Saturday, 14 September 2024 12:46

ሴቶች ከማጀት ባሻገር

Written by  አብዲ መሃመድ
Rate this item
(1 Vote)

ያገራችን ባህል የሴቶችን አካላዊ ውበት ብቸኛና ጠቃሚ ገጽታ አድርጎ በመቁጠሩ ሳቢያ ብዙ ሴቶችን ነፃ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ሌሎች ባህርዮቻቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ በቤት ውስጥ ተቀንብቦ ለሚኖራቸው ተግባራት መጐልበት ብቻ ቅድሚያ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሴቶች የአካላዊ ውበታቸውን ጠቀሜታ አጉልተው እንዲመለከቱ፣ አድምቀው እንዲጠብቁ ለሚያደርግ አስተሳሰብ የተጋለጡ እንዲሆኑ…አባዊ ርእዮተ-አለም ሰፊውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምረው በትምህርት ላይ፣ በአስተሳሰብ ልቀት ላይ ከማተኮር ይልቅ ብዙ ጊዜያቸውን ራሳቸውን ለማቆነጃጀት ያውላሉ፡፡ የወደፊት ምኞታቸውም ሚስት በመሆን ወይም የወንድ ጥገኝነት ላይ የተወሰነ ይሆናል’ ወይም ሲሆን ያጋጥማል፡፡
በ1960‘ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምዕራባውያን ምርቶች የሆኑት የከንፈር ቀለምና የፊት ፓውደር ወዳገራችን በመጡበት ጊዜ፣ ከትምህርታቸው ይልቅ መልካቸውና ቁመናቸው ላይ የሚያተኩሩ ሴት ተማሪዎች በብርቱ ይገሰጹ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ በወቅቱ ይሄንን የታዘበ መስፍን ሀብቱ የተባለ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ ይሄን ዝነኛ ስንኝ ቋጥሮ ነበር….“ቀዩን ቀለም አጥፊው ከከንፈርሽ ላይ ቁንጅና ውበትሽ ጎልቶ እንዲታይ”…፡፡
 በሰባዎቹ አጋማሽ የሴቶች የቁንጅና ውድድር በሚደረግበት ወቅት ከፍተኛ የትችት አስተያየት ይወነጨፍበት ነበር፡፡ በአንድ ወገን ስለውድድሩ ጠቃሚነት ሲነሳ፣ በሌላኛው ወገን ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይብሳል የሚል ነቀፋ ይሰነዘራል፡፡ በወቅቱ ክርክሩ ተባብሶ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እውቅ ጸሐፊያንና ትንታግ ገጣሚያን ይሳተፉ ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ ከፍ ያለ የሀሳብ ፍጭት ስለሚደረግ ህዝቡም ሆነ የሚመለከተው አካል ግንዛቤ ይጨብጥበት ነበር፡፡ ጋዜጠኛና ደራሲ ተክሉ ታቦር ባሰናዱት ግለ ህይወት ታሪካቸው ውስጥ ስለ ጉዳዩ ሲያስታውሱ…“ሀይሉ ገ/ዮሀንስ አሁን የብዕር ስሙ ገሞራው’ አሁን ከኛ ጋር አይደለም፡፡ በስደት እንዳለ በሰማንያ አመቱ አርፏል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳለ በየአመቱ በሚደረገው የስነ ግጥም ጉባኤ ላይ ጉልህ ስፍራ የነበረው ግለሰብ ነው፤ እሱ በወቅቱ የቁንጅና ውድድር መደረጉን ከማይደግፉት ወገኖች አንዱ ነበር፡፡ ”ተፈጥሮ ባደለን ስፍር ቁጥር በሌላቸው ትዕይንቶች ልንረካ እንችላለን” ባይ ነበር፡፡ የሰውን ገላ በማወዳደር እርካታ ለማግኘት የሚደረግ ውድድር አብሮት የሚመጣ ጠንቅ እንዳለ ምሳሌ በመስጠት ይሞግታል፡፡ ኢትዮጵያን ለመሰለች በልማት ወደ ኋላ የቀረች አገር ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ያለባት ለሌሎች ጉዳዮች መሆን ይኖርበታል የሚል አስተያየት ይሰነዝራል፡፡ ሀገርን ለማስተዋወቅ ልዩ-ልዩ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ልዩ-ልዩ የተፈጥሮ እጽዋትና የዱር አራዊት’ወዘተ…በተቀነባበረ መልኩ አቅርቦ ማስተዋወቅም ይቻላል፤ ይሉ ነበር እነ ገሞራው፡፡(ገጽ.201)
…በይበልጥ የሚያስፈራው ደግሞ ሴቶች ከዚህ ከተለመደ አዙሪታም ግብር ውጪ፤ አሊያም “የሴትነት መገለጫ ያልተላበሰ ድርጊት ነው›› ተብሎ ከሚታመን ባህሪም ሆነ አስተሳሰብ የተለየ ነገር ከታየባቸው ማህበረሰቡ በጅምላና በመንጋ ማሰይጠኑ፣ ማሸማቀቅና ማዋረዱ እራሳቸውን እንዳይሆኑና ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተወዳዳሪ ከመሆን አግዷል፤ ሲያግድም ለዘመናት ዘልቋል፡፡ ስንሰማ ያደግናቸው “ሴቶች ስሜታዊና ደካማ ፍጡሮች ናቸው” የሚለው አባባል በራሱ በማህበረሰቡ የተጫነባቸውን ዝቅተኝነት አጠናክረው የሚያስቀጥሉ ናቸው፡፡ ብሂሎቻችንን ስንፈታትሽም ከእነዚህ እምብዛም እርቀው ፈቅ ያሉ አይደሉም፡፡ ከሴት መምከር ለመስከር፣ ሴት መውደድ ገሃነም መውረድ፣ የሴት ወበራ ትታጠቃለች ካራ፣ ምን ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ፣ ሴትና ዶሮ ሳያብዱ አይውሉም…ወዘተ፡፡ በሌሎችም ምሳሌዎቻችን ውስጥም ሴቶችን በክፋት የተሞሉና ማመዛዘን የጎደላቸው ፍጡሮች እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ የተለመደ እንደሆነ  ነቅሶ ማሳየት ይቻላል፡፡ የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትር የነበረችው ገነት ዘውዴ (ፒ.ኤች.ዲ) የታተሙና ያልታተሙ ስራዎችን ፈትሻ፤ የራሷንም ገጠመኞችና ትዝብቶቿን አካትታ ሴቶች ለነፃነት ለመብቃት ያደረጉትን ንቅናቄ ፍንትው አድርጋ ያሳየችበት ‹‹የኢትዮጵያ ሴቶች ትግል›› በተሰኘ መጽሐፏ ውስጥ፤…‹‹ሴቶችን የሚጨቁኑት ጎጂ ልማዶች፣ ህጎችና ተግባሮች ሕገ መንግስቱን የሚጻረሩ መሆናቸው ቢደነገግም፣ በስፋት በወንዶችና በሴቶች አዕምሮዎች ውስጥ የአባዊነት አሉታዊ እሴቶችና ድርጊቶች የሴቶችን እኩልነት የሚያሰናክሉ ደንቃራዎች እንደሆኑ ዛሬም ቀጥለዋል!…” ስትል በጥናቷ ታስረግጣለች፡፡ ገነት አያይዛ፣…ሴት ልጅ ጐበዝ፣ ተፎካካሪ ወይም ቆፍጣና ወዘተ ሆና ከተገኘችም እነኚህ ባህርያት ለሴቶች ባይተዋር የሆኑ ይመስል ማህበረሰቡ ‹ወንድ ናት› በማለት በአድናቆት ይገልጻታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች ቦታ ቤት ውስጥና ከባሎቻቸው በታች መሆኑን የሚገልጹ በርካታ ዜማዎች፣ ግጥሞችና አባባሎች አሉ፡፡  አባዊነት የተጠናወተው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሴቶች ትምህርት እንዳያገኙ፣ የሚረባ ስራ እንዳይዙ ወይም ንብረት እንዳያፈሩ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው አንቆ ስለያዛቸው በሂደት ተዋርደው የአባቶቻቸው፣ የባሎቻቸውና የልጆቻቸው ጥገኞች ለመሆን ተገደው ቆይተዋል፡፡ በዚህም አገሪቱም ለልማት ከሴቶች የምታገኘውን አስተዋጽኦ አጥታለች፡፡ የሴቶችን የንብረት ባለቤትነት፣ የትምህርት፣ የጤና እና የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶች መቀበል ሴቶችን ማብቃት ብቻ ሳይሆን መላ ቤተሰብንና ማህበረሰብንም ማብቃት ነው …ትላለች፡፡ (ገጽ.145)

እራስን የመፈለግ ኃሰሳ
ያሳለፈችውን ህይወት በማሰስና በመከለስ ምናልባት ለሌሎች እንስቶች ማነቃቂያና መማሪያ፣ የነገን ብርሃንና ብሩህ ተስፋ ማመላከቻ ሊሆን የሚችል ህይወት ያሳለፈች ባለታሪክ ናት - ሐና ኃይሉ፡፡ የህይወት ክህሎት አሰልጣኝ፣ ጸሐፊና የማህበረሰብ ስራ ፈጣሪም ጭምር ነች፡፡ ብዙ የማወራው ነገር የኖረኝ ብዙ ያለፍኩበት ነገር ስላለ ነው… ስትል ጀምራ ……በፍኖቷ ሁሉ የገጠሟትን የህይወት ተግዳሮቶች፤ እራሷን ለማብቃት ከልጅነት እስከ እውቀት በተሰማራችባቸው፣ በወጣች በወረደችባቸው መስኮች ሁሉ ህልሟን ለመኖር ንቁ ተሳትፎ ባደረገችባቸውና አባዊ ስርዓትን እንደምን ተቋቁማ እንደታገለች፣ አሸንፋም እንደወጣች ቁልጭ አድርጋ በ“ምስሌን ፍለጋ” ውስጥ ታስነብበናለች፡፡ ሐና ለሌሎች ሴቶችም ጥሩ አርዓያ ለመሆን እምትበቃም ጭምር ነች፡፡ እንደ ሐና በድፍረትና በንቃት አይውጡ እንጂ የሉም ማለት እንዳልሆነ ግን መታወቅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ከማጀት ውጪ ያከናወኗቸው ተግባሮች በርካታ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ተነግረውም ሆነ ተተርከው አልተቋጩም፣ ተጽፈው አላለቁም፣ አልተዘገቡም፡፡ የላቀ ዋጋ እንዳላቸው ሳያውቁት ቀርተው ይሁን አሊያም በሌላ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ታሪካቸውን አውጥተው ሳይጽፉት ይቀራሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት ከወጡ ጥቂት የማይባሉ የህትመት ውጤቶች ውጪ እንዲህ አይነት በራስ ላይ ያተኮረ፣ ምስልን የመፈለግ ጉዞ ያስቃኘ መጽሐፍ በግሌ አላጋጠመኝም፡፡ (ሐዊር የተሰኘ የአንዲት ሴት መጽሐፍ ከሐና ጋር ተስተካካይ ነውና እሱን ግን አያካትትም)…ስለ ኢትዮጵያ ሴቶች ከተጻፉ በርካታ የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ከነገስታቱ ሚስቶች፣ ንግስቶችና ልዕልቶች ወይም በፖለቲካው ውስጥ ተደማጭነት ከነበራቸው ወንዶች ጋር ቅርበት ካላቸው ጥቂት ሴቶች በስተቀር የሴቶች ገድል የሚቀርበው ከፍ ሲል ለማሳየት እንደሞከርኩት አንሶና ተንኳሶ ነው፡፡ የዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በወቅቱ ተንሰራፍቶ የነበረው ‹ሴቶች ታሪክ አይሰሩም› የሚለው አመለካከት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ሐና እራሷን ፍለጋ፣ ትክክለኛውንና ሙሉ የሚያደርጋትን ምስል ለማየት በምታደርገው እልህ አስጨራሽ ኃሰሳ ውስጥ እግረ መንገዷን አያሌ የሴትነት የነፍስ ጥያቄዎችን እያነሳች ትጥላለች፡፡ የራሷ የሆነውን ሙሉነት ያዘለውን የህይወት ምስል በአስተውሎት መፈተሽ፣ በአንክሮ ማሰላሰል የጀመረችውም ማልዶ ነበር፡፡ በውስጧ ያለው ለብዙዎች የመድረስ መሻት፣ የመለወጥ፣ የማደግ ጥማት የቱን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ እንኳን ሌሎች እራሷም በቅጡ አትረዳውም ነበር፡፡…‹‹ለኔ የከፋ ህመም የሆነውና እንቅልፍ የነሳኝ “ህልሟን መኖር ያልቻለች ሴት” ላለመሆን የማደርገው ከራሴ ጋር የተያያዝኩት ፍልሚያ ነበር፡፡ የምፈልገው ገንዘብ ወይም ቁስ ሳይሆን፣ የማድግበትን ጥበብ፣ ሰው የምሆንበትን ትምህርት፣ የምመራበትን ስልጠና፣ ቦታ፣ መጽሐፍ ወዘተረፈ…እንዲሰጡኝ ነበር፡፡ ይኼንን ላደረገ ግለሰብና አካል ትልቅ ቦታ ስደርስ ወሮታውን እከፍላለሁ እያልኩ አልፎ አልፎ እጨምርበት ነበር፡፡ (ገጽ.87)
 ሐናን አንድ ነገር ላይ ብቻ እንድታተኩርና ምኞቷን እንድትሰበስብ ያልነገራት ወዳጅና ዘመድ አልነበረም፤ ይሁንና ልጅት በጄ እምትል አልነበረችም፡፡ ተማሪዎችን የማስጠናት፣ በውዝዋዜ፣ በነዳጅ ማደያዎችም የሽያጭ ሰራተኛ፣ የኪነጥበብ ዝግጅቶች መድረክ የመምራትና ማድመቅ …ለመስራት ከሞከረቻቸው የስራ ዘርፎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የተፈተነችባቸው ምርጫዎች በርካታ ነበሩ፡፡ አንዳንድ የህይወት ክህሎት አሰልጣኞች እንደሚሉት ከሆነ፤ በልምድና በእውቀት እንዲሁም በእድሜ ከእኛ የተሻሉ ሰዎች እየተከታተሉ ሲያስተምሩንና ሲያሰለጥኑን፣ ትንሽዋ ልባችን ውስጥ የተተከለችውን የሀሳብና ምኞት ችግኝ ውሃ እያጠጣ፣ እየኮተኮተ እንዲያድግ ይረዳናል፡፡ ትክክለኛውን መጽሐፍ፣ የትምህርት ቦታና ሰዎችን እንድናገኝ ይረዳናል፤ ይቆጣጠረናል!...ይላሉ፡፡ ሐና መዳረሻዋና ግቧ ሩቅ ነውና ወደፊት በብዙ መድረኮች ላይ እንደምትቆም ያወቀችው በጣም ልጅ እያለች ነበር፡፡ ከልቧ ባለህልም ናት፡፡ ድርሳኗ ሙሉ ለሙሉ ለዚህ አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ በምትማርበት ወቅት ከሚፈጠርባት ችግርና ጫና ሁሉ ለማምለጥ የምታደርጋቸው ጥረቶች፣ የምትጠቀመው ብቸኛ አማራጭ ህልሟን ነበር፡፡ ራሷን በስራ በመዝፈቅና በመጥመድ የምታደርገው ሙከራ በርካታ ጥሩ እድሎችን እንድታገኝ ምክንያት ሆኗታል፡፡ አስቸጋሪ ተግዳሮት ሲገጥማት እራሷን ወደ ላይ ማስፈንጠር ያበረታታ’ታል፤ ይሄ የግሌ የምትለው መፍትሄ ነበር፡፡ ይሁንና ከቀለም ትምህርቷ ጎን ለጎን በቻለችው መንገድ ሁሉ በመጣር ሌላም ብዙ ትምህርት ከልምድ አግኝታለች፤ ገብይታለችም፡፡ እራሷን ከአዲስ ነገር ጋር በማለማመድ፣ ሲዳምኛ ቋንቋውን በማጥናትና ስለሌሎችም ባህሎቻችን በመማር፣ ወደ ናይሮቢ ወደ ኬንያ በማቅናት አያሌ አመለካከቶቿን ቀይራለች፡፡ በአለም ላይ ስላሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ ባለታሪኮች፣ የሚጎበኙ ስፍራዎች በማየት ያገኘችው ትምህርትና ከስልጠናዎች፣ ከስብሰባዎች፣ ከሰዎች ጋር በመገናኘት፣ በመማርና በማስተማር ወዘተ፡፡ ይህን የምታደርገው በምታገኛቸው ሰዎች ውስጥ ብዙ እድል አለ ብላ ስለምታምንም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ጊዜያቶች ሁሉ የህይወት ተሞክሮዋ አካል ናቸው፡፡ በእነዚህ ስንክሳሮች ውስጥ ተደብቃ ነው እንግዲህ ለዛሬ ማንነቷ የበቃችው፡፡ ሴቶች ከዚህ ጥንካሬ፣ ከዚህ የህልም ብርታት መነሻነት የራሳቸውን እጣ ፈንታ ለማሻሻል ሃናን እንደ አርአያ መከተል እሚኖርባቸው  ለዚህ ነው፡፡

Read 483 times