Saturday, 21 September 2024 13:14

“ከእኔ ሥልጣን ይልቅ የሀገሬ ደኅንነት ይበልጣል”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

  ስለ ሀገር ብዙ አባባል፣ሺህ መፈክር እልፍ ትንታኔ ሰንሠማ ስንሰማ ስለኖርን እንደ አዲስ ማውራት ያስፈልገናል ብዬ አላምንም። ምናልባት የደርጉ ዘመን ከሌሎቹ ይልቅ ሀገርን የእናት ያህል ቅርብ አድርጎ በማንጸር፣ ጡት ያጠባች ወላጅ አድርጎ፣ነፍሳችንን እንድንሰጣት ሰብኮናል፤ወንጌላችን ሆና በአደባባይ ዘምረን፣ በጓዳ ተቀኝተናል። ይሁን እንጂ አንዳችንም ገቢራችን የወሬያችንን ያህል አልሆነም፤መስዋዕትነታችን በእሳት አልተፈተነም። አንዳችንም “ከሀገሬ በፊት” ብለን ራሳችንን አልሰጠንም።
በርግጥ ኢትዮጵያ ለሺህ ዐመታት በነገሥታት የምትተዳደር፣ሥርዐተ- መንግሥቷም ሥር የሰደደ ሀገር ስለነበረች፣ነገሥታቱ ዳር ድንበሯን በማስከበር እስከ ሞት ዘልቀዋል። ይሁን እንጂ ከሀገርና ከባንዲራ ክብር ጀርባ የየራሳቸው ክብርና ዝና እንዳለ አይካድም። አንዳንዴም እነርሱ የራሳቸውን ጥቅም፣ሥልጣንና ዝና በማስቀደማቸው ሀገሪቱ መትረፍ ከምትችልበት አደጋና ማትረፍ ከምትችለው ነገር ጎድላለች።
አፄ ዮሐንስ ሀገራቸውን ከሥልጣናቸውና ሹመት አነሰኝ ካሉበት ጉድለት በላይ አድርገው ቢያዩ፣አፄ ቴዎድሮስ ሞተው የሀገሪቱ አንጡራ ሀብትና የታሪክ ድርሳናት ባልተዘረፉ ነበር። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ እርሳቸውም ተራ ደርሷቸው ንጉሠ ነገሥት በነበሩ ጊዜ፣ እግር የሚለካኩት የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ሥልጣናቸው ባይበልጥባቸውና በምጽዋው ጦርነትና በደርቡሾች በኩል ቢቆሙላቸው፣እስከ ዛሬ የመጣብን ችግር  ላይፈጠር ይችል ነበር። አጠቃላይ ታሪካችንን ስንገመግም፣እስካሁን የሀገራችን መሪዎች “እናት ሀገር” የሚሏት ራሳቸው የሚገዟትንና የሚቆጣጠሯትን ኢትዮጵያን ነው።
ነገሥታት ብቻ ሳይሆኑ ያኮረፉ መሳፍንትና መኳንንት በየዘመኑ ከጠላት ጋር በማበር ሀገራቸውን ለመውጋት የተሰለፉት በዚሁ መዘዝ ነው። አንዱ ከሌላው ባዕድ ጋር ሆኖ የገዛ ወገኑን የወጋውም ለዚያ ነው። ስለዚህም፣ብዙዎቹ ስለሀገራቸው ዋጋ ከመክፈል ይልቅ ሀገራቸውን ዋጋ አስከፍለዋል።
ይሁንና አንዳንድ የጦር መኮንኖች ግን ከራሳቸው ሕይወትና ምቾት ይልቅ የሀገራቸውን ክብርና ልዕልና መርጠው፣ነፍሳቸውን ሰጥተዋል። ያዋረዳቸውን የፖለቲካ ሥርዐት ታግሰው በክፉ ቀን ለሀገራቸው አጥር ሆነው ቆመው፣እንደ እሳት ነድደው አልፈዋል። የኮሎኔል አብዲሳ አጋ አይነቱና መሰሎቹ እንዲሁም በደርጉ ዘመን በኤርትራ ምድር ያለፉ ጦረኞች፣ ውርደት መቀበል ጠልተው ሽጉጣቸውን ጠጥተው አልፈዋል። በሀገራችን ጉልህ ታሪክ ያላቸው ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስም ከአርበኞች ጋር ሆነው ጠላትን ለማጥቃት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በፋሽስቶች እጅ ወድቀው፣ባርነትን ተቃውመው፣በጀግንነት መሞታቸው ሌላው የታሪካችን ገጽታ ነው።
ይሁንና በሌላ በኩል፣ሥልጣን አጠገብ ደርሰው፣ዙፋኑ ደጅ ተጠግተው፣ “ሀገሬ ከምትመሳቀል እኔ ይቅርብኝ፤ክብሯ ከሚገሰስ የኔ ክብር ይቅር” የሚሉ ልጆች በማጣቷ እስከ ዛሬ ባሩድ እየታጠነች፣ወጣቶቿን እንደ ችቦ እየማገደች ትኖራለች።
በተደጋጋሚ በታሪክ እንደታየው፣በፖለቲካ ለውጥ ሰሞን ስለ ለውጥ የሚያወሩና ለሕዝብ የሚሟገቱ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች  ፍላጎታቸው የሀገርን ጉዳይ ማስቀደም ቢመስልም፤ልባዊ ስላልሆነ ለሥልጣን መገፋፋትና “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል አፈሙዝ የሚማዘዙ ሆነው ታይተዋል። ለምሳሌ በላይ ዘለቀ በእንጨት ሲሰቀል፣ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ ቆሞ ሲያሰቅል፤መንግሥቱም ሲሰቀል ቆሞ ያሰቀለ ሌላ ተረኛ ነበረ። ሁሉም በየተራው የተሰቀለው፣ሥልጣኑን ከሀገሩ በታች የሚያደርግ ስለጠፋ ነው።
በሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ንጉሡ ሀገር ጥለው ሄደው ሲመለሱ፣ሥልጣን ላይ የተፈናጠጡት፣አርበኞች ብቻ አልነበሩም፤ከጣሊያን ደሞዝ እየተቆረጠላቸው አርበኞችን ያሳደዱ ባንዳዎች ነበሩ። ይህም የሆነው የንጉሡን የሥልጣን ሚዛን ለመጠበቅ እንጂ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከንጉሡ ሥልጣን በላይ ሆኖ አልነበረም።
ይሁንና ንጉሡ ከተመለሱ በኋላ “አሻፈረኝ፣ንጉሡ የከዷትን ሀገር መልሰው ሊገዙ አይገባቸውም”ብለው እስከ መጨረሻው የተፋለሙ እንደእነ ብላታ ታከለ ወልደሐዋርያት ያሉም አሻፈረኝ ባዮች ነበሩ። ይሁንና የአንዳንድ ሀገራትን ታሪክ ስናይ ሀገራቸውን ከሥልጣናቸው በላይ፤ክብራቸውን ከሀገራቸው በታች አድርገው ታሪካቸውንና ሀገራቸውን በክብር ሲያቆዩ፣ ሰናይ መንፈሳዊ ቅንዐት ይሰማናል።
ከነዚህ አብነቶች መካከል ልጆቿ በታላቅ ተጋድሎና መሥዋዕትነት ታሪኳን ትልቅ አድርገው ከሠሩላት አሜሪካ ብዙ እንማራለን። የነፃነትን አዋጅ አርቅቀው በግንባር ከተዋጉላት መሥራች አባቶች ጀምሮ፣ለአንድነቷ መቀጠል፣ለብሔራዊ ልዕልናዋና ብልፅግናዋ መስፈን ሕይወታቸውን የሰጡና ለስሟ ሲሉ ስማቸውን የተውትን ውዶች  እናስባለን። እነዋሽንግተን፣ አዳምስ፣ ጀፈርሰን፣ ሐሚልተን፣ ፍራንክሊንና መሠል ሰዎችን ትተን ከበርካታ ዐመታት በኋላ ብቅ ብለው ፌዴራል መንግሥቱ እንዳይፈርስና ግዛቶቿን ጠብቃ በነፃነትና እኩልነት፣ በኅብረት እንድትኖር ያደረጓትን ልጆቿን ለማስታወስ ከታሪክ ጥቂት እንዘግናለን።
ከነዚህ መካከል አንዱና ሊታወሱ የሚገባቸው በ1850 ዓ.ም የአሜሪካን ፌዴራሲዮን ለማጠንከርና ከመፍረስ ለማዳን በሚል በጎጥና በወገን ተከፋፍሎ የቆመውን አስጊ ሁኔታ ለመለወጥ ሲሉ፣የቆሙበትን ወገንና አካባቢ በመተው፣መራራ ለመጋት ወስነው፣አንዲት ጠንካራ ሀገር መፍጠር ይሻላል በሚል፣በአሜሪካ ታሪክ ዝነኛ የሆነውን “የመጋቢት 7 ቀን ንግግር” በማድረግ የሀገሪቱን የዘመመ አንድነት፣ወደጠበቀ ኅብረት እንዲለወጥ ያደረጉት ሴናተር ዳንኤል ዌብስተር በግንባር ቀደምትነት በታሪክ የሚዘከሩ ናቸው።
የንግግራቸው ዐቢይ ጉዳይ በአሜሪካ ውስጥ የሚደረገውን የእርስ በርስ ጦርነትና የውስጥ ለውስጥ መቆራቆስ የሚቃወም ሲሆን፤ንግግራቸው የማያስደስታቸውና እንደከዳተኛ የሚቆጥሯቸው የአካባቢያቸው ሰዎችም ነበሩ። ይሁን እንጂ ለዌብስተር ሁሉም ከሀገር አይበልጡም። ይህ የአካባቢያዊነት ፈተና ከሀገር ክብር በታች አድርገው ካላዩት እጅግ ፈታኝ ነው። እንኳን እኚህን አንድ ሴናተር ቀርቶ፣ፌደራል መንግሥቱን በጽኑ ይደግፍ የነበረውን ጀነራል ሮበርት ሊ ን ቨርጂኒያዊነቱ ጠልፎት፣የአንድነት ኀይሉን እንዲወጋ አስገድዶታል።
ከዌብስተር እንዳየነው፣ለዚህ መድኀኒቱ አንድ ነው፤ራስን ስለ ሀገር መስጠት፤ክብርን ስለ ሀገር ክብር መተው!
እንደዚያ በአደባባይ መከራ የተቀበሉላት  ሀገራቸው ግን ለእርሳቸው  እንደዚያ ነበረች?...በፍፁም!...ደሞዛቸው ለተሻለ ኑሮ የምትበቃ ስላልሆነ ደሃ ነበሩ። ሲሞቱ እንኳ ዕዳ ነበረባቸው። ግን የሕዝብ ተወካይነቱ ሥራ ባይኖርባቸውና ያንን ባያስቀድሙ፤በግል የሕግ አገልግሎት ቢሰጡ ኑሯቸው የተሻለ ይሆን ነበር። ለእርሳቸው ግን ይህ ሀገር ቀደመ። ጓደኛቸው ያቀረበላቸውን ሐሳብ ይዘው ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ የፖለቲካ አቅጣጫ ተቀየረ።
እርሳቸው ግን ያጡት ቀላል አልነበረም። የፖለቲካ አቋማቸውን በመቀየራቸው ብዙ ጓዶቻቸውን ከማጣታቸው ባሻገር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመሆን ዕድላቸውን ገደል ከቶታል። እርሳቸው ግን “ፌዴራሲዮኑ ከሚፈርስና የአሜሪካ አንድነት ከሚጠፋ፣የራሴ የግል ምኞትና እንጀራዬም ቢዘጋ ግድ የለኝም” በማለት ነገሩን ደመደሙት።
ኢትዮጵያን እንዲህ ያላት፣“እኔ ተዋርጄ አንቺ ክበሪ”በማለት ቀኝዋ የቆመ፣በተለይ ሥልጣኑን ጥሎ “አንቺ ብቻ ኑሪ!”ያለ ይኖር ይሆን?...አይመስለኝም። ስለዚህ ጉዳይ ሳስብ እኛ ሀገር ንጉሥ-ከንጉሥ ጋር፤ደርግ፣ከደርግ ጋር፤ኢሕአፓ-ከኢሕኣፓ፤ወያኔ-ከወያኔ ጋር የተባላውና የተናጨው ትዝ ይለኛል፤አሁንም ያላባራው ሕመም ይኸው ይመስለኛል።
ሀገርን ከሥልጣን በላይ አድርገው፣ወንበራቸውን ከገፉ፣ምርጫቸውን ትተው “ሀገሬ ሰላም ትሁን” ካሉት መካከል አንድ የማደንቀው ቻይናዊ አለ። ይህ ቻይናዊ ማኦ ዜዱንግ ወደ አደባባይ ከመምጣቱ በፊት የጨቋኙን ሥርዐት ሲታገሉ ከነበሩት ቻይናውያን መካከል አንዱ ሲሆን፣ሀገር በምጥ ውስጥ ስትገባ “ከእኔ ሥልጣን ይልቅ የሀገሬ ደኅንነት ይበልጣል”በሚል ሥልጣኑን ይቅርብኝ ያለ ነው።
“Mao Zedung’s China” የሚለው መጽሐፍ፣ “ሰን/sun” ስለሚባለው ግሩም ሰው ያሰፈረውን እንዳለ አስቀምጣለሁ፦
Sun was proclaimed leader of the new government by his supporters. Yuan, a strong military leader, dominated northern China, and wanted to be a head of a government established in Beijing. To avoid civil war, Sun agreed to a Yuan allow to head the government, with Beijing as Capital.
እንግዲህ ሀገር መውደድ ለእኔ ይህ ነው። ከራስ ጥቅም ይልቅ ሀገርን ማስቀደም። ከዚህ ውጭ በአንደበት ብቻ መፎከር፤ማቅራራትና መሸለል አይደለም። ይልቅስ እንደ ክርስቶስ የሚገባንን፣እንደማይገባን መቁጠር!
አንዳንዶቻችን ሀገራችንን በብር፤ሕዝባችንን በጥቅማ ጥቅም፣መሸጥ ካልተውን የእኛም ታሪክ፣የሀገራችንም ክብር ከንቱ ይቀራል። ስለዚህ ሀገር በታሪክ ሚዛን ስትቀመጥ እንዳትቀልልና ስሟ እንዳይጎድፍ፣በድኽነትም እንዳትመታና እንዳትዋረድ መራራውን ዋጋ መክፈል ያለብን ይመስለኛል። ታዲያ...በአንደበትና በቃል ብቻ ሳይሆን፣ለኢትዮጵያ ክብር ምቾታቸውን የሚገድሉ፣ሥልጣናቸውን የሚሰው ሰዎች የምናገኘው መቼ ነው?...
ጽሑፌን ስቋጭ ግን በቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ አንድ ዐረፍተነገር ነው፤እንዲህ፦
“አገሩን አፍቃሪ የሆነ ሰው ትግሉና ሩጫው ሁሉ ለትውልድ በሚሆን ነገር እንጂ ለራሱ በሚሆን ነገር ገንዘብና ርሥት ለማግኘት፣ በጠቅላላው ሀብት ለማድለብ ስላልሆነ ዛሬ በሞት የሚያልፈው ሰው የማይሞትና የማያልፍ፣ ለትውልድ የሚሆን ነገር ሠርቶና ትቶ መሄድ አለበት፡፡”
ግን ለዚህች ምስኪን ሀገር ሥልጣኑን በመተው ምኞቱን የገደለ፣ወይም የሚገድል ማነው?...
ከአዘጋጁ፡-
ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ መጣጥፎችን አስነብቧል፡፡ በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና አቅርቧል፡፡ ደረጀ በላይነህ ገጣሚና አርታኢም ነው፡፡ 12 ያህል መጻሕፍትን አሳትሞ  ለአንባቢያን አድርሷል፡፡



Read 896 times