Tuesday, 24 September 2024 11:49

ለመፍትሔ የተጠራች ነፍስ!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

የማኅበረሰብ አገልግሎት ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፤ በግል እና በተቋም መንቀሳቀስ፣ ትውልድ እና ሀገር ላይ መሥራት ሞትን ከማሸነፊያ መንገዶች መካከል ዋንኛው ነው፤ መማር፣ ወይም የቀለም ትምህርት እያንዳንዱን ትምህርት አንጥሮና በጥሩ ውጤት አጠናቅቆ አንቱታን ማትረፍ ብቻ አይደለም፤ የቀለም ትምህርት በሥነ-ምግባር፣ በቅንነት፣ በአሳቢነትና በማገልገል ሥሜት ካልቃኘና ካልተናበበ ዋጋ ቢስ ነው፤ በተቻለ መጠን ማኅበረሰቡን የማያገለግል ምሑር የመማሩ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፤ ምክንያቱም የመማር ተቀዳሚ ዓላማ ሀገርንና ወገንን ማገልገል ነውና…
…ደግሞም ነፍስ በከንቱ ተንገዋልላ ወደ ሰማይ መትመም የለባትም፤ የቁብም ቢሆን አበርክቶ ሊኖራት ግድ ይላል፤ አለበለዚያ ኪሳራ ነው ትርፏ፤ ለመክሰር የተፈጠረ የለም፤ ከተፈጠረ በኋላ ግን የሚከስር አለ፤ በተቻለ መጠን አገልግሎ ማለፍን የመሰለ ነገር የለም…
…የጥፍር ቁራጭዋን ታኽል ሳናበረክትና ሳንሠራ ራሳችንን እየካብን መክነን ተከታይ አምክነናል፤ ራሳችንን ለመሳም ስለምን ከናፍሮቻችንን እናጠይማለን? ለሰብዕናችን እንዴት ጣዕምናን መስጠት ታከተን? ከተራ ቁልምጫና፣ ከጤዛዊ ሽንገላ ይልቅ ሰብዕና አይበልጥም? ማነው፣ የቱ ነው ሥራን የሚያስከነዳ?... ማዕረግ ከሥራ ይበልጣል?...
…ማን ነበር Our ego is our burden ያለው? ራሳችንን ለመሸለም፣ ለመሳም ለምን ይህን ያህል ከንፈራችንን እንኩላለን? የትኛው የረባ ሥራችን ነው የመመጻደቂያ መከዳ ላይ ያፈናጠጠን?
በቴዎድሮስ ታደሠ አንደበት አድሮ፡-
‹‹ምኞቴን ከመጠንኩት፤
እንደራስ ካደረ‘ኩት፤
ከበቃሁ ለቁርሴ፣
እንዳቅም እንደኪሴ፤
አይቀርም እንደሰው፣ አንጀቴን ማራሴ፤››
ማለት ማንን ጎዳ? መትጋት ይከተላል፤
የቱ አንሶን፣ የቱን በለጥን? ደረጃ መዳቢ ያደረገን የትኛው አካል ነው? ማዕረግ ያከናነበንም ይጠየቅ! ማዕረጋችንን ራሳችን አይደለን አቀላልጠን፣ አንጥረን አናታችን ላይ ቂቢብ ያደረግነው? ማዕረጋችን ከሥራችን የተናበበ ነው? ስለምን ከሥራችን ጋር ዕኩል መጓዝ ታከተን?...
…አዎን አብረን እናዝግም፤ የተቦጨቀ ቆብ ማዕረግ አይሆነንም፤ የተሠራበት መሆን አለበት፤ ወላ ወደ ኋላ መለስ ብለን ሠርተንበታል፣ ደክመንበታል ብለን እንጠይቅ።
እናም፡- ሥራችን ይቅደመን፣ ወይም ከሥራችን ጋር ዕኩል እንጓዝ፤ አለበዚያ መጨረሻችን እንደዛ ትዕቢተኛ ንጉሥ (እድምተኛው ‹‹የምንሰማው የእግዚሔር ድምጽ ነው እንዴ? ተብሎ ተጠይቆ፣ የራሱን ድምጽ ‹‹አዎ የእግዚአብሔር ድምጽ ነው›› እንዳለው) በትል መመታት ይሆናል…
…ሥራችን ሆይ ጠብቀን፣ አብረን እንሂድ…
…ሥራን ያስበለጠ ሥም እንጎብኝ - በፍሬዓለም ሽባባው ‹‹ሀገር በአንድ ሺህ ቀን›› ውስጥ፤ ሀገር በልጆች ትሸለማለች፤ ሀገር በልጆች ትረገማለች፤ የአዕምሮ መቀንጨርን ለማስወገድ የተደረገና እየተደረገ ያለ ሰናይ ተግባር አነበብሁ፤ የአንድ ሺህ ቀናት ሚስጢር እንሆኝ÷ ‹‹ሀገር በአንድ ሺህ ቀን›› በተሰኘ መጽሐፍ፣ ፍሬዓለም ሽባባው የሕልውና ሥጋት የሆነውን ረሀብ በዘላቂነት ለመመከትና የልጆች የአመጋገብ/‹‹ኒውትሪሽን›› እጥረትን ለማስወገድ ሁነኛ መፍትሔ ይዛ ቀርባለች።
ልጆች ከተጸነሱበት ጊዜ ጀምረው ተወልደው ሁለት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ባለው ጊዜ (በ1000 ቀናት ውስጥ) የሚያገኙት ምግብ ለአዕምሯቸው ዕድገት ያለውን ተጽዕኖ ሣይንሳዊ በሆነ መልኩ አስቃኝታናለች፤ የአመጋገብ ሥነ-ሥርዐታቸው የተመጣጠነ ልጆች የጤናማ አዕምሮ ባለቤት ሲሆኑ÷ ነገሮችን አመዛዝነው፣ የክስተቶችን መነሻና መድረሻ አጢነውና ከስሜታዊነት ይልቅ ሚዛናዊነትን አስቀድመው በትምህርት ገበታቸው ላይ አዲስ ሀሳብን ለማመንጨት የሚተጉ፣ ለለውጥ የተዘጋጁና ሀገር የማገልገል ባሕልን የሚያዳብሩ መሆናቸው ተተንትኗል፤ ይኼንን ሀሳብ ከግብ ለማድረስ፣ በዚህ መጽሐፍ  አዘጋጅ አነሳሽነት ከመንግሥት ጋር በመተባበር በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ ሥራና የ‹‹ኒውትሪሽን ዲክላሬሽን›› የመንግሥት የፖሊስ አካል ሆነው ሲተገበሩ እናስተውላለን።     
ጸሐፊዋ፣ የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት ላይ ያተኮረ አኩሪ ሥራ ስታከናውን እናገኛለን፤ በመጽሐፉ  ውስጥ ዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገው ትውልድ መድረሻ ወለል ብሎ ይታያል፤ የትውልድ ዕጣ-ፈንታ ላይ የተሠራ ልብ የሚያሞቅ ተግባር ሆኖ አግኝቼአለሁ።
ተማሪዎችን መመገብ፣ የተማሪዎች አዕምሮ ላይ መሥራትና የተማሪዎች የአዕምሮ መቀንጨርን በዘላቂነት ማጥፋት በዋናነት ተካትተዋል፤ ከዚህ ሥራ ዕኩል፣ ጸሐፊዋ የተማሪዎቹን ሥነ-ልቡና የሚጎዱ ቃላትን በሚዲያና በተለያዩ መድረኮች ትሞግታለች፤ አሳማኝ በሆነ መልኩ ሕጻናት ይደገፋሉ።
በአጭሩ፣ ቻግኒ አካባቢ የሚኖሩ የጸሐፊዋ ወላጆች ጠንካራ ሠራተኞች በመሆናቸው ከራሳቸው ተርፈው አካባቢውን የሚመግቡ ናቸው፤ በመሆኑም፣ ሁሉም ሰው በተድላና በጥጋብ የሚኖር ይመስላት ነበር፤ በ1977ቱ ድርቅ ምክንያት ከወሎ አካባቢ ተፈናቅለው በአካባቢዋ አቅራቢያ የሠፈሩ የረሀብ ተጠቂዎችን ስታስተውል ልቧ ተነካ፡፡
አሜሪካ ለሥራና ለትምህርት በሄደችበት በነገር እየጎነተሉ ሥነ-ልቡናዊ ጫና አሳደሩባት፤ በኋላ በተወዳጅ እህቷ በእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የተቀነቀነውን ‹‹ፍቅር ነው የራበኝ›› የሚል ግጥም አሰናዳች፤ የወገኖቿ ነገር አላስችል ሲላት፣ የ3ኛ ዓመት የኮሌጅ ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ሀገሯ ተመልሳ መሥራት ጀመረች፤ ተማሪዎች ለከፋ የረሀብ ችግር እንደተጋለጡ አረጋገጠች፡፡
በትምህርት ዘርፍ ፕሮጀክት ነድፋ የተማሪዎች ምገባን በይፋ ጀመረች፤ መንግሥትም፣ ሀሳቧን ተቀበላት፤ ነገር ግን ልጆቹ ተጸንሰው፣ ከዚያ ተወልደው ሁለት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚገጥማቸው የ‹‹ኒውትሪሽን›› ችግር አስቀድሞ መቀረፍ እንዳለበት ታምናለች፤ ሀሳቧንም ለመንግሥት ታቀርባለች፡፡
‹‹ሰቆጣ ዲክላሬሽን›› ብላ በመሰየም ከመንግሥት ዕውቅናን አግኝታ 52% የነበረውን የአዕምሮ መቀንጨር በ2030 ዓ.ም. ወደ ዜሮ ለማምጣት ዘመቻውን ትጀምራለች፤ ተሳካላት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዚህ አኩሪ ሥራዋ ዕውቅናን ይሰጣታል፤ አራት የአፍሪካ ሀገራትም ይኼንን ልምድ በመቅሰም ተግባራዊ ያደርጋሉ።
የጸሐፊዋ አዕምሮ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማመንጨት የማይቦዝን ነው፤ በቀላል ወጪዎች ያሰበቺውን ስታሳካ ተገንዝቤአለሁ፤ በሰው ልጆች ላይ ውጤት የሚያመጣ ተግባርን አከናውናለች፤ ከዚህ በመነሳት፣ ማንኛው ዜጋ ለሀገሩ የመፍትሔ ሀሳብ ማምጣት እንደሚችልና በሚችለው ሁሉ እገዛን ማድረግ እንዳለበትም ተሰምቶኛል፡፡
መጽሐፉ፤ በማኅበረሰብ ሣይንስ፣ በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት፣ በጤና አጠባበቅ ዙሪያ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ምጣኔ-ሀብታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለሚደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች ሁነኛ ምንጭ በመሆን ያገለግላል የሚል ዕምነት አለኝ።  
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።


Read 164 times Last modified on Wednesday, 25 September 2024 20:33