Saturday, 28 September 2024 20:04

በመንግስትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት በርካቶች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

• ተኩስ አቁም ተደርጎ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቋል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ በመንግሥትና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት ሳቢያ በርካታ የአማራ ክልል ነዋሪዎች መገደላቸውን አስታውቋል። ኮሚሽኑ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው የሩብ ዓመት ሪፖርቱ፣ በአማራ ክልል ተኩስ አቁም ተደርጎ፣ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ጠይቋል።
በዚሁ ሪፖርት ላይ በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ፣ ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. እና የቀወት ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂ ቡድን አባላት በመኖሪያ ቤታቸው መገደላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌሊት ደግሞ የፋኖ ታጣቂ አባላት ከክልሉ አዊ ብሔረሰብ ዞን፣ ቲሊሊ ከተማ፣ አሽፋ ቀበሌ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የመንግስት የጸጥታ አካላት ወደ ቀበሌው በመግባት፣ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋት ጀምሮ እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት ድረስ ቤት ለቤት በመፈተሽ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ትቀልባላችሁ፣ ቤት ታከራያላችሁ”፣ እንዲሁም “የፋኖ አባላት ናችሁ” ብለው የጠረጠሯቸውን 10 ሲቪል ሰዎች በጥይት መግደላቸው ታውቋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን፣ ሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ ወተት ዓባይ ቀበሌና በአካባቢው በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂ አባላት መካከል ከነሐሴ 6 እስከ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተካሄደ ውጊያ ጋር በተያያዘ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በመንገድና ቤታቸው ውስጥ ያገኟቸውን በግጭቱ ተሳትፎ ያልነበራቸውን 7 ሰዎች እንደገደሉ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ መጠቆማቸው በሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። ከሟቾች ውስጥ በአካባቢው የማሕበረ ስነ ልቦና ጉዳት እንዳለበት የሚታወቅ አንድ ግለሰብና አንድ የ17 ዓመት ልጅ እንደሚገኙበት ተመልክቷል። በተጨማሪም፣ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከንጋቱ 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ ቄስ አወቀ መኮንን የተባሉ አረጋዊ፣ ሃይማኖታዊ ስርዓት ለማከናወን ወደ አቡነ ዘርዓብሩክ ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ላይ እያሉ፣ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በጥይት እንደተገደሉ ለማወቅ እንደተቻለ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የቦምብ ጥቃት እንደሚፈጸሙ የሚያትተው የኢሰመኮ ሪፖርት፣ ለአብነት ያህል ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡50፣ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ፣ ነሐሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. እና ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 1፡00 ገደማ በአማራ ክልል፣ ባሕር ዳር ከተማ በፋኖ ታጣቂዎች አባላት እንዲሁም ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸሙ የቦንብ ፍንዳታዎች በነዋሪዎች ላይ የደሕንነት ስጋት ከመደቀናቸው ባሻገር ለጊዜው ብዛታቸው ባልታወቁ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።
ኢሰመኮ ባጠናቀረው ሪፖርት መሰረት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ
አዋሽ አርባን ጨምሮ በተለያዩ መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች ከእስር የተለቀቁና ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገ መሆኑ አበረታች መሆኑን አስረድቷል።
ይሁን እንጂ በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የሕግ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስልጣን የሌላቸው የጸጥታ አካላት ጭምር ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለው የነበረ መሆኑን በመግለጽ፣ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ በርካታ ሰዎች ብሔርን መሰረት ያደረገ ስድብ፣ በቂ ብርሃን በማያስገባ ጨለማ ቤት መያዝ፣ ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸሙባቸውና ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተዳረጉ መሆኑን ተጎጂዎች ለኢሰመኮ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለበርካታ ወራት በእስር ቆይተው የተለቀቁ ግለሰቦች በእስር ለቆዩበት ጊዜ አሁን ድረስ መረጃ ለማቅረብ ባለመቻላቸው ወደ ስራቸውና ማሕበራዊ ሕይወታቸው ለመመለስ ከፍተኛ ችግር ያጋጠማቸው መሆኑን አክለው ለኢሰመኮ አስረድተዋል።
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ፣ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጥሪ ያቀረበው ኢሰመኮ፤“በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም ይቆጠቡ” ሲል አሳስቧል፡፡
በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፣ እንዲሁም በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፣ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Read 1197 times