ሼኽ ወይም ኡስታዝ የእስልምና ሃይማኖት ሊቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ለብዙ ዓመታ ዓሊሞች አሉ በተባሉበት ቦታ ሁሉ እየተገኙ ቀርተዋል፡፡ የሃይማኖት አዋቂ ለመሆን ብዙ ኪታቦችን አገላብጠዋል፡፡ አሁን በተራቸው የቃረሙትን ሁሉ ለሌሎች ለማካፈል ሲሉ ማስተማር ጀምረዋል፡፡ ምላሳቸው የተባረከ ነው፡፡ የሃይማኖት ዕውቀትን ማሳወቅንና ተናግረው ማሳመንን ተከነውበታል፡፡
ተማሪዎቻቸው አፋቸውን ከፍተው ነው የሚያዳምጧቸው፡፡ “የኔ አንድም አስተዋፅኦ ወይም ታላቅ ጥረት ሳይታከልበት እንዲሁ እንደዘበት ይህን ተሰጥኦ ለሰጠኝ አላህ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ሲሉ ብዙ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡ ሚስታቸውን እንኳን ለሌላ ነገር የሚመኝ ቀርቶ መልኳንና ቁመናዋን የሚያውቅ የለም፡፡ ይህን የሚያውቁት እናትና አባትዋ፣ እህትና ወንድሞችዋ እና እስከ አጎትና አክስት ድረስ ያሉ ዘመዶችዋ ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች መልኳንም ሆነ ቁመናዋን ለማወቅና ለማድነቅ አልታደሉም፡፡ ምክንያቱም በሰፊ ጥቁር አባያና ከላይ በምትደርበው ትልቅና ሰፊ ጅልባብ ሰውነትዋ ተሸፍኗል፡፡ መላው ፊትዋና ከአንገት በላይ ያለው የሰውነት ክፍልዋ በኒቃብ ኃይል ከሰው ዓይን ተጋርዷል፡፡
ይወድዋታል፡፡ የእሳቸው ብቻ ስለሆነች ደግሞ ኩራት ይሰማቸዋል፡፡ ይኮሩባታል፡፡
ሼኽ ወይም ኡስታዝ ኡስማን ቀይ ናቸው፡፡ ፂማቸው የተንዥረገገ ነው፡፡ ይህ የሆነው ፂም ማሳደግ ሱና ስለሆነ ነው፡፡ አናታቸው ላይ ጥምጣም እንደጠመጠሙና ከላዩ ላይ ነጭ ኩፊያ እንዳጠለቁ ነው የሚውሉት፡፡ ዘውትር ሽክ የሚሉ ሰው ናቸው፡፡
“ምን ነው?” ቢሏቸው “ንጽህና የኢማን ግማሽ ነው ብለዋል ነቢያችን (ሲ.ሠ.ወ)” ይላሉ፤ ድብዳብ የመሰለውን ወፍራም ከንፈራቸውን ከጥርስ ግርዶሽነት አላቀው ፍንጭት ጥርሳቸውን እያሳዩ፡፡
ፈገግ ሲሉ ነጫጭ ጥርሶቻቸው መሀል ተሸንቁሮ ጠባብ መንገድ የመሰለው ፍንጭታቸው ለእይታ ይጋለጣል፡፡
ከልብስ ጀለቢያና ቶብ ያዘወትራሉ፡፡ በቅጥነታቸው ምክንያት እዛ ሰፊ “ድንኳን” ውስጥ ኢምንት መስለው ይታያሉ፡፡ ጥምጣም፣ ነጭ ኮፍያና፣ ነጭ ጀለብያ ወይም ቶብ መለያ ምልክቶቻቸው ናቸው፡፡ ጀለብያ ወይም ቶብ ሆነ ወይም ሱሪያቸው ከቁርጭምጭሚታቸው በላይ የሚቀሩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ይህም ሱና ነው፡፡
“ደረሳዎቼ ስሙ!” አሉ ከስራቸው የተኮለኮሉትን ወጣች አፈራርቀው እየተመለከቱ፡፡
“ምን ጊዜም ቢሆን ነብሳችሁን ማሸነፍ አለባችሁ፡፡ ለምን? ብትሉ ነብሲያ ቆሻሻ ነች፤ የማይሆን ቦታ ላይ ትጥላለች፡፡ የማይበጅ ጉድጓድ ውስጥ ሰውን ትከታለች፡፡”
በእስልምና ሃይማኖት “ነብሲያህን አሸንፍ” የሚል አስተምህሮ አለ፡፡ ኡስታዝ ኡስማን እያስተማሩ ያሉት ይህንን ነው፡፡
“የግል ፍላጎታችንን ለሌሎች ሰዎች ስኬትና ለወል ጥቅም ስንል ማሸነፍ አለብን፡፡ ለነብሲያ ውስወሳ ቦታ መስጠት የለብንም፣ ነብሲያ እኔ እኔ ማለትዋና ለኔ ለኔ እያለች መጮህዋ መቼም አይቀርም፡፡”
የተማሪዎቻቸውን የተለያዩ ፊቶች ቃኙ፡፡
ጥቁር ፊት አለ፡፡
ጠይም ፊት አለ፡፡
ቀይ ፊት አለ፡፡
ነገር ግን ከሁሉም ፊቶች ላይ የሚነበበው ጥልቅና ረቂቅ የሆነ ነገር ነው፡፡ ሃይማኖትን የማወቅና በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት ለመኖር የመመኘት ስሜት፡፡ ሁሉም የጀነት ቁልፍ እጁ ቢገባ ይወዳል፡፡ ከጀሀነም እሳት የመጠበቅና የጀነት ሰው ሆኖ ለመገኘት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል የሚያስወስን ጥልቅ ፍላጎት አለ፡፡
እርግጥ ነው፡፡ ትዕዛዛትን ሁሉ አክብሮ በአስተምህሮው መሰረት ህይወቱን በመምራት ለጀነት የሚበቃው ወይም ለጀነት የሚያበቃውን ስራ የሚሰራው ጥቂት ነው፡፡ ምክንያቱም ህይወት አለ፡፡ ገና ከሞት በኋላ የሚመጣውን ህይወት ማሰብ ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ዘላቂውንና አዋጩን ከመምረጥ ይልቅ በእጃችን ላይ ያለውን ህይወት ማቅናትና ኑሮን ማሸነፍ ቀድሞ ይገኛል፤ ለብዙዎች፡፡
አሁንም እርግጥ ነው የማይመኝ የለም፡፡ ግን ምኞትና ተግባር፣ ፍላጎትና ኑሮ ደቡብና ሰሜን የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
“እና” አሉ ሼህ ኡስማን
“እና ፍላጎታችንን መደፍለቅ፣ ስሜታችንን መግራትና መልካም ተግባር ላይ መገኘት ይገባናል፡፡” በጥርሳቸው የነከሱትን መፋቂያ እየነቀነቁ፡፡
“ለምሳሌ አንድ የወደድነውና የራሳችን ለማድረግ ያሰብነው ነገር ይኖራል፡፡ ወንድማችን ያንኑ ነገር መፈለጉን ካወቅን ነብሲያችንን አሸንፈን ያንን ነገር ለወንድማችን ቅድሚያ በመስጠት መተው ይኖርብናል፡፡ እስልምና መስዋዕትነትን የሚያበረታታ እምነት ነው፡፡ ለኔ ከማለት ይልቅ ለወንድሜ ማለትን ማስቀደም አለብን፡፡”
ተማሪዎች ዝም እንዳሉ ተቀምጠው የተማሩትን ትምህርት እንዴት አድርገው በህይወታቸው እንደሚተገብሩ እያሰቡ ትምህርቱን ይከታተላሉ፡፡
“ልብ በሉ ነፍስያ የዋዛ አይደለችም፡፡ ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) “ጦር ሜዳ ሄዶ ጠላትን ከማሸነፍ ይልቅ መጀመሪያው እንዲሁም ትልቁና ዋናው ጀሀድ ነፍስያን ማሸነፍ ነው!” ያሉትን አትዘንጉ፡፡
“የሆነ ነገር ብንፈልግና ወንድማችን ያን ነገር የሚፈልግ ከሆነ ነፍስያችን አትስጠው አትስጠው ማለትዋ አይቀርም፡፡ እኛ ግን ነፍስያችንን በማሸነፍ ያን ነገር ለወንድማችን መተው ወይም መስጠት አለብን፡፡”
ኡስታዝ ኡስማን ማስተማሩን ከጨረሱ በኋላ ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን ሰሞኑን ወደ ተጠሩበት ቦታ ሄዱ፡፡ ቦታው የአንድ ሙስሊም ባለ ሀብት ቤት ነው፡፡ የተጠሩትም ለሰደቃ ነው፡፡
ቤቱ ደረሱ፡፡
ገቡ፡፡
ምግብ በአንድ ትሪ ላይ ሆኖ ለኡስታዙና ለተማሪዎቻቸው ቀረበ፡፡
ሼሁና ደረሳዎቻቸው የቀረበላቸውን ምግብ ጠቅልለው መጉረስ ጀመሩ፡፡
ቀይና አልጫ የሆነ ስጋ ወጥ እንጀራ ላይ ፈስሶ ቀረበላቸው፡፡
እንጀራው መሀል ላይ አንድ አጥንት ወድቃለች፡፡ ኡስታዝ ኡስማን ፈጠን ብለው አጥንቷን በማንሳት መጋጥ ጀመሩ፡፡
ከተማሪዎቹ አንዱ፡-
“ምን ነው ኡስታዝ?” አለ
“ምን ነው?” አሉ አጥንት እንዳገኘ ውሻ በመስገብገብ አጥንታቸውን እየጋጡ፡፡
“ቅድም ነብሲያችንን ማሸነፍ አለብን! ብለው እያስተማሩ አልነበር?”
“እኮ!”
“ምነው ታዲያ አጥንትዋን ቀድመውን አነሱ?” አለ ተማሪው በመደነቅ፡፡
“እኮ!” አሉ ኡስታዙ በድጋሚ፡፡
“ነብሲያዬ ስጥ ስጥ ስላለችኝ እሷን አሸንፌ እየበላሁኮ ነው፡፡” አሉ ኡስታዝ ኡስማን፤ እንደዋዛ ፈገግ ብለው፡፡
ተማሪዎቹ ሁሉ በሳቅ አውካኩ፡፡ “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንደተባለው መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡
ተማሪዎቹ በሳቃቸው መሀል እውነትና እውቀት፣ ማስተማርና መሆን ምን ያህል እንደሚጣረሱ እያሰቡና እየተገረሙ ወደ ትሪው አጎነበሱ፡፡
(ከመሐመድ ነስሩ (ሶፎንያስ አቢስ) “ጥቁር ሽታ” የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ የተወሰደ፤2011 ዓ.ም)
Published in
ጥበብ