Tuesday, 24 September 2024 11:04

“አፍሪካ ታከብራለች” በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“አፍሪካ ታከብራለች” ከጥቅምት 27 እስከ ሕዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም.  በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ መሆኑን ተገልጿል። በዚህ መርሐ ግብር ላይ በርካታ ሁነቶች እንደሚከናወኑ አዘጋጆቹ ሐሙስ መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል።

ሌጄንደሪ ጎልድ ሊሚትድ እና ማያልዝ ኤቨንትስ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከኢሲኤ ጋር በመቀናጀት የሚያዘጋጁት ይህ መርሐ ግብር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድጋፍ እንደተደረገለት በመግለጫው ተጠቅሷል። በአፍሪካ ሕብረት እና ኢሲኤ አዳራሾች ውስጥ የሚከናወን መርሐ ግብር ሲሆን፣ “በአፍሪካ አሕጉር ያለው ብዝሃነት ውስጥ የሚገኘውን አንድነት ለማሳየት እና የኢኮኖሚ ብልጽግናን በኪነ ጥበብ ስራዎች፣ በባሕል፣ በቅርስ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ እንቅስቃሴዎች ለማጉላት ታልሞ የተዘጋጀ ነው” ተብሏል።

የዘንድሮው መርሐ ግብር መሪ ቃል “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ አስተምህሮ” እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫው ተነግሯል። የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽሕፈት ቤት የሚካሄድ መሆኑን ተገልጿል።

በተከታታይ አራት ቀናት የተለያዩ የውይይት መድረኮች፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ኤክስፖ፣ የባሕል እና የሽልማት ምሽቶች እንደሚካሄዱ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተብራርቷል።

Read 871 times