Saturday, 21 September 2024 12:56

“በልጄ አልተኛሁ፣ በልጄ ገዳይ አልተኛሁ” አለ አባት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 አንድ የአይሁዶች አፈ-ታሪክ አለ፡፡
አንድ ጊዜ አንድ ትንሽ ልጅ፣ አባቱና አያቱ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ አያትዬው በጣም ከማርጀት-ከመጃጀታቸው የተነሳ ዐይኖቻቸው ወደ አለማየት፣ ጆሮዎቻቸው ወደ አለመስማት፣ እጆቻቸው ወደ አለመጨበጥ በመሸጋገር ላይ ነበሩ፡፡ እያደርም ራሳቸውን ችለው በእግራቸው መቆም ስለማይችሉ የሰው ድጋፍ ይፈልጉ ጀመር፡፡ በተለይም ገበታ ላይ ሲቀመጡ አንዳንዴ፣ የሾርባ ማንኪያ እንኳ በጣታቸው መያዝ ያቅታቸዋል፡፡ ትንሹ ልጅ፣ የአባቱን አባት - አያቱን፣  ለመርዳት ያስባል ግን አቅም አልነበረውም፡፡
የልጁ አባትና እናት ክፉዎች ነበሩ፡፡
ሲያረጁ አይበጁ ነውና አያትዬው መንገድ የሚመራቸው ሰው ሲያጡ አይረዷቸውም፡፡ ጆሮዋቸው ስለማይሰማ አንዴ የተናገሩትን ድገሙልኝ ሲሉ የሚደግምላቸው የለም፡፡ መነሳት ሲያቅታቸው የሚደግፋቸው፣ መራመድ ሲያቅታቸው መንገድ የሚያሻግራቸው አንድም ሰው አጡ፡፡
ታዲያ አንድ የፋሲካ ጊዜ ቤተ-ዘመድ ሁሉ ተጠርቶ ምግቡ ሁሉ ቀርቦ፣ መጠጡ ተሰናድቶ ባለበት ሰዓት አያትዬውም ተጠርተው እንደምንም እየተንገዳገዱ ገበታ ቀረቡ፡፡ ሆኖም እርጅናው በጣም ስለባሰባቸው የተሰጣቸውን የሾርባ ማንኪያ አንስተው፣ ሾርባ ቀድተው ወደ አፋቸው ሲሰድዱት፣ እጃቸው ተንቀጠቀጠና ሾርባውን ካማረው ነጭ የጠረጴዛ ልብስ ላይ አፈሰሱት፡፡ አፋቸውም ሾርባውን በቅጡ ለመሰብሰብ ስላልቻለ ሲዝረከረክባቸው ነጭ ሸሚዛቸው ተበከለ፡፡
ባልና ሚስቱ ቤተ - ዘመድ ፊት እንደተዋረዱ ቆጠሩት፡፡ ስለዚህም ያ ሁሉ ሰው ባለበት ሚስትዬው ባሏን፤
“እኚህን አባትህን አንድ ትላቸው እንደሆነ አንድ በላቸው፡፡ በበኩሌ ከዛሬ ጀምሮ አብረውን ገበታ እንዲቀርቡ ፈቃደኛ አይደለሁም!” አለችና ተመናቅራ ወደ ጓዳ ገባች፡፡
ባልየው ተከትሏት ወደ ጓዳ ይገባና በጣም ያባብላታል፡፡ ከብዙ ልመና በኋላም፣ አባቱ ሁለተኛ ወደ ገበታው እንደማይቀርቡና፣ ይሄንንም አሁኑኑ ቤተ-ዘመድ ባለበት በይፋ እንደሚናገር ቃል ይገባላትና፣ ተመልሳ ወደ ገበታው ለመምጣት ፈቃደኛ ትሆናለች፡፡
’ሴት የላከው ሞት አይፈራም‘ ሆነና አባ-ወራው ተነስቶ አባቱን፣
“ከዛሬ ጀምሮ ከእኛ ጋር ገበታ አትቀርብም፡፡ ለብቻህ ማድቤት ሆነህ እንድትበላ” ሲል አዘዘ፡፡
ከዚህ ጊዜ ወዲህ አያትዬው ማድቤት አንድ ጥግ ላይ ቁጭ ብለው እንዲመገቡ ይፈረድባቸዋል፡፡ ምግቡም የሚቀርብላቸው በአንድ በሸክላ በተሰራ ገበቴ ላይ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ከዚያ የክፋው ደግሞ የምትቀርብላቸው ምግብ ራሱዋ በጣም ጥቂት ትርፍራፊ፣ ሆድ እንኳ በአግባቡ የማትሞላ ሆነች፡፡
አያትዬው ምግብ በቀረበላቸው ቁጥር እንባቸው በአይናቸው ይሞላል፡፡ ምርር ብለው ያዝናሉ፡፡ “ሆድ ይፍጀዋ፣ እስቲ ይሁን!” ይላሉ በረዥሙ ተንፍሰው፡፡
አንድ ቀን በሸክላው ገበቴ ምግብ ተሰጥቷቸው፣ እሱን ይዘው ወደ ማድቤት ሲሄዱ እጃቸው ክብደቱን አልችል አለና መሬት ላይ ወድቆ እንክትክቱ ወጣ፡፡ ምግቡም ወለሉን ሞላው፡፡ ጦማቸውን ዋሉ፡፡ ተለዋጭ ምግብ የሰጣቸው ሰው የለም፡፡
ሚስትዬው ተቆጣች
“አለመብላት መብትዎ ነው፡፡ ያንገበገበኝ የሸክላ ገበቴዬ ነው! ለሁለተኛው ግን አንድ የእንጨት ገበቴ ይሰራልዎትና በዚያ ይበላሉ!” ብላ እንደ ልማዷ እየተመናቀረች፣ ለሳቸው የማይሰማቸውን ስድብ እየተሳደበች ወጣች፡፡ እሳቸው ምንም አልመለሱላትም፡፡
ከዚያን ቀን ወዲህ ሽማግሌው ምግባቸውን የሚበሉት በእንጨት ገበቴ ሆነ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ትንሹ ልጅ አንድ በአንድ ያስተውል ኖሯል፡፡
አንድ ቀን ጠዋት ያ ትንሽ ልጅ፣ ደጅ ሜዳው ላይ ተቀምጦ፣ አንድ ትልቅ የእንጨት ጉማጅ መሬት ላይ አጋድሞ በመዶሻና በመሮ ለመፈልፈል ሲፍጨረጨር ይታያል፡፡ እናትና አባት የሚሰራው ነገር ግራ ገብቷቸው ወደ ልጁ ይመጣሉ፡፡
አባት - “ልጄ ምን እየሰራህ ነው?” ይሉና ይጠይቁታል፡፡
ልጁም- “እኔ ትልቅ ሰው በምሆንበት ጊዜ አባትና እናቴ ማድቤት ቁጭ ብለው ምሳ የሚበሉበትን የእንጨት ገበቴ ካሁኑ ላዘጋጅላቸው እየሞከርኩ ነው!”
አባትና እናት እርስ በርስ ተያዩ፡፡ በድንጋጤ ዐይናቸው እንደፈጠጠ ለደቂቃዎች ቆዩ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዐይናቸው የፀፀት እንባ ሞላ፡፡
ከዚህች ቅፅበት በኋላ አያትዬውን እንደ ዱሮው ወደ ገበታው ደግፈው እያመጡ እያስቀመጡ፣ ምግብ ቢንጠባጠብባቸው እንኳ አፋቸውን በደንብ እየጠረጉ፣ በሚገባ መንከባከብ ጀመሩ፡፡
*           *           *
“አጓጉል ትውልድ
ያባቱን መቃብር ይንድ”
ይላሉ አበው ከላይ ያየነውን አይነት አባትና አያት ታሪክ ሲያጋጥማቸው፡፡ ከቶውንም ዛሬ በአባቶቻችን በአንጋፋዎቻችን ላይ የምናደርሰው በደል፣ ነገ በእኛ ላይ ሊደርስብን የሚችለውን መከራ ጠቋሚና አመላካች ነው፡፡ የሀገራችንን የእለት እለት የፖለቲካና ማህበራዊ አካሄድ ስናስተውል፣ ነገ ለሚደርስብኝ መከራ ነገ ራሱ ይጨነቅ የሚል አይነት የምን-ግዴ እምነት ያለ ይመስላል፡፡ የአንዳንድ ግለሰቦች፣ የመሪዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችም ነገረ-ሥራ “እድሜው ያጠረ በግ፣ ተኩላ ቤት ሄዶ ያወጋል” የሚባለውን አይነት ሆኗል፡፡ በትንሽ በትልቁ መጋጨት፣ ግንዱን ትቶ በቅርንጫፉ መጠላለፍ፣ የቅርፅ አቤቱታ ማብዛት ያበዛሉ፡፡ ያንኑም በወጉና በትክክለኛው ጊዜና ቦታ አለማዋል ሁለተዜ ጥፋት ነው፡፡
ሌሎች ደግሞ ዋና ህፀፃቸው “የጓደኛህን እግር አይተህ ዝለል” የሚለውን ተረት አለመገንዘብ ነው፡፡ ሌላው በገባበት አረንቋ ያላንዳች ማወላወል ዘልሎ መስመጥን፣ እስከዛሬ የሚታገሉት ቦታውን ፍለጋ እንጂ ሀገር-አቀፉን አላማ በስራ ላይ ለማዋል አይመስልም፡፡ በዶሮው ቀርቶ በላባው የሚጣሉ ትልቁን ሀገር የመምራት ኃላፊነት በአግባቡ ተሸክመው ለመምራት፣ ምረጡኝ ይሉ ዘንድ ይቻላቸዋልን? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡
አንዳንዶቹ፤ ትራፊክ እንዳይዘው ለማምለጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየነዳ ተገልብጦ እንደሚያዝ ሾፌር፣ መኪናውን ከጥቅም ውጪ ከማድረግም፣ ህይወትን አደጋ ላይ ከመጣልም፣ ከመያዝም የማያድን እርምጃ ሲወስዱ ይታያሉ፡፡ በጥንቃቄ መንዳት፣ አስቀድሞ መድረሻን ማወቅ፣ የትራፊክ ህግጋቱን በቅጡ ማጤን፣ የትላንትናውን ስህተት ጠንቅቆ አውቆ መጓዝ ዛሬም አንገብጋቢ ጥያቄ ይመስላል፡፡ “ጠላቴ ጧት ሞቶ እኔ ልሙት ማታ” በሚል የጥድፊያ ፉከራና መንደርደር ያልታየ ኩርባ፣ የፈረሰ ድልድይ፣ የተዘጋ መንገድ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡
የነቃና የተባ ትውልድ መፍጠር የቀዳሚው ትውልድ አደራ ነው፡፡ ሞገደኛና ጠበኛ ልጅ ወልዶ እንቅልፍ ማጣት ብቻ ሳይሆን ሰንብቶ አጉል ጦርነት ውስጥ መግባት ሊከተል ይችላል፡፡ ኋላ ውሎ አድሮ ደግሞ የልጅን አጥቂና አጥፊ፣ አጠፋ ብሎ ሌት - ተቀን በሽምቅና በህቡዕ አድፍጦ ጥይት እንዳጎረሱ፣ ማደርም ይመጣል፡፡ ልጅ፤ ከአብራክ የወለዱት ልጅ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በዘመኑ ተዘርቶ የበቀለው ሁሉ ነው፡፡ አስተማሪ ለሆነ ተማሪው ልጁ ነው፡፡፡ ቀጥሮ ለሚያሰራ ተቀጣሪው ልጁ ነው፡፡ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ለተሰማራ ምልምሉ አባሉ ልጁ ነው፡፡ መሪ ሆኖ ለተመረጠ ተመሪው ልጁ ነው፡፡ በየመሥመሩ፣ በየክልሉ፣ በየቢሮው፣ በየፓርቲው አባትና ልጅ አለ፡፡ ደህና ልጅ የመፍጠር ተግባር አገር የማዳን ተግባር ነው፡፡ ሞገደኛ ልጅ፣ ጋጠ-ወጥ ልጅ፣ አፈንጋጭ ልጅ፣ ነገር-ፈታይ ልጅ፣ ያለኔ ልጅ አይኑር የሚል ልጅ ወዘተ… የልጅ አይነቱና መልኩ እልቆ-መሳፍርት የለውም፡፡ መልካም ልጅ ለመፍጠር ያልተጋ አባት፣ “በልጄ አልተኛሁ፣ በልጄ ገዳይ አልተኛሁ” እንዳለው አባት ከመሆን አይድንም፡፡

Read 686 times