Tuesday, 17 September 2024 11:37

የዘሪቱ ከበደ “አይደለሁም ስም”

Written by  መክብብ ፍቃዱ
Rate this item
(0 votes)

“ንጋት” የተሰኘ ወጣትና አንጋፋ ድምጻዊያንን ሥራ የያዘ አልበም የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ለአድማጭ ጆሮ ደርሷል። ጥሩ ሥራዎችን፣ የናፈቁንን ድምጾች ያገኘንበት አልበም ነው።
በዚህ አልበም ጅማሮ፣ በተራ ቁጥር አንድ ላይ የሚገኘውና ልማዳዊውን የሕይወት ጉዞ የሚገዳደር፣ በጥልቅ የሀሳብ ተብሰልስሎት የታሸ ግሩም ሥራ ተካቷል። እሱም የዘሪቱ ከበደ “አይደለሁም ሥም” የተሰኘው ዜማ ነው።
ዘሪቱ ከበደ “ዘሪቱ” ከተሰኘው ከ1998 አልበሟ አንስቶ በየጊዜው በምትሰጠን ነጠላ ዜማዎቿ መፎረሽ ሳይነካት “አይደለሁም ሥም” ጋር ደርሳለች። በዚህ ዘፈን ውስጥ በእስካሁኑ ጉዞዋ ባገኘችው ዝናና ገናና ሥም መሰልቸቷን፣ሥም ሆኖ መኖር ሰው ከመሆን ጸጋ አጉድሏት ነፍሷን “ስላቀጨጨባት”፣ ከሥም እስር ተላቆ ሰው ሆኖ የመኖር ፍላጎትና ውሳኔዋን ታስደምጠናለች።
እኛ በሥራዎቿ የሰጠናትን ክብርና ከፍታ በሚቃረን ሀሳብ ታሽቶ የቀረበ ቢሆንም እንኳ፣ በዘፈኑ ውስጥ የነገረችን እውነት ከእነ ጭራሽኑ ሌላ የተሻለ ማማ ላይ እንድንሰቅላትና ዛሬም “ዘሪቱ” እንድንል የሚያስገድደን ሥራ ሆኖ እናገኘዋለን።
በዚህ እሷን ማክበራችን ልክ ግን እንደ ስጋቷ ሰው መሆኗን የመካድ ደረጃ ላይ ደርሰን “ብራንድ” ልናደርጋት ከመድፈር ይልቅ ያለችንን ሰውነቷን በተሻለ እምነት ተቀብለናት እንድናከብራት የሚያደርገን ነው።
የዘፈኑ ግጥምና ዜማ ደራሲ ራሷ ዘሪቱ ስትሆን፤ በሮክ/Rock ሙዚቃዊ ዘውግ/Genre ደምቆ የተሰራውን ሙዚቃ ያቀናበረው ደግሞ ወጣቱ አቀናባሪ ሚካኤል ሐይሉ ነው። ሙዚቃው (Introው) ሮክነቱን እንደያዘ ሳሳ ባለ የሊድ ጊታር ድምጽ ይነሳና በደመቀ የድራምና የቤዝ ጊታር ድምጽ አጀብ ወደ ዘፈኑ ሀሳብ ይመራናል። አዲስ ሀሳብና እይታን የታደለችው ዘፋኝ፤ “ኣ!?” አስብሎ በጥያቄ አፍ ሊያስከፍት በሚችል ግጥም ዜማዋን ትጀምራለች...
ዘሪቱ ከበደ ብራንድ
የተካበው እንዳይናድ
የተሰጣትን ከፍ ያለ የሥም ማንነት (ብራንድ) ተከትሎ የሚመጣው አደጋ ያሰጋት በሚመስል ድምጸት “የተካበው እንዳይናድ” ስትል በወጉ ባደመጣትም ባላዳመጣትም ዘንድ ተደጋግሞ የሚጠራውን ሥሟን በምጸት ታነሳለች።
“ዘሪቱ ከበደ ብራንድ” ስትል በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ አድርጋ/ሌሎች የሸለሟት ማንነት እንደሆነ ለማመልከት/ እንደጠራች የሚነግረን “የተካበው እንዳይናድ” ያለችው የላይኛው ስንኝ ማሰርያ ብቻ ሳይሆን፤ ቀጥሎ የምታወርዳቸው እሮሮ መሳይ አቤቱታና መሰልቸት የቃኛቸው ግጥሞች ናቸው።
እነዚህን ሁለት መስመሮች ተከትለው የሚመጡት ስንኞች ደግሞ ቁጭት የሚደመጥባቸው የእሮሮዋ መጀመርያ ናቸው።
“ለተቀረጸው ጣኦቴ
ነጻነቴን መሰዋቴ
ያስገደደኝ ሳይኖር አንድም
ያን አለብስም እዛ አልሄድም
በገና ለገና ታየሁ
ተደብቄ ተሰቃየሁ”
በሥሟ በተቀረጸው ጣኦት ተኩራርታና አጓጉል ትምክህት ውስጥ ገብታ፤በዝናና ሥም ካብ መነሻ ለራሷ ራሷን ሆና መኖር ተነፍጋ፣ባትገደድም በእውቅና ስውር ግፊት ከምትለብሰው እስከመሄጃዋ ለመጨነቅ መድረሷን፣በእውቅና እስረኝነት መንገላታት የተሰዋ ነጻነቷን፣ “የገና ለገና ታየሁ” የአደባባይ ፍርሃትና በውስጡ ያለውን ስቃይ በግልጽ ትነግረናለች።
ይሄን አድምጠን ወደ ቀጣዮቹ ስንኞች ከመሄዳችን በፊት ቆም ብለን አንዲት በሰላሳዎቹ የዕድሜ እርከን ላይ ያለች ሴት ዝና አታክቷት “ነጻነቴን” እያለች መጮኋ አስገርሞን፣ “ይሄን ያህል ለምን?” እያልን ስንጠይቅ፣ በቀጣዮቹ መስመሮች የተገለጠላትን እውነት ነግራ ጥያቄያችንን ታስቆመናለች።
“ልክ በሚመስል መሰልጠን
ራስን አስሮ መታፈን
በተቀናበረ ገጽታ
ውድ ለማድረግ ራስን”
እነዚህ አራት መስመሮች ውስጥ የምንሰማው ሐይለ ቃል፣ “ሁሉም የከንቱ ከንቱ!” የሚል መሰልቸት ብቻ ሳይሆን፣ ራስን ነፃ አድርጎ ያለመኖር አልባሌ ስልጣኔ፣ ከልክነት ያፈገፈገና የተጣላ መሆኑንም ጭምር ነው።
ሌሊሳ ግርማ በተባለው ጸሐፊ ሰውኛ ማንነታችን ውስጥ እንዳለ የተነገረን “ለሰዎች እይታ ሲባል የፊትን ገጽታ አስተካክሎ የማቅረብን ልማድ”፣ ዘፋኟ “የተቀናበረና ራስን ውድ ለማድረግ የሚከወን ከባድ የዝነኞች ዓለም ትግል” መሆኑን ትናገራለች።
ከዚህም አድካሚና “ትርጉም የለሽ ሕይወት” ለመላቀቅ መቁረጧን አሁንም በተቀየረ የዜማ አካሄድ እየነገረችን፣ ከዘፈኑም ዋና ጭብጥ ጋ ታደርሰናለች።
“ለተመልካች ልዩ መስዬ እንድታይ
ለጭብጨባ ከእንግዲህ መኖር በቃኝ
በሰራሁ(ኋ)ት መወከል አልፈልግም
እኔ ልኑር ሰውነኝ አይደለሁም ሥም”
“ለጭብጨባ ከእንግዲህ መኖር በቃኝ” ማለትን እውነተኞቹ የሀገራችን ከያንያን ሊኖሩት የሚሹት ሀቅ እንደሆነ የሚገባን፣ “ከጭብጨባ ማዶ ነኝ” ያለውን ታላቁን ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬን ስናስታውስ ነው። አይደለም በላብና በወዛችን ደክመን ባገኘነው ቀርቶ ባልደከምንበት፣ባለፋንበት ሙገሳን የምንሻ እልፎች በምንኖርበት ዓለም፣ “በሰራሁ(ኋ)ት መወከል አልፈልግም” የማለት የትህትና ጥግ ካልገረመን፣ “ሰውነኝ አይደለሁም ሥም” ማለቷ ሊገርመን መቻሉን እጠራጠራለሁ።

የዘፋኟ በዚህ ልክ “በሰራሁ(ኋ)ት መወከል አልፈ
ልግም” አስብሎ ከገዛ ልፋትና ጥረት ትሩፋት ያሸሻት እውነት፤ የተጋነነ? የዝነኝነት መንገድና የሥም ስጦታ፤ ሰው ሆና ከተፈጠረችበት ማንነት እያጠፋፋት መሆኑን፣ “እኔ ልኑር ሰው ነኝ አይደለሁም ሥም” ባለችበት መስመር በጉልህ ተገልጿል።
ኑዛዜዋ በዚህ ብቻ አያበቃም። በተጓዘችበት የዝና ጎዳና ባጋጠማት ሀሳቧን የመግለጽ ዕድል ላይ ሳይቀር የራስ ለራስ ትዝብቷን በማንሳት ያለ እርህራሔ ማንነቷን ትተቻለች። ትችቷም ከዛ አዋቂና በሳል ለመባል ቃላት ለጥጣ ከምታወራው የዝነኝነት ተጽእኖ ካረበበት ንግግር ተላቃ በእውነተኛ ማንነቷ ለመገለጥ መቁረጧን ከማሳየት ባለፈ፤ ከዝና ሕይወት ውጪ ያለነውንም ተርታዎቹን፣እኛን ሳይቀር ራሳችንን በነዚህ ስንኞች ውስጥ እንድንፈትሽ የሚጋብዝ ጭምር ነው።

“አዋቂ ለመምሰል በሳል
በሰው ፊት ጎልቶ ለመሳል
ይበቃል ቃላት መለጠጥ
በደረስኩበት ልገለጥ”

እነዚህን ወርቃማ መስመሮች ተከትሎ የሚመጣው የመሸጋገሪያ ግጥም መጀመርያ “ልክ በሚመስል መሰልጠን” ብሎ ከሚነሳውና ከተከታዮቹ መስመሮች ጋር የሀሳብ ተመሳስሎ ያለው ነገር ግን በአገላለጽ የሚለይ ይሆናል።
“ልክ በሚመስል መሰልጠን
ራስን ሰቅሎ ሰቀቀን
በተቀናበረ ገጽታ
ማሳደድ ከበሬታ”
በማለት የቃላትና ገለጻ ንፉግ አለመሆኗን እያሳየችን፤ ልክ መሳዩ ስልጣኔ የሚያመጣውን “ሰቀቀን” እንዲሁም አርቲፊሻል ክብር አሳዳጅነትን ትጠቁማለች።
የዘፈኑ ሀሳብ መቋጫ ሆነው የሚመጡት ሁለት መስመሮች፣ “በቃኝ” የሚል ውሳኔና የታሰረችበትን “የዝና ባርነት ሰንሰለት” በጣጥሳ መጣሏን ከላይ ከመጣችበት የዜማ አካሄድ በተለየ የምታበስርበት መስመሮች ናቸው።
“እንዳለ ያሰብኩት ክብር ስስት
መኖርን ትቻለሁ በባርነት”
የዘፈኑ ሀሳብ በስንኝ ድርደራ እዚህ ጋ ያበቃ ቢመስልም፤ ጨርሶ ግን የሚጠናቀቀው በመጣችበትና በያዘችው መንገድ ክፉኛ መታከቷን ለመግለጽ በምታሰማው ስልተ-ዜማ ባለው ጩኸት እንደሆነ እጠረጥራለሁ። የዘፈኑም ሆነ የታካች ጉዞዋ ማብቅያ በጩኸቷ ውስጥ ይገለጻል።
በመጨረሻም አንድ ነገር ብለን እናብቃ...
ዘፋኟ “የዝናና የሥም እስረኛነት ከሰውነት አርቆኛል፣ አጉድሎኛል...” ብትልም በዘፈኖቿ እንዴት እንደምታስብ በትንሹም ቢሆን የገባኝ እኔ፣ በተለመደ ሚዛናዊ ገለጻዋ ራስዋን ከፊት አስቀምጣ ወቀሰች እንጂ ዘፈኑ ከእሷ በላይ በዝነኝነት ሰክረው፣ ጭልጥ ብለው ከራሳቸው ለተጠፋፉት አንዳንድ ከያኒዎቻችን በልክ የተሰፋ ነው እላለሁ። ይኸው ነው።





Read 372 times