የሥነ-ጥበብም ሆነ የኪነት ሰዎች በገባቸውና በራሳቸው መንገድ፣ቋንቋና ፍልስፍና ስለ ዝምታ ሲነግሩን ኖረዋል። ለመንፈሳዊ ሕይወት ቅርብ የሆኑ፤ “በአርምሞ” ከፈጣሪያቸው መገናኘትን ግባቸው ያደረጉ እንዲሁም ከራስ ጋር ለማውጋት በሚሹ ግለሰቦች ጭምር ትልቅ ቦታ ይሰጣታል_ዝምታ።
ገጣሚ ነቢይ መኮንን ከመአዛ ብሩ ጋር ባደረገው ጭውውት፣ ለሰላሳ ዓመታት በዝምታ የሚቆይበት ገዳም አንዲት አውሮፓ ሀገር ውስጥ እንደሚገኝ ሲናገርም የሰማሁ ይመስለኛል። ለሰላሳ ዓመታት ያህል ከንግግር ተኳርፎ በዝምታ መቆየትን የሚያስመርጠው ዝምታ ዋጋዋ ምን ቢሆን ነው? ያሰኛል።
ንጉስ ዳዊት በመዝሙሩ “ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ።” አይደል ያለው? ለበጎ እንኳን ዝም አልኩ...
በዘፈን ግጥሞቻችን ውስጥ ከተንሸራሸሩ ሀሳቦች ውስጥ አንዱ ዝምታ ነው። ስለዝምታ አንጋፋዎችም ሆኑ የአንድ ዘመን ድምጻውያን አዚመዋል። በነዚህ ዘፈኖች ዝምታ ይሞገሳል፣ ዝምታ ይዋባል፣ ዝምታ ይሞሸራል። ጥቂቶችን እንይ...
ስለዝምታ ካዜሙ አንጋፋዎቻችን ውስጥ አንዱ ንዋይ ደበበ ነው። በሀገረሰባዊ ውብ የአገጣጠም ስልቱና በአስገምገሚ የዜማ ድርሰቱ የምናከብረውና የምንወደው ንዋይ ደበበ፣ በዚህ ዘፈኑ ውስጥ የዝምታን ጥቅምና አስፈላጊነት በጉልህ ይነግረናል።
ዋ የእኔ ዝምታ ዋ የእኔ ማቀርቀር
ወይም አላት ፍሬ ወይም አላት ነገር
ባለውለታዬ ሕይወቴ ጸጥታ
ዘንድሮ ተዋወቅን እኔና ዝምታ።
ሲል የዝምታውን ሁለትዮሽነትና ባለውለታነት በማስገንዘብ፣ ከሰፊው የመናገር ልምዱ ተላቆ የዝምታ ወዳጅ እንደሆነ በመንገር ወደ ሌሎች ሰበዞቹ ደግሞ እንዲህ እያለ ይወስደናል።
ዝምታ የእኔ ዝምታ
ዝምታ እውቀት ችሎታ
ለአንደበታም ሰው ባትመችም
ባለትግዕስትን አትሰለችም።
ዝምታ እንዲሁ ተራ ጉዳይ ሳይሆን ዕወቀትና ችሎታን የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን የሚጠቁመን ንዋይ፤ አፈ ቀላጤው ባይፈልጋትም ትግዕስተኛው ግን እንደማይሰለቻትም ያሳየናል።
ዝም አለው ቁም ነገር ያልተገለጸ
ዝም ዞሮ ሲያመጣ ልብ እያመጸ
ዝም አንድ ለመጥፎ አንድ ለጥሩ
ዝም ችለው ይለፉ ሳይቸገሩ።
የዝምታ ቁምነገር አጠያያቂ አይደለም። አጠቃቀሙ ግን እንደግለሰቡ እንደሚለያይ ንዋይ ያስታውሰናል፤ የመናገር ፍላጎት ተፈጥሮአዊ ቢሆንም ችሎና ታግሶ ማለፉ የተሻለ መሆኑንም ይጠቁመናል።
ሲታይ ማየት ነው መስማት ሲሰሙ
አጉል መሆን ነው መሽቀዳደሙ
ሰላም እረፍት ነው ጥሩ መኝታ
ሳይዘላብዱ የዋሉ ለታ።
በተለይ የንዋይ ይህቺ የመጨረሻ መስመር የተለየ ስሜት የምትሰጥ ሳትሆን አትቀርም። ዘላብደን በዋልንባቸው ቀን “ምን ሆኜ ነው ግን?” ያልንባቸውንና የቀን ውሏችንን የኮነንበትን ምሽቶች ሳያስታውሰን አይቀርም። በዚህም መነሻ ራስን ከመውቀስና ከመታዘብ የጸዳው ንጹህ ለሊት የሚገኘው ሳይዘላብዱ የዋሉ ቀን ነው በማለት ከንዋይ የዝምታ ሀሳብ ጋር እንስማማለን።
ዝምታን ወዳጅ አድርጎ በማሞካሸት ያዜመው ሌላኛው ዘፋኝ ደግሞ ግርማ ተፈራ ካሳ ነው። በግርማ ዘፈን ውስጥ የሰዎች ሐሜትና ነገር የሰለቸው ገጸ-ሰብ ነው የምናደምጠው። በዘፈኑ ውስጥም ይቅር ማለትንና መተውንም እናደምጣለን።
ዝምታዬ
ድርሻዬ ነው ፋንታዬ
ልኬ ነው በቃ
አያምረኝም ስሞታ
ምልልሱ አያምርብኝ
እነሱን መሆን እንዳይሆንብኝ
የተባለውን ችዬ
ይሁና ብዬ
አለሁ ዝም ብዬ።
ያለ ሥሙ ስም ተሰጥቶታል። ታምቷል። ተዘልፏልም። ነገር ግን ለዚህ ሁሉ መልስ በመስጠት እነሱን መስሎ መመላለስን አልፈለገም። “ይሁና” ብቻ ብሎ ዝምታን መርጧል።
መልስ የለም ሁሌም ለነገር
ተግባባው ባለመናገር
ምላስም ምላሽም የለኝ
በአርምሞ ማለፍ ቀለለኝ።
ለተባለው ሁሉ መልስ በመስጠት መድከምን አልመረጠምና “ምላስም ምላሽም” የለኝም ብሎ ያለፈ ብርቱም ጭምር ነው።
ይቅር ባይነቱን፣ መተዉን የሚነግረን ደግሞ የሌሎች ሰዎች ሐሜትና ክፉ ቃል ከሱነቱ አንዳችም እንደማያጎድል ለመግለጽ “...ከጸጉሬ አንዲት አትጎድልም” እያለ ትርፍ በሌለው ነገር እንደማይታገል ነግሮን በተከታዮቹ “አልወቅስም ሰውም አልጥልም” በሚሉ መስመሮች በማጀብ ነው።
አፍ ያለው ያሻውን ቢልም
ከጸጉሬ አንዲት አትጎድልም
ላይጠቅመኝ አልታገልም
አልወቅስ ሰውም አልጥልም።
የሱን ብርታት ያድለን ብለን ወደ ሌሎቹ ዘፋኞች ደግሞ እንለፍ...
በራሱ ዜማ፣ ግጥሙን ከሀብታሙ ቦጋለ ጋር በመሆን፤ ነገር ግን የሙዚቃ አሬንጅመንት ሀሳቡና የዘፈኑን መጠርያ ጨምሮ ከሙሉቀን መለሰ “ጭር ካለው ቦታ” ከተሰኘው ሥራ የተወሰደ የሚመስለው፤ ስለ ዝምታ ከተዜሙ ሥራዎች ውስጥ ሌላኛው ነው - የጎሳዬ ተስፋዬ ዘፈን፡፡ በዚህ ዘፈን ላይ ጎሳዬ ከሚካኤል ሀይሉ ጋር በቅንብርም ተሳትፏል።
ጎሳዬ በዚህ ዜማ ከግርግር ከጩኸትና ከኹካታ ተገልሎ ከራስ ስለማውጋትና ራስን ስለማዳመጥ እንዲህ በሚል መግቢያ ሊነግረን ይሞክራል።
ውስጤን ለማዳመጥ በዝምታ
እስኪ ሊሂድ ደግሞ ጭር ካለው ቦታ
ለልቤ ጓደኛ ራሴ ነኝ
ዛሬ ልስጠው ጊዜ ላጫውተው ያጫውተኝ።
ከብዙ ግርግር በኋላ ያገኛትን ዝምታ ከውስጡ ሰላም ጋር ስታኖረው፣ ስታረጋጋው እናደምጣለን። ከሰው ጋር ነኝ ብሎ ያምን ነበር ግን ደግሞ በሰዎች ችላ ተብሏል። ተዘንግቷል። ታድያ ለምን አድማጭ ሳይኖረኝ አወራለሁ? ራሴንስ ለምን በጩኸት እቀጣለሁ? እያለ ነው ዝምታን ሙጥኝ የሚለው።
ድንገት እንደነቃ እንደባነነ
ግራ መጋባቴን የሚነግረኝ
አንዳንዴም ከራሴ ሳወራ ነው
ከውስጤ ሰላም ጋር የሚያኖረኝ
ከሰው ጋር እየኖርኩ ሰው ከረሳኝ
ውስጤም በዝምታ ሰሚ ካጣ
ታድያ ለምን ብዬ አወራለሁ
ራሴን በጩኸት እስክቀጣ።
ሰው ባጣ እስኪ ልየው ይከፋኝ እንደው
ኧረ አንዳንዴም በዝምታ አለ ጨዋታ።
እንዲህ ካሉ ከብዙ ውብ መስመሮች መካከል ደግሞ አንዲት ለአሁን ሀገራዊ እኛነታችን የምትሰራ ደምቃ የምትሰማኝ መስመር አለች። ሁላችንም በጋራ ልንላት የምትገባ መንቶ ናት። እንዲህ ትሰኛለች።
ከዚህ ሀገር ጩኸት ከዚህ ሀገር ሁካታ
አረፍ እንበል ልቤ ጭር ካለው ቦታ።
ከዚህ ሀገር ጩኸት ከዚህ ሀገር ሁካታ...
*
*
ቀጣዩ... ዝምታን በዜማ የሚሞሽርልን ድምጻዊ ደግሞ እዮብ መኮንን ነው። እዮባ “እሮጣለሁ” በሚለው ሁለተኛ አልበሙ ውስጥ የንግግርን አስፈላጊነትና ዝምታን “አንደበቴ ተናገር” “ዝም እላለሁ” የተሰኙ ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦችን ሳይጣሉ፣ አስማምቶ አስደምጦናል።
ዝምታው እንዲህ ትደመጣለች...
ዝም እላለሁ እኔ
ምን አፍ አለኝ ዛሬ
ሳላውቅ ስንቱን ተናግሬ
ያልኩት ሳይሆን ሲቀር አይቼ አፍሬ
በመናገሩ የተጸጸተ ድምጽ። ያውም ባለማወቅ የዘባረቀ። ያወራውና እውነቱ እዛና እዚህ የሆነበትን ሰው ድምጽ ነው በእዮብ ዝምታ መግቢያ ላይ የምናደምጠው።
የዝምታን ክቡድነት የማድመጥን መዛኝነት እያወሳ፣ በሁሉን አዋቂነት መዘላበድ ራስን ለግምት እንደሚዳርግም በዘፈኑ አንጓ እንዲህ እያለ ያስገነዝበናል (እዚህ ጋ የንዋይን “ ...ሳይዘላብዱ የዋሉ ለታ” መስመርንም ያስታውሰናል)
ዝምታ ይከብዳል
ከማውራት ማድመጥ ሚዛን ይደፋል
ይቆጫል ያወጉት
ሆድ ባዶ ቀርቶ
ራስ አስገምቶ...
እዮባ በዚህ መልኩ ይወርድና የሰው ልጅን ተፈጥሮ ሚስጢራዊነት፣ እንቆቅልሽና ግራ አጋቢነትን ደግሞ ያስታውሰናል። የዚህኔም የባለቅኔውን የሎሬት ጸጋዬን የግጥም መስመር ልናስታውስ እንችላለን።
“የምርምር እንቆቅልሽ ቋሚ ትንግርት መፍጠር ሲያምረው
እግዜር...አፈር ዘገነና እፍ ብሎ ሰው ሁን አለው”
የምርምር እንቆቅልሽ...ቋሚ ትንግርት...ሰው
እዮብም ይሄንኑ በማውሳትና “ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል”ን ሀገራዊ ብሂል በሚያስታውሱ መስመሮች ነው ዘፈኑን የሚቋጨው።
ፍቺው ከባድ ግራ የሚያጋባ
ሰው ሰዋሰው ነው ቅኔ የማይገባ
ያዩት የሰሙት ሁሉ አይነገር
መች ከብዶት ለሆድ ነገር ማሳደር።
*
*
የመጨረሻው ባለ ዝምታ ብስራት ሱራፌል ነው። “ዝም አይነቅዝም” ይለናል። በዚህ ዘፈን ውስጥ ሀገረሰባዊ ብሂሎቻችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎች በጉልህ እየተነሱ በዘፈኑ የተወሳውን ሀሳብ ሲያጎለብቱና ሲያገዝፉ እናደምጣለን።
ይገርማል ካዩት ለአንድ አፍታ
ይጮሃል ለካ ዝምታ
ትግዕስቱ የበዛ
አይደለም የዋዛ
ይልቅ ከሚያወራው
ዝም ያለውን ፍራው።
የሚሉ መስመሮች መግቢያ ሆነው፤በተለይ ዝምተኛውን ከተናጋሪው ይልቅ እንድናከብር “ዝምተኛን ፍራ” በምትል ተለምዷዊ አባባላችን በማሳሰብ ይጀምርልናል።
ከላይ እንደተጠቆመው በተከታታይ መስመሮች ሀገረሰባዊ ብሂሎችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሀሳቦችን እያነሳሳ ለተነሳበት ጉዳይ አጽንኦት ይሰጣል። ክፉ ደግ በአንድ አንጀት አሳድሮ የሚወልደው ዥንጉርጉሩ የእናት ሆድ አቤልና ቃየን የተሰኙ የሀሰትና የእውነት ምሳሌዎችን ወልዶ አየሁኝ፤ አቤል ተከሶ...ሰውም ከይሉኝታ በመኳረፉ ቃየንም በምድሪቷ ነገሰ እያለን... በተከታዮቹ መስመሮች ደግሞ ለጥቅም የገዛ ወዳጅን አሳልፎ የመስጠትን እውነት (ይሁዳዊና እየሱሳዊ እውነት) አስከትሎ ... ከመጯጯህ ይልቅ አንገቱን ደፍቶ ዝምታ የመረጠውን ብልህ ያወሳናል። እንዲህ እያለ...
እናት ዥንጉርጉር እውነትም ነው ሆዷ
አየው ሁለት ሰው ክፉ ደግ ወልዳ
አቤል ተከሶ ሰው ተኳርፎ ከዩልኝታ
ቃየን ነገሰ በምድሪቷ።
በልጦበት ጥቅም ለዲናር ቆሞ
ወዳጅ ወዳጁን ይሸጣል ሥሞ
አውቆ ነው ያ ሰው አንገት መድፋቱ
ዝም ያለው ጠልቶ እሪ በከንቱ።
የዚህ ዘፈን አስኳል ዝምታ ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሱት መስመሮችም ሆነ በተከታዮቹ ሀቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ቃል ጠባቂነትና እውነተኛነት ይወሳሉ። እንዲሁም እዮብ መኮንን በአንድ አልበም ውስጥ በሁለት ዘፈኖች የመናገርንና የዝምታን አስፈላጊነት እንደነገረን ሁሉ፤ ብሥራትም በዚሁ ዘፈን ውስጥ በዝምተኛው ልክ “እውነትን ተናግሮ በመሸበት የሚያድረው...ጨዋና ድል አድራጊውም ይከበር” ይለናል።
ቃል እየበላ ለማደር የዛሬን ጎርሶ
አለ የሚኖር ከአራዊት አንሶ
ይከበር እንጂ ጨዋ ሆኖ ድል አድራጊ
እውነት ተናግሮ ባመሸው አንጊ።
...
ዝም አይነቅዝም አይነቅዝም
ዝም አይነቅዝም አይነቅዝም...
*
*
“ከቻልክ እውነት ተናገር ካልቻልክ ደግሞ ዝም በል...” ዝም ይሻላል!
Saturday, 28 September 2024 20:25
ዝምታን ያቀነቀኑ ድምጻውያን
Written by መክብብ ፍቃዱ
Published in
ጥበብ