Wednesday, 18 September 2024 20:17

የሚድያ ሰው ጌታቸው ኃይለማርያም ሊዘከር ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የዛሬ 30 ዓመት ህይወቱ ያለፈው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ በሙያ ባልደረቦቹ  የማስታወሻ ዝግጅት ሊደረግለት ነው፡፡

የፊታችን እሁድ መስከረም 12 ቀን  2017 ዓ.ም  ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ  በወመዘክር አዳራሽ  በሚከናወነው በዚህ ዝግጅት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን  ባልደረቦቹ  ይታደማሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የማስታወሻ ዝግጅቱ ሀሳብ አመንጪና አዘጋጅ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሲሆን፤  በዕለቱም የጋዜጠኝነትና ተግባቦት  ተማሪዎች  በመሰናዶው ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ በጠቅላላው ከ24 ዓመታት በላይ ያገለገለ ሲሆን፤ በተለይም በዜና አቀራረብና አንባቢነት ለብዙዎች አርአያ በመሆን ይታወቃል፡፡

በማስታወሻ ዝግጅቱ ላይ፣ ስለ ጌታቸው ምስክርነት የሚሰጡት ጋዜጠኛ ሚሊዮን ተረፈ ፤ ጋዜጠኛ ዋጋዬ በቀለና ጋዜጠኛ  ታዬ በላቸው ሲሆኑ፤ በተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን  የተዘጋጀ የ20 ደቂቃ የድምጽ ዘጋቢ ሥራም እንደሚቀርብ  ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሚድያ ሰው ጌታቸው ኃይለማርያም፣ አሁን በአንጋፋነታቸው እውቅና የተቸራቸውን  እንደ ነጋሽ መሀመድ፣ አለምነህ ዋሴ፣ ንግስት ሰልፉና ብርቱካን ሀረገወይንን የመሳሰሉ  ባለሙያዎች ለሙያዊ ብቃት እንዲደርሱ በማሰልጠንና ልምዱን በማካፈል የበኩሉን የተወጣ ባለሙያ ነበር፡፡ ዜና ፋይል የተሰኘውን ፎርማት ለመጀመረያ  ጊዜ እንዳስተዋወቀና እንደፈጠረ የሚነገርለት ባለሙያው፤ በብስራተ ወንጌል የሬድዮ ጣቢያም አገልግሏል፡፡
 
ታላቁ የሚድያ ሰው ጌታቸው፣ ከዚህ ቀደም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባሳተመው ‹‹መዝገበ አእምሮ የሚድያ ሰዎች ኢንሳይክሎፒዲያ›› ላይ ታሪኩ የተሰነደለት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ያነበባቸው ዜናዎችና ምስሎቹም ወግ በያዘ መልኩ ለታሪክ እንዲቀመጥለት ተደርጓል፡፡

Read 628 times