Saturday, 28 September 2024 19:49

በአማራ ክልል የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመሩ ተጠቆመ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

• ባለፉት 4 ወራት ከ76ሺ በላይ ተፈናቅለዋል

 ባለፉት አራት ወራት፣ በአማራ ክልል፣ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች  ቁጥር መጨመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም  ባወጣው ሪፖርት፣ ባለፉት አራት ወራት፣ በአማራ ክልል ስምንት ዞኖች ውስጥ መፈናቀል መከሰቱን አመልክቷል፡፡
በድርጅቱ ሪፖርት መሠረት፤ በክልሉ በዚህ ወቅት በአጠቃላይ 76ሺ 345 ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 34 በመቶ የሚሆኑት ከአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር ሲቀላቀሉ፣ አብዛኞቹ በተጨናነቁ የጋራ ማዕከላት መጠለልን መርጠዋል፡፡
እየቀጠለ ያለው  መፈናቀል በማያባራ  የጸጥታ ችግር መባባሱን ያመለከተው ድርጅቱ፤ ይህም መፈናቀሉን ማባባስ ብቻ ሳይሆን፤በአካባቢው ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁሟል፡፡
“ይህ የኑሮ መተዳደሪያ መስተጓጎልና በተቀባይ ማህበረሰቦች ላይ የሚያሳድረው ጫና፣ የሰብአዊ ቀውሱን የበለጠ አባብሶታል” ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
በቅርቡ  የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ለሚኖሩና በክልሉ 88 ጣቢያዎች ውስጥ ለተጠለሉ በርካታ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዋና መንስኤዎች ናቸው።
በጥር 2015 ዓ.ም፣ የአማራ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን፣በአማራ ክልል መጠጊያ የሚፈልጉ ተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ  መጨመሩን ያመለከተ ሲሆን፤ ቁጥራቸው ከ1 ሚሊየን እንደሚበልጥም አስታውቆ ነበር፡፡
ተፈናቃዮቹን ለመርዳት ጥረት ቢደረግም በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ በክልሉ በመንግስት ታጣቂዎችና በፋኖ መካከል በቀጠለው ግጭት ሳቢያ እርዳታውን ለፈላጊዎቹ ማድረስ አዳጋች ሆኗል ተብሏል፡፡    
ቪኦኤ በመስከረም 2016 ዓ.ም ባሰራጨው ዜና፣ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን፣ ለተፈናቃዮች በወቅቱ መድረስ የነበረበት የምግብ እርዳታ፣ በጸጥታ ችግር ሳቢያ መስተጓጎሉን ዘግቧል፡፡  በሌላ በኩል፣ በመጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች እንደጠቆሙት፤ የምግብ አቅርቦት እጥረቱ፣ በህጻናት ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አስከትሏል፡፡
የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለቪኦኤ በሰጠው ምላሽ፣ የምግብ አቅርቦት መጠነኛ መዘግየቶች በፀጥታ ችግሮችና በተወሰኑ አካባቢዎች በትራንስፖርት እጥረት መከሰቱን አምኖ፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡  
የትግራይ ሁኔታም እንዲሁ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት  እንደሚያመለክተው፣ በትግራይ ክልል ያለው የተራዘመ የመፈናቀል ችግር ያለማቋረጥ የቀጠለ ሲሆን፤አሁንም በርካታ ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በጋራ ማእከላት ይኖራሉ።
ድርጅቱ እንዳስታወቀው፣ ባለፉት ወራት 56 ሺህ  ሰዎች ወደ ትግራይ የትውልድ ቀዬአቸው  እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ወደ አላማጣ፣ ጨርጨር፣ ኮረም ከተማ፣ ላላይ ጸለምቲ፣ ማይጸብሪ ከተማ፣ ኦፍላ፣ ራያ አላማጣ፣ ራያ ጨርጨር፣ እና ዛታ የመሳሰሉ አካባቢዎች ተመልሰዋል፡፡
እየተካሄደ ያለው ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሂደት በአዎንታዊነት የሚታይ ቢሆንም፣ በ99ኙ የጋራ ማእከላት የቀሩት ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ችግር አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል።
ከአንድ ወር በፊት፣ አንድ የትግራይ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለስልጣን፣ በክልሉ ወደ 956 ሺ የሚጠጉ ተፈናቃዮች፣ በቂ እርዳታ ሳያገኙ መቅረታቸውን ገልጸዋል።
የዛሬ ዓመት በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ባወጣው ሪፖርት፣ ከአራት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ተፈናቅለው እንደሚገኙ አመልክቶ ነበር፡፡ ድርጅቱ በሁሉም ክልሎች ውስጥ ባደረገው ግምገማ፣ከ4.38 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ተፈናቅለው እንደሚገኙ ለመረዳት ችሏል፡፡
ከአራት ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑት ተፈናቃዮች መካከል 66 በመቶ የሚሆኑት በግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ መሆናቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ከግጭት በተጨማሪም ድርቅና በማኅበረሰቦች መካከል የሚያጋጥም ውጥረት በመንስኤነት ጠቅሷል፡፡



Read 940 times