ታላቁ በዕውቀቱ ስዩም « አገሬ » በምትል ግጥሙ ፦
« አገርን ለፈሪ አይሰጡም አደራ
ዳር አድርጎት ያድራል የመሀሉን ስፍራ »
በማለት የተጠንቀቁ አይነት የዘመን ምሬቱን በሚያስርበት ሙሿዊ ስንኞቹ ይቀጥልና፤
« አገርን ለፈሪ አደራ ብሰጠው
የዘላለም ቤቴን በአንድ አዳር ለወጠው » በማለት ቀደም ሲል የነበረውን የተጠንቅቆት ምክሩን ወደ መሬት ሲያወርደው፣ ምን እንደደረሰበት፣ በትዝታ የቁጭት መሀረብ የታሰረች ዓይኑን እየገለጠ ያወጋል።
ይህ ግጥም በዘመን ደጃፍ ሲፈከር ልክ አይሁን እንጂ Desmond Doss ን የወለደችው አሜሪካ ግን በውቄን የምትቀበለው አይመስለኝም። እንደውም በግዛቷ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዜጎቿን በማስተባበር የአንድ ቆየት ያለ ቃላዊ ግጥምን ከምናምን ዶላር ጋር በፖስታ አሽጋ፤
«ጀግና ብርሌ ነው ፥ ቶሎ ይሰየፋል
ፈሪ ተራራ ነው ፥ ዘላለም ይኖራል»
የምትለው ይመስለኛል።
እንዴት?
እንዴት ማለት ጥሩ ! ከእናት ሀገር አሜሪካም ባይሆን ከአባት ዜጋ ከእኔ ነገሩን ስሙ..!
አያ ዴዝመንድ ይባላል። ዴዝመንድ ዶስ። አንዲት መፅሐፍ ቅዱስ ብቻ በመያዝ አሜሪካና ጃፓን ባደረጉት የሁለተኛው ዓለም ጦርነት በመሳተፍ፣ ለ75 ወታደሮች ህይወት መትረፍ ምክንያት የሆነ ሰው ነው።
ዴዝመንድ ዶስ እ.ኤ.አ በ1919 የአሜሪካ ግዛት በሆነችው ቨርጂኒያ ውስጥ Blue Ridge mountain አካባቢ ተወለደ። Harold (Hal) Doss ከሚባል ከእድሜ አቻ ወንድሙ ጋር በዚያች ነፋሻማና ለምለም የተራራ ግርጌ ሰርጥ አደገ። ጉርምስናውን አገባዶ ወጣት ወጣት መሽተት ሲጀምር፣ እነዛ ሞገሳም ተራሮች የልጅነት ልቡን እያደመጡ፣ የፍቅር አየር እንዳይነፍስበት ሊያግዱ አልተቻላቸውም።
በሀያዎቹ የእድሜው መጀመሪያ ላይ ከባቢው ላይ ከምትገኝ አንዲት ልጃገረድ ጋር በፍቅር ወደቀ። ይህ ወቅት ለእሱ የአፍላ የፍቅር ሰሞን ቢሆንም፣ ለዓለም ደግሞ ከግዙፉ የአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ምናልባትም ከቀደመው እልቂትና ውድመት ሁለት እጅ በላቀ ሁኔታ መላውን ዓለም ለጥፋት እየጋበዘ የሚገኘው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከተጀመረ ሰንበትበት ያለበት ወቅት ነበር።
ሃያላን ሀገራት በእኔ እበልጥ በእኔ እበልጥ የበላይነት ስሜትና ጥላቻ ተዘፍቀው የገዛ ዜጎቻቸውን ነፍጥ በማስታጠቅና ለሞት በመገፍተር፣ የተባብረን እናጥፋ ዘመቻ ትኩስ ፍቅር ላይ ነበሩ። የጋራ ስብሰባዎቻቸውን በተለያዩ የጦር ጀነራሎቻቸውና የሀገራት መሪዎቻቸው እየዶለቱ ለጥጋባቸው ማስታወሻ የምትሆን እብሪት ላይ ይማከሩም ነበር።
ጦር መሳሪያ መግዛት ... መፈብረክ ለአውደ ውጊያ በሚሆን ልክ በማሰናዳት እንቅልፍን ለቆሌ ፥ ልባቸውን ለመብለጫ ተንኮል ፍለጋ በሚሰፍሩበት ፎሌ ቀድተው በመድፋት ላይ በተጠመዱበት ወቅት፣ ቀጭኑና ለጋው ዶስ ከፍቅረኛው ጋር እፍ ባለ ፍቅር ሩቅ ተሰደደ።
ሀገሩ አሜሪካ የብልጥ ልጅ ልብ ያላት አስተዋይ ባልቴት ናት። እያንዳንዱ ሀያል ሀገር ጀርባ በማደግ ላይ የሚገኙና እድገታቸውን የጨረሱ የቀጫጫ እሳቦት ደርዝ ያላቸው ሁሉ ለጦር ሲሰለፉ፣ እኔን የሚነካ እስከሌለ በማለት በ isolation policy ታፍራና ተከብራ ቁጭ አለች።
ጅማሮውን በ1939 ያደረገው ይህ ግዙፍ ጦርነት ግን ልክ በሁለት ዓመት እድሜው ማለትም በ1941 ታህሳስ ወር ላይ አሜሪካን ሳትወድ በግድ እስኪያሳትፋት እሱም ሆነ ሀገሩ የሰላም ድባብ ውስጥ ተዘፍቀው ነበር። Militaristic Japan በሩቅ ምስራቅ ቀጠና ታላቅ ግዛት በሚመሰርት ህልሟ ድንበሯን በመሻገር ደቡባዊውን የቻይና ግዛት (Manchuria) ን ወረረች።
ጃፓን ለአንዳንድ አላማዎቿ ማሳኪያ የአሜሪካን ውለታ ፈልጋ ደጅ ጠናች። በወቅቱ አሜሪካ የቻይና ወዳጅ ነበረችና የጃፓንን ደጅ ጥናት ችላ አለች። ጃፓን በበኩሏ፤ በ Pacific island Hawaii ላይ በሚገኘውንና Peral Harbour በሚሰኘው USA Naval Base ላይ ጥቃት ፈፀመች። ይሄን ጊዜ የዶስ ሀገር አሜሪካ ቁጭት በልታ .. ወይኔን ተግታ ዝም አላለችም። ወኔ ተሞልታ Allied powers ተብለው ከሚጠሩት ወገን ተሰለፈች። የተለያዩ አውደ ውጊያዎች ላይ በመሳተፍም ሩቅ ምስራቋ ሀገር ጃፓን የተሰነዘረባትን ጥቃት አፀፋ ለመመለስ ትግል ገጠመች። ይሄኔ ልበ ብርቱው ዴዝመንድ አሜሪካ ለምታደርገው አውደ ውጊያ በወታደርነት ተመዝግቦ ወደ ልምምድ ቦታው ሄደ። ነገር ግን የሚሰጠው ስልጠና እና የእሱ አቅም መጣጣም የማይችሉ ሆኑ። ከእድሜ እኩዮቹ በታች የሆነ አፈፃፀም ማሳየት ጀመረ።
በስልጠናው ቦታ ተሳክቶለት ስልጠናውን አጠናቆ ለውጊያ ዝግጁ መሆኑ ቀርቶ በሚያደርገው ድርጊት የሰልጣኞች መዘባበትና ሳቅ መፍጠሪያ ፍጡር ተደርጎ ቀረ። መሳሪያ አልነካም በሚል አቋሙ ከአሰልጣኞቹ ጋር በሚገባው እሰጣ ገባና የስልጠና ቀናቶቹን ለሀይማኖታዊ ግልጋሎት በመጠቀሙ ከመሰሎቹ ተለይቶ መታያ መንገዶቹ ሆኑ።
በዚህ ሰው ሁኔታ የጦር ማሰልጠኛ ተቋሙና ራሱ ሰውየው ፍጥጫ ውስጥ ገቡ። « የሀገር ፍቅር አለኝ፤ ለሀገሬ እዘምታለሁ፤ አዝምቱኝ ብያለሁ አዝምቱኝ! » አለ ዶስ
« ምን ይዘህ? » አሉት አሰልጣኞቹ
« መጽሐፍ ቅዱሴን ይዤ » አለ
« ነገሩ የጦር እንጂ የቤተስኪያን የምልጃ ፕሮግራም አይደለም » ቢሉት እምቢኝ አለ።
ትልቅ ሀገር ትልቅ ነውና የወጣቱን ሰው የሀገር ፍቅር መነሳሳት ባላቸው የስልጣን መዳፍ አዳፍነው አላጠፉም። ተያይዘው ፍርድ ቤት ቆሙ። ከብርቱ ክርክር በኋላ የፍርድ ሚዛኑ ለዴዝመንድ አደላ። ፍርድ ቤቱም፤ « የጦር መሳሪያ ሳይነካ ይዝመት » ሲል መዶሻውን አንስቶ አፈረጠ። ዶስ ፈገግ አለ። መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ሄደ። ለተወሰኑ ጊዜያት በመጀመሪያ እርዳታ አሰጣጥ ዙሪያ ሰለጠነ። የዘመቻው ቀን ደርሶ ሁሉም የሚይዘውን ሲይዝ ፤ እሱ በወታደር ልብሱ አጊጦ መጽሐፍ ቅዱሱን ይዞ ተነሳ።
ጦረኛቹ፤ « እስኪ ጠላትን ተሳድበህ አልያ ሰብከህ ትጥላቸው እንደሆን እናያለን » እያሉ መሀል አስገብተውት ነጎዱ።
ከቀናት በኋላ በጃፓን የምትገኘውን የ «ኦኪናዋ » ግዛት ለመያዝ Hacksaw በሚባል ሰርጥ ላይ ወሳኝ የሆነ ፍልሚያ አደረጉ። ከገመተው በላይ የጦር ሜዳ ሁነቶችን እየተመለከተ አምሽቶ አነጋ። ካየው በላይ ግን አልደነገጠም። የአቻዎቹን ብርታት ሲመለከት በሀገር ፍቅር ስሜት እየነደደች በደረት ኪሱ የያዛትን መጠነኛ መጽሐፍ ቅዱስ እየገጨች የምትመለስ ልቡ በወኔ ተሞልታ ብርትት አለች። የተስፋ በትሯን ጭብጥ በአንድ አምላኳ ስም ተክታ በመሰንበት ፤ በዚያ እልቂት በሞላበት ሰማይ ስር እግሯን ዘርግታ አረፍ አለች።
አንደኛው ወይም ሁለተኛው የውጊያ ክፍለ ጊዜ፣ በሁለቱም ወገን ብዛት ያለውን ወታደር ረፍርፎ ተጠናቀቀ። አሜሪካ ከሰርጡ በታች የጦር ካምፗን ዳስ በማቆም፣ ከላይ ወታደሮቿን በመስደድ መዋጋቷን ልብ ይሏል። በማፈላለግ ስልት ለጊዜ ግዝት ከወረደውና ከቁስለኛው መሀል እሱ ቢፈለግ ጠፋ። ያ ደቃቃ ፈሪ ወታደር ወዴት አለ ቢሉ፣ ቁስለኛው ሁሉ ከላይ እያሰረ ወደ ተራራው ንቃቃት በመላክ መተኪያ የሌላት ህይወታችንን የታደጋት መልዓክ እሱ ነው አሉ። ጉድ ተባለ።
በዚያ መሳሪያ እንደዶፍ በሚዘንብበት፣ መልዓከ ሞት ጥፍራም እጁን ኪሱ ከትቶ ሟች በዝቶበት በአይኑ እየቆጠረና እያፏጨ በሚዘዋወርበት ሰርጥ፣ ዶስ የዚህን ሁሉ ቁስለኛ ህይወት ታደገ? በዚያ መሬቱ በሞርታርና የመትረየስ ቀበኛ እንዲሁም በመድፍ እየታረሰ ሰማይ እልል ፥ ምድር ዝልል በምትልበት ቀጠና ሊያውም ፍርሃቱን በፍርድ ቤት ሞግቶ ያሸነፈ ሰው? ኧረ ተዉ፤ አለ ሀላፊያቸው። ቀጠለናም ሞት አስክሮ ቀባጥራችሁ እንጂ ይህስ እውነት አይደለም አለ። ዶስ ግን በአረር የጭስ ጉም ታጥሮ ሰማይ በጠቆረበት የጦር ሰፈር ውስጥ መሬት ለመሬት እየተንፏቀቀ፣ አካለ ጎደሎ የሆኑ ወታደሮችን በመሸከም ይሮጣል።
በመሀል በመሀል እጆቹን ለፀሎት እያጣመረ፤ « Help me gets one more » እያለና በሬሳ ላይ እየተረማመደ፣ ትንፋሻቸው ያልከዳቻቸው ወታደሮችን ተሸክሞ በመሮጥ ከተራራው ጫፍ ወደ ታች በገመድ በማውረድ ህይወት በማዳን ተሰለፈ። በስተመጨረሻም ከጠላት ወገን የሚሰራው ማዳን ተደርሶበት ሊገድሉት ሲራወጡ፣ አንድ ቁስለኛ በመታቀፍ ራሱን በገመድ አስሮ ዶስ ብቅ አለ።
ጉሮ ወሸባ ሆነ።
የሀይል ሚዛኑ ለጃፓኖች አድልቶ የተጠናቀቀው የጦር ውሎ ማግስቱን በተደረገ ውጊያ አሜሪካ ሙሉ ለሙሉ የ« ኦኪናዋ »ን ግዛት መቆጣጠር ቻለች። በዚህ ውጊያ መሀል ዴዝመንድ ግራ እጁን በመሳሪያ ከመመታት ባለፈ የ17 የቦንብ ፍንጣሪዎች ገላውን ወንፊት ከማድረግ አልታቀቡም ነበር። የሆነው ሆኖ በዚህ ሰርጥ ዴዝመንድ ዶስ በማይታመን ሁኔታ 75 የቁስለኛ ወታደሮችን ህይወት አተረፈ። አንዳንድ ፅሁፎች ላይ 75 የሀገሩን ዜጎች እንጂ ከጠላቶች ወገንም ያልተቆጠሩ ነገር ግን ህይወታቸውን ያተረፈላቸው ብዙ ወታደሮች አሉ የሚለውን እንደጥቁምታ አንስቼ፣ እ.ኤ.አ ነሐሴ 6 እና 9 በሁለት የጃፓን ከተሞች Hiroshima እና Nagasaki ላይ በተጣለ አቶሚክ ቦምብ ማጠቃለያውን አድርጎ፣ ጦርነቱ በአሜሪካ ድል ነሺነት ተጠናቀቀ፡፡
ዶስ፤ ሀገር በደረታም ጉልበታም ጎረምሶቿ ብቻ ሳይሆን፣ በለንቋሳ የራሳቸውን መዋጊያ በያዙ ሰዎችም እንደምትቀና በብርቱ ተግባሩ ለፈፈ። ፀደይ ሲከትም ፀደይ መስለው ለሀገር ከጃኖ የደመቁ እጆች በላይ መታፈርና መከበር የለም። ከብዙ ጭንግፍ ሀዘኖች መሀል የወጣች ሳቅም አርያም የምታካልል የሰው ልጆች የመዳን በረከት ነች። ሁሌም በመግደል ሳይሆን በማዳንም ህይወት እንደሚያብብ፣ ከብዙ ታላላቅ የዓለማችን ሰዎች መሀከል የሚጠቀስ ሰውም ነው ይህ ጀግና!
ዴዝመንድ ከወይኔ አድማሳቸው ማዶ የሀገር ሞቷን ደግሰው ለክተት የጠሯቸውን ጎልያዶች ለማንበርከክ ጎልያድ አክሎ መሳሪያ በመወደር ብቻ ሳይሆን፣ የራስን ስጦታ አክብሮ ጠጠር በመያዝ ዳዊት መሆንም ዋጋ እንዳለው ለድፍን አሜሪካ ወኔ ሆነ። በዚህም ታላቅ ጀብዱ በወቅቱ ከነበረው የአሜሪካ መሪ እጅ ከፍተኛውን የቆራጥነት ሜዳልያ ለመሸለም የበቃ የታላቅ ሰብዕና ባለቤትም ነው።
የዚህን ሁሉ ክብር ባለቤት የሆነው አስገራሚው ሰው ዶስ፣ በወደዳት ሀገር ተወዶ ባከበራት ሀገር ተከብሮ፣ ያቅላላችበትን የእርጅና ሞገሳም ፈረስ ሳይሳቀቅ ጋልቦ፣ በተወለደ በ87 ዓመቱ መጋቢት 2006 ዓ.ም ከዚህች አለም በሞት ተለየ። ከመሞቱ ሦስት ዓመት አስቀድሞ እውነተኛ የህይወት ታሪኩን ማዕከል በማድረግ በ Robert schenkkan & Andrew Knight ተፅፎ በሜል ጊብሰን ዳይሬክት ተደርጎ ለእይታ የበቃውና ኋላም የኦስካር ሽልማት አሸናፊ የሆነው Hacksaw Ridge (2003) ፊልም፣ ለክብሩ ከቆሙ የምስጋና ሀውሎቶቹ አንዱ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ The Conscientious Objector የሚለው የ47 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ ዶክመንተሪ ፊልሙም መላው ህይወቱን ለማስቃኘት የሞከረ ስራ ነው። ጀግና በዚህ ልክ ሲወደስ ደስ ይላል። የኋላው ከሌለ....ማለትም ይሄኔ ነው።
ታዲያስ አገርን ለፈሪ አደራ አይሰጡም? እውን ፈሪ ተራራስ አደለም..? በውቄስ ይሄን ቢሰማ የገዛ ግጥሙን ቀይሮ፤
“ወይ ገራምነቴ ፥ ወይ አለማወቄ
ጋሼ ዶስን ትቼ ፥ ጀግና መጠበቄ
በነትሩማን ቤት
የገድል ሰገነት
የጉድ ድምፅ ያሰማል ፥ እንደዴዝመን አይነት”
ሳይል ይቀራል ትላላችሁ?..
Monday, 16 September 2024 00:00
እነፈሪ ጦሱ ... ከሩቅ ይመለሱ! (Help me gets one more)
Written by በሲራክ ወንድሙ
Published in
ህብረተሰብ