Tuesday, 24 September 2024 11:46

የአደባባይ በዓላቶቻችን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ናቸው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
የሰው ልጅ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ አዳዲስ አካባቢን መጎብኘት ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ አዲስ አበባ ከመዝናኛነት ባለፈ ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና የባህላዊ ቅርሶች ባለቤት የሆነች ከተማ ናት፡፡ ከዚህም ባለፈ በዩኔስኮ  የተመዘገቡ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤትም ናት። ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ለአብነት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በወርሃ መስከረም ከሚከበሩ ሐይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው። ከሀገራችን የአደባባይ በዓላት መካከል በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ወጥቶ የሚሳተፍባቸው የፍቅርና የአብሮነት በአላት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል ደመራ እና በአብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው “የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ” ባማረ ድባብ፣ በከፍተኛ ድምቀትና ውበት፣ በእንግዳ ተቀባይነት ስሜት፣ ባህላዊ እሴቱንና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አብሮነት የምናከብረው፣ ትብብራችን ጎልቶ የሚወጣበት፣ ኢትዮጵያዊ ፍቅር እና ህብረ-ብሄራዊነት ደምቆና ፈክቶ የሚታይባቸው በዓላት ናቸው፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል በአለም አቀፉ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የጋራ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ፤ ሃማኖታዊ ትዉፊቱ ተጠብቆ በደማቅ ሥነ-ስርዓት የሚከበር ሐይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል ለአገራችን የገጽታ ግንባታና የቱሪዝም መስህብ በመሆን ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬን የሚያስገኝ የጋራ ሃብታችን ነው፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ካሏት ቱባ ባህሎችና እሴቶች መካከል አንዱ የገዳ አስተዳደራዊ ስርዓት አካል የሆነው የኢሬቻ በዓል፣ የራሱ የሆነ ውብ ባህላዊ መልክና ቀለም ያለው የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ ነው፡፡ ይህ በዓል ህዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለምለም ሳር በመያዝ በወንድማማችነት/እህትማማችነት ፈጣሪውን እንኳን ከደመና ወደ ፀደይ /ብርሃን/ አሸጋገርከን በማለት የሚያመሰግንበት እና ምህረት የሚለምንበት እንዲሁም የፈጣሪን ሀያልነት የሚያደንቅበት በተጨማሪም በፍጡራን እና በፈጣሪ መካከል ያለውን የግንኙነት ምስጢር ለትውልድ የሚገለጽበት የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፡ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተለያየ እምነት ተከታዮች የየራሳቸው ሀይማኖታዊ በዓላት ቢኖራቸውም፣ አንዱ የሌላውን በዓል በእኔነት በማክበር በእጅጉ ይታወቃሉ። እነዚህ በዓላት በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ሕዝብ ዘንድ በአብሮነት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት የሚከበሩ ሲሆኑ፤ የአንዱ በዓል ለሌላውም ቤት ፌሽታ ሆኖ ሲከበር ኗሯል፡፡ በተጨማሪም በበዓላት መልካም ምኞት መግለጫ ስጦታዎችን በመለዋወጥ ቤት ያፈራውንም በማቋደስ በአንድነት ባህላዊ ጭፈራዎችን በመጨፈር እና በመመራረቅ ሰላም፣ፍቅርን እና ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር የከተማው ማህበረሰብ ልዩ መገለጫ ነው፡፡ ከተማችን አዲስ አበባ በዘንድሮው ዓመት እነዚህን ሐይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላትን ከወትሮው በተለየ መልኩ በኮሪደር ልማት እጅግ አምራ እና ደምቃ ለበአሉ አከባበር ዝግጁና ምቹ ሆና እንግዶቿን በተለየ መልክ ለመቀበል ሽርጉዷን በማጠናቀቅ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡ እነኚህ በዓላት ስኬታማ እና ያማረ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የአዲስ አበባ ህዝብ የተለመደውን የግንባር ቀደምትነት ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ከተማዋን ከማስዋብ እና አካባቢን ከማፅዳት ጀምሮ እንግዶቹን በየአካባቢው ባማረ መስተንግዶ ለመቀበል፣ በዓሉ ሰላማዊ ድባቡን ይዞ እንዲጠናቀቅ መንደሩንና አካባቢውን በንቃት ከመጠበቅ፣ ጀምሮ የተለያዩ ሁኔታዎች ሲያስተውሉ በያሉበት አጋልጦ በመስጠት ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከወትሮው ላቅ ያለ ነው፡፡ በዓሉ ከከተማችን አልፎ የአገራችንን ህዝባዊ ትስስር ከማጎልበትና ባህላዊ እሴቶቻችንን ከማሳደግ አንፃር ያለውን ጉልህ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት የከተማ አስተዳደሩ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ህብረተሰቡም ለሰላምና ለአንድነት ይበልጥ ትኩረት በመስጠት በወንድማማችነት/እህትማማችነት መንፈስ በድምቀት ሊያከብረው ይገባል፡፡ በመሆኑም ከስንዴ ውስጥ እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ አንዳንድ የጥፋት ሀይሎች የከተማችንን መልካም ገፅታ ለማጉደፍና የሚከበረውን የመስቀል ደመራ እና ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓላትን በተሳካ መልኩ እንዳይገባደድ ፍላጎቶች እንደሚኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም ሰላም ወዳዱ ህዝብ፣ እንደወትሮው ከፀጥታ ሃይሎችና ከህዝባዊ ሠራዊታችን እንዲሁም ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት የጥፋት ህልማቸውን ማክሸፍ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም የሚድያ ተቋማትና የሚድያ ባለሙያዎቻችን በንቃትና በፍጥነት ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ የበዓሉን መልካም ገፅታ በማሳየት የህዝቡን አብሮነት በሚገባ ለአለም ህዝብ የማንጸባረቅ ሚናቸውን እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል፤ ወደ ከተማችን የሚመጡ እንግዶቻችን እንዳመጣጣቸው ወደ አካባቢያቸው በሰላም እስኪመለሱ ድረስ በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት እስከመጨረሻው ድረስ በትጋት እና በቅንጅት በመስራት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ፣ ሁላችንም ከወትሮው ይበልጥ ተጠናክረን በትብብር ስሜት ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
Read 265 times Last modified on Wednesday, 25 September 2024 20:44