Saturday, 14 September 2024 20:00

ልቦለድ መሳዩ ድንገቴ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ልቦለድ መሳዩ ድንገቴ

በ1972 አሥመራ ከተማ በቁም እስረኝነት ዘመኔ ካጋጠሙኝና ፈፅሞ ከማይረሱኝ ኹነቶች መካከል በአንዱ ቀን ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ።

ኒያላ ሆቴል አሥመራ ከሚገኙት ታላላቅ ሆቴሎች በቀዳሚነት የሚጠራ ትልቅ ሆቴል ነው። ያን ቀን እዚያ አካባቢ ለምን እንደሔድኩ ትዝ አይለኝም። ብቻ ከእሱ ፊት ለፊት ከሚገኘውና “ባር ዕምባባ” እየተባለ ከሚጠራው ቡና ቤት ጎራ ብዬ ጥግ ላይ ተቀምጬ መሎቲ ቢራ አዘዝኩ። ቢራዬ እስኪመጣም አካባቢዬን ስቃኝ፤ ከእኔ አንድ ጠረጴዛ አልፎ አምስት ሰዎች ከበው እየተሳሳቁ ያወራሉ። የሚያወሩት በአማርኛ ነው።

ጦር ሠፈር አካባቢ፣ ቃኘው ስቴሽን ውስጥ፣ ኮምፕሽታቶ ካሉት እነ ባር ጎንደር አካባቢ ወይም ክበቦች አካባቢ ካልሆነ እንደ “ባር ዕምባባ” ዓይነት ቡና ቤቶች ውስጥ የሚበዛው ትግርኛ ተናጋሪ እንጅ እንዲህ ዓይነት በአማርኛ ተናጋሪዎች የደመቀ ቤት ብዙ ጊዜ አይገጥምም። እና ብቻዬን ብገባም በቅርቤ የእነሱን ሞቅ ያለ የአማርኛ ጨዋታ በመስማቴ የብቸኝነት ስሜቴ ጥሎኝ ሲሸሽ ተሰማኝ።

ቢራዬም ቀርቦልኝ እየተጎነጬሁ አልፎ አልፎ ጆሮዬን ጣል እያደረግኩ ሳዳምጣቸው፤ ከወሬያቸውም፣ ከሁኔታቸውም ወታደሮች መሆናቸውን ተረዳሁ። በዕድሜም ትንሽ በሰል ያሉ ናቸው። ሲኒየር ወታደሮች ወይም መኮንኖች ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ጠርጥሬአለሁ። የመጀመሪያ ቢራዬን አጣጥሜ ሁለተኛ ቢራዬን ለማዘዝ ብንጠራራም አስተናጋጇ አላይህ ስትለኝ ድምጼን ጎላ አድርጌ፤ “ይቅርታ የኔ እመቤት!” ብዬ ሳጨበጭብ፤ “አንድ! ሁለት! ሶስት!” የተባለ ይመስል የወታደሮቹ ዐይኖች በሙሉ ዞረው እኔ ላይ ተተከሉ። ለአፍታ “በማጨብጨቤ አጥፍቼ ይሆን እንዴ?” የሚል መደናገጥ ቢሰማኝም፤ አስተናጋጇ እየፈገገችና ወደእኔ እየነጠረች ስትመጣ በምልክትም በንግግርም “ጨምሪልኝ!” አልኳት። ልጅቷ ቢራዬን ልታመጣልኝ ስትሄድ ከሰዎቹ አንዱ፤

“የኔ ወንድም... ና እኛ ጋ ተጫወት፤ ለምን ብቻህን አለኝ” ፈገግ እያለ።

ሲፈ’ግ በጥርሱ በስተግራ በኩል የወርቅ ጥርሱ ብልጭ አለች። እሱን ተከትሎ ሌሎችም፤

“ውነቱን ነው ና እኛ ጋ ና!” በሚል ወዳጃዊ ግብዣቸው አጣደፉኝ።

ግብዣቸውን እምቢ የምልበት ምንም ምክንያት የለኝምና፤ ልጅቷ ቢራዬን ከማምጣቷ በፊት ወንበር ተስቦልኝ፤

“ተስፋዬ እባላለሁ” እያልኩ ሁሉንም ጨብጬ መጀመሪያ ከጋበዘኝ ባለወርቅ ጥርሱ ሰውዬ አጠገብ ተቀመጥኩ። ስሙ አሰፋ ነው።

ቢራዬ መጥቶልኝ “ለእንግዳችን ክብር!” ተብሎ ጠርሙሳችንን አጋጭተን፣ የመጀመሪያ ትንፋሼን ተጎንጭቼ፣ ጠርሙሱን ቁጭ ሳደርግ፤ ከአጠገቡ የተቀመጥኩት ባለጥርሰ ወርቁ ሰው፤

“የመሐል አገር ሰው ነህ አይደል?” አለኝ፤ አሁንም እየፈገገና የወርቅ ጥርሱን ብልጭ እያደረገ፤

“አዎ!”

“መሐል አገር የት?”

“ወሎ!”

“እ...ወ...ወሎ? ወሎ የት?!” አጣደፈኝ፤

“እ... ኮምቦልቻ ነው ተወልጄ ያደግኹት!”

“እናትህም አባትህም እዚያው ኮምቦልቻ?” ሲል ከእኔ በስተቀኝ የተቀመጠው፤

“እንዴ አሰፋ! ...ኧረ ትንፋሽ ስጠው ይጠጣበት... አጣደፍኸው እኮ! ያንተ ነገር ወሎዬ ነኝ ካሉህ ማጀታቸው አይደለም አንጀታቸው ሳትገባ አትወጣ... የታወቀ ነው” ሲለው ሌሎቹም በሳቅ አጀቡት። እሱም እየሳቀ፤

“እሺ ጠጣ! ይቅርታ! ...እውነትም አጣደፍኩህ... ተስፋዬ ነው ያልከኝ አይደል ስምህን?” አለኝ።

“አዎ! ልክ ነህ!” አልኩት።

ቢራዬን አንስቶ አቀበለኝ።

ሰዎቹ በጣም ደስ ይላሉ። አሥመራ ወታደሮች ሰብሰብ ብለው ሲበሉም ሆነ ሲጠጡ ከደረሳችሁ “በሞቴ አፈር ስሆን” ተብሎ በግብዣ መወጠር የተለመደ ነው። ከአቅም በላይ ካልሆነባችሁ በስተቀር ግብዣቸውን የማትቀበሉበት አንዳች አቅም አታገኙም። ወታደር የምወደው በዚህ በዚህ ጭምር ሳይሆን ይቀራል? እና ያው አሰፋ ያልኳችሁ ጥርሰ ወርቁ ለአፉ ያህል “እሺ ይቅርታ” ቢልም ዐይኑ በፍጹም ከእኔ ላይ አልተነሳም። ቢራዬን አንስቼ ስጠጣም፣ ብርጭቆውን ሳስቀምጥም ትኩር ብሎ በዐይኑ ያጅበኛል። መሐል ላይ ያለው አንደኛው ጓደኛቸው፤

“አሰፋ! ኧረ ዐይንህን ንቀል የልጁ ቀለም ገፈፈ እኮ” ሲል እኔን ጨምሮ ሁላችንም በሳቅ አጀብነው። እሱም አብሮን ሲስቅ ቆየና፤

“ቆይ... በውነት ግን እናትህም አባትህም እዚያው ኮምቦልቻ ነው ትውልዳቸው?” አለኝ፤

“አይ! አባቴ የሸዋ ሰው ነው” አልኩት።

እውነት ለመናገር ዝርዝር ጥያቄው ብዙም አላስደሰተኝም። በውስጤ ምን ፈልጎ ነው? የምትል ሳሳ ያለች ንጭንጭ አቆጥቁጣለች።

“እናትህስ?” አለኝ ቀጥሎ፤

“እናቴ... እ... በእናቷ ወገን ተሁለደሬ ዋሄሎ ናት” ስል፤

“ዋሄሎ!” ብሎ እንደመደንግጥ አለና ተቁነጠነጠ “...እሺ ...ሀይቅ ...በአባቷስ” አለኝ?

“በአባቷ በኩል ኩታበር ናት!”

“ኩታበር!” ከመቀመጫው ተስፈንጥሮ ብድግ ሲል እንደመደንገጥ ብዬ፤

“እንዴ ሰውዬው ምን ነካው? ያመዋል እንዴ?” አልኩ በሆዴ።

“ኩታበር የማን ልጅ ናት?” አለኝ ፋታ ሳይሰጥ።

ግራ በመጋባት ለአፍታ ትኩር ብዬ አየሁት፤ ቁመቱ ወደ እጥረቱ የሚያደላ መካከለኛ ነው። የውትድርና ሕይወቱ አጠይሞት እንጅ መልኩ ብስል ቀይ የሚባል ዓይነት ነው። ከቅጥነቱ የተነሳ ጉንጮቹ ጎድጉደዋል። ዐይኖቹ ብርሃን እንዳረፈበት ውሀ የሚያብረቀርቁና ትንንሾች ቢሆኑም፤ ከእኔ የሆነ ነገር መስማት መፈለጉ በፈጠረበት ጉጉት ከጉድጓዳቸው ወጥተው ሊዘረገፉ ደርሰዋል። ደግሜ በልቤ “በዕውነት ሰውዬው ምን ፈልጎ ነው? ይሄን ያህል ጠልቆ ዘር ማንዘሬን የሚጠይቀኝ” እያልኩ ነግሬው ልገላገል በሚል፤

“የአሊ አማኑ ልጅ ናት!” ስል ጭንቅላቱን ይዞ ብድግ በማለት፤  

“አውቄዋለሁ! ሥጋዬ ነግሮኛል! ወ ን ድ ሜ” እያለ እየጮኸ በላዬ ላይ ተከመረብኝ።

በዚያ ሰዓት በእኔ ቦታ አያኑራችሁ። እንኳን እኔ ጓደኞቹ ሁሉ ግራ ተጋብተዋል። እንደምንም  ከኔ ላይ ሊያላቅቁት እየሞከሩ፤

“እስቲ ቆይ አሰፋ ተረጋጋ፣ ልጁንም እኮ ግራ አጋባኸው፣ ምንድነው የሆንከው?” ሲሉት፤

“አሁን ይሄንን ማን ያምናል?! እኔ ገና ሳየው እኮ ነው ያወቅኩት ...ልቤ ነግሮኛል ...ልክ አይዬን ራሱን እኮ ነው የሚመስለው” ሲል፤

“እ!” ብዬ እኔም ብድግ አልኩና፤

“አይዬን? ማነው አይዬ” አልኩት፤

“አሊ አማኑ ጎበዜ!” አለኝ።

አያቴን ቤተሰቡ ሁሉ አይዬ ነው የሚለው። እኛም እናታችን በምትጠራበት “አይዬ” ነው የምንለው። ሳላስበው ዕንባዬ ድንገት ተዘረገፈ። እና እንደምንም፤

“እና አንተ ማነህ?” አልኩት፤

“ይመር ፈለቀ!”

“ይመር ፈለቀ ...አሰፋ ነኝ አላልከኝም እንዴ?” አልኩት ኮስተር እንደማለት ብዬ፤

“እሱ ሌላ ታሪክ ነው! ወታደር ቤት ስገባ ነው የቀየርኩት”

“እና አንተ የየሺ ፈለቀ ወንድም ...የፈለቀ አማኑ ልጅ...!” ብዬ ሳልጨርስ በልቅሶ ተቃቅፈን ቤቱን ትኩስ መርዶ የተረዳበት


 ቦታ አስመሰልነው። ከዚህም ከዚያም ሰዎች ተሰበሰቡ። ጉድ ተባለ። የሠራዊቱ አባላት እንኳን እንዲህ ያለ ነገር አግኝተው እንዲያውም እንዲያው ናቸውና “ወንድማማቾች ተገናኙ” ተብሎ ...የደስ ደሱን ከግራ ከቀኝ መሎቲውን በሣጥን በሣጥን ያወርዱት ጀምር፣ ታላቅ ፌሽታም ሆነ።

አሰፋ መሐል ላይ ከደስታው መለስ ሲል፤



“እስቲ ተመልከቱት አንመሳሰልም? ቁርጥ አይዬን አሊ አማኑን እኮ ነው” እያለ ጓደኞቹ የማያውቁትን አሊ አማኑን መምሰሌን ያረጋግጡለት ዘንድ አገጬን ከግራ ቀኝ እያገላበጠ ያሳያቸው ገባ። እውነቱን ነው፤ እሱም ቁመቱ ከማጠሩ በስተቀር የፊት ገጽታው ቁርጥ አያቴን አሊ አማኑን ነው የሚመስለው። ልብ ብሎ ላየንም ስጋ ዘመድ መሆናችን ያስታውቃል።

ከእናቴ ጋር የወንድማማች ልጆች ናቸው፤ እውነተኛ ስሙ ይመር ፈለቀ የሚባልና የጠፋው የእናቴ አጎት የፈለቀ አማኑ ልጅ ሆኖ ተገኘ። ለካስ የአገራችን የወሎ ሰው “የአላህን መኖር እንዴት ታውቃለህ ሲሉት፤ አላሰብኩት ቦታ ሲያውለኝ” አለ የተባለው እንዲህ ያለው ገጥሞት ኖሯልና።

እናም የቁም የፖለቲካ እስረኛ በሆንኩበት ዘመን አሥመራ መሐል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥጋ ዘመድ የሚባል ነገርን በእንዲህ ዓይነት ልቦለድ በሚመስልና በማይታመን አጋጣሚ አገኘሁ። በዚያው ቀንም “ቤተሰብህን ሳታይማ አታድርም” ብሎ ቃኘው ስቴሽን ታንከኛ ሻለቃ ባለጓዝ ሰፈር ይዞኝ ሄደ። ከባለቤቱና ከሁለት ልጆቹም ጋር ተዋውቄ ባላሰብኩት ደስታ ተጥለቀለቅኩ። ባንድ ቀንም “አጎቴ!” በመባል መጠራት ጀመርኩ። በዚህ ምክንያትም እኔ ከቤተሰቦቼ ጋር በየጊዜው በደብዳቤም በስልክም እገናኝ ስለነበር ሁኔታውን ዘርዝሬ ለእናቴ በኤሮግራም ላኩላት። ሞቷል ብሎ ተስፋ የቆረጠው ቤተሰብ ሁሉ ተስፋም አንሠራራ።
 
አሰፋና (ይመር ፈለቀ) ቤተሰቡ ኤርትራ በሻዕቢያ እጅ ስትወድቅ ከእልቂት ተርፈው አዲስ አበባ ከገቡት የቀድሞ ሠራዊት አባላትና ቤተሰቦች መካከል ነበሩ። ባለቤቱ ልጆቿን ይዛ እዚህ አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ ዘመዶቿ ጋር ስትቀር፤ እሱም ወሎ “ሐይቅ” ሔዶ ከእህቱ የሺ ፈለቀና ከዘመዶቻችን መሐል ኑሮውን ቀጠሎ ከጥቂት አመታት በፊት አለፈ።

(ሁለገቡ የኪነጥበብ ባለሙያ ተስፋዬ ማሞ ሰሞኑን ለንባብ ካበቃው “ከማዕበል ማዶ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 160 times