Monday, 23 September 2024 00:00

ክብረ በዓላትን ከእልህ ፉክክር እናድናቸው፤ በመንፈስ እንድንድንባቸው!

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

           
          አብዛኛው ሰው፣ ጦርነት ምርር ብሎታል። አንገሽግሾታል። ነገር ግን፣ ጦርነትን የሚያስቆም ዘዴ መፍጠር አልቻለም። ድሮም ቢሆን፣ “ጦርነት ክፉ ነው፤ እልቂት ነው፤ ውድመት ነው” እያለ ማውራት አያቅተውም። ሊያወራ ይችላል። ነገር ግን፣ ጦርነትን መከላከል፣ በሩቁ ማስቀረት አልቻለም።
ምናልባት፣ በሕይወቱና በንብረቱ ላይ እስኪመጣበት ድረስ፣ እልቂቱና ውድመቱ ለዐይኑ ተጋርዶበት ለስሜቱ ርቆበት። ሕይወት ሲቀጠፍና ሲረግፍ በአካል ከተመለከተ በኋላስ? ቤት ንብረት ሲወድምና ኑሮው እየተነቃቀለ ሲፈርስ በዐይኑ ካየ በኋላስ?
የጦርነት ጥፋት፣ ዛሬ በቃላት ብቻ የሚገለጽ ሐሳብ ብቻ አይደለም። በአካል ክፉ ገሀነም ሆኖ መጥቶበታል። የጦርነትን ዘግናኝነት በተግባር አይቷል። በጦርነት የተማረረውም ለዚህ ነው። አዲስ አስተሳሰብ ስለጨበጠ አይደለም። ሕይወት በጦርነት ሲረክስ ስላየ ነው - ጦርነት ያንገሸገሸው። ኑሮ ወደ ስቃይ ስለተቀየረበት ነው።
ጦርነትን የጠላው፣ እጅግ ስለተፈላሰፈ ወይም ድንገት ስለተገለጠለት አይደለም። የፖለቲካ “አቋም” ለውጥ አድርጎ፣ ለሌላ ፓርቲ አድሮ፣ እንደ አዲስ ተጠምቆ አይደለም። ተቃዋሚ ወይም ደጋፊ የመሆን ጉዳይም አይደለም። “ፍትሕ”፣ “ሉዓላዊነት”፣ “ነጻነት”፣ “የግዛት አንድነት”… የሚሉ መፈክሮችን በማስተጋባትም አይደለም።
በጦርነት የተገኘ ትርፍ አላየም። ቅንጣት የለም። ጦርነት ሁሉንም ነገር እያሳጣው እንደሆነ ደግሞ አይቷል። እናም ጦርነት ሰለቸው። ስላየና ስለታዘበ እንጂ በትንታኔና በምርምር ስለተራቀቀ አይደለም። ጦርነት የምድር ገሀነም ስለሆነበት ነው።
እንዲያም ሆኖ ግን፣ ጦርነትን የመግታትና የማስቆም ዘዴ መፍጠር አልቻለም። ዐቅም አላገኘም።
ጦርነት አንዴ ከገቡበት በኋላ በቀላሉ አይገላገሉትም። ጦርነት አንዴ አምልጦ ከተለኮሰ በኋላ፣ በቀላሉ አያከስሙትም። በራሱ ጊዜ እየተቀጣጠለ ይራዘማል፤ ይባባሳል። ጦርነትን በሩቁ ለማስቀረትም ሆነ በፍጥነት ለማስቆም፣ በብርቱ መመርመርና መፈላሰፍ ሳያስፈልገው አይቀርም። ታዲያ የተፈላሰፉና የተመራመሩት የት ጠፉ? እነሱ እስኪገኙ ድረስ፣ ከመሻው ወደ ክፉ ነገር ላለመግባት ጠንቀቅ ብንል አይሻልም?
በክብረ በዓላት ላይ የሚፈጠር የእልህ ፉክክርም ከጦርነት ጋር ይመሳሰላል። አንዴ ከገባንበት በኋላ፣ በራሱ ጊዜ እየሾረ ይጦዛል፤ መውጫው ይጠፋል።

ክብረ በዓላትን እንወዳቸዋለን፤ የእልህ ፉክክራችን ግን ክብርን ያሳጣናል።   
ብዙዎቹ በዓላት ሕጻን ዐዋቂውን ሁሉ የሚያዝናኑና የሚያስደስቱ ናቸው። በእርግጥ ሁሉም አይደሉም። “የትካዜ ስሜትን” የሚፈጥሩ አንድ ሁለት በዓላት ይኖራሉ። የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ወይም ዕለተ ስቅለት፣ የጥሞና በዓላት ናቸው ማለት ይቻላል። መንፈስን የማነጽ ገጽታ ቢኖራቸውም፣ የፌሽታ በዓላት አይደሉም። እንዲህ ዐይነት በዓላት ብዙ አይደሉም።
አብዛኞቹ በዓላት፣ የደስታ በዓላት ናቸው። መውሊድና ልደት፣ ፋሲካና ኢድ አልፈጥር፣ የአዲስ ዓመት በዓልና የዐድዋ ድል በዓል… በብርሃን የደመቁ ወይም ርችት የሚያስተኩሱ በዓላት ናቸው። በሞቀ ዝማሬ ወይም በዘፈን ጭፈራ፣ በቤት ውስጥ ድግስ ወይም በአደባባይ ትርዒት ነው የሚከበሩት። እንደ ሌሎቹ በዓላት መንፈስን ለማነጽ ይጠቅማሉ። በዚያ ላይ ደግሞ መንፈስን ያድሳሉ። በአካልም በስሜትም ደስ ያሰኛሉ።
የወባ ቀን፣ የስደተኞች ቀን… የተሰኙና ሌሎች ተመሳሳይ ስያሜዎች፣ እንደ በዓል መቆጠራቸው ያጠራጥራል። እንደ በዓል ከተቆጠሩም፣ በየትኛው ረድፍ እንደሚመደቡ በትክክል እንደሚመደቡ እንጃ። የጥሞና በዓላት ናቸው ወይም የሐሴት? ምናልባት የወባ ቀን ማለት ፀረ-ወባ ቀን ለማለት ፈልገው ሊሆን ይችላል። የስደት ቀን ማለት ደግሞ ፀረ-ስደት በዓል? ዩኤን የሚሰይማቸውን ቀናት መከተል ከቀጠልን ግን፣ ማለቂያ ላይኖረው ስለሚችል ብንተወው ይሻላል።
ቡሄ፣ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ ሽኖዬ የተሰኙ በዓላትስ? ወይስ ጨዋታዎች ናቸው?… ልጃገረዶች በዘፈን የሚፈነጥዙባቸው የአዲስ ዓመት በዓላትና ጨዋታዎች… “ሸ” የሚል ድምጽ የተጋሩት በአጋጣሚ ይሆን? ትርጉማቸውስ ከምን ጋር የተያያዘ እንደሆነ እርግጡ ይታወቃል?
ለነገሩ፣ ቡሄ እና እንቁጣጣሽ፣ እዮሃ እና አሲና የሚሉ ከአዲስ ዓመትና ከገና በዓላት ጋር የተዛመዱ ቃላትም፣ ትርጉማቸው ሙሉ ለሙሉ ግልጽ አይመስልም። መስከረም የሚለው ስያሜስ፣ ከክረምት ጋር የተያያዘ ነው ወይስ “መዝከር”፣ “መስቃሎ”፣ “መስቃሮ” ከተሰኙ የአዲስ ዓመት በዓላት ጋር የተዛመደ ይሆን?
የሌላው መዝገበ ቃላት፣ መስከረም የሚለው ቃል፣ ከክረምት ጋር ዝምድና የለውም ይላል። “የመስቀል በዓል” ሳይጀመር በፊት ከነበሩ ጥንታዊ በዓላት ጋር የተገናኘ ስያሜ ይሆን? መስከረም የሚለው ቃል፣ “መዝከረ-ዓም” ከሚል ሐሳብ የመጣ ነው ሲሉ ሰምታችሁ ይሆናል። “የዓመት መታሰቢያ” እንደማለት ነው ብለውም ተርጉመውታል። ትክክል ይሆን? ሊሆን ይችላል። ላይሆንም ይችላል።
ሊታወቅ አይችለም ለማለት ፈልጌ አይደለም። በአንጋፋ በዓላት ዙሪያ ብዙ የማይታወቁ ቃላትና ስያሜዎች ያጋጥማሉ ለማለት ያህል ነው። እና ምን ችግር አለው? ምን ይደንቃል? ችግር የለውም። ደግሞም አይደንቅም።
አንጋፋዎቹ በዓላት ጥንታዊ ናቸው። ምዕተ ዓመታትን ያስቆጠሩ የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው። የዕድሜያቸው ያህልም፣ ከዘመን ዘመን ብዙ ገጽታዎችንና ትርጉሞችን፣ ብዙ ዐይነት አከባበርና ሥነሥርዓቶችን እያካተቱ መምጣታቸው አይቀርም። ባያካትቱ ነው የሚገርመው።
ነባር ገጽታዎችን በአዳዲስ መተካትም ይኖራል። አዲስ ገጽታ ቢላበሱም ግን፣ ከጥንት የተወረሱ ቃላትና ዜማዎች፣ የበዓል ስያሜዎችና የአከባበር ሥርዓቶችን ይዘው የሚቀጥሉ ይኖራሉ።
ኢትዮጵያ ደግሞ የብዙ ሺ ዓመታት ባለታሪክ አገር ናት። የአገሪቱ ክብረ በዓላትም የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው።
እናም በዘመናት ርቀትና በምዕተ ዓመታት የታሪክ ጅረት ምክንያት፣ ዛሬ ትርጉማቸውን የማናውቃቸው ቃላትና የግጥም መልዕክቶች ቢያጋጥሙን አይገርምም።
ይልቅስ፣ በቅጡ አለመጠናታቸው ነው አስገራሚው ነገር። ይህም ግን መነሻ ምክንያት ያለው ይመስለኛል። ክብረ በዓላት በብዙ የታሪክ ውርስ የበለጸጉ ቢሆኑም እንኳ፣ ይህን ታሪክ እንደ መልካም ጸጋ አንቆጥረውም። በዘመናችን እምነትና አስተሳሳብ አማካኝነት የተቀረጸ “ንጹሕ” ታሪክ እንዲኖራቸው ነው የምንመኘው።
በእርግጥ የበዓላትን ጥንታዊ ገጽታዎችን በሙሉ ጠብቆ ማቆየትና ማውረስ ተገቢ አይደለም። ጸዳ ጸዳ ያለውን ለመምረጥ፣ ጠቃሚና መልካም ገጽታዎቹን ለማጉላት መሞከር ተገቢ ነው። ባሕልና እምነት፣ ታሪክና አስተሳሰብ እየታነጸ የሚራመደው በሌላ መንገድ አይደለም። ከነባሩ ባሕልና እምነት ውስጥ፣ በጎ በጎውን በማጉላትና በማክበር ጭምር ነው።
የጥንት ሰዎች በየዘመናቸው በነበራቸው የዕውቀትና የኑሮ ዐቅም ልክ፣ በየዘመናቸው ዓመታዊ በዓላትን ካከበሩ፣ የዐቅማቸውን ያህል ሁሉ ፈጽመዋል ማለት ነው። ዛሬ በዕውቀትና በኑሮ ዐቅም ከድሮ እንሻላለን የምንል ከሆነ፣ በዚያው መጠን ከጥንታዊው የበዓል አከባበር ውስጥ በጎ በጎውን እየመረጥንና እያበለጸግን ማክበር ይጠበቅብናል።
አንዳንዴ፣ መንፈስን ከሚያንጹና ከሚያድሱ የበዓል ገጽታዎች ጋር ተቀላቅለው የሚመጡ መጥፎ ገጽታዎችም ይኖራሉ። በበዓል ዋዜማዎች ከወንዝ ማዶና ማዶ ሆኖ ለጸብ የመቆስቆስና የመወራወር ልማድ፣ ከበዓል አከባበር ውስጥ እየቀረ ሲመጣ በጎ ነው።
“ቱባ ባሕልን ጠብቆ ማክበር” በሚል ፈሊጥ፣ አላስፈላጊ ልማዶችን ከዘመን ዘመን እየወረስን፣ እኛም መድገም፣ በተራችን ማውረስ የለብንም።
ለጨዋታ ያህልም ቢሆን፣ የቃላትና የግጥም ዘለፋ በበዓል አከባበር ላይ የተለመደ ስለሆነ፣ በዚያው መቀጠል አለበት ማለት አይደለም። “ክፈት በለው በሩን” የሚል ዐይነት ነውጠኛ ስሜት የያዘ ዓመታዊ የበዓል አከባበር  በደቡብም በሰሜንም በየአካባቢው የሚጠፋ አይመስለኝም።
ልጃገረዶች በቄጤማ አጊጠው፣ ዜማቸውን በከበሮ አድምቀው የሰዎችን መንፈስ ከማደስ ውጭ ሌላ የጸብ ስሜት ላይነካካቸው ይችላል።
በብዙ አካባቢዎች በወንዶች ጭፈራ የተሟሟቁ ክብረ በዓላትስ?
የበዓላቱ ዋና ባሕርይ መልካም መንፈስን የተላበሰ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ በትንሹም ቢሆን ነውጠኛ ስሜት አይጠፋውም። ያያችሁትን መስክሩ። በበኩሌ ግን፣ እስከዛሬ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያየኋቸው የወንዶች ጭፈራዎች በሙሉ አንድ ተመሳሳይ ነገር አላቸው - ዱላ ማወዛወዝ።
የሁሉም አካባቢ ልማድ ይመስላል። ጩቤም ሊኖር ይችላል። እንዲህ ስል ግን፣ ዱላ መያዝ የነውጠኞች ምልክት ነው እያልኩ አይደለም። እንዲያውም፣ በቀድሞው ዘመን ዱላ መያዝ የግድ ነው።
ሕይወቱንና ክብሩን የወደደ ሰው፣ ዱላ ይጨብጣል። ዱላ አለመያዝ ለጥቃት ያጋልጣል፤ ለነውጠኞች ይመቻል። እናም ዱላ መጨበጥ ከነውጠኝነት ስሜት ጋር ብቻ የተቆራኝ ላይሆን ይችላል - ድሮ ድሮ። ግን እስከዛሬ አልተቀየረም። “እና በዱላ ምትክ ክላሺንኮቭ ያወዛውዙ?”
እኔ አላልኩም። እንደዚያ ከሚሆን በዱላ መሬት እየተመተሙ ሆያ ሆዬ ቢሉ ይሻላል። ቢሆንም ግን፣ በጎ በጎውን እየመረጡ፣ የማይጠቅመንን ደግሞ እየተውን ብንሄድ መልካም ነው።
ቢሆንም ግን፣ የአበባየሆሽ ግጥም ለመቀየር ዘመቻ ማካሄድ ማለት አይደለም። “በጨዋ ትምህርትና በግብረገብ ሐሳቦች” የታጨቀ አሰልቺ ግጥም፣ ከጥቅሙ ጥፋቱ ይበልጣል። እንደ ነበረ ቢቀጥል ይሻላል።
በዚያ ላይ ጥንታዊውን አከባበር መርሳትና እንዳልነበረ አድርጎ ማስረሳት ተገቢ አይደለም። ታሪክ ነው። የክብረበዓላት ታሪክ ሲታወቅ፣ ክብራቸው ይጎላል። ታሪክ ስናውቅ ለክብረ በዓላት ያለን ክብር ይጨምራል። የክብረ በዓላትን ታሪክና የዘመናት ውርስ አለማወቅ ወይም መርሳት፣ ኪሳራ ነው። መቅለል ነው።
በጊዜያዊ የአስተሳሰብ ወረት ተገፋፍተን፣ በጊዜያዊ የፖለቲካ ስሜት ሰክረን፣ ክብረ በዓላትን “ለወቅታዊ አጀንዳ አመቻችተን እንቅረጻቸውና እንጠቀምባቸው” ብለን የምናስብ ከሆነ፣ መንፈሳችን ይሳሳል፣ ይገረጣል።
ለወቅታዊ አጀንዳና ለዘመናችን ስሜት የማይስማማ ስለሆነ ብቻ፣ የክብረ በዓላትን ታሪክና ነባር ውርስ ለማድበስበስ፣ ለመርሳት ወይም ለማስካድ መሞከር፣ የታሪክ ባለጸጋነትን የሚያዋርድ ቀሽም ስህተት ነው። ቀሽም ቢሆንም ግን፣ ከስህተት የዳንን አይመስለኝም። የክብረ በዓላትን ታሪክ ለማጥናት ብዙም ሙከራ የማይደረገውስ ለዚያ አይደለም?
ክብረ በዓላትን፣ በወቅታዊ አጀንዳና በወረት ፖለቲካ መነጽር ስለምናያቸው፣… ወይም በጊዜያዊ ስሜት “ልንጋርዳቸው” ስለምንሞክርም ነው፤ አስቀያሚ የበዓል አከባበር “ፉክክር” የሚፈጠረው።
የበዓል አከባበር ፉክክር? ምን ለማትረፍ? ምንም።
አላስፈላጊ የበዓል አከባበር ፉክክር ውስጥ የምንገባው ጥቅም ኖሮት አይደለም። አላስፈላጊ የጥላቻና የጸበኝነት ስሜትን እየዘራን ለማዛመት እንጂ፣ ሌላ ምንም ትርፍ የለውም።
አስቀያሚውን ፉክክር ከጀመርን በኋላ፣ መጥፎነቱን ማየት ብንችልም እንኳ፣ “ፉክክራችንን” መግታት ይከብደናል። እንደ ውርደት ሆኖ ይታየናል። ከፉክክር ከወጣን፣ ክብረ በዓላችንን ያቀለልን የካድን ሆኖ ይሰማናል። እናም ወደ ጥፋት እንደሚያመራ እያየን፣ በዚያው ፉክክር እንቀጥላለን።
የምንወዳቸውና የምናከብራቸው በዓላት፣ መንፈሳችንን የሚያድሱና በበጎ ስሜት የሚያቀራርቡ መሆን ሲገባቸው፣ በእልህ ስሜት የሚያብሰለስሉና በጥላቻ መንፈስ የሚያንገበግቡ ዕዳዎች ይሆኑብናል።
የምናከብራቸውን በዓላት በአግባቡ ማክበር እንዴት እንደሚያቅተን ይታያችሁ።

በሌላ አቅጣጫ ለመረዳት፣ ከእግር ኳስ ፍቅር ጋር አነጻጽሩት።
የእግር ኳስ አድናቂዎች፣ ስታድየም ገብተው በሰላም መታደምና የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን መመልከት አልቻሉም። ለምን? እዚህ ላይም አላስፈላጊ የእልህ ፉክክር አለ። እግር ኳስን መውደድና ማድነቅ ማለት እንደዚህ ነው?
በእግር ኳስ ሰበብ አላስፈላጊ የእልህ ፉክክር ውስጥ በመግባት ነው የእግር ኳስ ፍቅር የሚገለጸው?
ብዙ ሰዎች እንደዚያ መስሏቸው ነበር። የእልህ ፉክክር ግን አንዴ ከተጀመረ በኋላ፣ የራሱ እግር አለው። ወደ ብሽሽቅና ወደ ስድብ ይሸጋገራል። ወደ ጸብና ወደ ድብድብ ይሮጣል። እንዲያውም ስታዲየም የእግር ኳስ ጥበብ የሚታይበት መድረክ መሆኑ ይቀርና፣ ሌሎች የእልህ ፉክክሮችን እየጋበዘ የሚጠራ፣ እየጎተተ እያግተለተለ የሚያመጣ የጸብ መናኸሪያ ይሆናል።     
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የእግር ኳስ ወዳጅና አድናቂ አለ ይባላል። ነገር ግን፣ የወደዱትንና ያደነቁትን ነገር በሰላም ማጣጣም የሚችሉበትን ዘዴ ለመፍጠር አልቻሉም።
ክብረ በዓላትስ? ብዙ ኢትዮጵያዊ ክብረ በዓላትን ይወዳቸዋል፤ ያከብራቸዋል። በአላስፈላጊ የእልህ ፉክክር ክብረ በዓላትን የሚበክላቸው ከሆነ ግን፣ በክብረ በዓላት የመደሰት፣ መንፈሱን የማደስና በበጎ ልቦና የመቀራረብ ጸጋ ያጣል።
አላስፈላጊ የእልህ ፉክክር፣ ከመነሻው ካልተከላከሉት ወይም በሩቁ ካላስቀሩት፣ አንዴ ካራገቡት በኋላ በቀላሉ አይረግብም። አንዴ ካንደረደሩት በኋላ የራሱ መንገድ አለው። እንደ ዋዛ ሊጀመር ይችላል። ግን እንደ ዋዛ አይገቱትም።



Read 394 times