በሂንዱ የሚነገር አንድ ተረት እንዲህ ይላል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን በአንድ ትልቅ ጫካ ውስጥ አንድ አንበሳና ሦስት ባለሟሎች ማለትም አነር፣ ዱኩላና ቁራ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡
አንድ ሌሊት የሚበላ ምግብ ፍለጋ ሲዘዋወሩ ከመንገደኞቹ ተነጥሎ ብቻውን የቀረ አንድ ግመል አገኙ፡፡ አንበሳም ከዚህ ቀደም ግመል አይቶ ስለማያውቅ
“ይሄ ምን ዓይነት እንስሳ ነው? በጣም እንግዳ አይነት ተፈጥሮ ያለው ነው!” ሲል ጠየቀ፡፡
አነሩ፣ “እንግደለውና አንብላው” አለ፡፡
“አዎ እራታችን ብናደርገው ይሻላል” አለ ድኩላው፡፡
“ኸረ ለእራትም ለቁርስም ይበቃናል፤ ብዙ ስጋ ተሸክሞ የሚዘዋወር እንስሳ’ኮ ነው፡፡”
“የለም አይሆንም!” አለ አንበሳ፤ “ብናጣራ ነው የሚሻለው፡፡ ስሙ ማን ይባላል? በዚህ በውድቅት ሌሊት እዚህ ምን ያደርጋል? ሂዱና ጠይቁት፡፡”
ሦስቱ ባለሟሎች አንበሳው እንዳዘዘው ሄዱና ግመሉን ጠየቁት፡፡ ግመልም ስሙ ግመል እንደሚባል፣ ከተጓዥ መንገደኞች ተለይቶ የቀረ መሆኑን ነገራቸው፡፡ ባለሟሎቹም ሄደው ለጌታቸው ለአንበሳ ይሄንኑ ገለፁለት፡፡
አንበሳም፤ “እንግዲያው በቃ ከእኛ ጋር ይኑር፡፡ በዚህ ጫካ ውስጥ ብቻውን መኖር አይቻለውም፡፡ ምን አደጋ እንደሚያጋጥመው በምን ይታወቃል፡፡ ከእኛ ጋር ይቀላቀል፡፡ እኔ እጠብቀዋለሁ፡፡ ሂዱ አምጡት” አለ፡፡
ባለሟሎቹ ሄደው ለግመሉ የምሥራቹን ነገሩት፡፡ ያም ሆኖ ሦስቱ ባለሟሎች ግመሉ ከነሱ ጋር በመቀላቀሉ ደስተኞች አልነበሩም፡፡ ተጨማሪ አባል ማለት ተጨማሪ ሆድ፣ ተጨማሪ ጭንቀትና በግድ ተስማምቶ መኖር ያለበት ተጨማሪ ወዳጅ ማለት ነውና፡፡
ግመሉ መጥቶ ከተቀላቀለ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በድንገት አንበሳ ከዝሆን ጋር ባደረገው የጦርነት ግጥሚያ ክፉኛ ቆሰለ፡፡ ከቆሰለም በኋላ፤
“እስከሚሻለኝ ድረስ እኔ ዋሻዬ ውስጥ እቀመጣለሁ፡፡ እናንተ ሄዳችሁ የሚበላ ፈላልጉ፡፡ አሁን አደን ተስኖኛል” አለ፡፡
አነሩ ድኩላውና ቁራው እርስ በርስ ተያዩና፤ “እዚህ ትተንህ ልንሄድ አንችልም፡፡ እኛ ሄደን ማን ሊያስታምምህ ነው?” ሲሉ ሀሳቡን ተቃወሙ፡፡
አንበሳ ግን “የለም፡፡ ሄዳችሁ የሚበላ ብታመጡ ነው የሚሻለው” አለ፡፡
ባለሟሎቹ ከአንበሳው ቃል አይወጡምና፣ ጫካው ውስጥ ለአደን ተሰማሩ፡፡ ግን ምንም ምግብ አላገኙም፡፡ ጥንቸል ወይም እርግብ አሊያም ሽኮኮ እንኳን አጡ፡፡
“ተስፋ አስቆራጭ ነገር ነው፡፡ ምንም አድነን የምንወስደው አልተገኘም፡፡ ይሄንኑ ሄደን ለአያ አንበሳ ብንነግረው ይሻላል!” አለ ድኩላ፡፡
ይሄኔ ቁራው፤
“እዚህ የሚበላ የሚቀመስ በሌለበት ጫካ ውስጥ ከምንንከራተት ወደዋሻው ተመልሰን ያንን ግመል ብንበላውስ?” ሲል ሃሳብ አቀረበ፡፡ ድኩላው ሲመልስ፣
“አያ አንበሳ እሺ አይልም፡፡ እንከባከብሃለሁ ያለውን ግመል እንብላው ብንል ፈፅሞ ፈቃደኛ አይሆንም፡፡”
“በዘዴ ካታለልነው እሺ ይለናል” አለ ቁራው፡፡ ከዚያም “ስሙኝ!” ብሎ ወደ ድኩላውና ወደ አነሩ ተጠጋና ዘዴውን በጆሮዋቸው ሹክ አላቸው፡፡
ሦስቱ አሽከሮች ወደ ዋሻው ተመለሱ፡፡ ከዚያም ድኩላው፤ “አያ አንበሶ ሆይ! በጣም እናዝናለን፡፡ የሚታደን ወፍ እንኳ ስላጣን ባዶ እጃችንን ተመለስን፡፡ እንግዲህ በረሀብ መሞታችን ነው፡፡”
“ኧረ በበለስ! በጣም አሳዛኝ ነገር’ኮ ነው!” አለ አንበሳው እያቃሰተ፡፡
ይሄኔ አነሩ፤ “እንዲህ አይናችን እያየ ስትሞትማ ዝም አንልም፡፡ ምንም ቢሆን፣ ታላቁ ጌታችን፣ ሀያሉ ጠባቂያችን፣ አዛዥ-መሪያችን ነህ’ኮ፡፡ እኔ ላድንህ እችላለሁ!” አለ፡፡
“እንዴት ልታድነኝ ትችላለህ?”
“በረሀብ ከምትሞት እኔን ብላኝ” አለ አነሩ፡፡
አንበሳም፤ “የለም አላደርገውም፡፡ ይሄን ያህል ዘመን ያገለገልከኝ ታማኝ ባለሟል ነህ’ኮ!” አለና በቁጣ ተቃወመ፡፡
ይሄኔ ድኩላው፤ “እንግዲያው እኔን ብላኝ ጌታዬ” አለ፡፡
“የለም አላደርገውም፡፡ አንተም ለብዙ ዓመታት ታማኝ ሆነህ የኖርክ ነህ!” አለ ኮስተር ብሎ፡፡
“በል እንግዲያው እኔን ብላኝ፣ የኔ ጌታ!” አለ ቁራ፡፡
“አትጃጃል፡፡ አንተንማ ልብላህም ብል ጥቅም የለህም፡፡ በጣም ደቃቃ ነህ፡፡ ምን ትሆነኛለህ!” አለ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግመሉ አጠገባቸው ሆኖ ያዳምጥ ነበር፡፡ ለራሱ እንዲህ ሲል አሰበ፡፡
“መቼም አያ አንበሳ አንዳችንንም ለመብላት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ግልፅ አድርጎልናል፡፡ እኔንማ እንደሚጠብቀኝና እንደሚንከባከበኝ ቃል ገብቶልኛል፡፡ ስለዚህ እኔም እንደሌሎቹ “እኔን ብላኝ” ማለት ይገባኛል” አለና “አንበሳ ሆይ፤ እንግዲያው እኔን ብላኛ!” አለና ግመል ራሱን አቀረበ፡፡
“አንተን?” አለና ጠየቀ አንበሳ፡፡
“አዎ እኔን!” አለ ግመል፡፡
ይሄኔ አነሩ ቀልጠፍ ብሎ፤ “ይሄ በጣም ቅንነትና ደግነት የተሞላ ትክክለኛ ጥያቄ ነው!” አለ፡፡
“በጣም ትክክል!” አለ ድኩላ በማጠናከር፡፡
“ጥርጥር የለውም! እንደ ግመል ትክክል ሀሳብ ያቀረበ የለም!” አለ ቁራ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ አንበሳ ይሁን አይሁን ብሎ እንኳን ከመወሰኑ በፊት አነሩ ድኩላውና ቁራው ግመሉ ላይ ጉብ አሉበት፡፡ ዘዴያቸው ሰራ፡፡
* * *
በሀሳብ ደረጃ እንኳ ቢሆን፣ “እኔን ብላኝ ጌታዬ” ከሚልም ሆነ “ያኛውን ብላው” ከሚል ባለሟል ይሰውረን፡፡ ያገኙትን እንብላ እያሉ መስገብገብ ከንቱ አድርባይነት ነው፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ምክንያት፣ ለጌታ አድሮ፣ ወዶ-ገባ ኮርማ መሆን፣ ቢሰቡ ለስለት፣ ቢከሱ ለጭነት ከመሆን አይታለፍም፡፡ ሁኔታዎችን መጠቀሚያ ለማድረግ “ሲፋጅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” ማለትም፣ ያው ዞሮ ዞሮ ዞሮ የአድር-ባይነት ዝርያ ነው፡፡ ሁሌ አዋቂ፣ ሁሌ ዘዴኛ፣ እኔ ብቻ እያሉ፣ “እሰይ አበጀህ የእኛ ሎጋ” ተብያለሁ፣ ብሎ በግል ምኞት መሯሯጥ “የባዳ ሞኝ ከልጅህ እኩል አርገኝ” ይላል እንደሚባለው (“የባለቤቱ ልጅ” እንዲል መፅሐፈ-አራዳ) መሆን ነው፡፡
በሰሞንኛ መፈክርና የግል-ምህዋር ዙሪያ ብቻ በመሽከርከር አርቆ አለመመልከት፣ ውሎ አድሮ አንድም፣ በአመለካከት ረገድ በውዥንብርና በዳፍንተኝነት (obscurantism) ሸረሪት ድር መተብተብን፣ ቀን ሲገፋም “እበላ ብዬ ተበላሁ….” ማለትን ግድ ይላል፡፡ ከቶውንም “እኔ ብቻ አዋቂ” ማለት በአካሄድ መወለካከፍን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ዝማሬ፣ ቅኝቱ “እኔ ብቻ ልግዛ” ወደሚል ዜማ የተሸጋገረ ዕለት ደግሞ፣ ናፖሊዮን ቦናፓርት “አገሬ እኔን የምትፈልገኝ እኔ ከምፈልጋት በላይ ነው” አለ፣ ወደተባለበት ደረጃ ያደርሳል፡፡ አይተኬ-ነኝ (indispensable) ወደ ማለትም ይነጎዳል፡፡ የዚህ የግል - ምኞት ውስጣዊ ግፊት የመጨረሻ መጠቅለያው ህዝብን መናቅ ነው፡፡ ያም ሆኖ በውስጣዊ መንፈስ ግን ዝቅተኝነትን ያረግዟል፡፡
ሼክስፒር፣ በብሩተስ አንደበት በግል-ምኞት የናወዙትን የሮማን የስልጣን ጥመኞች ሲገልፅ፤
“ወትሮም ዝቅተኛ - ስሜት፣ የትኩስ ምኞት እርካብ ነው
አንዴ ሽቅብ ያንጋጠጠ፣ ከቶም መመለሻ የለው፡፡
እንዲያም ሲል ስልጣን የወጣ…
አንደዜ አናት ከረገጠ፣ ላገር ጀርባውን ይሰጣል
የበላበትንም ወጪት፣ ሰባሪ ሆኖ ይገኛል
ዳመናውን እየቃኘ፣ የታቹን ቁልቁል ይዘልፋል
መርጦ ለዚህ ያበቃውን፣ ድምሩን ህዝብ ይራገማል…” የሚለን
ይሄንኑ በቅኔ አግዝፎ ሲነግረን ነው፡፡
በሀገራችን የፖለቲካ ድባብ ውስጥ በየወቅቱ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ የምሰጥ እኔና እኔ ብቻ ነኝ፡፡ የእኔና የእኔ መልስ ብቻ ነው ትክክለኛው፣ ብሎ በመገተር የታሪክ አይን እርሱ ላይ ብቻ የሚያተኩር አድርጎ የማየት ባህሪ፤ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአለቃ እስከ ምንዝር፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ-ሊቃውንትን ሲተናነቅ የኖረ ክፉ ጋግርት ነበር፡፡ ነውም፡፡
የብሪታኒያ ጠ/ሚኒስትር ቤንጃሚን ዴዝሬሌ፣ ባንድ ወቅት የብሪታኒያ መሪ ስለነበሩት ስለ ሰር ሮበርት ፒል በፃፉት ደብዳቤ፡-
“ለሁሉም ታላላቅ ጥያቄዎች መልስ ፈልጎ በማግኘት በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙን ለማስፈር የመጣር ከንቱ ድካም የሚደክም ሰው ነው፡፡ ነገር ግን የፓርላማ ህገ-መንግሥት እንዲህ ላለው በግል-ምኞት ለሰከረ ግለሰብ ምቹ አይሆንም፡፡ ምነው ቢሉ፣ ሥራዎች መከናወን ያለባቸው በፓርቲዎች እንጂ ፓርቲን እንደግል መሳሪያቸው በሚጠቀሙ ግለ-ሰቦች አይደለም” ብለዋል፡፡
“እኔ የሌለሁበት ፓርቲ፣ እኔ የሌለሁበት አመራር፣ እኔ የሌለሁበት ውይይት፣ እነ እገሌ መሪ ሆነው፣ እኔ ተመሪ ሆኜ ምን ቦጣኝ….” በሚል አባዜ መጠመድ፣ ሌላው ልክፍት ነው፡፡ እሊህ ሊቃውንትና መሪዎች የባላንጣቸውን የኃይል ሚዛን የሚያይ አይን ከቶ የላቸውም፡፡
የበለጠ የከፋው መርገምት ደግሞ አዲስ ፓርቲ ተቋቋመ ሲሏቸው፣ ጠላት መጣ ያሏቸው ያህል የሚበረግጉቱና ከቶም እንቅልፍ የማይተኙቱ ናቸው፡፡ እነሱ ባለፉበት በስነ-ፓርቲ ግንባታ ሂደታቸው ላይ የደረሰውን መከራና ፍዳ ሁሉ ተከታዩ ትውልደ-ፓርቲ እንዲቀምስ የሚመኙና የእንቅፋቱን መንገድ ብቻ የሚቀይሱቱ ናቸው፡፡
ወጣም ወረደ በግል-ጥቅም የሚታወር፣ በግል-ዝና የሚጋበዝ፣ በስልጣን-ጥም የሚንሸዋረር፣ አድርባይነት የሚጠናወተው፣ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈል የሚጥመው፣ ውሁድ ጥንካሬን ከመፍጠር ይልቅ መበታተን የሚያረካው፣ ለእልህ እስጨራሹ የዲሞክራሲያዊ ግንባታ ከቶም ካብ-አይገባ ድንጋይ ነው፤ ዲሞክራሲም ለእሱ የተከለከለች የበለስ ፍሬ ናት! ከዚህ ሁሉ በላይ ግን፣ በምንም ዓይነት መንገድ ህዝብን የሚንቅ ግለሰብም ሆነ ፓርቲ የህዝብን አደራ ተቀብሎ የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ይችላል ማለት ዘበት ነው፡፡ ይልቁንም የህዝብ ድምፅ እዳ አለበትና ዱቤ-ከልል ባርሜጣ ቢያደርግ እንኳ ከህዝብ እይታ አያመልጥምና ከሩቁ ይለያል፡፡ እንዲህ ያለው ሁሉ፤ “ዋና የማይችል ባህር አይግባ፤ ትግል የማይችል ልፊያ አይውደድ” የሚባለው ተረት ይጠቀስበታል፡፡ ልብና ልቦና ይሰጠው ዘንድ!
Published in
ርዕሰ አንቀፅ