፨ መለያየት፣ መበታተን፣ የአንድ አባት ልጆች እንዳልነበርን (የአደም) መከፋፈል፤ የጊዜያችን፣ የዘመናችን፣ የአለማችን ኹኔታ ነው። ተግባብቶና ተፋቅሮ መኖር፣ ለረዥም ዘመን ተፈጥሯችን እስካይመስል ድረስ። በሐገራችን ደግሞ የባሰ ነው። የውጭ ወራሪ ሲመጣ መመከት፤ እርስ በርስ ደግሞ መባላት። እርስ በርስ፤ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የማይችሉ፣ ተራ ጉዳዮችን እንደ ትልቅ አጀንዳ በመውሰድ እንተላለቃለን። አንድ የሚያደርጉን አያሌ ነገሮች እያሉ ለመጣላት ፈጠንን። አገራችን በርካቶችን አቅፋ ያኖረች ታላቅ ሐገር ናት። ተግባብቶ ቢሰራ፣ አንዱ ለአንዱ እንቅፋት ሳይኾን መከታ ሆኖ ቢኖር፤ በማንም ማዕቀብ የማትንበረከክ ሃያል ሐገር ትኖረን ነበር። ብናውቀው ሌሎች እሷን የሚያዩ እንጂ እሷ ‘እንደ ሌሎች ልሁን’ የማትል ሃገር ነበረችን። ለመለያየትና ለመከፋፈል ከምንሯሯጥ ምናለ የተራቡ፣ የታረዙትን ብንደግፍ? ሐገር ለምታ፣ አድጋ፣ ‘ታላቅ’ ኾና የተራበ ሳይሆን የሚሰራ የሞላባት ብትሆን? የሰውን ልብስ የሚያረጥበው የሃዘን እንባ ሳይሆን የስራ ላብ ቢሆን?...”እኔ እበልጥ፣ የኔ ይበልጥ”ን ትተን ፤ አገር ስንባል ጠላታችንን ረኅብ፣ ድህነት፣ ግለኝነት፣ ዘረኝነት አድርገን ብንነሳ. . .
‹‹የወሬ መዓት፣
ለክብር ሲባል የመጎራት፣
ድርት ታሪክ ግብዝ ድርሳን፣
በጦር ልቆ፣ በነጻነት መንቦጣረር።
በወሬ ብቻ ገኖ መክበር።
ቂጣ’ም አይሆን ወይ አሻሮ
ከድርቅ ችጋር አያላቅቅ፣...› ›(40) ብንባላ፣ ብንጣላ፣ ብንጋደልም ግን አንድ ነን። ተለያይተን እማንለያይ፤ ተገዳድለን የማንሞት ነን። አንድ ነን፤ የአንድ አባት ልጆች ነን፤ ፍቅር አለ መሃላችን። ‹ነው ነበረ› በሚለው ውብ ግጥም ገጽ 5 ላይ፦
‹‹ሽው ሲለን ውልብ ለአፍታ፣
በነገር እሳቤ ስንታኮስ፣
ስንማሰል ስንቧጨቅ፣
ስንቋሰል ስንማረር ላንባጠስ።
ነው ነበረ የምንኖር፣
አሁንም ያለን።››
አንድ ስንሆን ነው ሐገር እምናሳድገው፤ ከተለያየን አንዳችንም አናድግም።
‹‹‘ኔና አንተ ለሀገር፣ ውሃና እሳት ነን፣
ለየብቻ ጥፋት፣ ስናብር አብርተን፣
ለአገራችን ሙቀት፣ ሃይልን እንፈጥራለን።
ከተያያዝን ነው፣ ከዕድገት ሠንሠለት፣
ከማማው ምንወጣ
የማይጠፋ ብርሃን፣ በኢትዮጵያ ሚወጣ።›› (85) ግለኝነት ብቻ ካጠቃን እንወድቃለን።
‹‹እኔ፣ ለኔ፣ የኔ ባይ ብቻ ፈልፍሎ፣
ተንኮታኩቶ ወድቋል፣ በጀርባው ተንጋሎ።›› (109)
፨ በበርካታ የኪነ-ጥበብ ሞያው የምናውቀው ተዋናይ፣ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ አርታኢና ጋዜጠኛ ሁሴን ከድር በ2014 ዓ.ም “ንፋስን በወጥመድ” ሲል 54 ግጥሞች ያሉበት፣ 111 ገጾች ባሉት የግጥም መድብል መጥቷል። መድበሉ ከ80ዎቹ ልጅነት አንስቶ 2014 ጉልምስና ድረስ የተሰባሰቡበት የ26 አመታት ስሜቶች ናቸው። ራሱ እንደሚለው ሁሉም ግጥሞች በተነካው ስሜቱ የጻፋቸው ናቸው። ሐገሩን፣ ዘመኑን፣ ሃይማኖቱን፣ የህይወት ልምዱን፣ ገጠመኙን፣ ትዝብቱን. .ወዘተ ያሰፈረባቸው ናቸው። ስለ ሐገሩ እና ስለ ህዝቦች በምሬትም በስላቅም ጽፏል። ለኢራቅና ሶሪያውያን በማዘን በንዴት የጻፈው ‹ለሠላም› የሚለው ግጥም ለሐገራችንም የሚሆን ነው።
፨ ግጥሞቹ ስለ ሐገር፣ ስለ ዘመን፣ ስለ ሰው ልጅ ተብሰክሳኪ ናቸው። ሃዘን ያጠላባቸው፣ የተከፉ፣ መሸሻ ፈላጊ፣ አልቃሽ ግጥሞች ናቸው። ሁሉ የታከተው፣ በተስፋ መቁረጥ ላይ ያሉ ግጥሞች ይስተዋላሉ። ወደ መጨረሻ አካባቢ ባሉት ‹ተነስ› 98፣ እና ‹የሌሊት አዝመራ› 104 ከሚሉት ተስፋ አ(ስ)ሰናቂ ግጥሞች በቀር አብዛኛዎቹ ተስፋ የቆረጠ ሰው ድምጾች ናቸው። ገጽ 31 ላይ እንደሚለው፡-
‹‹..ብዬ እያሳየሁት፣ ቅዝቅዝ ያለ ፊቴን፣
ውድቅ ያለ ገጼን፣ ሙትት ያለ ሳቄን።›› አይነት ናቸው፤ ተስፋ መቁረጥ፣ ሃዘን ያጠላባቸው ግጥሞች ከሆኑት መሃል ‹ባዶ ልብ ለብቻ› ገጽ 25 ላይ ‹‹የጸጸት ቁራኛ፣ በሆንኩና፣
ችዬ በነበር፣ የውስጤን ቁስለት።
ወና ልብ በያዝኩና፣
ያልተሸጓጎጠበት ብክለት፤
ሰው መስዬ በነበርኩ፣
የመጣ የሄደውን የምችልበት።›› ገጽ 27 ላይ፦
‹‹ይዘንባል ይላሉ፣
ሲዘንብ አላየሁም፣
ሁልጊዜ ደመና፣
ሰማይ ሚያጨልም።›› ገጽ 35፦
‹‹በቃ እንግዲህ አሁን፤ ከአሁንም በኋላ፣
ተስፋ አያበላ፣
ምኝት አይሆን ጥላ።
እንኳንስ ለከርሞ፤ ነጋችንም እንጃ፣
ተቆርጧል ማገጃ፣››
ገጽ 61፦ ‹‹እየመሸ ይመስለኛል እየመሸ፣
የጸሃይ ብርሃንን ሳይ እየሸሸ፣
የልቤ ተስፋ እያነሰ፣ ጉጉቴም ቀስበቀስ ተኮላሸ።››
ገጽ 62 ‹የተረፈኝ›፣ 64 ‹መኖሬ ይገርመኛል›፣ 89 ‹ውሰደን› ‹‹ያ ረቢ ውሰደን፣ መሬት ጠልታናለች፣
በጨካኝ ፍጡሮችህ፣ ታስገድለናለች።››፣ 95 ‹ዘመን›፣‹ያለሁ መስሏችኋል› የመሳሰሉት ከተስፋ ቆራጭ ግጥሞች መሃል የሚጠቀሱት ናቸው።
፨ የኤርትራን፣ የሌሎች አካባቢዎችንም፣ አዱሊስ፣ ባሌ እና ኬኒያ ድረስ ያለውን ሁነት በማየቱ ‹መበታተን› በሚል ርዕስ ምሬቱን አሰፈረ።
‹‹እንዲህ ተበጣጥሰን፣
እንዲህ ተበታትነን፣
እንዳልነበርን አብረን፣›› (3) እያለ ይመረራል። “መች ነው የሚያበቃው ችግሩ? መች ነው የምንኖረው? ሃዘን ስቃይ አብቅቶ ተድላ ፌሽታ እሚከተለው?” - ይጠይቃል።
‹‹ያባት ልብ ስጠግን፣
የእናት እምባ አብሼ፣
የወንድም ችግር ስቀርፍ፣
ሆዴ እየተራበ፣ ቤተሰቤን ላትርፍ።
እህቴን ላሳርፍ፣ ስቃያቸው ያክትም፣
እኔ ጎሳቁዬ የቤት ችግር ልልቀም።
እያልኩ ምታገሰው፣ ለስንት አመታት ነው?
ለኔስ የምኖረው በየትኛው ቀን ነው?
በየትኛው አመታት በየቱ ዘመን ነው?›› (16) ይላል።
‹‹የጥርስ ህመም›› በሚለው ግጥሙ የራስን ጥቅም ለማስከበር ሃገር አይሸጥም፣ ህዝብ አይለወጥም፣ ወገን አይበዘበዝም ይለናል። ያን ችግር ለህዝባችን ብንነግረው ሐገሬው ይፈታልናል ይለናል። እንደ ጥርስ ህመሙ ምሳሌ ከሆነ “በፌጦ፣ በዳማከሴ እድናለሁ”፣ በሃገሬ በሌላ መዳን የለም ይላል።
፨ ‹ኢትዮጵያ - 2› በሚለው ግጥም ስለ ሐገሩ እና ስለ ህዝቦቿ ይመረራል። ‘እንዴት ሰው ሃገሩን ትቶ!’ ይላል። “ምሑር ይባልና አንቺን ወዲያ ጥሎ ለባርነት ይሮጣል። እንደዚ ከሆነ እንዴት ትለሚያለሽ?” ይጠይቃል። ‹‹ወደፊትሽን ሳስብ ሁሌ ወደ ኋላ።›› (48) ይላል። ከምንም በፊት የምትቀድመው ሃገር እንደሆነች በ ‹ብቻ አገሬ ትደግ› ያስገነዝባል።
‹‹ራበን አትበሉ፣
ደኸየን አትበሉ፣
ታረዝን ተጠማን፣
ተቸገርን አትበሉ፣
‘ኔን አርዳችሁ ጣሉ።›› (46) ይላል።
፨ ‹‹ታክሲ ውስጥ አንገቱን ደፍቶ ሲያለቅስ ላየሁት ወጣት›› ብሎ ‹አልቅስ› በሚል ርዕስ በ4 ገጾች የጻፋቸው ስንኞች፤ የወጣቱ ለቅሶ መነሻ ሆነው እንጂ የጻፈው ስለዘመኑ ነው። ገንዘብ ከሰውነት በላይ ለሆነበት ዘመን፡
‹‹ኑሮ ጣሪያ ነክቷል፣
የሰው ነፍስ በሽ በሽ ነው፣
ገንዘብ ዘውድ ጭኖ፣ ባሮቹን በውክቢያ፣ ቀልባቸውን ወስዷል።›› (22) እያለ ይገልጻል። ፈጣሪም፣ ሰዎችም የተዉህ ሲመስልህ ‹አልቅስ የኔ ጋሻ› ይላል። ዕንባ ሲፈስህ ነው ውስጥህ የሚነጣው፣ ሃዘን የሚቀልልህ ይላል። ‘ስታለቅስ ጽድት ትላለህ፤ ከዚያም ቀጥ ትላለህ። ደግመህ አትሸነፍም’ በማለት ይገልጻል።
‹‹አጥበህ ጥርት በል፣
ጽድት እንደ ጋቢ፣
ለክብር ሚደረብ፣
ለትልቅ ታሳቢ።
ኩልል እንደ ውሃ፣
ብርት እንደ ጸሃይ፣
ንጥት ከበረዶ፣
ከጥጥ ንጣት በላይ።
ዳግመኛ አትሸነፍ፣
እርም ይሁን ማንባትህ፣
በራስህ ቃል ጽና፣
ዳግመኛ አትንበርከክ፣
ተነስ እንደገና።›› (24) ይላል።
፨ ሰው የራሱን ትቶ ለሌሎች ሃሳብ ማድላቱን፤ የራስን፣ የሐገርን ትቶ የሌሎች መመኘትን፣ በራስ ሳይብቃቁ፣ ያላቸውን አስተውለው ሳያስተነትኑ ወደ ሌሎች ማማተርን፤ የአሁን ዘመናችን መልክ የሆነውን ‹መንገድ› በሚለው ግጥሙ ይገልጻል።
‹‹ማሰብ የለም ለአንድ አፍታ፣
ለራስ ማውራት በጎንታ።
ብቻ መሄድ ዳሩን ይዞ መሃል ገብቶ፣
ላለመውጣት ተጎትቶ።
ሁሌ መሄድ፣
በሰው መንገድ።›› (1)
፨ ስለ ሐገሩ እና ስለ ዘመኑ ሁኔታ ፈጣሪውን ይማልዳል፤ ይቅርታ ይላል።
‹‹አሥሩን አክብሬ አሥር አፈርሳለሁ፣
ሆኖም እኔ ያንተ ነኝ፣
መሐሪው ሩሕሩሑ፣
ምን ታረገኝ ይሆን? ሰዎች ይፈርዳሉ
የእሳት ነህ፣ እያሉ።
መሳጣሪዎቹ፣ እኔና አንተ ነን፣
እኔ አምንብሃለሁ ወዴትም አትጥለኝ።››( 8) ይላል።
፨ ራሱን ‹ኢብራሂም ያለ ሰው› በሚለው ግጥም ከነብዩ ኢብራሂም ጋር ሊያወዳድር ይከጅልና ዘመኑ ይከለክለዋል። ሰው አብሯቸው ካልበላ የማይበሉ የነበሩ እሳቸው፤ ራሱን እንዲያ ያደርጋል። መልሶ ደግሞ ‹‹ኢብራሂም ባይበላ አላህ ያበላዋል፤ እኔ የለፋሁበትን እንዴት እሰጣለሁ?›› ይላል። በረከት ጠፍቷል፣ አንድ ትሪን በሁለት ጉርሻ ነው የምንበላው። በዚህ ሁኔታ ያ(ብ)ባላኝን እረግማለሁ እንጂ እንዴት ሰጠዋለሁ? ብሎ ይጠይቃል።
‹‹ኢብራሂም ባይበላም፣ ጀሊሉ ያበላዋል፣
በየቱ ኢማኔ፣ ምግብ ይተርፈኛል?
የዘንድሮ ቀለብ፣ በረካ ነስቶታል።
ከሁለት ጉርሻ አይዘልም፣ የትሪውን ዙሪያ በጣት ለመሶምሶም፣... ››(33) ይልና በዚህ ፈጣሪ እንዳይቆጣው ይፈራል። “ሰው ሲሞት እኮ አዝናለሁ፣ ሰው ሲንገላታ፣ ሲከዳ ይከፋኛልና አቤቱ ማረኝ!” ብሎ ይለምናል።
‹‹ኢብሮ ረኅብ ይችላል፣ እኔ አይሆንልኝም፣
በዚህም ተናደህ፦
ለምን አባክ ብለህ፣
እሳት ዶልሃለሁ መቼም አትለኝም።› ›(34) ይለዋል።
፨ ሌላው የእስልምና ዕምነት ተከታይ ያልሆነ ሰው ሊረዳው የሚከብደው ቃላትን ተጠቅሟል። ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ጋሽ ተሾመ ብርሃኑ ከማል እንደጻፉት፤ ‹‹ምንም እንኳን ኢስላማዊ ፅሁፎች መታተም ከጀመሩ ጥቂት አስርታት ቢቆጠሩም ዓለማዊ በሆነ ግጥም ግን አረብኛ መጠቀም የተለመደ አልነበረም። በምትኩም ምርጥ ቃላት ለመጠቀም ሲያስፈልግ ከግዕዝ መዋስ የተለመደ ነበር። የፅሁፉንም ውበት ለመጠቀም ግዕዝ አገልግሎት ላይ ውሏል። ሁሴን ከድር ግን [አረብኛን] በግጥም መፅሐፉ በማካተት ፈር ቀዳጅ የሆነ ይመስለኛል።›› ይላሉ።
፨ በአጠቃላይ መጽሐፉ ውስጥ ያሉት ግጥሞች ሁሉም ውብ ናቸው። ለእኔ ደሞ በተለይ ለይቼ፣ ደጋግሜ ላነብ የምወደው ‹‹ነው ነበረ፣ አልቅስ፣ ኢብራሂም ያለ ሰው፣ ኢትዮጵያ - 2፣ ‘ኮምድ’ ለሐበሻ፣ የጥርስ ህመም፣ እዚያው ነበርኩ፣ የዘላለም አፍታ›› የሚሉት ናቸው።
ከአዘጋጁ፡-
ጸሃፊውን በቴሌግራም አድራሻው፡-
@NEBILADU ማግኘት ይቻላል፡፡
Tuesday, 24 September 2024 12:20
ኢትዮጵያና ዘመን፤ በሁሴን ከድር ግጥሞች
Written by ነቢል አዱኛ
Published in
ጥበብ