• የእነ ደብረጽዮን ህወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን እያደናቀፉት ነው
• ህወሓት የራሱን ህገ ደንብና የአገሪቱን ህግ ጥሷል
• ትግራይ አሁን በሁሉም ዓይነት ቀውስ ውስጥ ናት
• ስብሰባዎቹ ድጋፍ ማጠናከሪያ እንጂ ሌላ ፋይዳ የላቸው
ከህወሓት አንጋፋ ታጋዮች አንዱ ናቸው፤ አቶ ገብሩ አስራት። የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት አቶ ገብሩ፤ከ1993 ዓ.ም. የህወሓት ክፍፍል ወዲህ ደግሞ ወደ ተቃውሞ ጎራ በመቀላቀል አረና ትግራይ የተባለ ፓርቲ መስርተው 15 ዓመታት ያህል በአመራርነት ተሳትፈዋል፡፡ ህወሓት በ93 ዓ.ም ክፍፍል ወቅት እሳቸውን ጨምሮ በርካታ አመራሮችን ከህግ ውጭ ማባረሩን የሚያስታውሱት አቶ ገብሩ፤ አሁንም የዚያኑ ግልባጭ ነው ያደረገው ይላሉ፤ ከሰሞኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በ16 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ላይ የወሰደው እርምጃ ህገወጥ መሆኑን በመግለጽ፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአመሰራረት ችግር እንደነበረበት የሚገልጹት ፖለቲከኛው፤ ሥራ አስፈጻሚውን የሚቆጣጠር ም/ቤት ወይም አካል እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደር አወቃቀር አካታችነት እንደሚጎድለውም ይገልጻሉ፡፡ በተፋጠጡት የህወሓት ቡድኖች መካከል አንዳችም የርዕዮተ ዓለም ልዩነት እንደሌለ በመጠቆምም፣ የሚያሻኩታቸው የሥልጣን ጉዳይ ብቻ ነው ይላሉ፡፡
አቶ ገብሩ አሥራት ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ መጠይቅ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ድክመቶችና ተግዳሮቶች ያብራራሉ፡፡ ከመንግሥት ውጭ ያለው በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህይወት ቡድን እንዴት ጊዜያዊ አስተዳደሩን አላሰራ ብሎ እንቅፋት እንደሆነበትም ይገልጻሉ፡፡ ህወሓት የራሱን ህገ ደንብና የአገሪቱን ህጎች በመጣስ ህገወጥ ጉባኤ ማካሄዱን፣ 16 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንም በህገወጥ መንገድ ከፓርቲው ማገዱን ይናገራሉ፡፡ ህወሓቶች ከሻዕቢያ ጋር መሞዳሞድ መጀመራቸው ለትግራይም ለአገርም አደጋ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በትግራይም ብቻ ሳይወሰኑ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚካሄደው ጦርነት በፖለቲካዊ መፍትሄ መቋጨት ካልተቻለ፣ እንደ አገር እየተዳከምን በመሄድ፣ እንደ ግብጽ ላሉ ውድቀታችንን ለሚመኙ አገራት እንጋለጣለን ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሚኪያስ ጥላሁን ከአንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ አሥራት ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንዲህ ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡
የትግራይ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታን በቅርበት እንደሚከታተል አንጋፋ ፖለቲከኛ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?
እኛ እንግዲህ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ችግር አለበት ብለን ነው የምናምነው። መጀመሪያ ሲቋቋም ከመርሁና ከአመሰራረቱ ጀምሮ፣ ችግር ያለበት ሆኖ ነው የሚታየኝ። ይኸውም ምንድን ነው? በማዕከላዊ መንግሥትና በህወሓት ስምምነት የተፈጠረ አስተዳደር ነው። ነገር ግን በፕሪቶሪያው ስምምነት፣ ሁሉን-አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ይቋቋማል ነበር የተባለው፡፡ በመጨረሻ የተመሰረተው ግን የህወሓት አስተዳደር ነው። ፓርቲዎችንና ሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎችን አላሳተፈም። አካታች አልነበረም። ስለዚህ ችግር አለበት። ሌላ ደግሞ፣ በአስተዳደሩ ውስጥ ሥራ አስፈጻሚ እንጂ፣ ሥራ አስፈጻሚውን የሚቆጣጠር ሌላ አካል የለም። እንደ ምክር ቤትም ሆኖ፣ ይህን የሚቆጣጠር የለም። ስለዚህ ሥራ አስፈጻሚው ብቻውን ነው እያስተዳደረ ያለው፤ እርሱን የሚቆጣጠር ምክር ቤትም ሆነ ሌላ አካል የለም። እና፣ ከጅምሩ ችግር ያለበት ሆኖ ይታየኛል። ይህም ሆኖ ሌላው ትልቁ ችግር ደግሞ በመንግሥት በኩል ባሉ የህወሓት አባላትና ከመንግስት ውጭ ባሉት የህወሓት አባላት ወይም አመራሮች መካከል የተፈጠረው ግጭት ነው፡፡ ይሄ ሽኩቻ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ምንም እንዳይሰራና እንዳይላወስ አድርጎታል። በወረዳና በቀበሌ ያሉ ምክር ቤቶችንና ካድሬዎችን ከመንግሥት ውጪ ያለው አካል ነው የተቆጣጠረው፤እነ ደብረጽዮን ማለት ነው፡፡ መንግሥቱን ደግሞ እነ ጌታቸው ተቆጣጥረውታል። ስለዚህ ጭራሽ ሊያሰሯቸው አልቻሉም። እንግዲህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ይሆነዋል። ግን ይህ ነው የሚባል አመርቂ ስራ እስካሁን አልሰራም፡፡ እንዲያውም አሁን የስልጣን ሽኩቻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ስለደረሰ፣ ህዝቡ ተፈላጊውን የመንግሥት አገልግሎት እያገኘ አይደለም፡፡ እንዲያውም የጨነገፈ ዓይነት መንግስት ሆኖ ወሮበሎች፣ የጦር አበጋዞችና ካድሬዎች እንደ ልባቸው የሚቆጣጠሩት የወንጀል ማዕከል ሆኗል፤ ትግራይ። የወንጀለኞች መናኸርያ ነው የሆነው።
ሥራ አስፈጻሚውን የሚቆጣጠር ምክር ቤትም ሆነ ሌላ አካል የሌለው ለምን ይመስልዎታል?
እኔ የሚመስለኝ ከአቋቋሙ ጀምሮ ያለው ችግር ነው። ሲቋቋም፣ ሥራ አስፈጻሚ ብቻ እንጂ እርሱን የሚቆጣጠር ሌላ አካል እንዲቋቋም አልፈለጉም። ኋላ ቆይቶ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህ ነገር እንደሚያስፈልግ ተገንዝቦ ሊያቋቁም ሞክሮ ነበር። “የአማካሪ ካውንስል” የሚባል ሊያቋቁም ሞከረና ህወሓት ሳይቀበለው ቀረ፡፡ ህወሓት፤ “ይሄ ነገር እኔን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ ነው” ብሎ ስላሰበ፣ ካውንስሉ እንዳይቋቋም አጥብቆ ነው የተቃወመው፡፡ ስለዚህ ይህ የአማካሪ ካውንስል ወይም ተቆጣጣሪ አካል እንዳይኖር አሁን ዋናው ደንቃራ፣ የእነ ደብረጽዮን ህወሓት ነው። እንግዲህ በደንብ ደረጃ እንዲቋቋም እነ ጌታቸው ደንብ ካወጡ ወራትን አስቆጥሯል። ሆኖም ሌላው ቡድን ስለተቃወመው እስካሁን ድረስ ሳይቋቋም ቀርቷል። ሥራ አስፈጻሚው የሚሰራው ሥራ በማን ነው የሚጠየቀው? የሚያወጣው ገንዘብ፣ የሚመድበው በጀት በትክክል ስራ ላይ ውሏል ወይ? የሚለውን ማን ይቆጣጠረዋል? የሚሰራቸውን ሥራዎች፣ ዕቅዶች--ተግባራዊ መሆናቸውን ማነው የሚቆጣጠረው? ተቆጣጣሪ በሌለበት እንዳሻው ነው የሚሄደው ማለት ነው። እናም፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከአቋቋሙ ጀምሮ ችግር ያለበት ሆኖ ይታየኛል።
የአካታችነት ጉዳይን በተመለከተ አንዳንድ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ አካታች ነው” ብለው የሚያምኑ ወገኖች፣ “በሚመሰረትበት ወቅት ከምሁራን፣ ከተዋጊዎችና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተወሰኑ አካላት ወደ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲገቡ ተደርገዋል።” ብለው ይሞግታሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
እንግዲህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች...የራሳቸው የሆነ ደጋፊ ማሕበረሰብ አላቸው። ፓርቲው ሲወከል እርሱ የሚወክለው ማሕበረሰብ ይወከላል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ፓርቲዎች ከአንድ ፓርቲ በስተቀር አልተሳተፉም፤ ባይቶና ከሚባለው ፓርቲ ውጪ። እርሱም እንደገና ተቃውሞ ተቆርጦ የቀረ እንጂ ፓርቲዎችን አላካተተም። ከጅምሩ ህወሓት ከፓርቲዎችም ጋር አልተስማማም። እርሱ እንደሚፈልገው ነው የቀየሰው እንጂ ፓርቲዎች እንዲሳተፉበትና እንዲነጋገሩበት አላደረገም። እናም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እዚህ ላይ አልተሳተፉም። ሁለተኛ፣ የማሕበረሰብ አካላት የሚባሉትም ቢሆኑ፣ የተሳተፉ እኮ የሉም። GSTS የሚባል የትግራይ ምሁራን ስብስብን ወክያለሁ ብሏል። ከዚህ ውጭ ሌላ የተሳተፈም የለም። እንግዲህ ዋናዎቹ ተሳታፊዎች TDF ወይም ሰራዊቱ እና ህወሓት ናቸው ማለት ነው። ሰራዊቱም እንደምናየው የህወሓት ደጋፊ ነው። ስለዚህ ጠቅላላውን ስታየው፣ የህወሓት ነው እንጂ ሌሎቹን ያላካተተ ነው። በማሕበረሰብ ደረጃም አላካተተም። በፓርቲዎች ደረጃም አላካተተም።
ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ያስቆጠረው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የራሱን የቤት ስራዎች አልሰራም በሚል የሚወቅሱት ወገኖች አሉ። ለምሳሌ፦ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ከመመለስ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲዳረስ ከማድረግ እንዲሁም ጸጥታ ከማስፈንና ወንጀልን ከመቀነስ አንጻር በቂ ሥራ አላከናወነም ይላሉ፡፡ እርስዎ ከመንግሥት ውጭ ያሉት የህወሓት ቡድን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እኒህን ሃላፊነቶቹን እንዳይወጣ እንቅፋት ሆኗል ብለው ያምናሉ?
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ወደፊት እንዳይራመድ የሚያደርጉ ሁለት ሃይሎች አሉ። አንዱ ማዕከላዊ መንግሥት ነው። ተፈናቃዮችን የመመለስ ጉዳይ፣ የነበረውን አስተዳደር ወደ ቀድሞው ሁኔታ የመመለስና የመሳሰሉ ሥራዎች በዋነኛነት ማዕከላዊ መንግስት መፈጸም ያለበት ነው። ተፈናቃዮች ቶሎ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ፣ ሰራዊቱም ቶሎ ትጥቅ እንዲፈታና እንዲቋቋም፣ አስተዳደሩም ቶሎ ወደነበረበት እንዲመለስ የሚል ስምምነት አለ። እኔ እንደሚመስለኝ፣ በዚህ በኩል ተጠያቂው ማዕከላዊ መንግሥት ነው። ማዕከላዊ መንግሥት ፈቃደኛ አይደለም። ይህ ነገር እንግዲህ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አቅም የሚሰራ አይደለም። ማዕከላዊ መንግሥቱ በጣም ብዙ ገንዘብ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ማሰባሰብ አለበት። ምክንያቱም ውድመቱ በጣም ከፍተኛ ነው። የተፈናቀለው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው። ሰራዊቱም ብዛት አለው። እነዚህን ለማቋቋም ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ብዙ እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ በዚህ በኩል ጊዜያዊ አስተዳደሩን አንወቅስም። ለዚህ ተጠያቂው ማዕከላዊ መንግስት ይመስለኛል።
በሁለተኛ ደረጃ የሚከሰሰው ህወሓት ነው። “ስልጣን እኔ ካልያዝኩ በስተቀር እነ ጌታቸውን ማደናቀፍ አለብኝ” ብሎ ከጅምሩ፣ “እነዚህ የብልጽግና ሰዎች ናቸው፣ እነዚህ የሲአይኤ ሰዎች ናቸው፣ እኛን አይወክሉም” እያለ ምንም ዓይነት ሥራ እንዳይሰራ ያደረገው የደብረጽዮን የሕወሓት ቡድን ነው። ይህም ሆኖ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩም ቢሆን፣ ሊሰራቸው የሚችላቸው ለሕዝብ ግልጽ የሆኑ ሥራዎች እኔ አላየሁም። በዕቅድ የሚታወቁ “ይህን እፈጽማለሁ” ብሎ ሕዝብ የሚያውቃቸው፣ ሕዝቡን አሳትፎ የሚሄድበት መንገድ ስለሌለ፣ እርሱም ተጠያቂ ነው። ሦስቱም በየራሳቸው መንገድ ተጠያቂዎች ናቸው።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ሕዝባዊ ስብሰባ እያደረጉ ነው፡፡ በእርስዎ ዕይታ እነዚህ ሕዝባዊ ስብሰባዎች መፍትሄ ያመጣሉ?
እኔ ሳየው፣ ስብሰባዎች ምንም ማለት አይደሉም። ነገሮች መፍትሔ የሚያገኙት በስብሰባ አይደለም። የተቀናጀ ዕቅድ ይዞ፣ የተቀናጀ ስትራቴጂ ወይም ደግሞ የተቀናጀ ፍኖተ ካርታ ይዞ መሥራት ነው እንጂ በስብሰባ የሚፈታ ነገር ብዙም አይደለም። ስብሰባ ወይ የፕሮፓጋንዳ ነው፣ ወይም ደግሞ ዕቅዶችን የማሳወቅ ጉዳይ ነው። አሁን ህወሓት ለሁለት ተሰንጥቆ በተካረረበት ጊዜ ስብሰባዎቹ ድጋፍ የማግኘት ጉዳይ ወይም ድጋፍን የማጠናከር ነገር ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ የላቸውም። ዋናው ነገር ግን ሕዝቡ ፍላጎቱን አሳይቷል። ከእንግዲህ ወዲህ ህወሓት እንደማይጠቅመው፣ ላለፉት ዓመታት እንደጨቆነው በድፍረት የገለጸበት አጋጣሚ ነው፡፡ ህወሓት ሁሉንም ዓይነት ኋላቀር አስተሳሰቦችን የያዘና ለሕዝቡ ጭራሽ የማይፈይድ ድርጅት እንደሆነ ወጣቱ ያሳየበት ሁኔታ ነው የተስተዋለው። እኔ በሦስቱም ስብሰባዎች እንደተመለከትኩት ማለት ነው። ከዚያ የበለጠ ፋይዳ ግን ያለው አይመስለኝም።
ባለፈው እሁድ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሽረ ከተማ የጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ በተቃውሞ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ መንግሥት የጠራውን ስብሰባ የማቋረጥ አቅም ያለው ቡድን አለ ማለት ነው?
የስብሰባው መቋረጥ እንግዲህ የህወሓት ሥራ ነው። የሕዝብ ሥራ አይደለም። ህወሓት የትግራይን ሕዝብ በልማት ቡድኖች እና “አንድ ለአምስት” በሚል ጠፍሮ የያዘበት ሁኔታ ነው ያለው። እነዚህ ባልፈረሱበት ወይም ባልተዳከሙበት ሁኔታ፣ መንግሥትን ይቃወምበታል፤ ተቃዋሚዎችን ይቃወምበታል። ይቃወሙኛል የሚላቸውን ሃይሎች በእነዚህ በኩል ነው የሚደፍቀው። እነዚህ የልማት ቡድኖችና “አንድ ለአምስት” የሚባሉት እስካልፈረሱ ድረስ፣ የትግራይ ሕዝብ ምንጊዜም ቢሆን ነጻነት ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ወጣቱም፣ ሕዝቡም መገንዘብ ያለበት፣ ይህ ጊዜያዊ መንግሥት ቢቀበሉትም፣ ባይቀበሉትም መንግሥት ነው። መስማት ማዳመጥ ነበረባቸው። ህወሓት በስብሰባው ውስጥ የራሱን ቡድን አደራጅቶና አስገብቶ ማፍረሱ ለእኔ አዲስ ነገር አይደለም። እኔ የአረና ፓርቲ አባል ነበርኩ። ባለፉት 15 ዓመታት ባካሄድናቸው ስብሰባዎች ካድሬዎችን፣ ወሮበሎችንና የተለያዩ የልማት ቡድኖችን በማሰለፍ፣ በእኛ ላይ የስድብ ውርጅብኝ፣ ለድብድብ መቃጣት፣ ስብሰባን ማፍረስና ሕዝቡ ወደ ስብሰባ አዳራሽ እንዳይገባ ማስፈራራት የህወሓት ባሕርይ ነው። እርሱን የሚቃወም ወይም የማይደግፍ ካለ፣ ወይ ያፈርሰዋል፤ ወይ ይቃወመዋል፤ ወይም እስከ መግደል ድረስ ይሄዳል። በሽረ የተፈጸመው ድርጊት የህወሓትን ባሕርይ ፍንትው አድርጎ ያሳየ እንጂ ሌላ አዲስ ነገር የለውም።
ህወሓት ባለፈው ባካሄደውና በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ባልተሰጠው ጉባኤ ላይ ያልተሳተፉ አመራሮቹን ከድርጅቱ ማባረሩን አስታውቋል። እነዚህ አመራሮች የተባረሩበት ሁኔታ እርስዎና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ከተባረሩበት ከ1993ቱ ክፍፍል ጋር የሚመሳሰል እርምጃ ነው ማለት ይቻላል?
በትክክል ይመሳሰላል። ህወሓት በሕጋዊ መንገድ አይደለም የሚሰራው። በራሱና በአገሪቱ ሕግ የማይገዛ መሆኑን ያመላከተበት ተግባር ነው። አሁን ስታየው ጉባኤው ራሱ ምርጫ ቦርድ ያልተቀበለው ነው። በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት፣ ማንኛውም ጉባኤ ምርጫ ቦርድ የታዘበውና ዲሞክራሲያዊና ሕጋዊ ነው ብሎ የመሰከረለት ካልሆነ በስተቀር፣ በሕግ ደረጃ ተቀባይነት የለውም። ህወሓት ደግሞ የአገሪቱን ሕጎች፣ ተቋማትና ሕገ መንግስቱን ተቀብያለሁ በማለት በፕሪቶሪያ የፈረመውን ስምምነት እያፈረሰው ነው፤ አፍርሶታልም። የራሱን ሕገ ደንብ አላከበረም። ቁጥጥር ኮሚሽኑ ተቃውሞታል። 16 ያህል የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተቃውመውታል። ስለዚህ ይህ ጉባኤ ምንም ተቀባይነት የለውም። በእኛም ጊዜ የሆነው ይህ ነው። በርግጥ፣ ጉባኤ ላይ አልደረስንም። ማዕከላዊ ኮሚቴው ግን ሕገ ደንቡ በማይፈቅደው መንገድ ነው እኛንም ያባረረው። አሰራሩ በኔትዎርክ የታጠረ ነው። ውስጥ ውስጡን ነው የሚሄደው። እኔ ደጋግሜ እንደምለው ይህ ስብሰባ እንጂ ጉባዔ አይደለም። በዚህ መንገድ ሌሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ማባረር፣ ሕጋዊ ዕውቅና የሌለው ነው።
የአሁኑ የህወሓት ክፍፍል ዋነኛ መንስዔ ምን ይመስልዎታል?
እዚህ ላይ ማየት ያለብን ዋናው ነገር፣ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ያለው ግልጽ የሆነ የስልጣን ሽኩቻ ነው። በአብዛኛው በመንግስት በኩል ያለው የህወሓት አመራርና ከመንግስት ውጭ የሆነውና ስልጣን የቋመጠው የህወሓት ቡድን መካከል ያለው ፍጥጫና ቅራኔ ነው እንጂ ሌላ የሃሳብ ልዩነት አላየሁም። ምክንያቱም በእነ ጌታቸው ወይም በአስራ ስድስቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በኩል ከእነዚህ የተለየ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሲፈነጥቁ አላስተዋልኩም። እነ ደብረጽዮን በግልጽ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ መንግሥት የሚሉትን ለውድቀት የዳረጋቸውን ርዕዮተ ዓለም ተከትለው ለመሄድ ነው የተስማሙት። ስለዚህ በጉባኤ የመጣ አዲስ ነገር የለም። ከጉባኤ በፊት የታዩ የርዕዮተ ዓለም ለውጦችም የሉም። እንዲያውም ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይኖር ነው በግልጽ ያወጁት። በዚህም በኩል ያየሁት የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የለም። ያም ሆኖ ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ያነሷቸው ነጥቦች አሉ። የአጀንዳ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፦ “ጦርነቱን እንገምግም” ብለዋል። ትክክለኛ ሃሳብ ነው። አንዳንዶቹ “ይህ ታሪክ ነው፣ የወደፊቱን እንመልከት” ይላሉ፡፡ ግን ትክክል አይደለም። በትግራይ ሕዝብ ከደረሰው እልቂትና ውድመት አንጻር ስንመለከተው፣ ጦርነቱ የታሪክ ጉዳይ አይደለም። አሁንም ያለ ጉዳይ ነው። በዚያ በኩል የተፈጠረው ችግር ሳይታይ፣ መቀጠል ስሕተት ይመስለኛል። በሌላ አገር ቢሆን፣ እነዚህ መሪዎች ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ በሕግም ጭምር መጠየቅ ያለባቸው ናቸው። እንጂ በመደበኛ ሁኔታ ውስጥ ለመቀጠል ሞራል ያላቸው አይመስለኝም። “ምንም እንዳልተፈጠረ እንቀጥላለን” የሚሉት ነገር ትክክል ሆኖ አይሰማኝም። ስለዚህ ይህ የወጣው አንደኛው ቡድን፣ “ይህ ነገር እንደገና እንዳይደገም እንደ አጀንዳ እንየው” ብለዋል። ሌሎቹ ደግሞ፣ ይህንን ማየት አይፈልጉም። ምክንያቱም ያስጠይቀናል ብለው ስለሚሰጉ፣ አለባብሰው መሄድ ይፈልጋሉ። ቅድም ካነሳኸው የ93ቱ ክፍፍል ጋር የሚመሳሰል ትይዩ አጋጣሚ ነው። 93 ላይ “የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት እንገምግም” ስንል፣ “ችግራችን ይህ አይደለም፣ ቦናፓርቲዝም እና መበስበስ ነው ችግራችን” ብሎ፣ ያኔ መለስ የሌለ አጀንዳ ነበር የፈጠረው። እነዚህም ዋናውና ሕዝቡን የሚመለከተው፣ ለዚህ ሁሉ ዕልቂት የዳረገውን ጉዳይ ትተው ሌላ አጀንዳ አስቀምጠዋል። ምንም ሳይለወጥ፣ እንደ ድሮው አቋም ወስደዋል። ስለዚህ የእነ ጌታቸው ቡድን በአንድ በኩል፣ “ይህንን ጉዳይ እናንሳ” ብሏል። ሌላው ደግሞ ትንሽ ፍንጭ የሚሰጠው “መንግሥት እና ፓርቲ መለያየት አለባቸው” የሚለው ነጥብ ነው። በእነዚህ ሁለት አጀንዳዎች ሁለቱ ቡድኖች ይለያያሉ። አጠቃላይ ለውጥን በተመለከተ ግን በፖለቲካ አቅጣጫቸው በኩል ያየሁት ልዩነት የለም።
በህወሓት ውስጥ ከኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት የፈጠረ ወይም ለመፍጠር ዝግጁ የሆነ ቡድን አለ የሚሉ ወገኖች አሉ። በእርግጥም ከኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት ስለመፍጠሩ የሚያሳይ ማስረጃ አለ?
እኔ ከሦስት ሳምንታት በፊት ከተለያዩ ሚዲያዎች ጋር ባደረግኋቸው ቃለ መጠይቆች ከሻዕቢያ ጋር እንደሚገናኙ በግልጽ አስቀምጫለሁ። ምክንያቱም መረጃው አለኝ። የታወቀ ነው። “ህወሓቶች ከሻዕቢያ ጋር እየተገናኙ ነው” ብዬ ስናገር፣ የእነርሱ ደጋፊ የሆኑ ሚዲያዎችና ካድሬዎች በጣም ነው የጮኹብኝ። “ምን ማስረጃ አለህ? ከየት አመጣኸው?” ብለው ተችተውኛል። በቅርቡ እንደተሰማው፣ ደብረጽዮን “ከሻዕቢያ ጋር ግንኙነት እንፍጠር ብለን ወስነናል” ብሎ ወጥቶ ተናግሯል። በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ ነው የወሰኑት። የመጀመሪያው ግንኙነት ዱባይ ላይ በጌታቸው ረዳ አማካይነት “ከሻዕቢያ ጋር ተገናኝተናል” ብለዋል። ይህ ከሚዲያ የሚደበቅ ነገር አይደለም። አሁንም እየቀጠሉ ነው። ግብጾችም ይህን ይፈልጉታል። ሻዕቢያም ይፈልገዋል። ህወሓትም ይህን ይፈልጉታል። እንግዲህ ለዚህ ግንኙነት ምክንያት ሲያስቀምጡ፣ “ሰላም ስለፈለግን ነው” ይላሉ። ሻዕቢያ በትግራይ ውስጥ እስከ ጄኖሳይድ የሚደርስ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸመና አሁንም የትግራይን ብሎም የኢትዮጵያን መሬት ተቆጣጥሮ ያለ ሲሆን፤በትግራይ ላይ ከፍተኛ ውድመት ከፈጸመ ድርጅት ጋር ተጠያቂነት ሳይኖር “ግንኙነት እንፍጠር” ማለት የራሳቸውን ስልጣን ለማስጠበቅ እንጂ ለሕዝቡ ደንታ እንደሌላቸው ያሳዩበት ነው። ጌታቸው ከባለስልጣናቱ ጋር የተገናኘው በእነርሱ ውሳኔ ነው። ግን ዋናው ቁም ነገር ጌታቸው “ይህ ነገር ወደ ጦርነት ስለሚወስደን ማድረግ የለብንም” እንዳለና እነርሱ ደግሞ በያዙት አቋም ለመቀጠል፣ ብሎም ከእነርሱ ጋር ሆነው በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠርና ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን ከሻዕቢያ ጋር እንደተሞዳሞዱ፣ ከእርሱም ጋር ዝምድና እንደመሰረቱ ራሳቸው ተናግረውታል። ያለሃፍረት ነው የተናገሩት።
ከሰሞኑ ደግሞ ግብጽ፣ ኤርትራና ህወሓትን ለማሸማገል ስላላት ፍላጎት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል። ይህን ፍላጎት ሰፋ አድርገን ካየነው፣ ጉዳዩ ቀጣናዊ መልክ እየያዘ እየመጣ ነው ብንል አያስኬደንም?
አዎ፣ ነው። እንግዲህ በአካባቢው የግብጾች ፍላጎት የታወቀ ነው። ኢትዮጵያን አዳክመው በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት ተጽዕኖ እንዲቀንስ፣ የዓባይን ውሃ እንዳትጠቀምና እንዳትቆጣጠር የማድረግ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ፖሊሲ አላቸው። በ19ኛው ክፍለዘመን ጦርነት አድርገዋል። ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እያለች በጉራዕ እና በጉንደት ከአጼ ዮሐንስ ጋር ያደረጉት ጦርነት አለ። እስከ 1885 ዓ.ም. ድረስ ሐረርን ተቆጣጥረው ነበር። ኢትዮጵያን በቀጥታ የመቆጣጠር ፍላጎታቸው መክኗል፤ አልቻሉም። በሁሉም በኩል ተሸንፈው ነው የወጡት። ከዚያ በኋላ ግን የውክልና ጦርነት በማድረግ ነው የቀጠሉት። በሶማሊያ በኩል፣ እንዲሁም የኤርትራ ድርጅቶችን በመደገፍ ኢትዮጵያን የማዳከም፣ ጦርነትና ብጥብጥ ውስጥ ቆይታ ስለ ልማት እንዳታስብ፣ ወንዞቿን እንዳትጠቀም የሚያደርገው ሂደት የቆዩበትና የሚቀጥሉበት ነው። አሁን ደግሞ እንደ 1969 ዓ.ም. ሁሉ፣ ኢትዮጵያን ያዩበት አተያይ አለ። ኢትዮጵያ አሁን “እየፈራረሰች ነው” የሚል ግምገማ አላቸው። በተወሰነ መጠን ትክክል ነው። የዚያን ወቅት ዓይነት ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሯል። ከትግራይ ጋር የተደረገው ጦርነት በውል አልተቋጨም። በአማራ ክልል ያለውን ጦርነት እናውቀዋለን። በኦሮሚያ ውስጥ ያለውንም እናውቀዋለን። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች አገጣጥመው ከ’69 ዓ.ም. ሁኔታ ጋር አመሳስለውታል። አሁን ከሱዳንም ይሁን ከሶማሊያ ጋር ተባብረው፣ ግብጾች በአካል ወደ ድንበሮቻችን እየተጠጉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። በሰሜን በኩል ደግሞ መሳሪያቸው የሆነው ሻዕቢያ -- የዓረብ ሊግ ታዛቢ አባል ነው -- ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር እንዳትጠጋና ዓባይን እንዳትጠቀም እያደረገ ነው። እዚህ ላይ የሚገርመኝ የህወሓቶች ነገር ነው። እንግዲህ ይህ የህወሓቶች አካሄድ የዓባይን ተፋሰስ ማለትም ተከዜንም፣ ባሮንም እንዲሁም ሌሎቹን ወንዞች እንዳናለማ የሚያደርግ ነው። አጼ ዮሐንስ ይህን ተገንዝበው ነው የተዋጉት። የአሁኖቹ ህወሓቶች ግን ከግብጽና ከኤርትራ ጋር ለመስራት እየቋመጡ ያሉት ለራሳቸው ስልጣን ሳይሆን፣ እንዲያው ከስትራቴጂ ጥቅም አንጻር ነገሩን አልተመለከቱትም። ግብጾች ወደዚህ ከተጠጉ፣ እኛ ተከዜን፣ በአጠቃላይ ተፋሰሱን መጠቀም አንችልም። ስለዚህ ለሌላ አገር አሳልፎ የመስጠትና ተወካይ ሆኖ በውክልና ጦርነት ለመሳተፍ ወደ ኋላ አይሉም፤ እኔ እንደተመለክትኩት። ከሻዕቢያ ጋር ለመተባበር ከፈቀዱ እዚያው ላይ ከግብጽ ጋር የማይተባበሩበት ምክንያት የለም፤ ለስልጣናቸው ሲሉ፣ ከስትራቴጂ አንጻር ጥቅማቸውን የሚጎዳ ነገር ሁሉ ሊያደርጉ ስለሚችሉ። የሰሜኑ ሻዕቢያ የታወቀ ነው። በግልጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም ከግብጾች ጋር እየተሰለፈ ነው። ህወሓት ከሻዕቢያ ጋር ዝምድና እንደፈጠረ ራሱ ነግሮናል። በተዘዋዋሪ ከግብጽ ጋር ሊገናኝ ነው ማለት ነው። ይህ ነገር ኢትዮጵያን በምስራቅም፣ በሰሜንም ለማፈን እየተሰራ ያለ ስራ ነው። በትግራይ አንጻር ስመለከተው፣ የግብጾች ጉዳይ ተከዜንም ሆነ ሌሎች ወንዞችን እንዳንጠቀም ወይም ለመቆጣጠር ካልሆነ በስተቀር፣ ወደዚህ የሚመጡበት ሌላ ምክንያት የላቸውም። አጼ ዮሐንስ መክተው ከመለሷት ግብጽ ጋር መሞዳሞድና መሥራት ታላቅ ክህደት ነው ብዬ አስባለሁ።
የጊዜያዊ አስተዳደሩና የህወሓት ፍጥጫ በዚሁ ከቀጠለ የትግራይ ፖለቲካዊ ሁኔታ ወዴት ሊያመራ ይችላል ብለው ይገምታሉ?
በጣም አስቸጋሪ ነው። የትግራይም ይሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከተበላሸና ከተመሰቃቀለ ከራርሟል፡፡ በእኔ ዕይታ፣ ቀውስ ውስጥ ከገባ ቆይቷል። ዓመታትን አስቆጥሯል። የፖለቲካ ቀውስ አለ፣ የማሕበራዊ ቀውስ አለ፣ የአለመረጋጋት አለ፣ የኢኮኖሚው ቀውስ አለ። በአጠቃላይ ሁሉም ዓይነት ቀውስ ያለበት አገር ነው የሆነው። የትግራይን ሁኔታ ስንመለከት፣ ችግሩ በትግራይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ወደ ሌላም አካባቢ የሚዛመት ነው። በዚያ ታጥሮ አይገደብም። የትግራይን ሕዝብ አስቦ ተፈናቃዮችን እንዳይመልስ፣ አስተዳደሩን መልሶ እንዳያዋቅር፣ የወደመው መሰረተ ልማት እንዳያገግም የሚያደርግ የስልጣን ሽኩቻ ነው። ይህ ነገር በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና ይኖረዋል። በህወሓት በኩል ያለው ሽኩቻ እነዚህ ትልልቅ ስራዎች እንዳይሰሩ እንቅፋት የሚፈጥር ነው። በትግራይ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ጸጥታ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በግልጽ የምናየው ነገር ነው። ትግራይ አሁን የሁሉም ዓይነት ችግሮች መገለጫ ሆናለች። የማዕድን ስርቆት፣ የሐብት፣ የመሰረት ልማትና የመሬት ዝርፊያዎች፤ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚታዩባት አካባቢ ሆናለች፤ መንግሥት ስለሌለ። ሁሉም መስተካከል የሚችለው መጥፎም ቢሆን መንግሥት ሲኖር ነው። መንግሥትን በሚጎዳ ጭቅጭቅና ቀውስ ላይ ጊዜ ከተወሰደ፣ በትግራይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ በትግራይ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያም የሚተርፍ ቀውስ ነው የሚሆነው።
ሌላው በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ማየት አለብን። በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ጦርነት ካልቆመ፣ ኢትዮጵያ ችግር ላይ ነች። በእኔ ዕይታ፣ የዚህ ሁሉ ምንጭ የፖለቲካ ችግር ነው። ቁጭ ተብሎ በንግግር ፖለቲካዊ መፍትሔ ማግኘት ካልተቻለ በቀር፣ ሌላ መላ የለውም። ኢትዮጵያ መጠንከር አይደለም ባለችበት ለመቀጠል የሚያስቸግራት ይሆናል። ይህን ያዩት ናቸው ጊዜው አሁን ነው ብለው በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያሰፈስፉት። በትግራይም ይሁን በአገር አቀፍ ደረጃ የውስጡ ፖለቲካው መፍትሔ ካላገኘ በቀር -- (መፍትሔ ሲባል የብልጽግና ፓርቲ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም።) በትግራይም ህወሓት ብቻውን መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም። ሁሉን ያካተተ እውነተኛ ድርድርና ውይይት ተደርጎ የውስጣችንን ፖለቲካዊ ችግር እስካልፈታን ድረስ፣ ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ መቆየት የምትችል አይመስለኝም። የውስጡ እንዳለ ሆኖ፣ የውጭም ተጽዕኖ ተጨምሮበት ከፍተኛ ችግር ላይ ልንወድቅ እንችላለን።
Saturday, 21 September 2024 13:01
አቶ ገብሩ አሥራት፤ ስለ ህወሓት ሽኩቻ፣ ”መሞዳሞድ“፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩና ሌሎች ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች----
Written by Administrator
Published in
ነፃ አስተያየት