ሥርዓታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ባየኋቸው የስራ ቦታዎች ሁሉ የታዘብኩት ነገር ነው፡፡ የጃፓን ህዝብ የስራ ክቡርነትና የጊዜን ጠቀሜታ በሚገባ ተገንዝቦ እነኚህን እሴቶች ተግባራዊ በማድረጉ፣ በኢኮኖሚ በልፅጎ አሁን የደረሰበት ደረጃ ደርሷል፡፡ እኛስ? እኛም የስራ ክቡርነትና የጊዜን ጥቅም በሚገባ ተረድተን ተግባራዊ ማድረግ ስንጀምር ማደግ አንጀምራለን፡፡ መቼ? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ለናንተ ትቼዋለሁ፡፡
የደን ሽፋን፡ የጃፓን የቆዳ ስፋት የኢትዮጵያን ሲሶ ያህል ቢሆን ነው፡፡ ከዚህ የቆዳ ስፋት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ሰው ሊኖርበት የማይችል ጋራና ተራራ ነው፡፡ በመሆኑም ሰው ሊኖር የሚችልበት መሬት ከቆዳ ስፋቷ 30 በመቶ ላይ ብቻ ነው፡፡ ቶኪዮና ኦሳካን ጨምሮ ትላልቅ ከተሞቿ በአብዛኛው በባህር አጠገብ(Coastal area) የተቆረቆሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የህዝብ ብዛቷ ወደ 127 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ የደን ሽፋኗ እኔ በሄድኩበት ወቅት 66% አካባቢ ነበር፡፡ ይህም ማለት ሰው ሊሰፍርበት የማይችለው ጋራና ተራራዎቿ ቢያንስ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ሊባል በሚችል ደረጃ በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በባቡር ሲኬድ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው፡፡
የጃፓን ከተሞች ፅዱና የተዋቡ ናቸው፡፡ ፓርኮች በብዛት አሉዋቸው፡፡ ከከተማ በባቡር ወይም በመኪና ሲወጣ የሚታየው በአብዛኛው የሩዝ እርሻ ወይም እርሻ ከሌለ የተፈጥሮ ደን ነው፡፡ ከከተማቸው ባልተናነሰ የገጠሩ አካባቢ ልምላሜ እጅግ በጣም ይማርካል፤ ያስቀናል፡፡ አሁን ያለው የደን ሽፋናቸው ቢያንስ ቢያንስ ከዛሬ ሰላሳ ሁለት ዓመት በፊት ከነበረው 66%  እንደማያንስ እርግጠኛ  ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የጃፓን መንግስት በፖሊሲው የደን ሽፋኑን በመጠበቁ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡም ከተፈጥሮ ጋር ተከባብሮ፤ ተጠባብቆና ተዋዶ የመኖር የረዥም ጊዜ ባህል ያለው በመሆኑ ነው፡፡ (በኛም ሀገር የተፈጥሮ ደንን መጠበቅ ባህላቸው የሆኑ ብሄረሰቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡)
ይህ የጃፓን ህዝብ አመለካከት ከሚከተሉት ፍልስፍናና እምነት ጋርም በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ከተማን ከመገንባት ባሻገር ከተፈጥሮ ጋር ተከባብሮና ተደጋግፎ በመኖር ደኖችን መጠበቅ የስልጣኔ አንዱና ዋናው ምልክት መሆኑን በተግባር ያስመሰከረች ሀገር ናት፥ ጃፓን፡፡ በዚህም ጉዳይ ላይ እኛስ? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በኔ ግምት መልሱ የሚታዩ ጅምሮች አሉ፥ ይሁን እንጂ ብዙ መንገድ ይቀረናል።
የቤተሰብ ስም (Family name)፡ ጃፓን በወሰድኩት ትምህርት ላይ ከ8 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጣን 8 ተማሪዎች ነበርን፡፡ ፕሮግራሙ አስር ተማሪዎች እንዲኖሩት የታቀደ ቢሆንም፥ ከኮንጎ ኪንሻሳ መምጣት የነበረበት ልጅ ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ላይ ስለነበረች ባለመምጣቱ፥ የዚምባብዌው ልጅ ደግሞ ጃፓን ድረስ መጥቶ ትምህርት ከመጀመራችን በፊት ሙሉ የጤና ምርመራ በተደረገልን ወቅት ከባድ የጤና እክል ስለታየበት ወደሀገሩ እንዲመለስ በመደረጉ ስምንት ተማሪዎች ብቻ ነበርን በስልጠናው ላይ የተሳተፍነው፡፡ የተሳተፍነው ከኢትዮጵያ፥ ኬንያ፥ ታንዛኒያ፥ ሱዳን፥ ማላዊ፥ ዛምቢያ፥ ጋናና ሴኔጋል የተውጣጣን የአፍሪካ ልጆች ነበርን። የእኔና የሱዳኑ ልጅ የቆዳ ቀለማችን፥ የፀጉራችን የከርዳዳነት ደረጃ፥ የአፍንጫና የከንፈራችን ቅርፅ በጣም ተመሳሳይነት ስላለው “መንትዮቹ”፥ “the twins” እያሉን ይጠሩን እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ወደ ፍሬ ነገሩ ልመለስ፡፡ አንድ ቀን ምሳ በልተን የትምህርት ሰአት እስኪደርስ  በመጫወት ላይ እያለን፣ በጨዋታ መሀከል ታንዛኒያዊው ጓደኛዬ፤ “What is your Family name?” “የቤተሰብ ስምህ ማነው?” አለኝ፡፡  እኔም፤ “እኛ ፋሚሊ ኔም የሚባል ነገር የለንም” አልኩት፡፡ ታንዛኒያዊው፤ “እንዴት? ምን ማለትህ ነው?” አለኝ፡፡ እኔም፤ “አንተስ ምን ማለትህ ነው? አልገባኝም” አልኩት፡፡ የሁለታችን ንግግር በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለ የቀሩት ስድስቱም ጓደኞቻችን እሱን ደግፈው፤  “እንዴ ምን ማለትህ ነው? እንዴት ፋሚሊ ኔም የለንም ትላለህ?” ብለው አፋጠጡኝ፡፡ ክርክራችን ሰባት ለአንድ ሆነ ማለት ነው፡፡ ወዲያው በውስጤ እንዴት የኔ አመለካከት ከነሱ ተለየ? እኔ ምን ከነሱ የተለየ ያለኝ ወይም የሌለኝ ነገር ኖሮ ነው ሀሳቤ ከሰባቱም ሊለይ የቻለው? ብዬ አሰላሰልኩ፥ ወዲያው ትዝ ሲለኝ ልዩነታችን ገባኝ፡፡ “Famiy name” የሚባለው አጠራር የአፍሪካውያን ባህል ሳይሆን፤ የፈረንጆቹ፥ ማለትም የቅኝ ገዢዎቹ ባህል ነው፡፡ ደግሞም የሁሉም ጓደኞቼ ሀገራት በቅኝ የተገዙ ናቸው፡፡ የኔ ሀገር ግን አልተገዛችም፡፡ ይህ ነው የልዩነታችን መሰረት፡፡ ከዚያ ወኔ ተሰማኝ፡፡ በጣም ጥሩ መከራከሪያና ማሳመኛ ነጥብ አገኘሁ ብዬ አሰብኩ፡፡ ይሄኔ ፍርጥም ብዬ በልበ ሙሉነት፤ “ስሙ ይሄ “Family name” የምትሉት ነገር መሰረቱ ወይም ምንጩ የአፍሪካ ባህል ቢሆን ኖሮና እኔ ባላውቀውና ባህሌ ባይሆንም እንኳን ትልቅ ክብር ይኖረኝ ነበር፥ ነገር ግን የባህል መሰረቱ የፈረንጆቹ ወይም የቅኝ ገዢዎቹ ስለሆነ ብዙ ቦታ አልሰጠውም፥ ምክንያቱም በቅኝ ገዢዎቻችሁ የተጫነባችሁ ነገር ስለሆነ ነው” አልኳቸው፡፡ ቀጠሉናም፤ “ፋሚሊ ኔም ከሌለህ ማንነትህ እንዴት ነው የሚታወቀው?” አሉኝ፡፡ እኔም፤  “ማንነቴ የሚታወቀው በራሴ ስም፥ በአባቴ ስም፥ በአያቴ ስም፥ በእናቴ ስም፥ በተወለድኩበት አካባቢ ወዘተ” ብዬ መለስኩላቸው፡፡ በጣም የገረመኝ ነገር ይህ አባባሌ ሊገባቸው አለመቻሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ ልብ ሊለው የሚገባውና የሚያሳዝነው ነገር፣ ሁሉም ጓደኞቼ ፋሚሊ ኔም የሚለውን ስያሜ ልክ እንደራሳቸው ባህልና ቅርስ አድርገው ከማየታቸው የተነሳ እኔ የምላቸው ነገር ፍፁም ሊገባቸው አለመቻሉ ነው፡፡ ይገርማል! ያሳዝናል! እነኚህ አፍሪካዊ ጓደኞቼ የነጩ ባህል በደምስራቸው ውስጥ ገብቶ ከደማቸው ጋር የተዋሀደ መሆኑን በመረዳቴ ሀዘን ተሰማኝ፡፡ በመጨረሻም ብዙ ተከራክረን መስማማት ባለመቻላችን፣ ላለመስማማት ተስማምተን፥ እኔም እነሱም የምናምንበትንና የምናውቀውን ይዘን ወደ ሌላ ጨዋታ ውስጥ ገባን፡፡
ስንቅ፡ ጃፓን በሄድኩበት ወቅት እናቴ ለስንቅ ይሆንሀል ብላኝ በትልቅ አገልግል እኔ ነኝ ያለ ጩኮ አዘጋጅታ ይዤ መሄዴን አስታውሳለሁ፡፡ እናቴ በሴት ልጅ ሙያ እንከን የማይወጣላት ነበረች፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለእናቴ የሚገባትን ዋጋ፥ “credit”፤ ለመስጠት በሚል ስሜት አንድ ነገር አንስቼ ልለፍ፡፡ ከዛሬ 50 አመት በፊት በ1960ዎቹ አጋማሽ አካባቢ እናቴ የምትጥለው ፊልተር ጠጅ በጣም ምርጥና ተወዳጅ ስለነበረ፥ አንድ ሊትር ፊልተር ጠጅ በአንድ ሙሉ ውስኪ የአባቴ ጓደኞችና ዘመዶች እንደተቀያየሩ አስታውሳለሁ፡፡      
ከዚያ ዕቃዬን ሸክፌ(pack አድርጌ) ጉዞ ወደ ጃፓን ሆነ፡፡ በአንድ ትልቅ አገልግል በደምብ የታጨቀ ጩኮ ምን ያህል እንደሚከብድ ይታያችሁ፡፡ በኤርፖርቶች ለዕቃ ማመላለሻ የሚያገለግሉ ጋሪዎች ባይኖሩ ጩኮው ወገቤን ይፈትነው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ በሙምባይና በሆንግኮንግ አድርጌ ቶኪዮ ደረስኩ፡፡ በቶኪዮ ደረጃ ያለ ዘመናዊ ከተማ ሳይ በህይወቴ  ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ የቶኪዮ ኤርፖርት ከመሀል ከተማው በግምት ሰባ ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን፥ በኤርፖርቱ የደረስኩት ከቀኑ አስራ አንድ ሰአት ላይ ነበር። የኤርፖርት ውስጥ ፍተሻ ጨርሰን ቶኪዮ ከተማ መሀል ስንደርስ መሽቶ ነበርና ከተማዋ በተለያዩ ውብ መብራቶች የተንቆጠቆጠች ሆነችብኝ። በዚያ ምሽትና በወጣትነት አእምሮዬ ያየሁዋት የቶኪዮ ከተማ ምስል እስከዛሬ  ከአእምሮዬ አልጠፋም፡፡ ያ የቶኪዮ ምስል በድሮ ዘመን የጎጃም ነጋዴ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ከሀገሩ ተነስቶ እንጦጦ ጫፍ ደርሶ አዲሳባን ሲያያት፤ “እንጦጦ ላይ ሆኜ አዲስን ሳያት ባለፈርጦች ሰማይ መስላ አገኘኋት” ብሎ የገጠመውን ሲያስታውሰኝ ይኖራል።
በመቀጠል ኤርፖርት ውስጥ የመግቢያ ቪዛችንና የያዝነው ዕቃ ሲፈተሽ ፈታሾቹ አገልግሉን ሲያዩ ግራ ገባቸው። ከዚያ ክፈተው አሉኝ፥ ከፈትኩት፥ ጩኮውን ሲያዩ ይበልጥ ግራ ገባቸው፥ ግራ ከመጋባት አልፈው አንድ እኔ ነኝ ያለ ሀሺሽ አስተላላፊ(drug trafficker) የያዙ መስሎዋቸው በጥርጣሬ አይን አዩኝ። “ይሄ ምንድነው?” አሉኝ። “የሀገራችን ባህላዊ ምግብ ነው” አልኳቸው። እነሱ ግን አላመኑኝም። ከዚያ ለምርመራ ለሌላ ሰው አስተላልፈው ሰጡኝና፣ እነሱ የፍተሻ ስራቸውን ቀጠሉ። ወደ ከተማው መግባቴ ቀርቶ ወደ ማረፊያ ሊወስዱኝ ነው ብዬ ፈራሁ፥ አንድ ክፍል ውስጥ አስገብቶ ጩኮውን በአንክሮ ተመለከተው፥ አሸተተው። ከዚያ ፈታሾቹ የጠየቁኝን “ይሄ ምንድነው” የሚለውን ጥያቄ በድጋሚ ጠየቀኝ። እኔም ፍርጥም ብዬ ያለፍርሀት “የሀገራችን የባህል ምግብ ነው” አልኩት። ያልፈራሁት የያዝኩትን ነገር ምንነት ሲረዱ በነፃ እንደሚለቁኝ ስለማውቅ ሲሆን፥ ፈራሁ ብዬ ከላይ የገለፅኩት ደግሞ ምንነቱን እስኪያውቁ ድረስ ሊያጉላሉኝ ይችላሉ ብዬ ነው።  የያዝኩት ሀሺሽ-ነክ ነገር ቢሆን ኖሮ “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” እንደሚባለው ሊነቃብኝ ይችል እንደነበር ገመትኩ። “ከምንድነው የሚሰራው?” አለኝ። “ከገብስና ከቂቤ ነው የሚሰራው” አልኩት። “እስቲ ቅመሰው” አለኝ። እኔም በማንኪያ ቀመስኩት። ግራ የመጋባት ነገር ግማሽ ልብ እንዲሆን አስገደደው። በሙሉ ልብ እንዳያምነኝ ጥርጣሬ አእምሮውን ሰቅዞ ያዘው። ከዚያ ንፁህ ቢላ ይዞ መጥቶ ጩኮውን ከሁለት ቦታ ከፍሎ ከውስጡ በማንኪያ ቆንጥሮ በማውጣት እንደገና ቅመሰው አለኝ። እኔም በትዕዛዙ መሰረት ቀመስኩት። ከላይ ያለውና ከውስጥ ያወጣው የተለያየ ቢሆን ኖሮ፣ በዝርዝር እስኪጣራ ድረስ ችግር ይፈጠርብኝ እንደነበረ ተረዳሁ። በመቀጠልም ከአለቃው ጋር ረዘም ላለ ጊዜ በስልክ ከተነጋገረ በኋላ አገልግሉን መልሶ በማሰር ሰጠኝና አሰናበተኝ። እኔም ዕቃዬን ይዤ የሚቀጥለውን ፍተሻ ከጨረስኩ በኋላ በኤርፖርቱ መግቢያ ላይ ሙሉ ስሜን በሰፊ ወረቀት ላይ ፅፎ ከሚጠብቀኝ ሰውዬ ጋር ተገናኝቼ፣ ቶኪዮ በሚገኘው የአለም አቀፍ ሰልጣኝ ተማሪዎች ወደሚያርፉበት ማዕከል ወሰደኝ።
ብርሀኔ ዳምጠው፡
አቶ ብርሀኔ ዳምጠው በኦሳካ ኮቤ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው። በ1967 ዓ.ም አካባቢ ጃፓን ለአጭር ጊዜ ስልጠና ሄዶ እዚያው የቀረ ሀበሻ ነው። ሙያው ከመኪና ጥገና ጋር የተገናኘ የቴክኒክ ሙያ በመሆኑ የሚሰራው ከሙያው ጋር በተገናኘ መስክ እንደሆነ አጫውቶኛል።
አቶ ብርሀኔ የሀገሩ ሰው ይናፍቀዋል። እኔ ጃፓን በሄድኩበት ጊዜ አንድ ኢትዮጵያዊ በኦሳካ ኢንተርናሽናል የስልጠና ማዕከል መኖሩን ሰምቶ በማሰልጠኛው የማዞሪያ ስልክ ደውሎ በስልክ ተገናኘን። ከዚያም በአካል በተገናኘንበት ወቅት ስንጨዋወት አልፎ አልፎ ወደማሰልጠኛው ስልክ ይደውልና ኢትዮጵያዊ ሰልጣኝ መኖሩን ካጣራ በኋላ፣ ካለ ደውሎለት በስልክ ያገኘዋል። ከዚያም በአካል አግኝቶት ስለሀገር ቤትም ሆነ ስለተለያዩ ነገሮች ይጫወታሉ። እንደገመትኩት አቶ ብርሀኔ ጃፓን ለስልጠና በሄደበት ዘመን እንኳን ኢትዮጵያዊ ይቅርና ማንኛውንም ጥቁር ሰው በጃፓን ሀገር ውስጥ ማየት ብርቅ ነበር። የዚህን አባባል እውነትነት እኔ በ1984 ዓ.ም. ጃፓን በሄድኩበት ዘመን በአንዳንድ አካባቢዎች እኔንና አፍሪካዊ ጓደኞቼን ሲያዩን እንደብርቅ ያዩን የነበሩ ሰዎች የመኖራቸው ሀቅ ምስክር መሆን ይችላል።         
ከላይ በጠቀስኩት ምክንያት ከአቶ ብርሀኔ ጋር ብዙ ጊዜ በአካል ተገናኝተን ተጫውተናል፥ ቤቱም ጋብዞኛል፥ በአፓርታማ ውስጥ ነው የሚኖረው፥ ፓርኮችና የተለያዩ ቦታዎች አስጎብኝቶኛል። አንድ ቀን እሱ በሚኖርባት ኮቤ በምትባል፥ በኦሳካ ከተማ አጠገብ የምትገኝ የወደብ ከተማ ውስጥ ያለ አንድ ጃፓናዊ የሬስቶራንት ባለቤት ጓደኛው ጋ ወስዶ የጋበዘኝ ሾርባ የሚመስል የጃፓን ምግብ እስካሁን አይረሳኝም። ሾርባው ውስጥ ያለው ስጋ ከባህር ውስጥ የሚገኝ የአሳ ዝርያ መሆኑን ነው የነገሩኝ፥ እውነቱን ግን እግዜር ይወቀው፥ ምክንያቱም ቅርፁ የእባብ ስለሚመስል ነው። ስጋው በጣም ለስላሳ ነበር፥ እኔ በምግብ ላይ ብዙ ወግ አጥባቂ ስላልሆንኩ የቀረበልኝ ምግብ በጣም ጣፍጦኝ ነበር የተመገብኩት።
ታዲያ እንደወትሮው አንድ ቀን የሆነ ቦታ ተገናኝተን ሻይ ቡና እየተባባልን እያለ አንድ ፍፁም ያልጠበቅሁት ነገር ተፈጠረ። በጨዋታ ድባብ ውስጥ የነበረው የአቶ ብርሀኔ ፊት ቀስ በቀስ ተለውጦ በሀሳብ ባህር ውስጥ ሲሰምጥ ታየኝ። “አቶ ብርሀኔ ምን ሆንክ? ደህና አይደለህም እንዴ?” አልኩት። እሱም ምንም መልስ ሳይሰጠኝ አንገቱን ደፋ ከአደረገ በኋላ ቀና ብሎ ምንም ሳልጠብቀው እንባ በግራና በቀኝ ጉንጮቹ እየወረዱ ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ። እየሆነ ያለው ነገር ፍፁም ሊገባኝ አልቻለም። ግራ ገባኝ። “አቶ ብርሀኔ ምን ሆንክ? ለምንድነው የምታለቅሰው?” አልኩት፤በድጋሚ።
 አቶ ብርሀኔ ገዘፍ ያለ መልከመልካም ጠይም ሰው ነው። ከኔ በግምት አስር አመት ይበልጠኛል። በዚህ ላይ ስልጠናውን ከጨረሰ በኋላ በታወቀ የጃፓን የመኪና አምራች ኩባንያ ውስጥ ሲሰራ ቆይቶ ከሙያው ጋር የተገናኘ የግል ስራ እንደሚሰራ አጫውቶኛል። ስራው መኪኖችን ወደ ጎረቤት የእስያ ሀገራት  መሸጥ ነበር። በጣም ጥሩ ገቢ ያለው ሰው መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው። ታዲያ ከአፍሪካ የሄደ እንደኔ አይነቱ ቺስታ እንዴት ብዬ፣ ይህ ሰው ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል ብዬ ልገምት? አቶ ብርሀኔ ለቅሶው ቀለል ሲለው የሚከተለውን አጫወተኝ። “እኔ እዚህ ጃፓን ላለፈው 17 አመታት ኖሬያለሁ፥ በዚህ ዘመን ውስጥ ትምህርቴን ጨርሼ በታወቀ ኩባንያ  ውስጥ ጥሩ ስራ ነበረኝ፥ ከዚያ የራሴን የግል ስራ ጀምሬ ጥሩ ገቢ ማግኘት ችያለሁ፥ ምንም የኢኮኖሚ ችግር የለብኝም፥ ከራሴ አልፌ ለሰው የምተርፍ ነኝ። ነገር ግን ይሄን ያህል ዘመን እዚህ ሀገር ውስጥ ስኖር ጃፓንን እንደራሴ ሀገር አላያትም፥ የትም ቦታ ስሄድ የሚያጋጥመኝ ሰው እንደ አዲስ የሀገሩ ሰው ነው የሚያየኝ ወይም የሚቀበለኝ፤ ይህ ሁኔታ የባይተዋርነት ስሜት እንዲያድርብኝ አደረገኝ፥ ለዚህ ነው ሆድ ብሶኝ ያለቀስኩት” አለኝ።
አቶ ብርሀኔ ሀበሻና ሌሎች ጥቁሮች በብዛት በሚገኙበት በምዕራባውያን ሀገሮች፥ ለምሳሌ አሜሪካና እንግሊዝ፥ ውስጥ የሚኖር ቢሆን ኖሮ፣ ይህ የባይተዋርነት ስሜት አይሰማውም ነበር። አቶ ብርሀኔን ሆድ አስብሶት እስከማልቀስ ያደረሰው የስነ ልቦና ችግር እንደሆነ ገባኝ። አቶ ብርሀኔ ለሀገሪቱ በፈረንጆቹ አባባል “belongingness” አልነበረውም ማለት ነው። ይህ ተሞክሮ በዚያ የወጣትነት እድሜዬ አንድ ትልቅ ትምህርት አስተምሮኝ አለፈ፥ ሀብትና ገንዘብ ብቻ ለሰው ልጅ ምንም ነገር እንደማይፈይዱ። የታወቀው የማኔጅመንት ምሁር አብርሀም ማስሎው፤ “Hierarchy of needs” ብሎ ካስቀመጣቸው መሀከል አቶ ብርሀኔ በተሰማው የባይተዋርነት ስሜት ምክንያት የተሟላ “safety” (ደህንነት) እና “love” (ፍቅር) ስላልነበረው ሆድ አስብሶት ተንሰቅስቆ እንዲያለቅስ አደረገው።
ምግብ፡ የጃፓን ምግብ በአብዛኛው አትክልት፥ ቅጠላቅጠልና የባህር ምግቦች ናቸው። የራሳቸው የምግብ ማጣፈጫ(sauce) አላቸው። አንዳንድ የምግብ ማጣፈጫዎቻቸው ጣዕም ለየት ስለሚሉ በአማርኛ ቃላት ላገኝላቸው ባለመቻሌ ጣዕሙ ምን አይነት እንደሆነ ለሰው ለመግለፅ በወቅቱ አስቸግሮኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። በሂደት ግን ምግባቸውን ለምጄ በጣም ወድጄው አረፍኩት። ሀገር ቤት ከተመለስኩ በኋላ የጃፓን አሉምኒ አሶሲዬሽን ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ስለነበርኩ (በአንድ ወቅት የአሶሲዬሽኑ ፕሬዚደንት ሆኜ አገልግያለሁ)፣ አልፎ አልፎ እዚህ ያለው የጃፓን ኤምባሲ ግብዣ ይጠራን ነበርና፣ እንደሱሺ አይነቱን የጃፓን ምግብ በኤምባሲው ውስጥ በሚጋብዙን ወቅት በጣም በፍቅር ነበር እበላ የነበረው። (ሱሺ ባህር ውስጥ በሚገኝ ቅጠል መሰል አልጌ የተጠቀለለ አሳና ሩዝ ያለበት የጃፓን ምግብ ነው። አረንጓዴው አልጌ “Spirulina” የሚባለውና የምግብ ይዘቱ በጣም ከፍተኛ የሆነ ምግብ ነው፥ የምግብ ይዘቱ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ውጪ ሀገር በታብሌት መልክ በየሱፐርማርኬቶቹ ይሸጣል፥ እኔ አላጋጠመኝም እንጂ በኛ ሀገርም ሊገኝ ይችላል)።
 ምግባቸው ጨው፥ ስኳርና የከብት ቅባት(ቅቤና ጮማ) ስለሌለበት ለጤና በጣም ተስማሚ መሆኑን እመሰክራለሁ። የጃፓን ህዝብ በአለም ላይ ረዥም ዕድሜ ከሚኖሩ ህዝቦች መሀከል በአንደኝነት የሚጠቀስ የመሆኑ ሚስጥር በዋናነት  በሚበሉት ምግብ እንደሆነ የተረጋገጠ ነገር ነው። ከምግብ ጋር የተያያዘ ሌላ ነገር ላንሳ። ከጓደኞቼ ጋር አንድ ቀን ምሳ እየበላን በነበረበት ወቅት አንዱ ጓደኛዬ ትኩር ብሎ አየኝ። አበላሌ ከሌሎቹ የተለየ አልነበረም፥ ገበታ አስደንጋጭ የምባል አይነት ሰውም አይደለሁም፤ ኖርማል አበላል ነበር የምበላው፥ እየበላን የነበረውም የተለመደ ምግብ ነው፡፡ ጓደኛዬ፤ “እዚህ አሁን እንዲህ እንደልብህ እየበላህ ሆድህን አስፍተህ ሀገርህ ስትመለስ ምን ትበላ ይሆን?” አለኝ። ምናልባት ሌላ ሰው እንዲህ ቢባል ቢያንስ ሊናደድ ወይም ሊጣላ ይችል ነበር። የኛ ሰው ውጪ ሀገር ሲሄድ የዚህ አይነት ነገር እንደሚያጋጥመው ጠንቅቄ አውቃለሁ፥ በተለይ እኔ ጃፓን የሄድኩበት ዘመን ከ1977ቱ ረሀብ 7 አመት ብቻ ስለሚራራቅና በወቅቱ የነበረው የሀገራችን ረሀብ ትዝታ ትኩስ ስለነበረ የዚህ አይነት ነገር ቢያጋጥም አይገርምም። በመሆኑም ጥያቄው ብዙ አልገረመኝም፥ ወይም አልተናደድኩም። እኔም በምላሼ፤ “ኢትዮጵያ ተራበች ሲባልኮ ሁሉ ቦታ ረሀብ አለ ማለት አይደለም፤ ረሀብ የነበረው በሰሜኑ ክፍል ነበር” አልኩት። እሱም(ሌሎቹም አብረው) “ሰሜኑም ይሁን ደቡቡ እኛ የምናውቀው ኢትዮጵያ ረሀብተኛና ችጋራም መሆንዋን ነው” ብለው ረሀብተኛነታችንን ለመሸፋፈን የፈለግሁ አስመሰሉኝ፡፡ ኢትዮጵያ ተራበች ሲባል ህዝቡ በሙሉ በጠኔ ያለቀ አስመስሎ የማቅረብ አባዜ አለባቸው፤ የምዕራብ ዘመም አመለካከት ያለባቸው የውጪ ዜጎች። በሌላ ጊዜ ደግሞ ታንዛኒያዊው ጓደኛዬ፤ “እኔ ሁልጊዜ ግርም የሚለኝ ሆዳችሁን መሙላት ሳትችሉ ኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሰለ ኩባንያ  እንዴት መመስረት እንደቻላችሁ ነው!” አለኝ። የዚህ አይነት ክብረ-ነክ ጥያቄዎች በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ያጋጥማሉ፥ ኢትዮጵያዊ ከሆንክ።

መቻያ ትዕግስቱን ካልሰጠህ አስቸጋሪ ነው። ትልቁ ቁምነገር በምትጠየቀው እነኚህን መሰል ጥያቄዎች ምክንያት የሚሰማህ ስሜትና የምትመልሰው መልስ ነው። የሚሰማህ ስሜትና የምትመልሰው መልስ አይነት ያንተን የውስጥ ጥንካሬ መለኪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ቪክቶር ፍራንኬል  የተባሉ ታላቅ ሰው ያሉትን አስታወሰኝ፤ “You cannot control what happens to you in your life; but you can always control what you will feel and do about what happens to you.” “በህይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙ ነገሮችን መቆጣጠር አትችልም፥ ነገር ግን በአንተ ላይ በሚያጋጥሙ ነገሮች ምክንያት የሚሰማህን ስሜትና የምትወስደውን ርምጃ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ትችላለህ።” ይህን አባባል እንደ አንድ የህይወታችን መመሪያ ወስደን ብንተገብረው ይጠቅመናል።
(ይቀጥላል)



Read 528 times