በአለም ታሪክ ከጥንት እስከ አሁን ተደጋግሞ እንደታየው፣ የፖለቲካ ስልጣን ያለ ጠልፎ መጣል ዘዴ፤ ተንኮልና ሴራ የማይታሰብ ይመስል፣ አብዛኛዎቹ መሪዎች ስልጣን ላይ የወጡት/የሚወጡት በዚህ ጠልፎ የመጣል ስልት ታግዘው ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ይህ የበለጠ ሃቅ ነው፡፡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የራስ ተፈሪን አነሳስና ለንግስና መብቃት በዳሰሰው ፅሁፍ፤ የያኔው ራስ ተፈሪ በአልጋወራሽነት ዘመኑ አስቀድሞ ላለመው የንጉሰ ነገስትነት ስልጣን ስጋቶቼ ይሆናሉ ብሎ የለያቸውን የምኒልክ ሹማምንት፣ እንዴት በረቀቀና የራሱ የተፈሪ በሆነ ስልት እንዳስወገደ አይተናል፡፡ ራስ ተፈሪ ታላላቆቹን የምኒልክ ሹማምንት በማስወገድ ሂደት ቀኝ እጁ የነበረው እራሱ ተፈሪ ያደራጀው የመሃል ሰፋሪ ተብሎ የሚጠራው የአድማ ስብስብ ነው፡፡ በኋላ ገሃድ እንደወጣው የዚህ መሃል ሰፋሪ የአድማ ስብስብ የሃሳብ አቀባይና ሴራ መምህሩ የነበረው እራሱ ተፈሪ ነው፡፡
ራስ ተፈሪ በጊዜው የስልጣን ታላላቆቹ የነበሩትን ሹማምንት ጉልበት ሲፈትሽ የነበረውም በዚህ የመሃል ሰፋሪ በሚባለው የአድመኛ ስብስብ በኩል ነው፡፡ ራስ ተፈሪ ሁሉን ካስወገደ በኋላ “ሰዩመ እግዚአብሄር ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ” ተብሎ ዘውድ ጫነ፡፡ በዙፋኑ ላይ ግማሽ ክፍለዘመን ለሚሆን ግዜ ተቀመጠበት፡፡ ግማሽ ክፍለዘመን ለሚሆን ጊዜ በኢትዮጵያ የንጉሰ ነገስት የዙፋን ወንበር ላይ ተደላድሎ የተቀመጠው አፄ ሃይለስላሴ፤ የመሃል ሰፋሪ የሚባለውን ስብስብ አምሳያ በሆነውና እራሱን ደርግ ብሎ በሚጠራው ሚስጥራዊ፤ ወታደራዊ ስብስብ፣ ንግስናህ ይብቃህ ተብሎ ወረደ፡፡
ደርግ በመስመራዊ መኮንኖችና ዝቅተኛ ማእረግ ባላቸው ወታደሮች ለአድማ የተጠራራ ወታደራዊ ስብስብ ነው፡፡ የዚህ ወታደራዊ መኮንኖች ስብስብ የመጀመሪያ ወራት የምክክር አስተባባሪና አደራጅ የነበረው ኮሎኔል አጥናፉ አባተ ነበር፡፡ በሂደት የሃረር ጦርን ወክሎ የመጣው ሻላቃ መንግስቱ ሃይለማርያም ገኖ መውጣት ቻለ፡፡ የአጥናፉንም ወንበር ተረከበ፡፡ መንግሰቱ የሃረር ጦርን ወክሎ ወደ አዲስ አበባ የተላከው ከሌሎች የተሻለ ሆኖ ሳይሆን፣ በረባሽነቱ ስለሚታወቅና ለጊዜውም ቢሆን ከፊታቸው ዞር እንዲልላቸው በመፈለግ ነበር፡፡ ቆይቶ ግን በደርግ ውስጥ ገኖ መውጣቱ ያላማራቸው የጦር አለቃዎቹ፣ መንግስቱ ቀድሞ ወደላካቸው ክፍለ ጦር እንዲመለስ ጥሪ ቢያደርጉለትም እሱ ግን እንደማይመለስ አስታወቀ፡፡ ለእምቢታው መቀጣጫ እንዲሆን በማለትም ሚስቱንና ልጆቹን በቁም እስር መልክ በቁጥጥር ስር እንዳደረጓቸው አሳወቁት፡፡ መንግስቱ ለእሱ ብቻ ከዳመናው ጀርባ የምትታየውን ስልጣን በማሰብ፣ “ስትፈልጉ ቀቅላችሁ ብሏቸው” አላቸው፡፡ ስልጣን ላይ ሲወጣ የመጀመሪያውን ሰይፍ ያሳረፈው በእነሱ ላይ ነው፡፡
ይህ ወታደራዊ ስብስብ ከወሰናቸው ውሳኔዎችና ከወሰዳቸው እርምጃዎች ጀርባ ፈርጣማ ጉልበት የነበረው ሻለቃ መንግስቱ ነው፡፡ ሻለቃ መንግስቱ እንደ ራስ ተፈሪ ወደ ሊቀመንበርነት ባደረገው ጉዞ የወደፊት ስልጣኑ ተቀናቃኞቹን ያለርህራሄ በጭካኔ አስወገደ፡፡ የመንግስቱ ከተፈሪ የሚለየው እርምጃዎቹ የአደባባይና በደም የተጨማለቁ መሆናቸው ነው፡፡
የ17 ዓመቱ የመንግሥቱ ዘመን በግድያ የታጀበና ጸሃይ የሞቀው አለም ያወቀው ሀቅ ቢሆንም፣ መንግስቱ ግን ትኋን እንኳን አልገደልኩም ባይ ነው፡፡ በሱ የስልጣን ዘመን ለተፈፀሙት ግድያዎች ተጠያቂ የሚያደርገው አንድም የመንግስቱ የግድያ ካራ ባረፈባቸው በሟቾቹ በራሳቸው አልያም በንኡሳን ደርግ አባላት ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ መንግስቱ የራሱ ሳያንሰው በ60ዎቹ ግድያ የደርግ አባላት ተጠያቂ አይደሉም በማለት፣ ለዚያ ውሳኔ ያበቃን የንኡስ ደርግ አባላት ጫና ነው ሲል ጥፋቱን በሌሎች አላኳል፡፡ እንደ መንግስቱ ከሆነ፣ በዚህ ግድያ ውስጥ መንግስቱም የደርግ አባላትም የሉበትም፡፡
ለ17 አመታት ስልጣን ላይ የቆየውና ኢትዮጵያን በደም እንድትጨማለቅ ያደረጋት መንግስቱ ግን ማን ነው? ልጅነቱንና የቤተሰቡን ሁኔታ ትተን በወታደራዊ መኮንንነት ጊዜው ወዳጆቹ የነበሩት የሚሰጡትን ምስክርነት ስናነብ፣ መንግስቱ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ በስራ ባልደረቦቹ ተደጋግሞ እንደተጠቀሰው፤ መንግስቱ ሲበዛ “ፈሪ፣ ተጠራጣሪ፣ ጨካንና ቂመኛ” ሰው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሀረር ሦስተኛ ክፍለጦር ውስጥ በነበረበት ጊዜ በነበረው ምግባረ ብልሹነትና አልታዘዝ ባይነቱ ተደጋጋሚ ቅጣት ደርሶበታል፡፡ መንግስቱ በወታደር መኮንንነቱ ለበላዮቹ የማይታዘዝ አድመኛ በመሆኑ የ3ኛ ክፍለጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ሃይሌ ባይከዳኝ የደረጃ እድገት ነፍገውታል፡፡ ለሁለት አመት ምንም አይነት የደረጃ እድገት እንዳያገኝ ቅጣት ተጣለበት፡፡ መንግስቱ አቀበትና ቁልቁለት የበዛበትን የፖለቲካ መልክአምድር አልፎ የደርጉ ዋና ሰው ሲሆን፣ ሰይፉን የመዘዘው ሀረር ሳለ የደረጃ እድገት በከለከሉት ወታደራዊ ሃላፊዎች ላይ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ እንደሚሉት፤ መንግስቱ ጨካኝ የነበረው ፈሪ ስለነበረ ነው፡፡ መንግስቱ በአደባባይ ባደረጋቸው ንግግሮቹና በብሄራዊ ሸንጎ በተደረጉ ስብሰባዎች ይህን ፍርሃቱን ደንዳና በሆኑ ቃላት ለመሸፈን ሞክሯል፡፡ የመንግስቱን ንግግሮች ልብ ብሎ ላዳመጠ ከንግግሮቹ ውስጥ የፍርሃቱን ድምፅ ማዳመጥ ይችላል፡፡ የስነልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ፍርሃት ሁሉን እንድንጠራጠርና እንደ ጠላት እንድንመለከት ያደርገናል፡፡ መንግስቱም ፈሪ ስለነበር ሌላው ቀርቶ የራሱ ጥላ እንኳን የሚያስፈራው ሰው ነበር፡፡ ስር በሰደደ ፍርሃቱ ምክንያት መንግስቱ ፍጹም ጨካኝ ሆነ፡፡
መንግስቱ በአስተዳደጉ፤ በመልኩና በቆዳ ቀለሙ ስለሚያፍር የበታችነት ስሜት ይሰማው እንደነበር ቅርቡ የነበሩ ሰዎች ፅፈውታል፡፡ ይህ የበታችነት ስሜት ለስልጣን ከነበረው ጥማት ጋር ተዳምሮ በቀለኛ አደረገው፡፡ በበቀል ስሜት ተገፋፍቶ ለወሰዳቸው እርምጃዎችና ብዙዎችን ለሞት በዳረገው የ17 አመት ስልጣን ዘመኑ፣ መንግስቱ ከደሙ ንፁህ ነኝ ባይ ነው፡፡ ለዚህ ከደሙ ንፁህ ነኝ ለሚለው ነውሩ ምስክራችን እንዲሆነን መንግስቱ በመጨረሻው የሸንጎ ስብሰባ ካደረገው ንግግር የሚከተለውን እንጥቀስ፡፡
“የዚህችን ሀገር አንድነት በደማችን፤ በአጥንታችን፤ በሃይላችን እናድን ወይም የአገራችንን አንድነት አስረክበን ስናበቃ በታሪክ ፊት ዘላለም ተወቃሽ እንሁን፡፡ ከፊታችን ያለው ጥያቄ ይህ ነው፡፡ እኔ ሃላፊነቴን ተወጥቻለሁ፡፡ ታሪክ አይፈርድብኝም፡፡”
ታሪክ አይፈርድብኝም ማለት እንግዲህ ከደሙ ንፁህ ነኝ ማለት ነው፡፡ መንግስቱ በርእሰ ብሄርነቱ ጊዜም ሆነ የደርጉ አደራጅና ምክትል ሊቀመንበር በነበረበት ጊዜ ለተፈፀሙት ዘግናኝና አረመኔያዊ ግድያዎች ጣቱን የሚቀስረው አንድም ወደተረሸኑት ሰዎች አንድም በንኡስ ደርግ አባላት ላይ ነው፡፡ መንግስቱ በተለምዶ ስልሳዎቹ የሚባሉትን የቀዳማዊ ሃይለስላሴ መንግስት ባለስልጣናት ያለወንጀላቸውና ያለፍርድ ሂደት በእጅ ማውጣት ብቻ ህይወታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልፍ ያደረገ ጨካኝ መሪ ነው፡፡ ይህን ያህል ተብሎ በቁጥር ሊገመት የማይችል ወጣት የጨፈጨፈ፤ የሃገራችንን ታሪክ በቀይ ነጭ ሽብር ደም ያጠበ ጨካኝ ሰው ነው፡፡ መንግስቱ በራሱ አንደበት ደጋግሞ እንዳለው፣ ይህን ሁሉ ያደረገው ለሃገር አንድነት ሲል ነው፡፡ ለመንግስቱና ለመሰሎቹ አብዮት ያለደም ግቡን አይመታም፡፡ መንግስቱ በስሜት ቀስቃሽ ንግግሩ ሽፋንነት፣ እራሱን ከተፈጸሙ ወንጀሎች ለመሸሸግ ሞክሯል፡፡
መንግስቱ በትምህርቱ ብዙ ባይገፋም የንግግርና የመተንተን ችሎታ ነበረው፡፡ ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ “እኛ እና አብዮቱ” በተባለው መፅሐፋቸው እንዳሰፈሩት፤ “መንግስቱ እንደ ብዙዎቻችን ተወካዮች ሳይሆን፣ ገና ከጠዋቱ የስልጣንን ጥቅም የተገነዘቡ፣ ግባቸው ላይ ለመድረስም በጥንቃቄ በመራመድና አሻግረው በመመልከት ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ ለዚህ እንዲረዳቸውም በደርግ ውስጥ የነበሩትን ወታደሮች ድጋፍ ማግኘት ቻሉ፡፡” መንግስቱ አሰቃቂ ግድያዎቹን የፈፀመው በእነዚህ ለእሱ የጭፍን ድጋፍ በሰጡ ወዳጆቹ ድጋፍ ታግዞ ነው፡፡ መንግስቱ ባካሄደው የግድያ እርምጃ፣ በደርግ አባላትና በወታደሩ በመወደሱ፣ በደርግ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ሆኖ እንዲወጣ አደረገው፡፡
የኢትዮጵያ አብዮት በዝነኛነቱ ከ1917ቱ የሩሲያውና የፈረንሳይ አብዮት ጋር የሚስተካከል ነው፡፡ በሩሲያና በፈረንሳይ እንደሆነው ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ለዘመናት ጸንቶ የኖረው ዘውዳዊ ስርአት ሰላማዊ በሆነ አብዮት መውረድ ችሎ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ የደርግ ጊዜያት መመሪያቸው የነበረውን “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን መፈክር ያስተዋወቀው መንግስቱ ነው፡፡ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም”፡፡ የተገመተው ያለምንም ደም ለውጥ ፍጹም ያልተገመተውን የደም ጎርፍ አስከትሎ መጣ፡፡ አገር አማን ብለው እጃቸውን በሰላም የሰጡት የንጉሱ ባለስልጣናት፣ ምንም አይደርስብንም ብለው ገምተው ነበር፡፡ በህግ የተያዘ ጉዳይ ነው ስለተባለ የእስረኞቹም የህዝቡም እምነት የነበረው ጉዳያቸው በህግ እልባት ያገኛል የሚል ነበር፡፡ አማን ሚካኤል አንዶምን ጨምሮ 59 ባለስልጣናት የመንግስቱ ሰይፍ አረፈባቸው፡፡ ደርግ ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ፣ የጄነራል አማን ሚካኤል አንዶም እምቢታ የስብሰባው አጀንዳ ሽፋን ሆኖ፣ 59 ባለስልጣናት የመንግስቱ የግድያ ጥይት ተርከፈከፈባቸው፡፡ መንግስቱና ግብረአበሮቹ ቂማቸውን ተወጡባቸው፡፡ መንግስቱ ግድያው ተገቢ እንዳልሆነ ያምንና ግድያው የተወሰደው በንኡስ ደርግ አባላት ተፅእኖ ስር ወድቀን ነው ይላል፡፡ ጄነራል ሃዲስ ተድላ በቅርቡ ባወጡት መፅሐፍ እንደሚነግሩን ግን መንግስቱ “በንኡስ ደርግ አባላት ተፅእኖ ስር ወድቀን ነው ብሎ የተናገረው ትክክል ካለመሆኑም ሌላ እርሱ ባይደግፈው ኖሮ፣ አጀንዳው ለውይይት አይቀርብም ነበር፡፡”
መንግስቱ ኮሎኔል አጥናፉን ካስወገደ በኋላ የደርጉ ብቸኛ ሊቀመንበርና ርእሰ ብሄር ለመሆን በቃ፡፡ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ግን ሁለቱን የደርግ ሊቃነመናብርትና ስድስት የደርግ ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ገድሏል፡፡ “መንግስቱ ልባቸው በቀላሉ የማይገኝ ድብቅና ቂም የሚቋጥሩ ናቸው፡፡ ማታ እርምጃ የሚወሰድበት ሰው እንኳን ቢያጋጥማቸው ስቀውና አጫውተው በሁለት እጃቸው ጨብጠው ነበር የሚያሰናብቱት፤” ይሉናል ኮለኔል ፍስሃ ደስታ፡፡ ለአብነት ሲጠቅሱም፤ “አንድ እሁድ ቀን ደርግ ፅህፈት ቤት በሚገኘው ካፍቴሪያ ከኮሎኔል መንግስቱ ጋር በመጨዋወት ላይ እያለን የሰደድ ከፍተኛ አመራር የነበረ ሻለቃ ጌታቸው አግዴ ድንገት ይመጣል፡፡ መንግስቱ እኛን ተወት አድርገው ከጌታቸው ጋር በከፍተኛ ሳቅና ፈገግታ በታጀበ ሁኔታ ጨዋታ ቀጠሉ፡፡ በማግስቱ ጠዋት ግን ከቢሮዬ ሆኜ ስመለከት ሻለቃ ጌታቸው አግዴ፣ በሁለት ጠመንጃ የያዙ ወታደሮች ታጅቦ፣ ዘብጥያ ወርዶ ሳይመለስ ቀረ፡፡” በዚህ አይነት መንገድ ብዙዎች ተሸኝተዋል፡፡
ተደጋግሞ እንደታየው መንግስቱ በስልጣኑ ለሚመጣበት ሰው እርምጃ ለመውሰድ በእጅጉ ፈጣንና ጨካኝ ነው፡፡ ጄነራል ተፈሪንና እነ አለማየሁ ሃይሌን እንዴት ፈጣን በሆነ እርምጃ እንዳስወገደ ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ኮሎኔል አጥናፉም በተመሳሳይ መንገድ ተወገደ፡፡ በቁስል ላይ እንጨት ስደድበት እንደሚባለው፣ መንግስቱ አጥናፉን አልገደልኩም ለማለት “አጥናፉን አብዮቱ በላው” ሲሉ ቀጠፉ፡፡
ጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም፣ የሊቀመንበሩን ስልጣን ለመወሰን በወጣ አዋጅ መሰረት “ለአብዮቱ ለኢትዮጵያ አንድነትና ደህንነት አደገኛ በሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ አብዮታዊ እርምጃ ለመውሰድ እንዲችል ህጋዊ” ሽፋን ሰጠው፡፡ ኢትዮጵያ ትቅደም እንዳልተባለ ሁሉ የህዝብና የሃገር ጉዳይ ሁለተኛ ስፍራ እየያዘ፣ ዋነኛ ትኩረታቸው ስልጣናቸውን ማጠናከርና መጠበቅ ብቻ ሆነ ሲሉ፣ ጓድ ፋሲካ ሲደልል “የሻምላ ትውልድ” በተባለ መፅሐፋቸው አስፍረዋል፡፡
መንግስቱ በደርግ ውስጥ በምክትል ሊቀመንበርነት ዘመኑ፣ ንኡሳኑን የደርግ አባላት በሃሳብ በማነሳሳት ሊወስድ ላሰበው እርምጃ ያዘጋጃቸው ነበር፡፡ ጄነራል አማን ላይ እንዲያ አይነት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሰውየውን በተደጋጋሚ ሲተነኩሳቸውና ስሜት ውስጥ እንዲገቡ ሲያደርጋቸው ነበር፡፡ በመጨረሻም የመንግስቱ የጥይት እራት ሆኑ፡፡
ሌላው የመንግስቱ ባህሪው ቀጣፊነቱ ነው፡፡ የብርሀነን፣ የሃይሌን ፊዳን፣ የወዝሊግ አባላት ግድያን እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡ የገነት አየለ “የኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ትዝታዎች” የተባለው መፅሐፍ፣ የመንግስቱ ውሸቶች ስብስብ ነው፡፡ ለእሷ በሰጠው ቃለ ምልልስ፣ በአንዱም ጉዳይ እጁ እንደሌለበትና ምንም እንደማያውቅ በተደጋጋሚ ቀጥፏል፡፡ ራሱ በፃፈው መፅሐፍም ይህንን ቅጥፈቱን ደግሞታል፡፡
ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው መንግስቱ ፈሪ ስለነበር ሁለቴ ለማሰብ አይሞክርም ነበር፡፡ አምባገነኖች መፈራትን ከመወደድ፣ መግደልን ከጀግንነት ይቆጥሩታል፡፡ ባህላችንም አመፀኛና አፄ በጉልበቱ የሆነን ከጀግና፤ በጥበብና በስክነት የሚጓዝን በተቃራኒው ይረዳዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ውስብስብና መልከ-ብዙ ችግር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የመንግስቱ እጅ አለበት፡፡ ግድያ የዘመኑ ቋንቋ ስለነበር በመግደል ችግሮችን መቅረፍ እንደሚቻል ያምን ነበር፡፡ ሰላማዊ ንግግር፤ ውይይት የሚባሉ ምክረ ሃሳቦች አለርጂኮቹ ናቸው፡፡ በለው ፍለጠው ማለትን የለመደው መንግስቱ፤ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንፍታ የሚለው ምክረ ሃሳብ ቢያባንነው አይገርምም፡፡
Saturday, 28 September 2024 20:11
አምባገነን መሪዎችና የሥልጣን ረሃባቸው
Written by በደረጄ ጥጉ
Published in
ነፃ አስተያየት