የሚወዳት ፍቅረኛው ጥላው ከሀገር በመውጣቷ ምክንያት ለአዕምሮ ህመም ተዳርጎ በተለምዶ ጎፋ ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጠዋት ሄዶ ሲመሽ ስለሚመለሰው ኢንጅነሩ ለማ ብዙ ብዙ ሲባል እሰማለሁ (አነባለሁ)። ይሄ አፍቃሪ ሰው ጠዋት ሄዶ ከመሸ የሚመለሰው ከሀገር ጥላው ሄደች ከተባለችው ፍቅረኛው ጋር የሚንሸራሸርበት ሥፍራ በመሆኑና አንድ ቀን ትመጣለች የሚል ተስፋን ይዞ ነው።
(ከእለታት በአንዱ ቀን ጥላ የሄደችው ፍቅሩ ተመልሳ ብትመጣም ሊያስታውሳት አልቻለምና በሀዘን ተሰብራ ተመልሳ ሄደች የሚል ግማሽ እውነትም ይነገራል።) ግን ዛሬም ድረስ ራሱን ሳይቀር ረስቶና አጥቶ፣ ጥላው ከሀገር የወጣችውን ፍቅሩን እየጠበቀ አለ።
(ይሄ ጉዳይ አሉባልታ ነው ስትሉም ሰማሁ ልበል? )
ለማንኛውም... ይሄንንም ሰው መነሻ ያደረገ አንድ ዘፈንም በሀይለ እየሱስ ግርማ ድምጽ በኩል አድምጠናል። በአማኑኤል ይልማ ግጥምና ዜማው ተደርሶ “ከሌለሽበት ቦታ” የተሰኘው ዘፈን የዚሁ ታሪክ መነሻ መሆኑም ይታወቃል። በሀይለ እየሱስ ድምጽ ሕይወቱን የሚነግረንም ኢንጅነሩ ለማ ነው።
ከሌለሽበት ቦታ ብቻዬን ተጉዤ
ሲመሽ እመለሳለሁ ሀሳብ ትዝታሽን ይዤ።
ከሌለሽበት ቀርቶ ትዝታሽ
ያመላልሰኛል ባትኖሪ እንኳን በጭራሽ
ዝንት ዓለም ቢያልፍ ዕድሜ በተርታ
እኔ ግን ከዛው ነኝ ከተውሽኝ ቦታ።
ቢያልፍም ጊዜው ቢነጉድም
ሌላ እኔ አለምድም
ይሂድ ጊዜ ይለፍ ዕድሜ
አንቺን ሳይ ቆሜ።
ይሄንን ያነሳሁት ደጋግማችሁ የሰማችሁትን ታሪክ ለመድገም አይደለም። ለሌላ ጉዳይ መነሻ እንዲሆነኝ ብቻ ነው። በእርግጥ ይሄም ታሪክ እንግዳችሁ አይደለም ይሆናል።
የለማን ታሪክ ድምጻዊው ሐይለእየሱስ እንደተጫወተው ሁሉ፣ ከፍቅረኞቻቸው የመለያየትን የግል ታሪካቸውን ህመም በገዛ ድምጻቸው አንጎራጉረው ስላስታመሙ አንድ ሁለት ድምጻዊያን ለማውሳት ነው።
1, ጋሽ ማህሙድ አህመድ
ጋሽ ማህሙድ “አልማዝ” የምትሰኝ ፍቅረኛ ነበረችው። ይዋደዳሉ። እሱ ደግሞ “አልማዝ አልማዝዬ ሁሉም ሰው ይላታል” ብሎ እስከመዝፈን ያደረሰው መውደድ ነበረው። በአጋጣሚ ከሀገር ወጣችና ፍቅራቸው ተቋረጠ። ይሄንን የመለየት ሀዘን መቋቋም ያልቻለው ጋሽ ማህሙድ፤ በህመሙ ሲብሰለሰል የሸዋልዑል መንግስቱ አንድ ግጥም ይዛ ልታስታምመው ተከሰተች (ዜማ የማን ይሆን?) ጋሽ መሐሙድም ይሄንን ግጥም በመዝፈን ትንሽም ቢሆን ህመሙን አስታገሰ። ዘፈኑ ደግሞ “አታውሩልኝ ሌላ” የተሰኘው ውብ ዘፈን ነበር።
አታውሩልኝ ሌላ ከእሷ ዜና በቀር
አስራኝ ትብትብ አርጋኝ ሄዳለች ከሀገር።
ላጠቅመኝ ወድጃት ላታዛልቀኝ
አሁን ከሀገር ሄዳ ናፍቆቷ ጎዳኝ
ብጠራት አትሰማ ያለችው እሩቅ
ምን ትጠቀማለች እንዲህ ስማቅቅ።
...
የእኔ ሀሳብ እሷ ነች የልቤ ወለላ
የእሷን የእሷን እንጂ አታውሩልኝ ሌላ
እንደዚህ ስባዝን ናፍቆቷን ስባጅ
ኖራስ አትጨክንም ሞቷ እንደሆን እንጂ።
የኋላ የኋላም ከሀገር የወጣችው ፍቅረኛው ከሀገር ተመልሳ ፍቅራቸውን እንደቀጠሉም ይነገራል።
2, ጋሽ ታደለ በቀለ...
ታደለ በቀለም “አላስቀየምኳትም” የተሰኘችውን ዘፈን ያንጎራጎረው ለገዛ የመለያየት ህመሙ ነበር። ጋሽ ታዴ ስለዚህች ታሪክ እንዲህ ሲል ሲያወራ በአንድ ወቅት ሰምቼዋለሁ።
“በጣም የምወዳት ፍቅረኛ ነበረችኝ። ፓስታ እወድ ነበርና ከሥራ በተመለስኩኝ ቁጥር ፓስታ ገዝቼ ቤቷ እየሄድኩኝ ሰርታ ታበላኝ ነበር። በአንዱ ቀን እንደለመድኩት ከሥራ መልስ ፓስታዬን ገዝቼ ሰፈሯ ሄድኩኝ።
ሳስጠራትም ያገኘሁት መልስ ያልጠበኩትና የሚያስደነግጥ ነበር። ከሀገር ወጥታለች ነበር የተባልኩት። ከሀገር ለመውጣት ስለማሰቧ አንድም ቀን ነግራኝ አታውቅም። ቢያንስ ለምን እንዳልተሰናበተችኝ እንኳን ማወቅ አልቻልኩም። በዚህም በጣም አዝኜ ጉዳዩንም ለጋሽ ተስፋዬ አበበ (የክቡር ዶ/ር) ነገርኩት። እሱም “አላስቀየምኳትም”ን ከነዜማው ሰርቶ ሰጠኝ። እኔም ዘፈንኩት።”
አላስቀየምኳትም ፍቅሬ ምን አስቆጣት
እወዳታለሁኝ ምንም አልበደልኳት
ጥላኝ ከምጠፋ እኔን ብቸኛ አርጋኝ
ምናለ ጥፋቴን ገልጻ ብታስረዳኝ።
እሷን ትቼ መኖር ፍጹም አልወደድኩም
ያለኝን ስሜት ልቤን አልደበኩም
ምንድነው በደሌ በግልጽ ይነገረኝ
ባልሰራሁት ጥፋት ቆርጣ ከምተወኝ።
3, ብዙነሽ በቀለ (ብዙዬ)
በቡዝዬ ዘፈን ላይ እንኳን እርግጠኛ አይደለሁም። ብቻ እንዳለ ጌታ ከበደ “በዓሉ ግርማ ሕይወትና ሥራዎቹ” በተሰኘ መጽሐፉ ላይ ስለ በዓሉ እና ስለ ቡዝዬ የአንድ ወቅት እፍ ክንፍ ያለ ፍቅር ይተርክልናል። ከሚጠቀሱት ታሪኮች ውስጥም መጠጥ ቤት ገብተው ጠረጴዛ በስልት እየደበደበች፣ እንዲሁም ራዲዮ ክፍል በ1950ዎቹ በዜና አንባቢነት በሚሰራበት ወቅት በቢሮ ስልክ ደውላለት ትዘፍንለት እንደነበር፣ በዓሉን በቃሉ ብላ ትጠራው እንደነበረ፣ አሜሪካን ሀገር ለትምህርት በሄደበት ወቅት “በቃሉዬ የሚመጣበት ቀን የተቃረበ አይመስልህም? መቼ የሚመጣ ይመስልሃል?” እያለች አንድ ወዳጁን ትጠይቅ እንደነበርም፣ በቃሉ የምትለውም በቃሉ ይገኛል ለማለት ነው? በቃሉ በንግግሩ ማርኮኛል ለማለት ነው? የሚሉ ጉዳዮችን እንዳለጌታ ከበደ በመጽሐፉ ያነሳሳል። በተጨማሪም መጽሐፉ በዓሉ ግርማ ከብዙዬ ተለያይቶ ልጆች የወለደችለትን ሕጋዊ ሚስቱን አልማዝን እንዳገባም ይናገራል (በዓሉ ግርማ ሕይወትና ሥራዎቹ ከገጽ 120-124)።
የዚህንም ጉዳይ ጫፍ ይዤ ደራሲው እንዳለ ጌታ ከበደ በመጽሐፉ ላይ ባያነሳልንም እንኳን ምናልባት ብዙነሽ በቀለ “ፈረንጅ ሀገር ሳትሄድ” የተሰኘውን ዘፈን የተጫወተችው ለበአሉ ግርማ ይሆን? የሚል ሀሳብ ይመጣብኛል።
ፈረንጅ ሀገር ሳትሄድ ገና እዚሁ ሳለህ
የገባኸውን ቃል እንዴት ታፈርሳለህ
የእውነት ሰው መስለኸኝ ክቡር የከበረ
ቃልኪዳኔን ይዤ ጠብቄህ ነበረ።
ትምህርቴን ጨርሼ ሀገሬ ስመለስ
አደራ ጠብቂኝ ፍቅሬ የእኔ መንፈስ
ብለህ ያልከኝን ቃል እንዴት ዘነጋኸው
እኔን ገሸሽ አርገህ ሌላ ልጅ ያጨኸው?
...
ከአይሮፕላን ወርደህ ሀገርህ ስትገባ
በናፍቆት ተቃቅፈን ያፈሰስነው እምባ
ከንቱ በመቅረቱ ቁምነገር ሳያገኝ
ከልቤ የማይጠፋ መሪር ሀዘን ሆነኝ።
በዓሉን በቃሉ ብላ መጥራቷን “በቃሉዬ የሚመጣበት ቀን የተቃረበ አይመስልህም? መቼ የሚመጣ ይመስልሃል?” ብላ ወዳጁን ትጠይቅ እንደነበረና በዓሉም ከእሷ የነበረውን ፍቅር አቋርጦ ወ/ሮ አልማዝ አበራን ማጨቱን ስናይ፣ ይሄ ዘፈን ለዚህ ታሪክ ወደመሰራቱ እውነት ያቀርበናል።
Saturday, 21 September 2024 13:29
የመለያየት ህመማቸውን ያንጎራጎሩ አንጋፋ ከያኒያን
Written by መክብብ ፍቃዱ
Published in
ጥበብ