በአለም አቀፍ መረጃ መሰረት ከ6 ጥንዶች አንድ ጥንድ የመውለድ ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ቀደም ባሉ ህትመቶች አስነብበናል፡፡ በእርግጥ እንደየሀገራቱ ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን ከስምንት አንድ ወይንም ከአስር አንድ በሚባል ደረጃ ጥንዶች ልጅ ለማግኘት ከባድ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን በታዳጊ ሀገራት ከስድስት አንድ የሚሆኑ ጥንዶች በእርግጠኝነት ልጅ መውለድ አይችሉም፡፡ ይህም በጣም ትልቅ ቁጥር በመሆኑ በአሁኑ ወቅት መውለድ አለመቻል በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ አንድ ትልቅ በሽታ የሚቆጠር ሆኖአል፡፡ ይሄ ጉዳይ ከአሁን ቀደም ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን በዙሪያው ያሉ ነገሮችን በመመራመር መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ነገሮች በሳይንሱ ዘርፍ ስፍራን አግኝቶአል፡፡ በዚህ ዙሪያ ለዚህ እትም መልስ እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው ባለሙያ ዶ/ር ሙህዲን አብዶ የማህጸንና ጽንስ ህክምና እስፔሻሊስትና በአሁኑ ወቅት በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የስነ ተዋልዶና ኢንፈርቲሊቲ በሚባለው ትምህርት ክፍል ለሁለት አመት ያህል ትምህርታቸውን ተከታትለው ለመመረቅ በዝግጅት ላያ ያሉ አንጋፋ ሐኪም ናቸው፡፡
ዶ/ር ሙህዲን እንደሚያምኑት እና በየህክምናው አጋጣሚም እንደሚስተዋለው መካንነት የሚከሰተው በሴትዋ እንጂ በወንዱ አይደለም የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ናቸው፡፡ ሴትየዋ መውለድ ባለመቻልዋ እንጂ ወንዱ መውለድ ሳይችል ቀርቶ አይደለም የሚለው የብዙዎች እምነት ነበር፡፡ በዚህ ላይ ወደሁዋላ ፈቀቅ ብሎ የሰዎች ድርጊት ምን ይመስል እንደነበር ማስታወስ ሁኔታውን ለመገንዘብ ይረዳል ብለን እናምናለን፡፡ የአንድ የእትማችን አንባቢ የሆኑ ሴት የነገሩኝ ነው፡፡ ነገሩ እንደሚከተለው ነው፡፡
‹‹….በስራ አጋጣሚ የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ አንድ ቀን ወደ ስራ ስንገባ ሁለቱም ጉዋደኛሞች በስራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም፡፡ ምን ሆነው ነው ሲባል ትንሽ የጤና ችግር ገጥሞአቸው ነው ተባለ፡፡ እኔ ግን በተለይም አንዱን እቀርበው ስለነበር ሁኔታውን ሳጣራ ያንን ጉዋደኛውን ከሴት ጋር ለማስተዋወቅ ሲል እንደመሸባቸውና ትንሽ መጠጥ እንደቀመሱ ነገረኝ፡፡ ለምንድነው …እቤት ያለችው ሚስቱስ….ስለው…አ..አ..ይ…እሱዋማ ልጅ አትወልድም አለኝ፡፡ በጣም አዘ ንኩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሰውየው ከሌሎች ሴቶች ጋ ተመላልሶ ልጅ ማግኘት ሲያቅተው በቤተሰቡ ሌላ ሙከራ ተደረገ፡፡ እህቶቹ ከገጠር መጥተው የማትወልድ የተባለችውን ሚስቱንሴ አባርረው ሌላ ሚስት አስቀምጠውለት ሄዱ፡፡ ያቺ የተባረረች ሴት ከሌላ ወንድ ጋር ተጋብታ አመት ሳትቆይ እንዲያውም መንታ ወለደች፡፡ ይህች ሰውየው ሁለተኛ ሚስት አድርጎ ያገባት ሴት ግን አልወለደችም፡፡ የሰውየውን እህት አግኝቼ ሳናግራት የነበራት መልስ….እኛ በዘራችን መሐን የለም፡፡ ወንድሜ የሚያገኛቸው ሴቶች መሀን ሆነው ተቸገርን እንጂ እሱማ መሀን አይደለም የሚል ነበር መልሱዋ ፡፡ ሰውየው ህክምናም ሳያውቅ እንግዲህ አረጀን፡፡ ከስራችንም በጡረታ ተገለልን ፡፡ እስከ አሁንም አልወለደም….›› የሚል ነበር ያኘሁት መረጃ፡፡
ዶ/ር ሙህዲ …ከላይ የተሰነዘረውን አስተያየት ይጋራሉ፡፡……እኛም የህብረተሰቡ አካል እንደ መሆናችን ይህንን እንገነዘባለን፡፡ ከህክምናው ጋር በተያያዘም ብዙ ጊዜ የሚገጥሙን አታካራና ክርክሮች ይህን የመሰሉ ናቸው፡፡ ልጅ ካለመውለድ ጋር በተያያዘ የማህበረሰቡ ግፊትና ጫና የሚበዛባቸው ሴቶች ናቸው፡፡ ለምርመራ ሴቶች ሲቀርቡ ወን ዶቹ አይመጡም፡፡ በእርግጥ አሁን አሁን ብዙ የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸው ወንዶች ቢኖሩም ቀደም ሲል ግን እኔ ስለመ ካንነት አያገባኝም፡፡ የራስሽ ችግር ነው፡፡ ሂጂና ታከሚ የሚሉ ወን ዶች በርካታ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ካልተመረመሩ መፍትሔውን ማግኘት ያስቸግራል፡፡
መካንነት የሴት ብቻ ችግር ሳይሆን የወንዶችም ችግር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በህክምናው አለም ለመካንነት ምክንያት የሚሆነው ችግር የማን ከማን የበለጠ ሆኖ ይገኛል ሲባል የወንዶች መካ ንነት ችግር ከሴቶች ጋር ባልተናነሰ ሁኔታ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ይህ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በብዙዎች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ፤በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ ሀገራት ጭምር በእኩል ደረጃ እንዲያውም አንዳንድ ሀገራት ላይ የወንዶች የመካንነት ምንያት ከሴቶቹ በልጦ የሚገኝበት መረጃ አለ፡፡
የወንዶች መካንነት ፡-
በምእራብ አውሮፓ……..50%
አሜሪካ………………….50%
በደቡብ አሜሪካ ……….52%
በኤሽያ በጠቅላላው……..32%
አውስትራሊያ……………40%
አፍሪካ ………………….ከ40-43%
መካከለኛው ምስራቅ …..ከ60-70%
ከላይ የተገለጸው ወንዶች ለመካንነት ምክንያት የሚሆኑበት ድርሻ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጋ መካንነት በሴቶችና ወንዶች እኩል በእኩል የሚከሰት ሲሆን አንዳንድ ሀገራት ደግሞ በመጠኑ የወንዶች መካንነት ከሴቶች ዝቅ ይላል፡፡ አንዳንዶቹ ጋ ደግሞ በሚያስደነግጥ ሁኔታ የወንዶች መካንነት ከሴቶች ይልቅ ከፍ ብሎ ይታያል፡፡
ዶ/ር ሙህዲን እንዳሉት ምክንያቶቹ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በአለም የጤና ድርጅት እንደሚታ መነው ወንዶች የዘር ፍሬ እንዳይኖራቸው ወይንም ልጅ መውለድ እንዳይችሉ ምክንያት የሚሆኑአቸው አብዛኞቹ ነገሮች የማይታወቁ ተብለው ይገለጻሉ፡፡ ከ40% - 50% የሚሆኑት የወንዶች መካንነቶች በቅጡ ምክንያታቸው ይህነው ብሎ ለመለየት የሚያስቸግሩ ናቸው፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን ከወንድ የዘር ፍሬ የማምረት ኡደት ጋር በተያያዘ ለምሳሌ እንየደም ዝውውርን የሚገቱ ቴስቲኩላር ቫሪኮስ የመሳሰሉ በቀዶ ህክምና የሚስ ተካከሉ ህክምናዎች አሉ፡፡ ከጊዜ በሁዋላም ይሁን በተፈጥሮ የዘር ማምረቻው ጨርሶ ለማምረት አለመቻል፤የወንድ ስርአተ ኡደት የዘር ፍሬ የሚያስተላልፈው ቱቦ መዘጋት፤ኢንፌክሽኖች፤ከውስጥ ደዌ ጋር በተገናኘ ፤ከአኑዋኑዋር ፤የአፈጣጠር ችግር፤ከቀዶ ህክምና ጋር በተያያዘ፤…ወዘተ የወንድ የመራቢያ አካልን ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ከተጠቀሱት ውጪ የወንድ የዘር ፍሬ በቂ መጠንና ቅርጽ እና ፍጥነት አለመኖርም ሌላው ለመካንነት የሚያጋልጥ ምንያት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ከዚህ ውጪ ከአመጋገብ ወይንም ከባህርይ ጋር በተያያዘ የወንዶች መካንነት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ለምሳሌም በአንዳንድ አኑዋዋሮች የሚታዩት ነገሮች ከልክ በላይ ውፍረት መጨመር እና በዚህም ሳቢያ እንደ ስኩዋር ላሉ ተጉዋዳኝ በሽታዎች መጋለጥ ይኖራል፡፡ ይህ መነሻ ሆኖ ህመሙን ለማስታገስ የሚረዱ የህክምና አይነቶች፤የሚወሰዱ መድሀኒቶች፤ የአልኮሆል መጠጥ በብዛት መውሰድ፤ጫት ከመጠን በላይ መውሰድ የመራቢያ አካላት ስርአተ ኡደትን በከፍተኛ ሁኔታ ያዛባል፡፡ ከዚህም ውጭ ከመጠን በላይ ሲጋራ ማጤስ እንዲሁም የተለያዩ እጾችን መውሰድ፤ወጣቶች የሚወስዱአቸው አንዳንድ መድሀኒቶች፤ በዘመናዊ አኑዋዋር እንኖራለን ሲሉ የሚደፍሩአቸው ልምዶችም ለወንዶች መካንነት መንስኤ ይሆናሉ፡፡
የመካንነት ችግርን ለማወቅ የሚደረጉት ምርመራዎች የወንዶቹ እንደሴቶቹ ከባድ አይደለም፡፡ በቀላሉ ምክንያቱን ለመለየት የሚያስችል አሰራር ነው የሚተገበረው፡፡ ህክምናውን ለማድረግ የመ ጀመሪያው አካሄድ ምክንያቱን ማወቅ ነው፡፡ የባህርይ ለውጥ በማምጣት፤ ሱስን በማስወገድ ፤የአ ኑዋ ዋር ዘዴን በማስተካከል፤ ክብደትን በመቀነስ ፤የአመጋገብን ስርአት በማስተካከል ብቻ መካንነ ትን ማስወገድ ይቻላል፡፡ከዚያ ካለፈ በመድሀኒት ተስተካክሎላቸው የሚወልዱ ይኖ ራሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ካለፈ ግን በ IVF ከወንዱ የዘር ፍሬ ተወስዶ ከሴትዋ እንቁላል ጋር ተዋህዶ በላቦራቶሪ እገዛ ልጅ እንዲወልዱ ማድረግ ይቻላል ብለዋል ዶ/ር ሙህዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡
በአጠቃላይም መካንነት የሴቶች ችግር እንጂ የወንዶች ችግር አይደለም የሚለው አስተሳሰብ ከምን መጣ የሚለውን ስንመለከት ሲወርድ ሰወራረድ የመጣው የህብረተሰቡ ልማድ ወንዶችን ከምንም ችግር ጋር ያለማያያዝ ፤ከበሬታ የመስጠት ፍላጎት ወይንም ልማድ ጋር የተያያዘ ይመስላል፡፡ በማህበረሰቡ አስተሳሰብ ፤በትምህርት ሁኔታ፤በሀይማኖት…በመሳሰሉት ደረጃዎች ሲገለጽ ወይንም ሲታመንበት መኖሩ አይካድም፡፡ ከጥቂት አስርት አመታት ወዲህ ግን እንደቀድሞው ሳይሆን ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ ወንዶች ከሚስቶቻቸው ጋር ለምርመራው ስለሚቀርቡ የመካንት ችግሩ በቀላሉ ይፈታል ብለዋል ዶ/ር ሙህዲን በስተመጨረሻው፡፡
Saturday, 21 September 2024 13:15
መካንነት--- ከስድስት--- በአንድ ጥንድ፡፡
Written by ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Published in
ላንተና ላንቺ