Tuesday, 17 September 2024 00:00

ዝክረ - ነቢይ መኮንን ውሃ እና ወርቅ

Written by  በነቢል አዱኛ
Rate this item
(2 votes)

፨ እ.ኤ.አ በ1859 የታተመው <On The Origin Of Species> የተባለው የእንግሊዛዊው ባዮሎጂስት ቻርለስ ዳርዊን(1809-1882) መጽሃፍ የአውሮፓን አስተሳሰብ ነቀነቀ። አዲስ ሃሳብ ይዞ መጣ። እነ ማክስ ዌበር’ን(1864-1920) የመሰሉ የሶሽዮሎጂስት አባት መጽሐፉን አንብበው ተገረሙ። ኸርበንት ስፔንሰር (1820-1903) የተባለ የእንግሊዝ ፈላስፋ መጽሐፉ ከታተመ ከሰባት አመት በኋላ <ሶሻል ዳርዊንዝም> በማለት <Survival Of The Fittest> የተባለውን ሃሳብ አስተዋወቀ። ‹ያሸነፈ፣ ጉልበት ያለው፤ ጉልበት የሌላቸውን ጥሎ ይብላ፣ ያሸንፍ።› አሁን ዓለም እየተዳደረችበት ያለው የካፒታሊዝምን እሳቤ ያጸና ኾነ። ሞራል ተረሳ፣ ሥነ-ምግባር ተተወ፣ የሃይማኖት እሴቶች ተሻሩ፤ እንዲያውም ‹ሃይማኖት ወደ ሥልጣኔ እንዳይደረስ የሚያደርግ እንቅፋትና ጎጂ ባህል ነው።› ተባለ። The Father Of Capitalism እና Economics የሚባለው አዳም ስሚዝ፤ ‹ድኀ ማለት ሃብታሞችን እንዲያገለግል የተፈጠረ ነው።› አለ። የጀርመናዊው ፈላስፋ አርተር ሾፐንሃወር ‹ለድኀ ገንዘብ መስጠት እሱን መጉዳት ነው።› የሚለው አስተሳሰብ ተስፋፋ። ‹ምድር ላይ ለመኖር ተወዳዳሪነት ያስፈልጋል፤ የሚያሸንፈውም ያለው፣ የጠነከረው ነው። ያላት፣ የጠነከረችዋም አውሮፓ ናት። የዓለም ሁሉ ማዕከልና የበላይም እሷ ነች።› አሉ። ካንት የተባለ ፈላስፋቸው እንዳለው፤ ‹‹እኛ አውሮፓውያን ብርሃኖች ነን፤ ሌሎቹ ጨለማ ናቸው።››
ከዛን ጊዜ ወዲህ አፍሪካም ኾነ ሌላው ዓለም በነሱ አስተሳሰብ ሥር እንዲኖር ሰሩ። በጦርነት ቅኝ መግዛት ቢተዉ በአስተሳሰብ ገዙን። ፋሽን፣ ሞዴል እያሉ እነሱ የራሳቸውን ገበያ ይሰራሉ፤ እኛ የነሱን ‘ዕውነት ነው’ እያልን እንከተላለን። እንደነሱ ያላሰበ፣ እንደነሱ ያልለበሰ፣ ያልኖረ፣ ሃገሩን የሚወድ ‹ኋላቀር ነው› ብለን እንድናስብ አስደረገን። ከላይ የጠቀስናቸው እነ ማክስ ዌበር፣ ቻርለስ ዳርዊን አንድነትን ሳይኾን ግለኝነትን፣ መተጋገዝን ሳይኾን ተወዳድረን፣ የወደቀውን ጥለን ራሳችንን ብቻ እናስቀድም የሚሉ ናቸው።
፨ ‹‹እነሱ ሙሉ በሙሉ ልክ አይደሉም እያልን አይደለም። ግን እነሱ እንዳሉት፣ እንደጻፉት፣ እንደኖሩት መኖር አንችልም፤ የነሱን ጠቃሚ ሃሳብ አምጥተን በሃገራችንና በህዝባችን አኗኗር ዓይነት፣ አውዳዊ አድርገን እንኑር። ‘የኛ ማኅበረሰብ ስለ ድህነትና አንድነት የሚያውቅ ነው። ስለዚህ የነሱን ሃሳብ ቀጥታ እንደወረደ ማስቀመጥ ለኛ ሃገር አይኾንም።›› የሚል ሃሳብ ያለው ነው የሙሐመድ አሊ(ቡርሃን አዲስ) <ውሃ እና ወርቅ> ፊልም።
፨ ፊልሙ የዘመናችን መልኮች የሆኑት፣ እንደ ኋላ ቀር የሚያስቆጥሩትን እንደ ስለ ሃገር ማሰብ፣ ሃገርን መውደድ፣ ሙስናን መቃወም፣ ራስን ሳይኾን ሌሎችን ማስቀደምን እንደ ድሮ ሰው መቁጠርን በዶክተር ደጀኔ በኩል ይቃወማል።
 ‹‹እኔ በናንተ ውስጥ፤ እናንተ በኔ ውስጥ ስንሆን ነው ሙሉ የምንኾነው።›› ዶክተር ደጀኔ።
፨ <ውሃ እና ወርቅ> በአንድ የኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ኮሌጅ ውስጥ ‹‹ትናንት የጅል ትዝታ ነው። መቆዘሚያ ክራር ነው። አባቶች፣ ተረት፣ ባህል ወዘተ.. የሚሉትን ትተን ስለ ዘመናዊነት፣ ስለ ሰለጠኑ አውሮፓውያኖች ነው ማሰብ ያለብን። እነሱ እንደኾኑትና እንዳረጉት ነው ማድረግ ያለብን። እምነት፣ ባህል ማለት የኋልዮሽ የሩጫ ውድድር፣ ወደ ስልጣኔ እንዳይደረስ እንቅፋት ነው።›› በምትለዋ መምህርት ሪሃና እና ‹‹ኢኮኖሚያችንን ማኖር ያለብን በሃገራችን እንጂ የኛ ሃገር ነዋሪ ያልሆኑና ሃገራችንን በማያውቁ ፈረንጆች በተቀመጠ ቀመር አይደለም። የኛ ሃገር ኢኮኖሚስት ምሁራችን የጉሊቷ እናታችን ናት። የሷ’ን አሰራር በፈረንጆቹ ትምህርት አድርገን ሃገርኛ ለዛ አላብሰን ለሃገራችን ማድረግ ነው ያለብን። እኛ የምንመስለው የተወለድንበትን ማኅበረሰብ ነው። የጉሊቷ እናት፣ የራበውንና የቸገረውን ስለምታውቅ ዱቤና ምርቃት ትሰጣለች። የዘመናዊው የኢኮኖሚክስ አባት አዳም ስሚዝ ግን ስለ ዱቤ አያውቅም። እሱ ‘ድኅ ሃብታምን ያገለግል ዘንድ ተፈጠረ’ ብሎ የሚያምን ነው። እኛ የኢኮኖሚክስ እናት እንጂ፤ አባት የለንም።›› በሚለው ዶክተር ደጀኔ መሃል ያለ ትዕይንት ነው።
፨ ሃገራዊነት፣ የሃገር ፍቅር የሚባለው ጠፍቷል። ህዝባችን ስለ ምዕራቡ ዓለም ዴካርት እንጂ ስለ ሃገራችን ወልደህይወት የሚያውቅ አይደለም፤ ማወቅ የሚፈልግም አይደለም። ይህንን ደግሞ በትውልዱ ላይ፣ በተማሪዎቻችን ላይ መስራት አለብን” ይለናል በግብሩ ዶክተር ደጀኔ። ‹‹እግዚአብሔር ሰዎችን ይፈጥራል፤ መምህራኖች ደግሞ ተማሪዎችን ይፈጥራሉ።›› በንግግሩ። መምህርት ሪሃና ‹‹መኖር ያለብን እንደ ምዕራቡ (እንደ ሰለጠነው ዓለም)፣ ማሰብ ያለብን እንደነሱ ነው›› ትላለች። ዶክተሩ ደግሞ ‹‹ትምህርት ቤቶች ስለ ኢትዮጵያዊነት እስካላቀነቀኑ ድረስ ኢትዮጵያዊነት የሚለው በመታወቂያችን ላይ ብቻ የሚቀር ይመስለኛል።›› ይላል። አሁን ያሉት ተማሪዎችም የትኛውን ደግፈው የትኛውን እንደሚቃወሙ፣ የትኛውስ <ውሃ> (ግዴታ አስፈላጊ) ነው? የትኛውስ <ወርቅ>(ለመገበያየት ብቻ አስፈላጊ) ነው? የሚለውን ያሳየናል።
፨ አሁን ያለውን ማኅበረሰብ ኂስ ከሚያደርግበት ውስጥ አንዱ የተማረ፣ የሰራ ሳይሆን ጉልበትና ገንዘብ ያለው ያሸንፋል፤ ይህም ዘመናዊነት ነው የሚለውን አስተሳሰብ ነው። አንዱ ገጸ-ባህሪ እንደሚለው፤ ‹‹በጣም መማር ግን ኋላ ቀርነት ነው።›› አቶ ወንደሰን የተባሉት ገጸ-ባህሪም ‹‹ሰው በስራው ይሞገሳል እንጂ ምንድነው ከፍሎ ‘አድንቁኝ’ ማለት..?›› ሲል ‹‹ዘመናዊ ሁን እንጂ›› ይባላል። ጉቦ መክፈል፣ ሙስናን እንደ ዘመናዊነት ማሰብ የዘመናችን መልክ ነው።
፨ ወርቁ የቱ ነው? ውሃውስ? እያለ ከሚያሳየን ውስጥ አንዱ፤ ፊልሙ ሲጀምር መጀመሪያ ላይ የሚናገረው ጋዜጠኛ...‹‹ታሪካችን ከድንጋይ ጋር የጠበቀ ቁርኝት አለው። አክሱም ድንጋይ ነው። ላሊበላም ድንጋይ ነው። የዘመናችን ኮብልስቶን እንኳ ድንጋይ ነው። ማንነታችን ከድንጋይ እና ከድንጋይ ዘመን አመለካከት ጋር ተሳስሯል። የሶስት ሺህ አመት ታሪክ ያለን እና ሶስት ሺህ አመት በበሬ እያረስን ያለን ኋላቀር ህዝቦች ነን።›› የሚለውን... መምህርት ሪሃና ‹‹ማን ያምጣው? ማን ይትከለው? ያልታወቀ ድንጋይ ያላት ሃገር ናት።›› ስትል ዶክተር ደጀኔ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ እንደነ ሼክስፒር እና ሞናሊዛ የማይሰረዝ፣ የማይደለዝ፣ ለገበያ የማይቀርብ በድንጋይ ላይ የተቀረጸ ዕምነት አላት›› ይለናል። ዋናው ጉዳይ “ይሄን ድንጋይ እያየን ሁሌ ስለሱ ማውራት፣ ‘ኢትዮጵያ ታላቅ ነበረች፤ ታላቅም ትኾናለች’፣ ብሎ ሁልጊዜ መለፈፍ ሳይኾን ከፈረንጅ የተማርነውን ወደኛ ዘዬ ማምጣትና ሌላ አክሱምን የሚያስንቅ ስራ መስራት ነው።” ይለናል ደራሲው። ይህንንም በግሩም እርስ በርስ ተገፋፍቶና ተጣጥሎ መጓዝ ሃገራችንን፣ ራሳችንን እንዳናገኝ ያደርገናል። ሳንጣጣልና ማንም የበላይ፣ ማንም፣ ማንም ላይ ጉልበተኛ ሳይሆን ያገኘውን እርስበርሱ ቢቀያየርና፣ ቢቀባበል ራሳችንን፣ ማንነታችንን፣ ሃገራችንን ማግኘት እንችላለን በማለት በ’ፊኛ’ው ምሳሌ በሚደንቅ ሁኔታ እንድናስብ ያደርጋል።
፨ ትምህርት ቤት የሚከፈተው ለትርፍ እንጂ ትውልድን ለማነጽ አይደለም። በዚህም ምክንያት ታላቅ ሙያ የሆነውን መምህርነትን ክብሩን የሚያበሻቅጡ፣ ምንነቱ ያልገባቸው ‹መምህርነት ማለት ወር ጠብቆ ደሞዝ መቀበል ነው› የሚሉ ‘መምህራን’ ተገኝተዋል። ዶክተር ደጀኔ ለመምህርነት ዘብ ይቆማል። ‹‹ሀገር የምትለካው ባላት መምህራኖቿ ነው።›› እያለ.. ወደ ኮሌጁ ግቢ ሲገባ ለመኪና የሚከፈተውን በር አስከፍቶ ‹‹ያስከፈትኩህ ለኔ ሳይኾን ለመምህርነቴ ነው።›› ይላል።
፨ መምህርነትና ዕውቀት ምን ማለት እንደኾኑ በፊልሙ እናያለን። “ዕውቀት ማለት የተሸመደደ ሳይኾን፤ ተምሮ የተገኘው ላይ አዲስ ነገር መፍጠር መቻል ነው።”፤ መምህርነት ደግሞ “ማስሸምደድ ሳይኾን ሆኖ በመገኘት ስነ-ምግባርን ማሳየት ነው።” ይላል። ለምሳሌ የሚያጨስ አስተማሪ ‹‹አታጭሱ! ማጨስ ጎጂ ነው።›› ብሎ ቢያስተምር ‘አስተማረ’ አይባልም። የተባለውን ማስተላለፍ ሳይሆን መሆን ነው።
፨ ሌላው የተነሳው ጉዳይ፤ በካፒታሊዝም ህግ መሰረት ግለኝነት እና የራስ ኪስ እስከሞላ ድረስ ሌላው የለፋውን፣ ያገዘውን አካል ትኩረት አለመስጠት ነው። ለምሳሌ አንድ ድርጅት ሲመሰረት ከፍተኛ ገቢ እስኪያመጣና ታዋቂ እስኪሆን የለፉ ሰራተኞችን፤ ድርጅቱ ሲታወቅ ማባረር እና እዛው የሚሰሩ ከኾነ ገቢያቸው ምንም መሻሻል የሌለው በጣም ዝቅተኛ እንደኾነ በብዙ መልኩ የሚስተዋል ነው። ‹‹የትኛውም የዓለም ሥልጣኔ ወዛደሮችን ያማከለ ነው። የሚያሳዝነው ግን የወዛደሮችን ህይወት የሚያኖር በቂ ክፍያ አለመኖሩ ነው። ቀኝ እጃችን ይሰራል፤ የሚያጌጠው ግን ግራው ነው። በሁሉም ዘመን የተነሱት ሰርቶአደሮችም ሆነ ሙያተኞች ተጨቋኞች ናቸው። ለዚህ ነው እንግዲህ የሃብት ክፍፍሉ ኢ-ፍትሐዊ የሚኾነው።›› ይላል ዶክተር ደጀኔ። ለዚህም እንደ መፍትሔ ብሎ የሚያስቀምጠውን ከአንድ የድርጅት ኃላፊ ጋር እያወራ እንዲህ ይላል፦ ‹‹የገንዘብ ትርፍ ማምጣት እኮ አይከብድም። የመንፈስ ባዶነት ካልሆነ በቀር ከፍተኛ ትርፍ ያገኛሉ። ላባቸውን ጠብ አድርገው ለሚሰሩ ሰራተኞች በቂ ዋጋ አለመ’ከፈሉ ነው ችግሩ። እርስዎም ቢኾኑ ከሚያገኙት ትርፍ ላይ ለሰራተኞችዎ ከ100% ሰላሳ ያህሉን ቢሰጧቸው ከገንዘብዎ አያጎድልም።›› ይላል።
፨ በአጠቃላይ ፊልሙ የሃገር ፍቅርን የሚያሰርጽ፣ ለበታቾቻችን ማዘን እንዳለብን የሚገልጽና ራሳችንን አግኝተን ራሳችንን መሆን እንዳለብን የሚጠቁም ነው።





Read 377 times Last modified on Saturday, 21 September 2024 12:17