Saturday, 21 September 2024 13:29

መኃልይ ዘመንበረ ማርያም! (የመጽሐፍ ዳሰሳ)

Written by  በዙፋን ክፍሌ
Rate this item
(1 Vote)

 የመንበረን “የጊዜ ሠሌዳ” አነበብኩ። ሳነበው ሙዚቃውና ወዙ በል ፥ በል አለኝ። ልል ስነሳ ደሞ ይተወኛል። በዚህ መሃል ጸደይ ወንድሙ(ዶ/ር)፣ በማሕበራዊ ሚዲያ መጽሐፉን ከሮማንቲሲዝም አንጻር  በምሕጻር(ባጭር) ብላ ያቀረበችውን ዳሰሳ አነበብኩ። ሰፊ ነገር ነበረው[ዳሰሳውን ፈልጋችሁ አንብቡት] እና ልል የነበረው አከተመ። ግን አንዳች ስሜት አሁንም ፥ አሁንም ይመጣና እንደ አውራ ዶሮ ዙሪያዬን እየዞረ ነገር ሲፈልገኝ ነበርና እስቲ ይሁንለት።
ሙዚቃ ልጋብዛችሁ አስቀድሜ፦
መሬት መዓዛ ሲከባት አሪቲ ጡንጁት ሲያጥናት
የልጃገረድ ውብ ዜማ እንደ ካህን ሲባርካት
እንደተኳለ ውብ ዓይን የውሃ ድፍርስ ሲጥራ
ኢዮሃ አበባ ሲዘመር
ለንጋት ለመጸው ብስራት ሲለኮስ ችቦ ደመራ።
(የጊዜ ሠሌዳ ገጽ 1)
በሉ ሙዚቃው እየቀጠለ እናውጋ።
1. ነገረ  “-ኢዝም”
መጻሕፍት በሚሄሱበት ወቅት አንዳንዴ ሃያሲው ከመካነ አዕምሮዎች(Universities) እና ንባብ ላጠራቀመው “-ኢዝም” እንዲያመች ብቻ ብሎ የሚያቀርበው ሂስ፣ የኅልዮቶች ትንታኔ ብቻ ይሆንና ስለ መጽሐፉ ምንም የማያነሳ - “ነገረ ዘርቅ” ፥ የቁረን ክምር እየሆነ ነው የምትል ሐሜት ቢጤ አለች። እውነትነትም አይጠፋትም። በሌላ በኩል፣ ነገረ  “-ኢዝም” እንዳይነሳባቸው የሚፈልጉ ፣ የሚቆጡ አሉ።
የአስኳላውን ደጅ ያንኳኳንና ዘመናዊ የሚባለውን ትምህርትና ንባብ የቀመስን ሰዎች  “-ኢዝም” እንግዳችን አይደለም። ነገርየው ስደራ ነው። ምደባ ነው። ነገድ ነው። ክፍለ ትምህርት ነው። አንድ የሆነ ብያኔ ፣ የሆነ ባሕል ፣ የሆነ ፍልስፍና ነው። ቀዬ ነው። ጎራ ነው።ስልት ነው።  ባገራችን ጉባዔ ቤቶች የላይ ቤትና የታች ቤት የሚባል የዜማ ስልት አለ። እየመላለሱ ዝኒከማሁ[ይኸም እንደዚህ ፣ እንደ እገሌ] እያሉ ከማታከት አንድ ርዕስ ሰጥቶ የሆነ ቀዬ ሰርቶ ጥቅልል አድርጎ መጥራት ነው - “-ኢዝም” ማለት። ቀላል ነው - አንድን ጭፈራ “ይኼ ምንጃር ነው ፥ ይኼ ጉጂ ነው ፥ ይኼ ጉራጌ ነው “ ስንል ጠቀለልን፤ ስም ሰጠነው ማለት ነው። ከዚህ ብዙም የራቀ አይደለም “-ኢዝም” ።
ይሄን ከተባባልን ዘንድ ወደ “የጊዜ ሠሌዳ” እንመለስ።
“ሮማንቲሲዝም” እና ሌሎች በ “የጊዜ ሠሌዳ”
ሮማንቲሲዝም በ18ኛው ክፍለዘመን መገባደጃ ላይ ብቅ ብሎ በ19ኛው ክፍለዘመን ሰፋ፥ፋፋ እያለ የመጣ እንቅስቃሴ ነበር። በዘመነ አብርሆት “አመክንዮአዊነት” እና ኢንደስትሪላይዜሽን ላይ እንደ ምላሽ የተነሳ እና ስሜትን፣ ግለሰባዊነትንና  ተፈጥሮን የሚያስቀድም እሳቤ ነው። ይኼ እሳቤ ስነጽሑፍ ላይ፤ በተለይም ግጥም ላይ ያሳደረውን ብቻ እንይ ብንል፣ ሁልጊዜም አብሮት የሚነሳው፥ የሚወሳው እንግሊዛዊው ገጣሚ ዊሊያም ወርድስወርዝ ነው። ወርድስወርዝ ተፈጥሮን በጽሑፎቹ በማንገስ የግጥም አጻጻፍ ይትበሃልን አንድ እርምጃ የለወጠ ገጣሚ ነው። ተራራው፣ ሸለቆው፣ ፏፏቴው፣ አበባው፣ ኮከብ፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ሰማዩ፣ ቀላዩ..ወዘተ ተንቆለጳጵሰውበታል። ተነግረዋል። ተዚመዋል። በነዚህና በሌሎች የሮማንቲሲዝም መገለጫዎች ወርድስወርዝ ይታወቃል።
ግጥም  ባብዛኛው የሮማንቲሲዝም ተጠቂ ነው።  ለአመክንዮና ለሒሳብ አይገዛም። ገጣሚው በግል ቅምምሱ (Experience) እና ስሜቱ (Emotion) ላይ ተመስርቶ ለሚናገረውና ለሚጽፈው ምክንያታዊ መሆን ግዴታው አይደለም። በዚህም የተነሳ ግጥምን እንደ አልባሌ ነገር ያዩት የነበሩ፣ የተቃወሙ የአመክንዮ ሰዎች ብዙ ናቸው።  
የመንበረ ማርያም “የጊዜ ሠሌዳ”፤ ከሮማንቲሲዝም ብልቶ፥
ተፈጥሮን፤ በአራቱ ባሕርያት (መሬት፣ ውሃ፣ እሳትና ነፋስ)፣ በብርሃን ምንጮች (ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ኮከብ)፣ በወቅቶች (ክረምት፣ በጋ፣ በልግ፣ ጸደይ..)፣ ሠማይ፣ ደመና፣ ዝናብ፣ አበባ፣ አዕዋፍ፣ ቢራቢሮ ..ወዘተ
ስሜትን፤ በትዝታ፣ በናፍቆት፣ በመለየት፣ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እንባ፣ ሳቅ፣ ፈገግታ..ወዘተ በየገጹ ትፈትለዋለች። ትሰፋዋለት። ትፈታዋለች፥ ትጠልፈፈዋለች።
‘ሮማንቲሲዝም’ን ከ‘ሳብጀክቲቭ አይዲያሊዝም’’  ጋር በጥብቅ የሚያቆራኘው ግለሰባዊ ቅምምስን (experience) ማስቀደምም በ”የጊዜ ሠሌዳ” ጎልቶ ይታያል። አጠቃላይ(ወይም አብዛኛው) የመድበሏ ስሪትና ስፌት ሮማንቲሲዝም ቅድ በመሆኑ አባሪ ግጥም እያመጣሁ ባላታክታችሁም ፤ ትንሿ ይቻትላችሁ ፡-
አበባ የብርሃን ጥላ
አበባ የእሳት ከለላ
አበባ የፀደይ ግምጃ
አበባ የመጸው ምልጃ
አበባ የምድር ሱባዔ
አበባ ደብተራ ድንኳን
የባለ ቅኔ ጉባዔ።......
(ገጽ 29)
ጥላ፤ ከብርሃን ምንጭ የሚመጣው ብርሃን በአንድ ነገር ተገድቦ ሲቀር የሚፈጠርና የጋረደውን ነገር ቅርጽ የሚይዝ ጨለማው ክፍል ነው። አጅሪት ግን “አበባ የብርሃን ጥላ” ትላለች። ኧረ የለም፥ ብርሃን ጥላ የለውም ብትሉ [ምንም እንኳ ይኼን ስንኝ የጻፈችው ሳታስበው ቢሆንም] ለየግል ቅምምስና ስሜት (Experience and emotion) ዋጋ ለሚሰጠው ‘ሮማንቲሲዝም’  እና ለሮማንቲሲዝም  ቦታ ላለው ግጥም ገለታ ይግባቸውና ወግዱ ልትለን መብት አላት። እውነትን ብዙ የሚያደርገው ‘ፖስት ሞደርኒዝም’ እና  የእውነትን ድንበር የሚጥሰው ሱርሪያሊዝም  ከጎኗ ናቸው - አሁንም ለነዚህ ሁሉ ክፍት ለሆነ(ች)ው ግጥም ገለታ።
2. ጊዜ!
ጊዜ ምንድነው? የዚህ ጥያቄ መልስ አንድ አይደለም። ጊዜ - ለፊዚክስ ሦስቱ የቦታ አውታሮች (ወርድ፣ ስፋት፣ ቁመት) ላይ እንደ አራተኛ አውታር(Dimension) የሚታይ የቦታና ጊዜ(Space-time) ትስስር አካል ነው። ጊዜ - በፍልስፍናና በተለያዩ ሃይማኖቶች ደግሞ ሌላ ብያኔ አለው። ሌላው ቀርቶ በአንጻራዊነት ኅልዮት ስናይ ፍቅር እየሰሩ ያሉ ጥንዶችና ምጥ ላይ ያለች እናት ስለ ጊዜ የተለያየ እይታ ነው የሚኖራቸው። በዚህም ‘ጊዜ’ ግለሰባዊ (Subjective) ብያኔ ወደማግኘት ይሄዳል። ጊዜ ትናንት ፣ ዛሬና ነገ ያለው ቀጥ ያለ (linear) ነው የሚሉና የለም እምቧለሌ (Cyclic) ነው የሚሉ ፈላስፎች አሉ። እንዲሁም እውነተኛው ጊዜ አሁን ብቻ ነው (Presentism) የሚልና የለም ትናንት  ፣ ዛሬና ነገ ዋጋ ያላቸው ጊዜዎች ናቸው(Eternalism) የሚሉ የጊዜ ፍልስፍናዎች አሉ።
ገጣሚዋ “ጊዜ” የሚለውን ቃል ገጽ በገጽ ታመላልሰዋለች። የጊዜ ጉዳይ ይገዳታል። ነገር ግን ለጊዜ ያላት እይታ ይሄ ነው ብለን መበየን አንችልም። ለ‘ፕሬዘንቲዝም‘ እና ለ‘ኢተርናሊዝም‘  እኩል ትዘምራለችና።
መንገዳችን የነፋሱ
መድረሳችን ውብ አድማሱ
ይሸረፋል ተሰባብሮ
ይጠገናል ተሰባጥሮ
ይራመዳል በጥቂቱ
ነገ ነው የሰው ዕለቱ። ...
(ገጽ 13)
‘ነገ ነው የሰው ዕለቱ’ ባለችበት ብእር ከዚያው ግጥም ሳንወጣ ገጽ 14 ላይ “ቅጽበቶች ነንና” ትለናለች፦
.....
ጊዜን ማን ይሁነው
ማን ይሁንህ አንተን
ማን ይሁነኝ እኔን?
ቅጽበቶች ነንና

ባለመሆን በኩል
መሰልነው መሆንን።
ምነው በአንድ ራስ ሁለት ምላስ እንዳንላት ገጣሚ ነች። ገጣሚ በአንድ ራስ ብዙ ነፍስና ብዙ ምላስ ልማዱ ነውና። ስለ ጊዜ ብዙ ስንኞች ፣ ብዙ ጥያቄዎችና መልሶች ፣ ብዙ ተምሰልስሎቶች በመድበሏ ተብለዋል።
3. ሙዚቃና መንበረ
ሙዚቃ ያልሆነ ምንድነው? ከልብ ምት አንስቶ እስከ ነጎድጓደ ክረምት ስልት የሌለው፣ ሙዚቃ ያልሆነው የቱ ነው? ፈረስ ሲጋለብ፥ ላም ስትታለብ - ዜማ የለውም? የዝናብ ኮቴ፤ የነፋስ ጉዞ፤ የትንኝ እኝኝታ፥ የትል ስርርታ - ቀለም የለውም? ምናልባት አንሰማም እንደሆነ እንጂ። ሰምተን አይገባን እንደሆነ እንጂ። አንጠረጥር፥ አናመሰጥር እንደሆነ እንጂ - ሁሉ(ቢያንስ ብዙው) ሙዚቃ ነው። የሙዚቃና ኢትዮጵያ ደሞ ለብቻ ነው። የያሬድ አገር ነው አገሩ። እየተዘራም፥ እየታጨደም፥ እየተቦካም፥ እየተደለቀም፥ እየተለቀሰ.. ያለ ሙዚቃ ያለ ምት፤ ያለ ቀለም ያለ ስልት የሚደምቅ ድግስ፥ የሚከበር ንግሥ የለም። የለማ!
ለግጥም ሙዚቃ ያባት ነው። የወግ ነው። ምት ግዱ ነው። የመንበረ ግን ከዚህ ሳያልፍ አይቀርም። ኧረ የለም! እዚህ ግጥም ሙዚቃዊ ሳይሆን፤ ሙዚቃ ነው ግጥማዊ የሆነው።
የቀደመ የግጥም መድበሏን “የቃል ሠሌዳ”ንም ሆነ ሁለተኛውን “የጊዜ ሠሌዳ”ን ስናይ ሙዚቃ የገጣሚዋ ዋና ሆኖ እናገኛለን። ሙዚቃ - በስም በመጠራት (ሙዚቃ፣ መኃልይ፣ መዝሙር፣ ማሕሌት..ወዘተ)፣ ሙዚቃ - በመሳርያ ስም(ክራር፣ ዋሽንት፣ መሰንቆ፣ ከበሮ፣ ጸናፅል.. ወዘተ፣  ሙዚቃ - በስልት (ትዝታ፣ አንቺሆዬ፣ ባቲ ዓይነት)፣ ሙዚቃ - በያሬድ ምልክቶች (ጭረት፣ ርክርክ፣ ሂደት፣ አንብር.. ወዘተ) እና ሌሎች ሙዚቃ ያልተወሳበት ሦስት ተከታታይ ገጽ ማግኘት ይከብዳል። “የጊዜ ሠሌዳ” ላይ ሙዚቃ ያልተዘከረበት ገጽ በቁጥር ከአስር ይበልጥ አይመስለኝም። ገጣሚዋ ቃላት ታመላልሳለች። ከነዚህ ተመላላሽ ቃላት ሰፊውን ቦታ የሚይዙት ሙዚቃ ነክ ቃላት ናቸው። ሙዚቃ በቃል ከመወሳት ባለፈ፤ በ“የቃል ሠሌዳ” በስርዓተ ነጥብ እየተከፈሉ ወደ ጎን ይዘረጉ የነበሩ ስንኞች አሁን በ “የጊዜ ሠሌዳ” ላይ ቁልቁል ባጭር፥ ባጭር የተሰደሩበት ቅርጽ/ስልት/ቅኝት - ግጥሞቹ በቅርጽ ጭምር ሙዚቃን እንዲያጦዙ ፣ በወግ እንደቃኙት ክራር ለንክኪ(ንባብ) ሁሉ ነዛሪና ዜመኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከሩቅ እንደ ገብረክርስቶስ፣ ከቅርብ ደግሞ እንደ ምግባር ሲራጅ ዝርው ትቀላቅላለች። ይሄ ግን ምቱን ሲያፈርስ አናይም። የጊዜ ሠሌዳ ግጥማዊ ሙዚቃ ነው። ሙዚቃዊ ግጥም ነው። ሙዚቃ ዋናው ነው። ሙዚቃ ተሳክቶለታል።
4.ከመኃልይ ወደ “ሞኝ ዘፈን?!”
የመንበረ ማርያም ቃላት ሴቴ ናቸው። ወንዴ አይደሉም። ሲቆጡ እንኳን አይጮኹም። በጥፊ አያላጉም። ጭናችንን ዳበስ ፥ ዳበስ ያደርጉና በቁንጥጫ ያነዱናል። እንደ ድመት ኮቴ ድምጽ የላቸውም ግን ዳና አላቸው። በተመስጦ እንጂ በግርግር እንደማይረዱት ሙዚቃ ናቸው።
የገጣሚዋን ሁለቱንም መድበሎች አያይዤ ሳነብ አንድ ነገር ቀልቤን ሳበው። ይኸውም ‘አንድ ነገር’ ገጣሚዋ የተለከፈችባቸው፥ የተነደፈችባቸው ጭብጦችና ቃላቶች መኖራቸው ነው። እነዚህ ቃላትና ጭብጦች እየመላለሱ መሆናቸው ጎልቶ አይታወቅም። ምናልባት ለራሷም አልታወቃትም። ቀጥዬ የምጠቅሳቸው ቃላት በየጥቂት ገጽ ራሳቸውን የሚደጋግሙና የሚያመላልሱ ናቸው፡-
ራሱ “ቃል” የሚለውን ቃል ጨምሮ፣  መለኮት፣ ጊዜ፣ አራቱ ባሕርያት (መሬት፣ ውሃ፣ እሳትና ነፋስ)፣ ትዝታ፥ ናፍቆት፥ መለያየት፣ ነፍስ፥ ስጋ፥ ልብ፣ ብርሃን፣ የብርሃን ምንጮች (ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ኮከብ)፣ ወፍ፥ ቢራቢሮ፣ አበባ፣ ወይን፣ ሠማይ፥ ደመና፥ ዝናብ፣ እንባ፣ ሳቅ፣ ፈገግታ፣ እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር፣ መንገድ፣ ሙዚቃ ነክ ቃላት ..ወዘተ።
ገጣሚዋ በግጥም - በሙዚቃና በምት፣ በውበት ጉዳይ የምትታማ አይደለችም።  በቃል ሃብቷም ደሃ እንዳልሆነች ይህ አዲሱ መድበሏ ምስክር ነው። ነገር ግን ግጥሞቿ ከመኃልይነት እንዳይወርዱ ስጋት ሳይሆን ስስት አለኝ። የእስከዛሬውን የሞኝ ዘፈን እንዳይሆን የከለከለው የገጣሚዋ ሙዚቃ መቻል ነው። የውብ ሙዚቃ አዝማች ሲሉት፥ ሲመላልሱት፤ መልሶ፥ መልሶ ይጥማል እንጂ አያሰለችምና። ለነገዋ ግን “ካልተጠነቀቀች መች ይቀርላታል..” ያስብላል። የቃል ጎተራዋን ደባብሳ፥ ሌላ ለብሳ ካልተመለሰች ወብ ዜማዋ “የሞኝ ዘፈን” እንደሚሆን ያለ እጣን፥ ያለ ካድሚያ የሚገባው የግጥም አውሊያ ይነግረኛል። ከዋሸም እጣናችሁ አልነደደም - ጉልበታችሁ አልሰገደም ምንተዳችሁ!!
ወደ መድበሏ ተመለሱና ሙዚቃችሁን ጨርሱት። መላልሳችሁ ስሙት። ደጋግማችሁ አንብቡት። ተወዛወዙት። ደንሱት።
ቸር እንሰንብት!!



Read 230 times