፨ ደንጊያ ቀረሽ ውርጅብኝ ከአንባቢዎቹ ሲወርድበት ወደ ኋላ ይወስዳቸዋል። ‹‹እኔን አትውቀሱኝ።›› ይላል። ከሃያ አመት በፊት ስለነበረው፤ ገና ሰላሳዎቹ ውስጥ እየገባ ያለ፣ ጺሙ ገና እያቀመቀመ ያለ ወጣት ጋዜጠኛ ያስታውሳል። ለጋዜጠኝነት ሥራ ከአዲስ አበባ ውጪ ሲወጣ ባለጋሪ፣ ለጋሪው ከለላ ሳይሰራ ከኋላው በተቀመጠች ሴት ዣንጥላ ተይዞለት ሲሄድ ያይና ተበሳጭቶ 25 ገጽ ይጽፋል።... ይቀጥላል፤ ህይወቱ ከል ይለብሳል። ከሴት አያቱ በቀር ማንም እስካይኖረው፣ የሚቀምሰው ሳይኖር ሁለት ሦስት ቀን ሲያድር፣ ‹‹መጽሐፌ ተሸጠ? አልተሸጠ?›› ሊጠይቅ ከካዛንቺስ በእሪ በከንቱ ፒያሳ እየሄደ፤ በተቀደደች ጫማው ውሃ እያስገባ፤ መጽሐፉ አንዳች ሳይሸጥ ተቆልሎ ሲጠብቀው. . . ብርድልብስ ተከናንቦ ተንሰቅስቆ ያለቅስ ስለነበረው ወጣቱ ዓለማየሁ ይነግራቸዋል። ያ ልጅ ነው ይህን መጽሐፍ የጻፈው። ‹‹በዚያ ሁኔታ ከዚህ የተሻለ ምን ሊጽፍ ይችላል?›› ብሎ ይጠይቃል። ሁሉም የጣለው፣ ሁሉም ያልፈለገው መሰለው፤ ፈጣሪውን ጨምሮ። ይኼ ህይወቱ ነው ወይም ዓለማየሁ የነበረበት ሁኔታ ነው። የሃገሪቱን ሁኔታ ደሞ አየ። ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ የዘረጋች ናት።›፣ ‹‹ኢትዮጵያ የተባረከችና በፈጣሪ ዘንድ የተወደደች ነች።›፣ ‹‹ኢትዮጵያ ሃያል ነበረች፤ ሃያልም ትኾናለች።›› . . .ወዘተ በሚል ብሂል ኢትዮጵያውያን -- እኛ ብሂሉን እየደጋገምን ከመስራት ይልቅ እንመጻደቃለን። ከመስራት ይልቅ ‹የተከበርን ነን› በሚል ተቀምጠናል፤ ይህንን በእጅጉ ይተቻል። ‹የተጠላው እንዳልተጠላ› ተጻፈ፤ በሃያኛ አመቱ ታተመ። በተለያዩ ክፍለሃገሮች እየተዘዋወረ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ነገር አጋጠመው፤ ሌላው ዓለም ከምድር ወጥቶ ጨረቃ ላይ፣ ማርስ ላይ ለመኖር ይሰራል። እኛ እዚህ ዘግተን ማምለክ ላይ ነን፤ ከማደግ ወደ ኋላ ሮጠናል። ይህንን በሚገርም ቋንቋ፣ በግጥማዊ ለዛ ይተቸናል።
‹‹የምንዥላቱን ጫማ ተጫምቶ
በምንዥላቱ ዓይን እያስተዋለ
በምንዥላቱ የወየበ አንጎል የሚያስብ
ተንከባላይ ጠይም እራስ
በፍጹም ሊኖር ባልተገባው ነበር።›› (104) እያለ ይሸረድደናል። በመጽሐፉ ‹‹የወደቀ መንፈስ ለማነሳሳት፣ አዲስ ባህል ለመውለድ፣ ልመናን በሥራ ለመተካት፣ ጨርሶ ከመጥፋት ለመታደግ›› (90) የሚያስችለውን መንገድ ይጠቁማል። ሌሎቹ ዘግተው ከማምለክ ሲርቁ፦ ‹‹እግዚአብሔርና ስሙ ከተሰለቹበት ከተማ ደረስሁ። የሰማይ አሞሮችና የባህር ነፍሳት ግን ጠግበዋል። የማያመሰግኑበትን በረከት አግኝተዋል።›› (10) ይላል።
፨ ፈጣሪን እየካደ አይደለም፤ ከጭፍን አምልኮ እንውጣ ነው የሚለው። ከ’አማኞቹ’ የበለጠ ለ’አማኞቹ’ ያዘነ ‘አማኝ’ ሆኖ መጣ። ረኀብ ሲቆላን፣ ድርቅ ሲያነፍረን አይቶ አዘነ። ቤተ-ዕምነት ውስጥ በመቀመጥ ብቻ ረኀብ ድል አይደረግም። መስራት ትተን በመጸለይ ብቻ ጊዜያችንን በማቃጠላችን ነው ፈጣሪ የተቆጣን። ሳይሰሩ መለመን ብቻ የዲያብሎስ መንገድ ነው።
‹‹- አትሩጥ አንጋጥ የሚለው አባባል ካንተ የመጣ ይሆን?
-- አይደለም። ዲያብሎስ የፈለሰፈው ጥቅስ ነው። ››
(‹አምላክ ስለ ኢትዮጵያ› ተስፋዬ ገብረአብ፣ እፍታ ቅጽ 5 - ገጽ 41)
አዲስ ነገር ከማሰብ ባለው መቀጠል የምንወድ ነን። መስራትን የተቃወምን ነን። ‹‹አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ወጣ ብሎ ግድብ ሰራን። ሰው ይራባል። ከግድቡ ጠልቆ ግን አያርስም። ለምን? ስንል የኢትዮጵያ አምላክ ከሰማይ ባልሰጠው ካመረትን ይቆጣል፤ በረከት ይነሳል አሉ።›› (6) ተነስቶ ከመቆፈር ቤተ-ዕምነት መንበርከክ እንመርጣለን። በላብ ከመራስ፤ በእንባ ታጥበን ከሰማይ ወርቅ እንዲዘንብ እንለምናለን። ይሄ ዓለማየሁን አስከፋው። የሃገሩንና የሌሎች ሃገራትን ሁኔታ ገመገመ። ‹‹ፈጣሪ ለኢትዮጵያውያን ወደ ኋላ እንተወው ዘንድ የማይቻለን የጉያ ጠላታችን አይደለምን?›› (8) አለ በምሬት። ለመለወጥ የተዘጋጁ አይደሉም። አንድ ሰው ሲናገር እንደሰማሁት፤ ‹‹ቻይናዊ፣ አሜሪካዊና አፍሪካዊ አብረው እየሄዱ፤ መንገዳቸው ላይ ገደል ያጋጥማቸዋል። ቻይናዊው መሻገሪያ ድልድይ አበጅቶ ተሻገረ። አሜሪካዊው መዝለያ አዘጋጅቶ ዘሎ አለፈ። አፍሪካዊው ገደሉ ጫፍ ቁጭ ብሎ ለረዥም ሰዓት ጸለየና በባዶ ለማለፍ ሲሞክር ገደሉ ውስጥ ገባ።›› በመጸለይ ብቻ እንጂ በመስራት አናምንም። ለማደግ፣ ለመለወጥ የተዘጋጀንም አይደለንም። ‹‹በኢትዮጵያዊነት ፋንታ የተከተረ ውሃ ላይ የፈላ የወባ ትንኝ ዕጭ አስተዋልሁ። በእንቅስቃሴ ውስጥ ለመኖር የሁለቱም ጠባይ አይፈቅድም።›› (107) አለ። ፈጣሪ አለ ብለን ከእሱ የተሰጠንን ዘነጋን። ‹እሱ እየወረደ በእጆቻችን አይሰጠንም›። ስንሰራ እንጂ ስንቀመጥ ጠብ የሚል ነገር የለም።
‹‹ኢትዮጵያውያን ዘንድሮም የሰማይ ደጆች ይከፈታሉ፣
እንበላውም ዘንድ መና ይዘንባል ብለው ይዋጃሉ።
እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድ ያሰናዳ ዘንድ ይችላልም ይላሉ።›› (6)
፨ ሰው የተፈጠረው እንዲያስብ ነው። አስቦ፣ ጭንቅላቱን ተጠቅሞ አዲስ እንዲፈጥር እንጂ የተሰጠውን አዕምሮ ደፍኖ፣ በፊት አባቶቹ ይኖሩበት በነበረው እንዲቀጥል አይደለም። ዓለማየሁ ‹ሰው ነገረኝ› እንዳለው፣ ነብዩ ሙሐመድ(ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ይላሉ፦ ‹‹ድንጋይ ከሆንክ ተገንባ፤ ዛፍ ከሆንክ ፍሬ ስጥ፤ ሰው ከሆንክ አስብ።›› ይላሉ። ሰው ካለ ምክንያት የተፈጠረ አይደለም። እንዲሁ በዘፈቀደ ባገኘውና በውልደት በተወዳጀው ላይ በመንጋ እየተመራ ጭፍን ሆኖ እንዲኖር አልተፈጠረም። ሌሎቹ ማሰብ ጀምረዋል። እኛ ቀደምቶቻችን ሲያስቡ በነበረው ላይ እያሰብን ነው ያለነው። ለጋሪ እንኳን ከለላ መስራት አቅቶን እንደ ድሮው በዣንጥላ የምንንቀሳቀስ ነን። “ፈጣሪ ጭቃ ማቡካትን ትቶ እንድንዋለድ እንደተወን ሁሉ በሁሉም ጉዳያችን ጣልቃ አይገባም።” ይላል። እኛ እንድንበረታ ተወን። እኛ ስንበረታ ራሳችንን እንችላለን፤ በሁሉ ነገራችን እሱን የምንጠራ፣ እሱን የምንወቅስ አንሆንም። ማረስ ትተን ልጃችን በረኀብ ሲሞት ‹ፈጣሪ ያሻው ኾነ› ማለት የለብንም።
‹‹ሰዎች ሲበረቱ እግዚአብሔር ያፈገፍጋል።
ከህሊናቸው፣ ከመንፈሳቸው፣ ከነፍሳቸው ይወጣል።›› (5) ይላል። ግን እኛ ራሳችንን አልቻልንም፤ ሁሉንም በእርሱ የምናላክክ ነን፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን መቼ ይበረታሉ? እግዚአብሔራቸው የሚያፈገፍግበት ቀኑ መቼ ነው?›› (6) እያለ ይጠይቃል። በበረቱበት ወቅት ሁሉን ያስችላሉ። ‹‹ሠዎች ሲበረቱ ስራቸው ጸሎቶቻቸውን ይወርሳል››( 7)
ስለዚህ. . .ተነሱ! ለ ‘ሀ’ ም ለ ‘ፐ’ ም ወደ ፈጣሪ አታላክኩ። ተነስታችሁ ስሩ። ‹ሁሉም የተፈጠረው በእኛ ደካማነት ነው› በሉ። ላባችሁ ምንዳችሁ ይሁን። ‹‹ድንቁርና በዕምነት ስም የሰማይ ዳርቻዎቻችሁን ከደነች።›› (75) አለ። ወንጀል የሆነባችሁ አለመስራታችሁ ነው።
‹‹--ሃገራችንን ደጋግመህ በረኀብ የምትቀጣበት ምክንያቱስ ምን ይሆን?
-- የመራባችሁ መነሾ ሽኩቻችሁና ስንፍናችሁ እንጂ እኔ ቅጣት ጥዬባችሁ አይደለም። ለእርሻ ይሆን ዘንድ ከሰጠኋችሁ ለም መሬት 17 በመቶው ብቻ ነው የታረሰው። ቀሪው ገና ጦሙን እንዳደረ ነው። በዚህም ምክንያት እናንተም ጦም እያደራችሁ ነው። ለሥራ ታጥቃችሁ ተነስታችሁ መሬቱን በአግባቡ የተጠቀማችሁበት ዕለት ረኀብ ደጃችሁ ላይ አይደርስም።›› (ተስፋዬ ገብረአብ : እፍታ ቅጽ 5 : ገጽ 36) ረኀብ እና ቸነፈር የሚፈራረቅብን ባለ መስራታችን ነው። ይህም ኃጢዓት ሆኖ እየፈጀን ነው፤ ተነሱ! ሰንበት ነው፣ ቅዳሜ ነው ብሎ ነገር የለም - ሁሉም ቀን አንድ ነው፤ ሁሉም የስራ ቀን ነው።
‹‹ምን ተሰርቶ ይታረፋል?
ተነስ ወዲያ፣ ቅዳሜውን ቆፍርበት፣
እሁድ ዝራ አብቅልበት፣
በልተህ ሳታድር፣ በባዶ አንጀት፣
ለዕረፍት ቀን መበጃጀት።
አቦ ተነስ!›› (ንፋስን በወጥመድ፣ ሁሴን ከድር፣ ገጽ 99)
ራሳችንን ሳንችል፣ ከረኀብ ሳንወጣ፣ ልጆቻችንን ሳናበላ እረፍት የለም። ‹‹እንደው ለመሆኑ፣
ምን አጥተው በሰንበት ለሥራ ታጠቁ?
ምድር አታሳዝኖትም፣ ከሰባት አንድ አታርፍም?›› (የተጠላው እንዳልተጠላ 43) ብሎ ነገር አይሰራም - ይለናል። ሳንሰራ፣ የልጃችንንም የራሳችንንም ሆድ ሳንሞላ ከየት የመጣ ዕረፍት?... ለሁሉም ለማይሰሩ ያዝናል - ዓለማየሁ፤ ኃጢዓት ሆኖ ረኀብ እየወረደብን ስለኾነ። ‹‹በዕምነት ስም ወደ ሰማይ የምትወረውሯት ስንፍና በራሳችሁ ላይ መዓት ሆና ትወርዳለች።›› (69) ይላል። እና ምን እናድርግ? ላለ ሰው’ም፦
‹‹በፈረሰው ቤተ-ዕምነታችሁ ፈንታ ሰማይ ጠቀስ ጎተሮችን ገንቡ፤ ጥጋብ እስኪሆንም ለእነርሱ ስገዱ።›› (77) ይህን ማለቱ (በእኔ አረዳድ) በቀጥታ መተርጎም የለብንም፤ ቀድመን እንዳልነው “ቁጭ ብለን ስንለምን ነው፤ ዳቦ የሚዘንብልን።” ብለን አምነን ያለነውን፣ በጭንቅላታችን ውስጥ ያለውን ቤተ-ዕምነት እናፍርስ፤ ቀጥሎም ጥጋብ እስኪሆን ጎተራ ገንብተን ወደ ሥራ እንግባ። ‹‹ዕምነታቸው ሲበሉ የማይወድ አዚም ነው። ልምዳቸው ከኋላ ቀርነት ጋር ሙጥኝ ያለ አዚም ነው።›› (6) ማለቱ በውስጣችን ያለውን ዕምነት እናስተካክል ዘንድ ነው።
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በቴሌግራም አድራሻው፡- @NEBILADU ማግኘት ይቻላል፡፡
Monday, 30 September 2024 00:00
አማኙና አዛኙ፤ ዓለማየሁ ገላጋይ
Written by ነቢል አዱኛ
Published in
ጥበብ