Saturday, 28 September 2024 20:13

የጃፓን ትዝታዎቼ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ካለፈው የቀጠለ

ካለፈው የቀጠለ
በ1984 ዓ.ም አስራ አንድ ወራት ያህል ለሚፈጅ ስልጠና  ጃፓን ሀገር ሄጄ ነበር፡፡ በጃፓን ሀገር ቆይታዬ ከማይረሱኝ ትዝታዎቼ መሀከል የተወሰኑትን ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ ተርኬላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ቀሪውን አጫውታችኋለሁ፡፡
የቤተሰብ ጉብኝት(Family visit): በጃፓን ቆይታዬ ወቅት የማይረሳኝ ሌላው ነገር የቤተሰብ ጉብኝት ነው። የቤተሰብ ጉብኝት አብይ አላማው፣ ከተለያዩ ሀገራት ለትምህርትና ለስልጠና ጃፓን የሚገኙ የውጪ ሀገር ዜጎች፣ በሀገሪቱ ቆይታቸው ወቅት ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ከጃፓን የተለያዩ ቤተሰቦች ጋር ተገናኝተው እንዲጋበዙና የአብሮነት ጊዜ እንዲኖራቸው፥ የጃፓንን ህዝብ አኗኗር እንዲረዱና የቤተኛነት ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው። በአስራ አንድ ወራት የጃፓን ቆይታዬ ወቅት ሦስት ጊዜ የቤተሰብ ጉብኝት እድል ያጋጠመኝ ሲሆን፥ በአንዱ የቤተሰብ ጉብኝት ፕሮግራም ውስጥ የጃፓናዊት ሴት ጓደኛ (girlfriend) ለማግኘት በቅቻለሁ።
ጃፓናዊቷ ጓደኛዬ ያዮኢ ትባላለች። ከእሷ ጋር ከተዋወቅሁ በኋላ በእረፍት ጊዜያችን በመገናኘት ጥሩ የፍቅር ጊዜ አሳልፈናል። ሀገር ቤት ከተመለስኩም በኋላ በደብዳቤ መገናኘት ቀጠልን። በመጨረሻም በ1987 ዓ.ም. እዚህ አዲስ አበባ ድረስ ልትጠይቀኝ መጥታ የተወሰኑ ቀናቶች በአዲስ አበባ፤ በሀዋሳና በወንዶገነት ካሳለፍን በኋላ ኬንያ በመሄድ ማሳይ ማራ የተባለውንና በኬንያ የታወቀውን ብሔራዊ ፓርክ ጎብኝተናል። የወንዶ ገነትን አካባቢ ስታይ “Nippon mitai!”፥ ትርጉሙም “ጃፓንን ይመስላል” ማለቷ ነበር። እውነቷን ነው። ወንዶ ገነት አካባቢ ደኑ እንዴት እንደሚያምር ያየው ያውቀዋል። ሀገሩ ከዳር እስከዳር እንደ ወንዶ ገነት በደን፤ ያውም በተፈጥሮ ደን ቢሸፈን እንዴት እንደሚያምር አስቡት፡፡
ጃፓን ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት በተለይ ከከተማ ውጪ በተፈጥሮ ደን የተሞላች ሀገር ናት። በሷ በኩል አቋሟ ኢትዮጵያ ውስጥ ከኔ ጋር ለመኖር ነበር። እኔ ግን በወቅቱ የነበርኩበት የኢኮኖሚ ሁኔታ እሷንና እኔን ሊያኖር የሚችል አልነበረም። የኔ አቋም ደግሞ በጃፓን ሀገር ከሷ ጋር ለመኖር ነበር። ይሁን እንጂ ጃፓኖች ለጥቁር ሰው ያላቸው አመለካከት ዝቅ ያለ በመሆኑ ልጅ ወልደን ጃፓን ሀገር ብንኖር በማህበረሰቡ የመገለል ችግር ያጋጥመዋል ብላ በመፍራቷ ወደሀገሯ ከተመለሰች በኋላ ግንኙነታችን ሳይቀጥል ቀረ፡፡  የጃፓኗንና የኔን ታሪክ የሚያውቅ የቅርብ የወንድሜ ጓደኛ “እሩቅ ምስራቅ ሳለሁ ጃፓኗን ወድጄ” የሚለውን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን እየዘፈነ ይቀልድብኝ ነበር።
በቤተሰብ ጉብኝት ወቅት የጃፓኖች የቤት ውስጥ አኗኗር ምን እንደሚመስል ልረዳ ችያለሁ። የሚቀመጡት ሶፋ ላይ ሳይሆን እንደ አረቢያን መጅሊስ አይነት መቀመጫ ላይ ነው። አረንጓዴ ሻይ (Japanese green tea) የመጀመሪያ ግብዣቸው ሲሆን፥ ሩዝ አትክልት፥ ቅጠላቅጠልና የባህር ውስጥ የአሳ ዝርያዎች ዋነኛ ምግባቸው መሆኑን አይቻለሁ። ቤታቸው ውስጥ ሲገባ በራፍ ላይ ጫማ ተወልቆ በተወሰነለት ቦታ ከተቀመጠ በኋላ በነጠላ ጫማ ነው ወደ ውስጥ የሚገባው። የቤታቸው ወለሉ ከንፅህናው የተነሳ ፊትን እንደ መስታወት የሚያሳይ የሚባልለት አይነት ነው። ጃፓን በእንጨት ምርት ታዋቂ ስለሆነች የቤታቸው ወለልና አብዛኛዎቹ የቤት ዕቃዎቻቸው በጣም ውብ በሆኑ የእንጨት ምርቶች የተሰሩ ናቸው። እንግዳ ሲቀበሉ በፊታቸው ላይ ትህትና የሚነበብባቸው ሲሆን፤ ልክ እንደኛ ባህል ጎንበስ ብለው ሰላምታ በመስጠት ያስተናግዱታል።                                         
አንድ ሰው የተሟላ ህይወት አለው የሚባለው የሚከተሉት አራት ነገሮች ሲሟሉለት ነው የሚል የድሮ የፈረንጆች አባባል አለ። (በእርግጥ ይህ የነሱን የኑሮ ስታንዳርድ መሰረት ተደርጎ የተነገረ ነው) “American home; British Rolce royce; French cuisine and Japanese wife”  (“የአሜሪካውያን መኖሪያ ቤት፥ የእንግሊዝ ሮልስ ሮይስ መኪና፥ የፈረንሳይ ምግብ እና ጃፓናዊት ሚስት” እንደማለት ነው፡፡) እንደምንሰማው የአሜሪካውያን ቤት ሰፊና ሁሉን ነገር የያዘ ነው፥ የእንግሊዝ ሮልስ ሮይስ መኪና ቅንጡ መሆኑ ይታወቃል፥ የፈረንሳዮች የምግብ አሰራርና የአበላል ስርዓት አርት እንደሆነ እንሰማለን፥ የጃፓን ሴቶች ለጓደኛቸው ወይም ለትዳር አጋራቸው የሚያሳዩት ፍቅር፥ አክብሮትና ታማኝነት አለም አቀፋዊ እውቅና የተቸረው ነው። ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት መሀከል ሦስቱን፥ ማለትም የቤቱን፥ የመኪናውንና የምግቡን የማየት ዕድል አላጋጠመኝም። አራተኛውን ግን፥ ማለትም የጃፓንን ሴት በሚስትነትም ባይሆን በጓደኝነት አይቻለሁ። በመሆኑም ስለነሱ ከላይ የተጠቀሰው ነገር ትክክል ስለመሆኑ እመሰክራለሁ።
ቋንቋ፡ በጃፓን ቆይታዬ የመጀመሪያ አንድ ወር ላይ የጃፓንኛ ቋንቋ ማታ ማታ ተምረናል። በዚህ የአንድ ወር የቋንቋ ስልጠና መሰረታዊ የሆኑ የዕለት ተዕለት መግባቢያ አነጋገሮችን አስተምረውን በቆይታዬ ወቅት ተጠቅሜባቸዋለሁ። እንደማንኛውም ሌላ ቋንቋ፣ ቋንቋው በየአካባቢው የራሱ የአነጋገር ዘይቤ ቢኖረውም፣ የጃፓን አጠቃላይ ህዝብ የሚናገረው አንድ የጃፓንኛ ቋንቋ ነው። ከጃፓናዊቷ የሴት ጓደኛዬ ጋር ስገናኝ የተማርኳትን ትንሽ የጃፓንኛ አባባሎችን ተጠቅሜ በጃፓንኛ ላናግራት እሞክር ነበር። ምንም እንኳን የቋንቋው ችሎታዬ በጣም ውሱን ቢሆንም፤ “ቶማስ ጃፓንኛ ስትናገር በጣም ጥርት ያለ አነጋገር ነው የምትናገረው” ትለኝ ነበር። የምችላትን የጃፓንኛ ቋንቋ እንዴት ጥርት አድርጌ ለመናገር ቻልኩ? ብዬ ሳሰላስል አንድ መልስ ላይ ደረስኩ። በጃፓንኛ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ድምዖች በሙሉ (በ”ረ” እና በ”ለ” ድምዖች መሀከል ያለ ድምፅ ካላት ፊደል በስተቀር) በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ አሉ። በመሆኑም የጃፓንኛ ቋንቋ ስናገር ጥርት አድርጌ የመናገር ምስጢሩ ይሄ ይመስለኛል።
በጃፓን ቆይታዬ ሌላው የታዘብኩት ነገር የእንግሊዝኛ ቋንቋን ይመለከታል። በኦሳካ አለም አቀፍ የስልጠና ማዕከል ውስጥ የነበርን ሰልጣኞች ከሰሜን አሜሪካ፥ ምዕራብ አውሮፓ፥ ከራሺያ፥ ከአውስትራሊያና ከኒውዚላንድ በስተቀር ከመላው አለም የተውጣጣን ሰልጣኞች ነበርን። የቋንቋው የአነጋገር ዘይቤና ችሎታ ይለያይ እንጂ ይሄ ሁሉ የአለም ህዝብ የሚግባባበት አንድ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነበር። ከፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገር የመጡ ሰልጣኞች እንግሊዝኛ ቢከብዳቸውም እንደምንም ሰባብረውም ቢሆን መናገር ግዴታቸው ነበር፤ ለመግባባት። አንዱ የኛ ጓደኛ ሴኔጋላዊ ነበር። ሴኔጋል የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ(Francophone) ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ይሄ ጓደኛችን ጃፓን መጥቶ ይህንን ሁኔታ ካየ በኋላ፤ “እኔ ሀገሬ ሴኔጋል እያለሁ እንግሊዝኛ የመማር ዕድል ነበረኝ፥ ነገር ግን ፈረንሳይኛ ስለምናገር ምን ይሰራልኛል? ሁለቱ ቋንቋዎች አቻ(እኩያ) ስለሆኑ አያስፈልገኝም ብዬ ተውኩት። ነገር ግን በተናጋሪ ብዛት እንግሊዝኛ ቋንቋ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ምን ያህል እንደሚበልጥ ያወቅሁት እዚህ ጃፓን ከመጣሁ በኋላ ነው።  እንግሊዝኛ ባለመማሬ በጣም የቆጨኝ አሁን ነው” አለኝ።
የጃፓን ህዝብ እንግሊዝኛ እምብዛም አይችልም። ሁሉን ነገር በራሳቸው ቋንቋ ስለሚሰሩ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ የተለያዩ አለም አቀፍ ግንኙነቶች በሚያደርጉበት ጊዜ እንግሊዝኛ ስለሚያስፈልጋቸው የተወሰኑ ዜጎቻቸውን ማስተማራቸውን አውቃለሁ። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎቻቸውም ውስጥ ትምህርት በእንግሊዝኛ እንደሚሰጥ መረጃ አለኝ። ከዩኒቨርሲቲ በታች በሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶቻቸውም እንግሊዝኛ ቋንቋ እንደ አንድ ትምህርት እንደሚሰጥ እገምታለሁ።
አሁን ደግሞ ስለራሴ ትንሽ ላውራ። እኛ፥ በተለይ ትንሽ ፊደል የቆጠርንና የመጀመሪያ ዲግሪ፥ ማስተርስ አለን ብለን የምንኮፈስ ሀበሾች፣ የእንግሊዝኛ  ቋንቋ ችሎታችን የሚፈተነው ከሀገር ውጪ ወጥተን የቋንቋ ችሎታችንን ከሌላው ጋር ስንመዝነው ነው። በጃፓን ከኔ ጋር የተማሩት ጓደኞቼ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሆነው ከሴኔጋሉ ልጅ በስተቀር ሁሉም ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ(Anglophone) ሀገሮች የመጡ ናቸው። እኔና የሱዳኑ ልጅ በሀገራችን እንግሊዝኛ በትምህርት ቤት የተማርንና ለስራ በተወሰነ ደረጃ ብንጠቀምም ዕለት ከዕለት የምንጠቀምባቸው የራሳችን ቋንቋዎች አሉን፥ አማርኛና አረብኛ። ሌሎቹ በሙሉ ግን የራሳቸው የሆነ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ቢኖራቸውም እንግሊዝኛን በስራ ቋንቋነት የሚጠቀሙ ናቸው። በመሆኑም የቋንቋው ችሎታቸው ከፍተኛ ነው። በዚህ ምክንያት እኔና የሱዳኑ ልጅ እንግሊዝኛ ስንናገር ተብታባ፥ ገመድ አፍ የምንባል አይነት ነን። በተለይ በጨዋታ ላይ በእንግሊዝኛ ለመቀለድ፥ ወይም “Informal” ቋንቋ ለመጠቀም ስሞክር ያየሁትን ፈተና ምንጊዜም አልረሳውም። ይህም ሆኖ የጋናው ጓደኛዬ፤ “በጣሊያን ተገዝታችሁ እንዴት ይህን የመሰለ እንግሊዝኛ መናገር ቻልክ?” ይለኝ ነበር። በእንግሊዝ ስላልተገዛን  አደነቀኝ እንጂ እኔ እንኳን የቋንቋው “fluent” ተናጋሪ የምባል አይደለሁም።
የእግር ጉዞ(Hiking): በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ካምፓስ እማር በነበረበት ዘመን አብሮኝ ይማር የነበረ ጴጥሮስ አብርሀ የተባለ ጓደኛዬ ጃፓን ለስልጠና ሄዶ እዚያው እንደቀረ ጃፓን ከመሄዴ በፊት አውቅ ነበረ።  በዚሁ መሰረት ጃፓን ልሄድ ስል አድራሻውን ከት/ቤት ጓደኞቻችን ወስጄ፣ ጃፓን ሄጄ ትንሽ ከቆየሁ በኋላ ደውዬ አገኘሁት። ከዚያ በሌላ ጊዜ ደውሎልኝ እሱ ወደሚኖርበት ናጎያ ከተማ ሄጄ ለመገናኘት በቃን።
ናጎያ ከተማ በተገናኘንበት ወቅት ጴጥሮስ የጃፓን ቆይታውን እንዲህ አወጋኝ። “ጃፓን ለአጭር ጊዜ ስልጠና ከመጣሁ በኋላ ስልጠናውን እየተከታተልኩ ሳለሁ፣ እንደ አጋጣሚ ለማስተርስ ዲግሪ ትምህርቴን ሊያስቀጥሉኝ የሚችሉ የፋብሪካ ባለቤት የሆኑ ጃፓናዊ ባለሀብት እንደ ልጅ ተቀበለውኝ (adopt አድርገውኝ) ጃፓን ቀረሁኝ”።  ጴጥሮስ ባጋጠመው ጥሩ ዕድል እንደ ቅናት አይነት ነገር፥ ግን መንፈሳዊ ቅናት፥ ሸንቆጥ አደረገኝ።  ጴጥሮስ አብርሀ የሚኖርባት ናጎያ ከተማ በቶኪዮና በኦሳካ ከተማ መሀከል የምትገኝ ሲሆን፥ ለኦሳካ ከተማ የምትቀርብና የቶዮታ ካምፓኒ ዋናው የማምረቻ ፋብሪካ (Manufacturing industry) የሚገኝባት ከተማ ናት። የጃፓን ከተሞች አንዱ ከሌላው በትልቅነት ይለያያሉ እንጂ ለነዋሪው በሚሰጡት አገልግሎት እምብዛም አይለያዩም። እንኳን ከተሞቹ ይቅርና ገጠር የሚባለው አካባቢ ቢያንስ ጥሩ መንገድ፥ መብራትና ውሀ የተሟላለት ነው። በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገሮች (Industrialized countries) ዋና መለያ ባህርያቸው ይሄ ይመስለኛል።        
ታዲያ አንድ ቀን ጴጥሮስ ደወለና፤ “በሚቀጥለው አርብ ማታ ናጎያ ትመጣና እኛ ዘንድ  አድረህ በማግስቱ ቅዳሜ የእግር ጉዞ (hiking) ፕሮግራም ስላለን አብረኸን ትሄዳለህ” አለኝ። “ኦሆ ተገኝቶ ነው!” አልኩኝ በሆዴ፥ ምክንያቱም የእግር ጉዞ በጣም ነው የምወደው፡፡  ግብዣውን ተቀብዬ ዐርብ ከሰአት በ11 ሰዓት ት/ቤቴ ከሚገኝበት ኪዮቶ ከተማ በባቡር  ወደ ናጎያ ሄድኩኝ።
ኪዮቶ ከተማ በኦሳካና በናጎያ ከተሞች መሀከል የምትገኝ ጥንታዊት የጃፓን ከተማ ነች። በጥንት ዘመን የጃፓን ዋና ከተማ ስለነበረች የድሮ ቤተመንግስትና የጃፓኖች ቤተመቅደስ(Shrine) በብዛት የሚገኙባት ከተማ ነች። ታሪካዊ በመሆኗ ጃፓን ውስጥ ከሚገኙ የቱሪስት መስህብ ከተሞች መሀከል በቀደምትነት የምትጠቀስ ከተማ ናት፡፡
ናጎያ ከተማ ከኦሳካ ከተማ መቶ ኪሎሜትር፥ ከኪዮቶ ከተማ ደግሞ ሰባ ኪሎሜትር ያህል ስለምትርቅ ከኪዮቶ ናጎያ ለመድረስ ሀያ ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀብን። ወደ ናጎያ የሄድኩበት ባቡር ሺንካንሰን በሚባለው ባቡር ሲሆን፥ የዚያን ዘመኑ ሺንካንሰን ባቡር በሰዓት 200 ኪሎሜትር የሚጓዝ ነበር። ከቶኪዮ ኦሳካ 500 ኪሎሜትር ስለሚርቅ  በሺንካንሰን(Bullet train) ባቡር የሁለት ሰአት ተኩል ጉዞ ማለት ነው። ይህ ማለት ንጋት በ12፡00 ከአዲስ አበባ ተነስተን ጧት በ2፡30 ድሬዳዋ መግባት እንችላለን እንደማለት ነው። በአሁን ጊዜ የጃፓኑ ሺንካንሰን ባቡር ፍጥነቱ በሰዓት ከሁለት መቶ ኪሎ ሜትር በጣም እንደሚበልጥ ሰምቻለሁ። እኔ የተጠቀምኩበት ሺንካንሰን ባቡር የኤሌክትሪክ ባቡር ሆኖ እግር ኖሮት በሀዲድ ላይ የሚሄድ ነው። በተለይ የአሁኖቹ ማግሌቭ(Maglev) ባቡሮች(ማግሌቭ የሚባሉት ባቡሮች በሀዲዱና በባቡሩ መሀከል በሚፈጠር ኤሌክትሮ ማግኔቲክ ፎርስ አማካይነት ባቡሩ ሀዲዱን ሳይነካ እንዲንሳፈፍ፥ የግራና ቀኝ ባላንሱን እንዲጠብቅና ወደፊት እንዲስፈነጠር በሚያደርግ ሀይል የሚንቀሳቀሱ ናቸው) በሰአት 500 ኪሎሜትር ፍጥነት አካባቢ ላይ እንደደረሱ ሰምቻለሁ። ይባስ ብለው አሁን ቴክኖሎጂ በደረሰበት ዕድገት የአየር ግፊት(Air resistance) ለማስቀረት በሚል በቫኪዩም ቲዩብ(አየር አልባ ቱቦ) ውስጥ ተንሳፋፊውን ባቡር ለሙከራ በነዱበት ወቅት ፍጥነቱ ከአውሮፕላን ፍጥነት እንደሚበልጥ ደርሰውበታል። አጃኢብ አያሰኝም! ይሄን ያህል ከዋናው ጉዳዬ ወጥቼ ስለቴክኖሎጂ ያወራሁት የዘመኑ በተለይም የወደፊቱ የቴክኖለጂ ፈጠራ በአለም ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ከፍተኛ ለውጥ(revolution) ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ እወቁልኝ፡፡
አርብ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰአት አካባቢ ከጴጥሮስ ጋር በናጎያ የባቡር ጣቢያ ተገናኝተን ወደ ቤቱ ወሰደኝ፡፡ ከላይ እንደገለፅኩላችሁ አባቱ የፋብሪካ ባለቤት ናቸው። እናም የቤታቸው ደረጃ ያሉበትን የኢኮኖሚ ደረጃ(ያውም በጃፓን) የሚመጥን መሆኑን መገመት አያዳግትም። ዓርብ ማታ ጴጥሮስ(ፒተር)፥ የፒተር አባትና እናት ጥሩ መስተንግዶ አደረጉልኝ። በነጋታው ቁርስ በልተን ከጧቱ 1፡00 አካባቢ ከእነ ፒተር ቤት በመኪና ወጣን። እዚያው ከተማ ውስጥ የሚኖር የፒተር አበሻ ጓደኛ ቤት ሄደን እሱን ከያዝነው በኋላ ጉዞ ቀጠልን። ይህን ጊዜ የእግር ጉዞአችን በሚያማምሩ የከተማው መንገዶችና ፓርኮች ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ። በመቀጠል መኪናችን ከከተማው ወጥታ ትንሽ ከተጓዘች በኋላ ከዋናው መንገድ ወጥታ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ለጥቂት ጊዜ ተጓዘች። በመጨረሻም አንድ ወንዝ ዳር ባለ መስክ ላይ ስትደርስ ቆመች፥ እኛም ወረድን።
የጉዞአችን መሪ በዚያን ጊዜ ዕድሜያቸው በግምት ስልሳ አምስት ዓመት የሚሆናቸው፣ ጃፓናዊው የፒተር አባት ናቸው። በጉዞው ላይ የተሳተፍነው የፒተር አባት፤ ፒተር፤ የፒተር ጓደኛና እኔ ነበርን። ጃፓናዊው የፒተር አባት ቀጠን ያሉ፤ ቁመታቸው ልከኛ፥ ፀጉራቸው ገብስማና ፊታቸው አስተዋይነት የሚነበብበት ሸንቃጣ ሰው ነበሩ። እሳቸውም የቀኑን የጉዞአችንን ዓላማ እንደሚከተለው ገለፁልን። “የዛሬው የእግር ጉዞአችን ዓላማ የዚህን ወንዝ መነሻ ማግኘት ነው” አሉን። ያለንበት አካባቢ ወንዝ ያለበትና በደን የተሸፈነ ነው። እንዴት አድርገን ነው በዚህ ደንና ወንዝ ውስጥ የምንጓዘው? አልኩ በሆዴ። በተጨማሪም እኔ የእግር ጉዞአችን በሚያማምሩ የከተማው መንገዶችና ፓርኮች ውስጥ ሊሆን እንደሚችል የገመትኩት ቀርቶ ወንዝ ተከትለን የእግር ጉዞ ልናደርግ መሆኑ አስገረመኝ። ጃፓኖች ለተፈጥሮ ያላቸውን ፍቅርና ቅርበት የሰውዬው ምርጫ አረጋገጠልኝ። የሁላችንም አለባበስ የስፖርት ቱታና ስኒከር ስለነበረ ለእግር ጉዞ ተዘጋጅተን መውጣታችን ያስታውቃል። ከዚያ ወንዙን ተከትለን ወደ ላይ መጓዝ ጀመርን፡፡ የ “adventure” ጉዞው  ተጀመረ። አካሄዳችን ወንዝ ውስጥ ድንጋዮች ካሉ እነሱን መሸጋገሪያ በማድረግ፥ ድንጋዮች ከሌሉ ደግሞ በወንዙ በቀኝ ወይም በግራ በኩል በሚገኝ ደን ውስጥ ነበር። ፏፏቴ ሲያጋጥመን ቀጥ ያለ ዳገት ቧጥጦ መውጣት ሁሉ ነበረበት። እርምጃችን ፈጠን ያለ ነበር። እንደ ጦጣ አንዴ ወንዝ ውስጥ ከድንጋይ ወደ ድንጋይ እየተሸጋገርን፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ በደን ውስጥ ነበር። እኔ፤ ፒተርና የፒተር ጓደኛ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ስለነበርን ጉዞው በጣም እንደማይከብደን መገመት ይቻላል፥ የስልሳ አምስት አመቱ ጃፓናዊ ሽማግሌ ግን ከኛ በማይተናነስ ቅልጥፍናና ፍጥነት ሲጓዙ ማየቴ በጣም ነበር ያስደነቀኝ። የደን ውስጥ ጉዞአችን ቀላል እንዳይመስላችሁ። ደኑ የተፈጥሮ ደን ስለሆነ በውስጡ የተካተቱት የዛፍ ዝርያዎች ብቻ ሳይሆኑ የሌለ የዕፅዋት አይነት አልነበረም። ሐረግ፥ ቁጥቋጦ፥ እሾክ ወዘተ ነበሩ። መንገዳችን ደግሞ ዳገታማ መሆኑን አትርሱ። ከእሾክና ከቁጥቋጦው ጋር ዳገታማው መንገድ ተጨምሮበት ጉዞአችን ከባድና ጉልበት ጨራሽ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደኑ በጣም ጥቅጥቅ ብሎ ማለፍ ያስቸግረናል፥ ወደ ወንዝ ውስጥ እንዳንገባ ደግሞ ድንጋይ የለውም። ይህ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ደኑን እንደምንም ፈልፍለን በደረታችን እንደ እባብ የምንሳብበት ሁኔታ ከአንድ ጊዜ በላይ አጋጥሞናል። በዚህ አይነት ሁኔታ እየተጓዝን ሳለ፣አንድ ቦታ ስንደርስ ደኑ አላሳልፍ ስላለን በደረታችን መሳብ ጀመርን። በደረታችን የምንሳብበት ቦታ ወደ ወንዙ ተዳፋትነት የነበረው ነበር። እንደ አጋጣሚ የወንዙ ጫፍ እኔ ካለሁበት ቦታ ቅርብ ነበር። ሳላስበው የያዝኩት ቁጥቋጦ አምልጦኝ ወደ ወንዙ ተንሸራተትኩኝ። ከዚያ እንደምንም የሆነ ነገር ይዤ መትረፍ ቻልኩ እንጂ ከላይ ተወርውሬ ውሀ ውስጥ ወይም አለት ላይ እፈጠፈጥ ነበር። ውሀ ላይ ካረፍኩ ዋና ስለምችል ችግር አልነበረውም፥ አለት ላይ ብፈጠፈጥ ኖሮ ግን ሊፈጠር የሚችለውን ነገር መገመት አልችልም።
ወንዙ ወደ ላይ በሄድን ቁጥር መጠኑ እየቀነሰ ሄደ። መነሻውን ለማግኘት ግን ፈተና ሆነብን። በዚህ አይነት ፈታኝ ጉዞ ወደ ሁለት ሰአት ያህል ከተጓዘን በኋላ ስለደከመን እረፍት አደረግን። በጉዞ ላይ በየመሀሉ የወንዙን ሁኔታ እንከታተል ነበርና በግራና በቀኝ በኩል ወደ ወንዙ የሚገቡ ብዛት ያላቸው ምንጮች አጋጥመውናል። ለዚህም ነው ወደ ላይ በሄድን ቁጥር የወንዙ መጠን እየቀነሰ የሄደው። በመጨረሻም ከሦስት ሰአት ጉዞ በኋላ የወንዙን መነሻ ሳናገኝ፥ ነገር ግን የወንዙ መጠን በጣም መቀነሱን አይተንና ለሁለተኛ ጊዜ እረፍት አድርገን ወደነበርንበት የመልስ ጉዞ ጀመርን። የወንዙን መነሻ ባናገኝም፥ የወንዙ መነሻ የምትሆነው የመጀመሪያዋ አንድ ምንጭ መሆንዋን ለመገመት አላዳገተንም፡፡
በመጨረሻም የመልስ ጉዞው ሁለት ሰአት ፈጅቶብን፥ በአጠቃላይ አምስት ሰአት ከባድ የእግር ጉዞ አድርገን መኪናችን ወደቆመችበት ቦታ ተመለስን። መኪናችን ለዚያን ያህል ጊዜ ስትቆም ያለጠባቂ መሆኑን ልብ በሉ። ከላይ እንደገለፅኩት ጉዞአችን በጣም አስቸጋሪና በ”adventure” የተሞላ ነበር። ከዚያ በፊት ሀገር ቤት በነበርኩበት ጊዜ የተለያዩ የእግር ጉዞዎችን አድርጌያለሁ። ከጃፓን ከተመለስኩ በኋላም በቡድን ጭላሎ ተራራን ወጥተን ተመልሰናል። የጭላሎው ጉዞ እንደ ጃፓኑ አምስት ሰአት ያህል የፈጀብን ሲሆን፥ ጉዞው የራሱ ፈታኝነት ነበረው። ይሁን እንጂ በሀገር ቤት ያደረግሁት የትኛውም ጉዞ ከጃፓኑ ጋር አይወዳደርም፥ ወደፊትም ከጃፓኑ ጉዞ ጋር የሚወዳደር የእግር ጉዞ አደርጋለሁ የሚል እምነቱም አቅሙም የለኝም። በዚህ ምክንያት የጃፓኑ የእግር ጉዞዬ በህይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚያጋጥም(ones in a life time) ክስተት ሆኖ በማለፉ የማይረሳኝ ትዝታዬ ነው።
 ጓደኝነት፡ በአንድ ፀሐያማ ቀን እኔና የጋናው ጓደኛዬ ወደ ከተማ ወጥተን ዘና እንበል፥ በዚያው “windowshop” እናደርጋለን ተባብለን ወደ ኦሳካ መሀል ከተማ ሄድን። የኦሳካ መሀል ከተማ እኛ ከምንኖርበት አካባቢ በግምት አስር ኪሎሜትር ይርቃል። ታዲያ መሀል ከተማ ደርሰን የተለያዩ ሱቆችን እየጎበኘን ሳለ፣ ሁለት ወጣት የጃፓን ሴት ልጆች ትኩር ብለው ሲያዩን እኛም አየናቸው። ከዚያ በቀጥታ ወደኛ መጥተው እንተዋወቅ ብለው ተዋወቅናቸው። ድፍረታቸው ገረመን፥ ግልፅነታቸውን ደግሞ አደነቅነው። በመቀጠል ለምን ሻይ አንገባበዝም? አሉን። ያልጠበቅነው ጥያቄ ቢሆንም፣ ግብዣውን በደስታ ተቀበልነው። ዕድሜያችን በሰላሳዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ስለሆነ ጉርምስናው ነበር። ሴቶቹም በሀያዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ስለነበሩ ልባችን ሸፈተ። ከዚያ ወደ አንድ ካፌ ገብተን የሚጠጣ ነገር ካዘዝን በኋላ ጨዋታ ጀመርን። የኛ እንግሊዝኛ ከነሱ የሚሻል ቢሆንም፥ እራሳቸውን በእንግሊዝኛ ለመግለፅ የሚቸግራቸው ልጆች አልነበሩም። ጨዋታ እንደጀመርን ከሴቶቹ አንዷ ግንኙነታችን ምን አይነት እንደሚሆን(code of conduct የሚመስል ነገር) በሚከተለው መንገድ ገለፀችልን።
 “እኛ እናንተን ስናይ ደስ ብሎን ተዋወቅናችሁ፥ ምክንያቱም የውጪ ሀገር ዜጎች ስለሆናችሁ ነው፥ ከውጪ ሀገር ዜጎች ጋር አልፎ አልፎ ጊዜ ማሳለፍ እንወዳለን፥ ነገር ግን አንድ በደምብ እንድታውቁት የምንፈልገው ነገር ወሲብ አንፈልግም፤ የወሲብ ነገር እንዳታነሱብን፥” አሉን። ግልፅነታቸው ያልጠበቅነው ስለነበረ ገረመን፥ ወደድናቸውም። ከዚያ ጨዋታው ቀጠለ። ብስኩት ነክ ነገርም ታዘዘ። ወደ አንድ ሰአት ያህል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስንጨዋወት ቆየን። በመጨረሻም ልንነሳ ስንል “ክፍያ በግል ነው”፥ “dutch system” አለችን አንዷ። እኛ በሀገራችን የለመድነው ግብዣ “dutch system” ከሆነ ቀደም ብለህ ትነጋገራለህ፤ ሳትነጋገር ከተገባበዝክ መጨረሻ ላይ ለመክፈል ትግደረደራለህ። እነሱ ግን መጨረሻ ላይ ነው የነገሩን። ደች ሲስተም የተለመደ “by default” የመገባበዝ ባህላቸው ይመስላል። በቂ ገንዘብ ባይኖረን ኖሮስ? አስቸጋሪ ነው። ለነገሩ በቂ ገንዘብ ባይኖረን ኖሮ የለንም ብለን መናገር ነዋ! የምን መጨነቅ ነው! የባህል ልዩነታችን ግን አስገረመን። በመጨረሻም ተመሰጋግነን ተለያየን።
ከላይ ካጋጠመን ሁለት ነገር ተማርን። የመጀመሪያው፤ የጃፓን ህዝብ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሲወዳደር ዝምተኛ፥ አይናፋርና ራሱን በደንብ መግለፅ የማይችል ህዝብ ነው የሚለው ነገር የተጋነነ መሆኑን ነው። ጃፓኖች ቀረብ ብለህ ካየሀቸው በጣም ግልፅና የሚፈልጉትን ነገር በቀጥታ የሚናገሩ መሆናቸውን ተረድተናል። ሁለተኛው ደግሞ በጃፓን ሁለት ጓደኛሞች ሲገባበዙ የኛ አይነት ባህል ሳይሆን፣ ወደ ምዕራባውያን የሚጠጋ ባህል ነው ያላቸው። ሁሉም የራሱን የሚከፍልበት ደች ሲስተምን ነው የሚመርጡት።
ቼሪ ብሉሰም(Cherry blossom): ቼሪ የሚባለው የአበባ አይነት እኔ እስከማውቀው ድረስ በጃፓን ሀገር የሚበቅል የአበባ አይነት ነው። አበባው በፀደይ(spring) ወቅት የሚያብብ አበባ ነው። በዚህ ወቅት ይህ አበባ ጃፓንን ስለሚያስውብ አበባውን መሰረት ያደረገ የባህላዊ በአል አከባበር አላቸው።
ታዲያ በአንድ ወቅት ለቼሪ አበባ አመታዊ በአል፣ እዚያው ኦሳካ ከተማ ውስጥ በአሉ የሚከበርበት ቦታ ወሰዱን። የቼሪ አበባ በዋነኛነት መልኩ ነጭ ሆኖ በግምት ሀያ በመቶ ያህል የሮዝ ቀለም የተቀላቀለበት የራሱ ውበት ያለው አበባ ነው። የበአሉ ስፍራ ስንደርስ በግምት አንድ ኳስ ሜዳ በሚያክል ቦታ ላይ ተጠጋግተው የተተከሉ የቼሪ አበባዎች የሚታዩበት ቦታ መሆኑን ተረዳን። የአበባዎቹ አተካከል ውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገድ እንዲኖረው ተደርጎ ስለሆነ፣ በአበባዎቹ መሀከል እየተዘዋወርን ጎብኘን። የቼሪ አበባዎቹ እንደዚያ በአንድ ላይ ተተክለው ሲታዩ እጅግ በጣም ያምራሉ። ቦታውን የምድር ገነት አስመስለውታል፡፡ እኛም የቼሪ አበባ አመታዊ አከባበርን ከጃፓኖቹ ጋር ስናከብር ውለን ወደ ቤታችን ተመለስን።
እ.ኤ.አ በ1912 ዓ.ም የቶኪዮ ከተማ ለአሜሪካዋ ዋሺንግተን ዲሲ ከተማ የቼሪ ዛፎች በስጦታ ማበርከቷ በታሪክ ይታወቃል። አሜሪካኖቹም ይህንን አበባ እንደ ጃፓኖቹ በአንድ ቦታ ሰፋ አድርገው ተክለው፣ በየአመቱ ፀደይ በመጣ ቁጥር የሚያከብሩት በአል እንዳላቸው አውቃለሁ። የበአሉ መሰረት ግን ጃፓን መሆኗን ልብ ይሏል።
ማጠቃለያ፡
እስካሁን  ከራሴ ተሞክሮ ተነስቼ ስለጃፓን የማውቃትንና የታዘብኩትን አጫወትኳችሁ። “ዞሮ ዞሮ ከቤት . . .” እንደሚባለው እኛስ? እንዴት ነው የምንኖረው? ለስራ፥ ለጊዜ የምንሰጠው ዋጋ ምን ያህል ነው? የቅድሚያ ትኩረት የምንሰጠው ለምንድነው? ለኢኮኖሚ ዕድገት ወይስ ወንዝ ለማያሻግር የፖለቲካ ሽኩቻ? ያውም ብሔር-ተኮር የፖለቲካ ሽኩቻ? የሚሉትንና ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እራሳችንን ብንጠይቅ የአሁኑ፥ የቅርቡም ሆነ የሩቁ ታሪካችን የሚያስገነዝበን አብዛኛውን ጊዜ ለሀገር በማይበጅ፥ እንደውም ሀገርን በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሳትፈን ወርቃማ ጊዜያችንን በከንቱ ማሳለፋችንን ነው። ከዚህ አንጻር በሚከተሉት አንኳር ሀሳቦች ላይ ብንሰራ እነ ጃፓን የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያግደን ነገር አይታየኝም።
ሀ. የፖለቲካ ባህላችንን ማዘመን ወይም መለወጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ልዩነቶቻችንን በክብ ጠረጴዛ መፍታት ግድ ይለናል። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም እኩል ሀላፊነት አለብን። ታሪካችንን ዞር ብዬ ሳየው ይህን አይነት የፖለቲካ ብስለት በቀላሉ ማምጣት እንደሚከብድ ይገባኛል፥ ነገር ግን ወደድንም ጠላንም ሀገራችንን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር የግድ ማድረግ ያለብን ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።
ለ. ለስራና ለጊዜ የምንሰጠው ዋጋ በጣም መሻሻል አለበት። ለዚህም ትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተከትለን ስራ መፍጠር፥ የአሰራር ሥርዓታችንን ማዘመንና ሰዉ ለስራና ለጊዜ የሚሰጠውን ዋጋ በተለያዩ ስልጠናዎች ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡
ሐ. ባለብዙ ብሔር ሀገር መሆናችን ጌጣችን እንጂ መሻኮቻ ምክንያት ሊሆን በፍፁም አይገባም። ሩዋንዳ ከስህተቷ ተምራ እንዳደረገችው፥ እኛ ደግሞ ካሳለፍነው መከራ ተምረን፣ ብሔር-ተኮር ፖለቲካ ማራመድ ወንጀል መሆኑ በህግ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን አለበት እላለሁ። ምክንያቱም አነሰም በዛ በብሔር ፖለቲካ ጦስ መከራውን ያላየ ብሔረሰብ በኛ ሀገር ማግኘት ይከብዳል። የብሔር ፖለቲካ ለውጪ ጠላት መሳሪያ ከመሆን ባለፈ ስልጣንና ህገወጥ ብልፅግና የሚገኝበት አቋራጭ መንገድ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ምስጢር ከሆነ ሰንብቷል።
ቢያንስ ቢያንስ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት አንኳር ነጥቦችን ተግባራዊ ማድረግ ከቻልን፣ ሀገራችንን ማሳደግ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ተግባራዊ ካላደረግናቸው ግን የመከራ ጊዜያችንን እናራዝማለን፥ ከታሪካችን ሳንማር ቀርተን ህዝባችን ከድህነት አዙሪት እንዳይወጣ በማድረግ እርባና ያለው ነገር ሳንሰራ እናልፋለን።



Read 554 times