Tuesday, 17 September 2024 12:06

ሙሉቀን መለሠ እና የቤት እንስሳ ፍቅሩ

Written by  በዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲዎችን ክፍያ በማሻሻል፣ በድምጻዊነት፣ በግጥምና ዜማ ደራሲነትና በአቀናባሪነት/በሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት የምናውቀው፤ ሙዚቀኛ ሙሉቀን መለሠ በርካታ ሥራዎችን ሰጥቶናል። በ1961 ዓ.ም. በሰለሞን ተሰማ ተደርሶ በፖሊስ ኦርኬስትራ የተቀናበረውን ‹‹የዘላለም እንቅልፍ›› ለመጀመሪያ ጊዜ አቀንቅኖ ተወዳጅነትን አገኘ፤ አቡበከር አሽኬ ደግሞ ‹‹ያላየነው የለም››ን ጀባ አለው፤ በማስከተል ተስፋዬ አበበ ‹‹ልጅነት››፣ ‹‹እምቧይ ሎሚ መስሎ›› እና ‹‹እናቴ ስትወልደኝ››ን ደረሱለትና በፖሊስ ኦርኬስትራ ታጅቦ ለመሰማት በቃ።  
ሙሉቀን መለሠ ድራመር ነው፤ ከዳሕላክ ባንድ ጋር በመሆን ሙላቱ አስታጥቄን በቅንብር ያግዘው ነበር፤ ግጥምና ዜማ ደራሲ ነው፤ ‹‹ያይኔ ነገርማ››፣ ‹‹አካል ገላ›› እና ሌሎች ሥራዎች ላይ የግጥም ማሻሻያዎችን አድርጓል፤ ‹‹እንዴት ልቻለው›› ሙዚቃ የዜማ ድርሰቱ ነው፤ ‹‹ሰውነቷ›› አልበም ላይ በርካታ የዜማ ድርሰቶችን ሠርቷል፤ ባለቤቱ አሥራት አንለይ ደግሞ ‹‹ወተቴ ማሬ›› እና ‹‹ፀሐይ›› የተሰኙ ዘፈኖችን ደርሳለታለች።
ከሠራቸው ሥራዎች መካከል፣ በግጥምና በዜማ ረገድ ለ‹‹ሰውነቷ›› እና ‹‹ሆዴ ነው ጠላትሽ›› ልዩ ፍቅር አለው፤ በቅንብር ረገድ ደግሞ ‹‹ቼ በለው›› እና ‹‹ውቢት››ን አብልጦ ይወዳቸው ነበር። ከላይ በተዘረዘሩ ዘፈኖች ውስጥ በድርሰትና ቅንብር ረገድ የሙሉቀን አሻራ አለ። የ‹‹ቼ በለው›› ደራሲ ተስፋዬ ለማ ናቸው፤ ቅንብር ደግሞ ‹‹ኢኩዌተርስ ባንድ›› ነው፣ 1967 ዓ.ም.።
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ምናልባትም እንደ ሙሉቀን መለሠ የተለያዩ የቤት እንስሳዎችን በሙዚቃው የጠቀሰ/ የተጠቀመ ያለ አይመስለኝም። ሙሊዬ በተለያዩ ሙዚቃዎቹ ብሶቱን፣ ማጣቱን፣ ጣመኑን፣ ፍዳውንና ሕመሙን ለቤት እንሰሶች ያዋያል፤ መንደርደሪያው የከብት ሥም ነው፤ መማጸኛውም ላም፤ በተለይ ከከብት ጋር ያለው ቁርኝት የሚገርም ነው!
ኑማ አንዳንድ ምሳሌዎችን እያነሳን እንቆይ!
1ኛ. ‹‹እምቧ በይ ላሚቱ››
በዚህ ዘፈን ሙሉቀን፣ ‹‹እምቧ በይ ላሚቱ፤
                    ኮርማ ወላዲቱ፤….››
በማለት ይንደረደራል፤ እዚህ ላይ ላሚቱን ያዋያታል፤ ችግሩን ይዘከዝክላታል፤ ናፍቆቱን ይነግራታል፤ ምናልባትም ለሰው መንገር ሰልችቶት ይሆናል - ስጋቱ ዘባባች አይታጣምና ነው እንግዲህ!
‹‹እምቧ በይ ላሚቱ››ን ኃይሉ መርጊያ ከዋሊያስ ባንድ ጋር በመሣሪያ (የሙዚቃ) ብቻ ያቀናበረው ወደ ተለየ ዓለም የሚወስድ ኃይል አለውማ!
2ኛ. ‹‹እምቧ ዘቢደር››
‹‹እምቧ ዘቢደር፣
ላም አለሽ ወይ ጊደር፤››….
እዚህ ላይ ‹‹እምቧ›› ማጀቢያ ነው፤ በሙዚቃውም ከ20-30 ጊዜ ድረስ ተጠርቷል፤ በተጨማሪ፣ ላም ያላትን/ጊደር ያላትን ሴት እየቋመጠ ነው፤ ጊደር ውብ ሴት ላም ነች፤ ነገ ልጅ የምትሰጥ፤ የምትታለብ፤ ቀጥሎ፡-
‹‹እምቧ ስል አድራለሁ - ግርግዳ ስቧጭር፤
ለዓይነ ከብላላ ልጅ፣ ለቁመተ አጭር፤….›› ይለናል፤
ለከጀላት ልጅ እንደ ላሚቱ ይሠራራዋል፤ በላማዊ ባሕሪይ እንደሚትከነከን ይናዘዛል፤ ሲቁነጠነጥና ሲፋጭር እንደሚያድር ያወሳናል! ዘለስ ይልና፡-
‹‹በቅሎዬ ስገሪ፣ እንግባ አገራችን፤
የመጣንበት - ሞልቷል ጉዳያችን፤››
የሚላት ብሂል አለቺው፤ ያሳካው ነገር አለ ማለት ነው፤ የልቡ መሻት ደርሷል፤ የቋመጣትን እንስት አወቃት ይሆን?!
3ኛ. ‹‹አካል ገላ››
በጣም ከምወዳቸው የሕዝብ ለዛ ካላቸው የሙሊዬ ዘፈኖች አንዱ ነው፤ በግጥም ረገድ ዓለምፀሐይ ወዳጆ እና አቶ ሙላቱ ደበበ ሲሳተፉ፣ ዜማው የዮናስ ሙላቱ ደበበ ነው፤ ዮናስ የአባቱን ግጥም ሰርቆ (ልጅ ሳለ፤ ከፍቅር የተነሳ) ለሙሊዬ እንደሰጠው ይነገራል፤ ኩኩ ሰብስቤም እንዲያ ታደርግ ነበር አሉ፡፡
‹‹አካል ገላ›› ሙሊዬ ከረቀቀባቸው ሥራዎች አንዱ ነው፤ በዲያሎግ መልክ ነው ዘፈኑ የሚቀርበው፤ የከጀላትን ሴት ያናዝዛታል፡-
‹‹አካል ገላ፣ አካል ገላ፣
ምን አለሽ ያ ቆለኛ?
አካል ገላ፣ አካል ገላ፣
ምን አለሽ ያ ደገኛ?...››
እያለ ይጠይቃታል፤ በጣም ማራኪ እና ያልተለመደ የአዘፋፈን እና የአተራረክ ስልት ነው፤ ሄደት ይልና፡-
‹‹ዝንጀሮ እንኳን ባቅሙ፣ ያውቃታል
ወዳጁን፤
የፈለፈለውን - ይሰጣታል የእጁን›› ይላል፤››
አየህ እዚህ ላይ እንኳን እኔና አንቺ ሰዎቹ ቀርተን ዝንጀሮም ይዘያየራልና ዘይሪኝ - ጀባታሽ አይለየኝ - ኧረ አንድ በዪኝ እቱ ነው እያላት ያለው፤ የድሮ ጅንጀና ግን ደስ ሲል! በዚህ ስንኝ ውስጥ የተነፈገው ነገር አለ፤ ማር ሊልስ ቋምጧል፤ ልጅት ግን እንደ ቅራሪ ለማንም አልቀዳም ብላዋለችና ልቧን ሊያርድ የዝንጀሮን ሆደ ባሻነት ይጠቅስላታል!
አልታከተም፡-
‹‹ሠጋር በቅሎንማ፣ መች አጣሁ ከቤቴ፤
ሳይሽ ፈረስ፣ ፈረስ - ይላል አካላቴ፤››
ብሏት እርፍ! ሊጋልባት ያምረዋል! ደግሞ እኮ ቤቱ ሠጋር በቅሎ አስቀምጧል! ኧረ ሙሊዬ ግን!!
4ኛ. ‹‹ናኑ ናዬ››
‹‹ወይ ላሚቱ አልሞተች፣ ወይ ጥጃው
አልጠባትም፤
ምን የቆረጠው ነው፣ እንዲህ ያለባት፤››
ሲል ገምዳላ ፈራጅን ይወቅሳል፤ ሙሊዬ ብቻ ብዙ ፍካሬዎች አሉት በቤት እንስሳ ዙሪያ፤ ዐውዱን ማዕከል በማድረግ በቆንጆ፣ ቆንጆ ስንኞች እየታገዘ ያሰግራል፤ ዘይቤአዊነትን ከተካኑ ሙዚቀኞች አንዱ ለእኔ ሙሉቀን መለሠ ነው!
‹‹ገብስ እሸት ፈትገን፣ ቁዪልን ብንላት፤
ይህቺ የባላገር ልጅ፣ የምታምሰው ናት፤›› - ናኑ ናዬ፤
ተጋበዙኝማ! አመሰግናለሁ!!
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።

Read 169 times