Friday, 20 September 2024 18:42

በአደንዛዥ ዕጽ አስከፊነት ላይ የሚያተኩር ማስተማሪያ መጽሐፍ ሊዘጋጅ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ላግዛት የበጎ አድራጎት ድርጅት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራጭ በአደንዛዥ ዕጽ አስከፊነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያግዝ ማስተማሪያ መጽሐፍ ሊያዘጋጅ መሆኑን አስታውቋል። ድርጅቱ ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በሐረሪ ክልል “ትውልድን ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ እንታደግ” የሚል ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

ዶክተር አንዱዓለም አባተ በአማካሪነት የሚሳተፍበት ይህ የበጎ አድራጎት ድርጅት በዚህ ፕሮጅክቱ በሐረሪ ክልል በሚገኙ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መምህራን እና የተማሪ ወላጆች እንዲሁም ከትምህርት ቤቶች ውጪ የሚገኘውን የህብረተሰብ አካል ስለ አደንዛዥ ዕፅ ሱስ አስከፊነት ግንዛቤ መፍጠር፣ በክልሉ የሚገኙ በሱስ የተጠቁ ዜጎች የሚታከሙበት ክሊኒክ እና ከሱስ ማገገሚያ ማዕከላትን ማቋቋም፤ እንዲሁም ወጣቶች ለአደንዛዥ ዕዕ ሱስ እንዳይጋለጡ የተለያዩ የክህሎት ማዳበሪያ ስልጠናዎችን መስጠት እና የስራ ዕድሎችን ማመቻቸት ለማሳካት ያቀዳቸው ግቦች እንደሆኑ በዚሁ መግለጫ ተገልጿል።

በተጨማሪም ልምድ ባላቸው ባለሞያዎች በመታገዝ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራጭ በአደንዛዥ ዕጽ አስከፊነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያግዝ ማስተማሪያ መጽሐፍ በድርጅቱ እንደሚዘጋጅ ላግዛት የበጎአድራጎት ድርጅት መስራች ወይዘሮ ጽዮን ዓለማየሁ ተናግረዋል። በቀደሙት ጊዜያት በአደንዛዥ ዕጽ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጁ መጽሐፍት እንደሌሉ ያስታወሱት ወይዘሮ ጽዮን፣ ይህ የሚዘጋጀው መጽሐፍ በጉዳዩ ዙሪያ የተጻፈ ልዩ መጽሐፍ እንደሚሆን አመልክተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ፣ ትምህርት ቢሮ፣ ሴቶች እና ህጻናት ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት፣ ከአደንዛዥ ዕጽ ሱስ የጸዳና አምራች የሆነ ብቁ ዜጋ መፍጠርን ዋና ራዕይ በማድረግ እንደሚሰራ ገልጿል። ለዚህም ስራ ዕውቁ የሐረሪ ሙዚቃ አቀንቃኝ የሆነው የኢህሳን አብዱሰላም ልጅ የሆነውን ዊሳም ኢህሳንን የክብር አምባሳደር በማድረግ ስራ አስጀምሯል።


ላግዛት የበጎ አድራጎት ድርጅት በ2014 ዓ.ም. የተቋቋመ አገር በቀል እና በቦርድ የሚመራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ የስሙ ትርጉም በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለውን ዕምቅ ሃይል በመጠቀም፣ ጤነኛ እና ብቁ ትውልድን በማፍራት የኢትዮጵያን የወደፊት እድገት ማገዝ ማለት እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል፡፡



Read 1244 times