Tuesday, 17 September 2024 12:08

ጉባኤው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

መሳፍንት እየተፈራቁ በነገሱበት ዘመን ንጉሥ አሊጋዝም የድርሻቸውን ገዙ፡፡ በዘመናቸው ብዙ እኩይና ሰናይ ክስተቶች ታዩ፡፡ እኔ ትሁት ጸሐፌ ትዕዛዛቸው ከሰማሁትና ካየሁት መካከል የመረጥኩትን ተረክሁ፡፡
በዚያን ዘመን ሀገራችን በድርቅ ተመታች፡፡
የሰማይ ግት ነጠፈ፡፡
መሬት ፍሬ ነፈገች፡፡
ሕይወት ያለፍሬ ያለቅጠል ቆመች፡፡
አልጋዎች ቃሬዛ ሆኑ፡፡
ግርማዊ ጃንሆይም መፍትሄ ፍለጋ ሊቃውንትን በአዋጅ ጠርተው በየእለቱ ጉባኤ ያደርጉ ጀመር፡፡ በዘመኑም ሰዎችን የሚያሰባስባቸው ጉባኤና ቀብር ሆነ፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን የተመረጡ ሊቃውንት የንጉሡን አዳራሽ ሞልተውት ነበር፡፡
ግርማዊ ጃንሆይ የጸሐይ ሽራፊ በመሰለ ዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ተደምጦ በማይጠገብ ድምጻቸው ይናገሩ ጀመር፡፡
“ወገኖቼ ሊቃውንት ጠቢባን… እንደምታዩት በየጊዜው አስፈሪ መአት እየተላከብን ነው፡፡ የዚያ ምክንያት ምንድን ነው? ራብን እንዳይመለስ አድርገን ለማባረር በምን አኳኋን መስራት አለብን? ይሄ የህይወት የህልውና ጉዳይ ነው… እስከአሁን አስራ ሁለት ጊዜ ተሰብስበናል --አስራ ሁለት ጊዜ ሊቃውንት… ዛሬ ግን ጉዳዩ እልባት ማግኘት አለበት፡፡ ይህን ጥያቄ ሳንመልስ ከዚህ አዳራሽ ንቅንቅ ማለት አንችልም፡፡ ሊቃውንት ናችሁ…መላችሁን ወዲህ በሉ፡፡”
ጸጥታ የእያንዳንዱን አንደበት ሸበበው፡፡
“በሉዋ ሊቃውንት…የምን መለጎም ነው?” ከማለታቸው ከፊት ከተኮለኮሉት አንዱ ተነሳ፡፡ ወገቡን ቆልምሞ እጅ ነስቶ ሲያበቃ “ጃንሆይ  እኔ….” ብሎ ሊቀጥል ሲል ድምጡ በፍርሃት ደከመበት፡፡
ጃንሆይ ለማበረታታት ራሳቸውን ሲያወዛውዙለት “እህህ” ብሎ ጉሮሮውን አጽድቶ ገባበት፡፡ “እሺ እንግዲህ እኔ ነጋድራስ የትምጌታ ነው ስሜ -- የእናቴና የእናቴ ዘመዶች መሸሻ ብለው ይጠሩኛል፡፡ ወላጅ አባቴ ዋልድባ ተመግባቱ በፊት የፍጻሜ መንግስት ተክለጊዮርጊስ አማካሪ ነበር፡፡ የሱ ታናሽ ወንድም ደሞ…”
የሊቃውንቱ ዝምታ ወደ ጉርምርምታ ተለወጠ…
“እንግዲህ ስለራሴ ይህንን ታልሁ … ወደ ዋናው ሀሳቤ እገባለሁ፡፡ እንግዲህ ከዚህ ቀደም በርስዎና በአባቶቻችን ፈቃድ ለንግድ በተለያዩ አገሮች ተመላልሻለሁ፡፡ ለመሆኑ የት የት ሄደሃል የሚለኝ ካለ የሄድኩባቸው ሀገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ሰማይ የሚታከኩ፤ ዓለምን የማረኩ ቢራሚዶች ባሉባት ግብፅ ነበርኩ፡፡ ተዚያም አስከትዬ የነውጠኛው እስክንድር አገር በሆነችው  መቄዶንያ ከራርሜ ወደ ፋርስ ተሻገርኩኝ፡፡ ተፋርስ ወደ ኑቢያ ተኑቢያም …”
“ማነህ ነጋድራስ፡-” አሉ ጃንሆይ ትዕግስቸው አልቆ “ነጋድራስ ነው ያልከኝ? አዎ ነጋድራስ… እኛ እዚህ ወርቅ ጊዜያችንን ቆጥበን የምንሰበሰበው ያንተን የዙረት ታሪክ ለማወቅ አይደለም፡፡ እኛን ያስጨነቀን ጉዳይ ራብ ነው፡፡ በራብ ጉዳይ ላይ መላ ካለህ መላህን ወዲህ በል… አለበለዚያ ለአሁኑ ይቅር ብለንሃል፡፡ ወደ ጥግህ ተመለስ--”
“ጃ… ጃንሆይ…” አለ ነጋድራስ የወረዛ ግንባሩን ባይበሉባው እየፈተገ “እንግዲህ መንገዴን ስቼ ንግግሬን እንደባልቴት አስረዝሜ ተሆነ በእውነቱ ግሳጼ የሚገባኝ ግም ሰው ነኝ፡፡ በውነቱ እኒያን ትልልቅ አገሮች መጥቀሴ ለከንቱ ውዳሴ ብዬ አልነበረም፡፡ ዘላንነት እጣ ፈንታ እንጅ ክብር እንዳልሆነ አውቃለሁ… ይህን ስል ጉዳዩን ረስቼ ሳይሆን በእኝህ አገሮች በነበርኩበት ጊዜ የቀሰምኩትን ጥበብ ለማካፈል አስቤ ነው…”
በጃንሆይ ፊት ላይ ወገግታ ታዬ፡፡
“እንዲያ አትለኝም?” አሉ በደስታ በተቃኘ ድምጽ “እንዲህ ያለውን ሊቅ ነው በመብራት ስንፈልግ የቆየነው፤ በል እስቲ የምታውቀውን ንገረን…”
“ጃንሆይ ሺ ዓመት ይንገሱ…” እንደገና ታጥፎ እጅ ነሳ፡፡ “እንግዲህ አስቀድሜ ወንዞቻችን ስለምን  አገር አቋርጠው እንደሚነጉዱ እገልጣለሁ፡፡ ለጥቄ እንዴት አድርገን አናሳ ወንዞችን መገደብ እንደምንችል አብራራለሁ፡፡ ያንን አንድ ባንድ ካስረዳሁ በኋላ መስኖ በምን አኳኃን እንደምናበጅና---”
ሌላ ጉርጉምታ ከሊቃውንቱ መጣ፡፡
“ምን ሆናችኋል?” አሉ ጃንሆይ “መሪጌታ ስነ እየሱስ---ምንድርን ነው ነገሩ? ቅር ያለህ ትመስላለህ?”
በገፈጅ የሚያክል አዳፋ ጥምጣም አናታቸው ላይ የደፉት መሪጌታ ስነ እየሱስ ብድግ ብለው እጅ ነሱ፡፡ ከዚያም ጣዝማ ያበጀችው ሽንቁር በመሰለው አንድ ዓይናቸው ጃንሆይን ሽቅብ እየተመለከቱ፤ እኔ እንኳን ቅር ያለኝ የነጋድራስ ነኝ ባዩ የቋንቋ አጠቃቀም ነው” ከማለታቸው
“እንዴት?” ጃንሆይ ተቀበሏቸው፡፡
“እንዴት ማለት ጥሩ ነው፤ ሊቁ አባታችን ጃንሆይ” አሉ መሪጌታ “ ወንድሜ ነጋድራስ አውቆ በድፍረት ይሁን ሳያውቅ በስህተት እንጃ የታፈረውን የተከበረውን ቋንቋችንን ሲዘነጣጥለው ባይ እንባዬ መጣ፣ ሆድ ባሰኝ፣ ቁጭት ልቤን መዘመዘው---አላስችል አለኝ--” እንደማልቀስ ቃጣቸው፡፡
“በመዠመሪያ ጅረት  ማለት ሲገባው አናሳ ወንዝ  አለን፡፡ ዝም አልነው፡፡ እሱ ግን ይህንን ሳያርም ሌላ ገደፈ፡፡ ቀጥዬ ማለት ሲገባው ለጥቄ ብሎ ተናረ፡፡ በዚህ መች አብቅቶ መስኖ ለመጥለፍ እል ብሎ መስኖ ማበጀት ብሎ አረፈ፡፡ እንግዲህ ይህንን ዝም ብሎ ማለፍ እንደምን ይቻላል?”
ግራ ቀኙን በዓይናቸው ገመገሙት፡፡
ዝምታውን “አበጀህ” በሚል ተረጎሙት፡፡
 “ጃንሆይ… አሳምረው እንደሚያውቁት የህዝብ አንድነት መሰረት ቋንቋ ነው፡፡ የሰናኦር ስልጣኔ የፈራረሰችው በቋንቋ ቅይጥ ምህኛት ነው፡፡ የቋንቋ ቅየጣስ ሰዋሰውን ባልባሌ ሁኔታ ከመጠቀም የሚመጣ አይደለምን ? መቼም የቋንቋ ሊቅ ለመሆን የሰዋሰው ጥበብ መማር አለብን እያልኩኝ አይደለም፡፡ አስተዋይ አድማጭ ለሆነ ቢያንስ የጃንሆይን ንግግር ለሁለት ሰዓት ያህል ማድመጥ የተባ አንደበተኛ አያረግም?--- አያረግም ወይ ሊቃውንት?...”
 “እስቲ ይሁንልህ” በሚል ምልክት ሊቃውንት ራሳቸውን ወዘወዙ፡፡
“ስለዚህ እንደኔ እንደኔ የቋንቋ ችግር አለብን፡፡ ይሄን የቋንቋ ችግር ታልፈታን እንደ ሰብአ ባቢሎን እንደምንፈታ ጥርጥር የለውም…”
“እህ…እህ….እህ…” አሉና ጃንሆይ ራሳቸውን ናጡ፡፡
“ማነህ?…ነጋድራስ ነጋድራስ ነኝ ነው ያልከኝ… አዎ ነጋድራስ ተቀመጥ እስቲ”
(ለካ ነጋድራስ ያንን ሁሉ በትር የተቀበለው በቁሙ ነው)
“እስቲ መሪጌታም ይቀመጡ… ለነገሩ እኔም በቋንቋችን ውስጥ ያለውን ጉድለት ጉዳይ ሲከነክነኝ ነው የቆየው… መሪጌታ እንዳሉት የቋንቋ ችግር ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የቋንቋችን ችግር ከየት የመነጨ ነው? በምንስ አኳኋን ሊታረም ይችላል? ሊቃውንት ከሞሉባት ሀገር ይህን ሳንመልስ ተዚህ አዳራሽ ብንወጣ የሚያፍረው መከረኛው ህዝባችን ነው---በሉዋ ሊቃውንት መሪጌታ ተርስዎ ልጀምር መሰል?”
”ጥሩ እንግዲህ” አሉ መሪጌታ “በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ በደንብ ባውጠነጥን ብዙ በተናገርኩ ይሁን እንጅ አሁንም ቢሆን የቋንቋ ችግርን የምንፈታው እንደ ተክለ አልፋ ያሉትን የሰዋሰው መምህራን ከፍልሰት ስንታደግ ነው ባይ ነኝ…”
“ተክለ አልፋ ምን ሆነ?”
“አዬ ጃንሆይ ተሚያስተምርበት ደብር አሳደዱት’ኮ”
“ተክለ አልፋን?”
“እንዴት ያለውን ሊቅ ጃንሆይ?”
“እኮ ለምን?”
“ምን አውቃለሁ ጃንሆይ ምህኛቱማ ዝምታ ነው”
“ነው?” አሉ ጃንሆይ ነገር በገባው ቋንቋ-- “ለነገሩስ የሊቃውንትን የፍልሰት ወሬ ታንድም ሁለት ጊዜ መስማቴን  እኔም አልሸሽግም፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ስር የሰደደ መሆኑ ግን አሁን ነው የተገለጠልኝ፡፡ መቼም የጅሎች ሁሉ በኩር ታልሆን በቀር በነግ እናቆየዋለን ብዬ አላስብም፡፡ ሊቃውንታችን የሚፈልሱበት ምህኛት ምንድን ነው--? ማነው የሚያፈልሳቸው---? ነገሩን ተሥር መሰረቱ ለማድረቅ ምን ማድረግ ይገባናል---? መልሱልኝ ሊቃውንት--”
“ጃንሆይ” አሉ መሪጌታ “በኛ አገር ጠቢብ መሆን አብሪ ትል መሆን ማለት ነው፡፡ አብሪ ትል ከሌሎች ትሎች የሚለየው ገላው እንደፍም ማብራቱ ነው፡፡ ታዲያ ብላቴኖች በጨለማ ሲያበራ ሲያዩት በገዛ ብርሃኑ ተመርተው ይመጡና አንስተው ይጨፈልቁታል፡፡ ለጠላቶቹ መንገድ ከማሳየት አልፎ የገዛ ብርሃኑ ለምንም አይጠቅመውም፡፡”
“ተክለ አልፋ የተባረረው ንዋየ ቅዱሳት መዝብሮ ነው---ጃንሆይ” አለ አንድ ከግራ ጥግ ተወርውሮ የመጣ ሻካራ ድምጽ፡፡
“ምን?” ጃንሆይ ገነፈሉ፡፡
“ጃንሆይ በደካማው ሥጋዬና በጠልጣላዋ ነፍሴ እምላለሁ፡፡ ተክለ አልፋ የሳር ውስጥ እባብ ነው፡፡ የስነፍጥረትን መጽሐፍ ሸሽጎ ሊወጣ ሲል እኮ ነው ለቅም ያረግነው”
“እኮ ተክለ አልፋ!?”
 “ማን ያምናል ጃንሆይ!...”
“ተነአህያው ሞተልሽ!” አሉ ጃንሆይ ተስፋ መቁረጥ በቃኘው ድምጽ “አልቀናል በሉኛ! እንግዲህ ንዋየ ቅዱሳቱ ተዘርፈው  ከወጡ ምን ቀረን? እኛስ አለን ወይ?---ህልውናችንን’ኮ ነው የመዘበሩት---እኛስ  እንግዲህ ማን ተብለን ልንጠራ ነው? በምን በኩል  ኢትዮጵያውያን ነን  እንበል? ጎበዝ እዚህ ላይማ ዋዛ የለም..!
“ተቀመጥ መሪጌታ---በሉ ሊቃውንት ይህንን ጉዳይ መልሱልኝ፡፡ ይህንን ሳንፈታ ብንወጣ የአባቶቻችን አጽም እሾህ ሆኖ ይወጋናል…በሉ እንጅ ምሁራን”
እዚህ ላይ እኩሌቶች ሊቃውንት አዛጉ አንጎላጁ፡፡
ይኼኔ ነው ኋላ ከተቀመጡት አረጋውያን ሊቃውንት መካከል አንደኛው የተነሱት፡፡ እኚህ ሊቅ እድሜም ጥበብም የጠገቡ እንደሆኑ ስለተመሰከረላቸው ሲነሱ አይን ሁሉ ወደሳቸው መጣ፡፡
“ግርማዊነትዎ ፍቃድዎ ከሆነ ብናገር…”
“ቀጥሉ” አሉ ጃንሆይ
“የተከበሩት ጃንሆይ--” አሉ የአቡዬ ገብሬን የመሰለ ረዥም ጺማቸውን እየላጉ፡፡ “አያሌ ሀያላን በሀገሬ ላይ ተፈራርቀው ሲነግሱ አይቻለሁ፡፡ በዚህ እፍኝ በማትሞላ እድሜ የብዙዎች አማካሪ የመሆን እድል አጋጥሞኛል፡፡ እኔ እንደታዘብኩት ከድርቅ፣ ከቸነፈር በላይ ይችን አገር ያደቀቃት ጉባኤ ነው፡፡ ጉባኤ ምን አተረፈልን? ተሰብስበን እንወጥናለን፡፡ ወጥነን እንበተናለን፡፡ ስለዚህ ከሁሉ አስቀድሞ የዚህ ጉዳይ ቢታይ ባይ ነኝ…”
ጃንሆይ ለጊዜው ምንም አላሉም፡፡ አርምሟቸው ግን ጊዜ አልፈጀም፡፡ “አዬ ጉድ…” በመዳፋቸው ጭናቸውን እየጠበጠቡ “እንዲህ ልክ ልካችንን ንገሩን እንጅ… ለነገሩስ አገሩ በጠቢባን እንደማይታማ አውቃለሁ፡፡ ግን በእድሜ ያልተፈተነ ጥበብ የገደል ማሚቶ ነው፡፡ ለመናገርማ ብዙዎች ሲናገሩ ቆይተው የለምን? እንዲህ የንስር ዓይን የታደሉ ብስል ሊቅ ግን ተሰውሮብን የነበረውን ጥበብ ገላለጡት፡፡ ልክ ነው ትልቁ የእኛ ራስ ምታት ጉባዔ ነው፡፡ ጉባያችን ለምን ፍሬ አጣ? እንዴት ፍሬ ይኑረው? ይህንን ተነጋግረን ካልፈታን ከዚህ ጉባዔ ንቅንቅ አንልም፡፡ ነቃ በሉ እንጅ ሊቃውንት፡፡”  
ተፈጸመ ዝንቱ መጽሐፍ
 ጉባኤው ግን ቀጠለ፡፡
ምንጭ፡- (በራሪ ቅጠሎች፤ 1996 ዓ.ም)


Read 518 times