መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ3 ሴቶች ውስጥ 2 ሴቶች በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ 1 ጊዜ የፋይብሮይድ (ማዮማ) እጢ ያጋጥማቸዋል ተብሎ ይገመታል። በይበልጥ እድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑ ሴቶች ማህፀን ላይ ለሚከሰተው ፋይብሮይድ (ማዮማ) እጢ ይጋለጣሉ።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ማዮማ ወይም ሞኝ እጢ ተብሎ የሚጠራው እጢ ከመሀፀን ግድግዳ የሚነሳ የማህፀን እጢ አይነት መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ማህፀን ላይ የሚፈጠር የእጢ አይነት በሁሉም ሴቶች ላይ የሚያጋጥም ነው። በይበልጥ እድሜያቸው ከ25 እስከ 40 ዓመት የሆኑ እና ኡደቱን የጠበቀ(በወር) የወርአበባ ያላቸው ሴቶች ለማዮማ እጢ እንደሚጋለጡ የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር አንዲት ሴት በመውለጃ (በተለይ በ20ዎቹ) የእድሜ ክልል ውስጥ ፅንስ ካልተፈጠረ(ልጅ ካልወለደች) ማለትም በእርግዝና ምክንያት የወር አበባ ካልተቋረጠ ለፋይብሮይድ እጢ የመጋለጥ እድል ይኖራታል።
ለፋይብሮይድ (ማዮማ) እጢ አጋላጭ ሁኔታዎች (መንስኤ)
እርግዝና አለመፈጠር ወይም ልጅ አለመውለድ (የወር አበባ አለመቋረጥ)
ከመጠን ያለፈ ውፍረት
ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ እና የተስተካከለ የአመጋገብ ስርአት አለመኖር
ጥቁር የቆዳ ቀለም (ጥቁር ቀለም ያላቸው ሴቶች)
ሴቶች የማዮማ እጢ ህክምና ካገኙ በኋላ በድጋሚ ለችግሩ ሊጋለጡ ይችላሉ። ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት በድጋሚ ለችግሩ በይበልጥ የሚጋለጡት የተስተካከለ አመጋገብ የሌላቸው ሴቶች ናቸው። ከፍራፍሬ እና አትክልት ይልቅ ጣፋጭ እና መሰል በብዛት ሲወሰዱ ጉዳት የሚያመጡ ምግቦችን የሚጠቀሙ ሴቶች ላይ ነው የሚያጋጥመው።
የፋይብሮይድ (ማዮማ) አይነት ወይም አቀማመጥ
የማህፀን ግድግዳ አከባቢ ያለ እጢ; በብዛት ለደም መፍሰስ የሚያጋልጥ ሲሆን እርግዝና እንዳይፈጥር ያሊያደርግ ይችላል።
ከማህፀን ውጪ የተፈጠረ እጢ; ምልክት ላያሳይ እንዲሁም ችግር ሳይፈጥር ለዓመታት ሊቆይ ይችላል። ነገር ግን ከባድ ህመም የሚያስከትለበት አጋጣሚ አለ። እንደዚህ አይነት ችግር ሲያጋጥም የቀዶ ጥገና ህክምና ይሰጣል። ከማህፀን ውጪ ተፈጥሮ ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ እጢ በብዛት የሚከሰት አይደለም።
የማህፀን የመሀል ክፍል ላይ የተቀመጠ; በብዛት ምልክት ላያሳይ ይችላል።
የፋይብሮይድ (ማዮማ) ምልክቶች
የወርአበባ መዛባት (መብዛት ወይም ቶሎ ቶሎ መምጣት)
ማህፀን አከባቢ ህመም መኖር
ምቾት መንሳት ወይም ሆድ አከባቢ ከፍተኛ ክብደት(እብጠት)
ኩላሊት አከባቢ ውሃ መያዝ እና ሽንት መቆጣጠር አለመቻል
70 በመቶ እጢው ምንም አይነት ህመም (ምልክት) እንደማያሳይ የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። እንዲሁም እጢው ያለበት ቦታ እና መጠን በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት የህመም ስሜት ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ችግር ሲፈጥር በብዛት አይስተዋልም። ምክንያቱም እጢው በብዛት የሚቀመጠው ማህፀን ውስጥ ስለሚሆን ብልት ላይ ችግር አያስከትልም።
እንደ ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ንግግር ሁሉም ማህፀን ላይ የሚያጋጥሙ እጢዎች ወደ ካንሰርነት አይቀየሩም። ወደ ካንሰር ከማይቀየሩ የእጢ አይነቶች ውስጥ ማዮማ (ፋይብሮይድ) አንዱ ነው። “ማዮማ ከማህፀን ግድግዳ የሚነሳ ከማህፀን ጋር ተመሳሳይነት ያለው እጢ ነው። ለተለያየ ችግር አያጋልጥም ማለት አይደለም። ነገር ግን የካንሰር አጋላጭነቱ ሲሰላ ከ1000 ሰው 1 ሰው ላይ የሚያጋጥም ነው” ብለዋል ዶ/ር ሰኢድ አራጌ። የህክምና ባለሙያው አክለው ይህን ቁጥር በማየት መጨነቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ምክንያቱም እጢው በእራሱ ጊዜ ሊጠፋ ይችላል። ነገር ግን እድሜ ከ45 ዓመት በላይ ወይም የወርአበባ ከቆመ በኋላ እጢው የማይቀንስ ወይም የማይጠፋ ሲሆን ህክምና ያስፈልገዋል።
ፋይብሮይድ (ማዮማ) የሚያስከትለው ችግር
ልጅ አለመውለድ (እርግዝና እንዳይፈጠር ማድረግ)
የወርአበባ ከቆመ (ከ55 ወይም 60 ዓመት) በኋላ እጢው ካልቀነሰ (ካልጠፋ) ወደ ካንሰርነት የመለወጥ እድል
ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት በብዛት የፋይብሮይድ እጢ ሴቶች በመውለጃ የእድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙበት ወቅት በምርመራ ይገኛል። ስለሆነም ለከፋ ችግር ሊያጋልጥ ይችላል የሚል ስጋት ሊኖር አይገባም። እንዲሁም “ማዮማ ያለባት ሴት ማርገዝ ትችላለች” በማለት እጢው የማይከለክልበት ወቅት መኖሩን የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ተናግረዋል። ነገር ግን እርግዝና ከተፈጠረም በኋላ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ፅንስ እንዲቋረጥ ማድረግ፣ የፅንስ አቀማመጥ ላይ ችግር መፍጠር፣ ለደም መፍሰስ እና መሰል ችግር የሚያጋልጥበት ሁኔታ አለ። ስለሆነም የህክምና ባለሙያ ማማከር እና ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል።
ህክምና የሚያስፈልገው
የደም መፍሰስ ሲኖር
እርግዝና የሚከለክል ከሆነ
የሚሰጠው የህክምና አይነት
መድሃኒት
ቀዶጥገና
እንደ ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ንግግር የማዮማ እጢ ህክምና ከተደረገ በኋላ በድጋሚ የማጋጠም እድል አለው። “ቀዶ ጥገና ከተሰራላቸው እናቶች ግማሽ የሚሆኑት ከወራት ወይም ከ2 ዓመት በኋላ ለድጋሚ ወይም ለተደጋጋሚ ማዮማ ሊጋለጡ ይችላሉ” ብለዋል ዶ/ር ሰኢድ አራጌ። አክለውም ይህ እጢ ተደጋግሞ መውጣቱ ለተደጋጋሚ ቀዶጥገና ስለሚያጋልጥ ነው እንጂ ቀድሞ ከነበረው እጢ የተለየ አደጋ (ወደ ካንሰር የመለወጥ እድል) አይኖረውም ብለዋል።
መከላከያ መንገዶች
የአኗኗር ዘይቤ (አመጋገብ) ማስተካከል
የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ
በመውለጃ እድሜ ክልል ውስጥ (ከ25 እስከ 35 እድሜ) መውለድ እና ማጥባት
ህክምና ከተደረገ በኋላ ችግሩ በድጋሚ እንዳያጋጥም ጥንቃቄ ማድረግ
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም ማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ሴቶች የፋይብሮይድ(ማዮማ) እንዲሁም ማንኛውም የማህፀን እጢ ሲያጋጥማቸው ባለመደናገጥ ህክምና እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
Saturday, 14 September 2024 12:59
ማዮማ (ፋይብሮይድ) እጢ
Written by ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Published in
ላንተና ላንቺ