Monday, 30 September 2024 00:00

አዲስ አድማስ ጋዜጣና ትዝታዬ!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

አንድ፡-
ቦንጋ…
‹‹ይመር፣ ይቦረሽ!›› /ጠዋት/
‹‹ጫማዎን አዲስ ላድርግልዎት!›› /ረፈድ ሲል/
የሊስትሮው ሥም ዳኪቦ ይባላል፤ የቦንጋ እንብርት ላይ ቂጢጥ ብሎ ጫማ ሲያቆነጅ የሚውል ባተሌ ነው፤ ጨዋታም ይወድዳል፤ ከጃፖኒ ላይ ሸሚዝ የደረቡ ወጣቶች እግራቸው የሊስትሮው ኮርቻ ላይ ይፈናጠጣል፤ እጃቸው ደግሞ የተገለጠ ነገር ይይዛል - አዲስ አድማስ ጋዜጣ…
…ቀልድ ሊመስልህ ይችላል፤ በቦንጋ ከተማ የእርድና ልኬት አዲስ አድማስ ጋዜጣን ማንበብ እንደሆነ፣ እኔም የእርድናው ተቋዳሽ ነበርኩና እማኝ ልሆን እችላለሁ…
ከአዲስ አበባ ቅዳሜ ተጉዞ፣ እሁድ ይነበባል፤ የእሁድ እለት አብዛኛው ሰው ጥጋት ይዞ ወይም ቤቱ ቡናውን እየጠጣ አዲስ አድማስን ተንተርሶ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስቶ ይጥላል፤ ሰኞ፣ ማክሰኞ… እያለ ጋዜጣው ከአንዱ እጅ ወደ ሌላው እጅ ይሽከረከራል፤ ጋዜጣውን የተንተራሱ ውይይቶች፣ ብሽሽቆችና ቀልዶች በከተማው ይደራሉ…
ካ…ካ…ካ…ካ…ካ….
‹‹እግርህን ቀይር እንጂ!›› ዳኪቦ ልቡ የጠፋበትን ጋዜጣ አንባቢ ያዝዛል…
‹‹ውይ የነቢይ መኮንንን ጽሑፍ ይዤ ረሳሁህ!›› ጫማ አስቦራሽ ይቅርታ ይጠይቃል፤
‹‹ጥሩ፤ ኤፍሬም እንዳለስ ምን አለ?›› ዳኪቦ ይጠይቃል፤
‹‹ነገ ያንተ ተራ ነው፤ አውስሃለሁ››
‹‹እሺ!››
‹‹መልካም ቀን!››
እጆች ‹‹የጥበብ አምድ›› የተባለን ስፍራ ለመግለጥ ይከታለፋሉ፤ ዓይኖች የመጽሐፍ ዳሰሳና ትንታኔን ለመያዝ ይታትራሉ…
…ዳሰሳውን አንብቦ ያጠናቀቀ፣ በዳሰሳው ተነሳስቶ ቀጣይ ከሚገዛቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ እዚሁ ጋዜጣ ላይ የተዳሰሰ እንደሆነ ማስታወሻ ይይዛል፤ አዲስ አበባ ጓደኛ ያለው ደግሞ ስልክ ይመታል - ‹‹ይኼንን መጽሐፍ ላክልኝ›› የሚል መልዕክት ያክላል።
ደራሲያን ሙያዊ በሆነ ለዛ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሥራ ይልቅ ግለሰብ ተኮር ንትርካቸውን ይለዋወጣሉ፤ ነፍስን የሚያሰለጥን ሥነ-ጥሑፋዊ ሒስ አንብቤ አውቃለሁ፤ አለፍ ሲልም ወገባቸውን ይዘው ‹‹አላውቅሽም እንዴ!›› የሚሉ ተተቺ ተቺዎችም አሉ።
ልጅ እያለሁ የቤታችን ታላቅ እህታችን ኮሌጅ ትማር ነበር፤ ጋዜጣና መጽሔት ከእጇ አይጠፋም ነበር፤ ከእሷ እየተዋስኩ ግጥም፣ ስፖርት፣ በትንሹ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ሙዚቃ… ሌላም ሌላም አነብብ ነበር፤ በሴቶቹም በኩል የእርድና ምልክትና የመማር ጣዕም ልክ የሚያገኙት ከአካዳሚያዊ ትጋት ባሻገር ጋዜጣና መጽሔት በማንበብም ጭምር ነው፡፡ ሙዚቃ ሞዝቄ ሃምሣ ሣንቲም የተሸለምኩበትን ጊዜ አልረሳም፤ ጉንጬ ላይ የተሳምኩትንም አልዘነጋውም፤ በተለይ በተለይ የኤፍሬም ታምሩን ነበር የምዘፍንላት!   
‹‹ፏፏቴ ሆቴል›› አካባቢ ስብ ቡናቸውን ፉት እያሉ፣ አለያም ‹‹ቀለመወርቅ ካፍቴሪያ›› ማኪያቶ እየላፉ ወጣቶች እና ጎልማሶች፣ ሌሎችም አዲስ አድማስ ጋዜጣን ያጣጥማሉ፤ ታላቅ ወንድሜን የመሆን፣ የመምሰል ጉጉት ያደረብኝ ‹‹ፏፏቴ ሆቴል›› አጠገብ ቡና እየጠጣ ጋዜጣ ሲያጣጥም ሳየው ተቀብዬ አነብብ ስለነበር ነው፤ ቡና ይጋብዘኛል፤ ከቡናው በላይ የነቢይ መኮንን ጽሑፎች ይጥሙኛል።  
ነቢይ መኮንን በሚጽፋቸው ጽሑፎች ምክንያት በልጅነት ልቤ ሰርጾ አቃበዘኝ፤ ሰናይ መናወዝ ነው ታዲያ፤ ጋዜጠኛ የመሆን ሕልም አለምኩ!
ሁለት፡-
ወልቂጤ…
…ወልቂጤ ሦስት ዓመት ለትምህርት ስከርም ‹‹ተስፋ መጻሕፍት መደብር›› ጎራ እያልኩ መጻሕፍትና ጋዜጣ ማንበብ ጀመርኩ፤ የእኔዋ አዲስ አድማስ አልፎ፣ አልፎ እጄ ትገባለች፤ ያን ጊዜ ታዲያ ዳቦ እንዳገኘ ሕጻን እንደመፍነክነክ ይሠራራኛል…
ለጋዜጠኝነት፣ ለትርጉምና ለኤዲቲንግ ኮርሶች ቆንጆ ግብዐት ሆነኝ፤ ጉራጌ እየፈገገ ያስነብበኛል፤ ‹‹ሶሬሳ ሆቴል›› በሚባል አካባቢ ቡናና ሻዬን እያጣጣምኩ የእነ ነቢይ መኮንንን ጥዑም ጽሑፍ አጣጥማለሁ፤ ጨዋታ አዋቂነታቸው፣ ጨዋነታቸው እየደመቀ ቅዳሜና እሁዴን አሳልፋለሁ፤ አዘቦቱ በዓል ይሆናል…
…ታዲያ፣ የ‹‹Introduction to Journalism›› ኮርስ መምህራችን ፈተናውን ቆንጆ ውጤት በማምጣቴ አስጠርቶ አቅፎ ስሞኛል፤ ፍቅሩንና ዕውቀቱን በዕቅፉ ውስጥ ሆኜ ሞቄአለሁ! የምወደውን ነገር ስለተማርኩ ተሳክቶልኛል ብል ደግ ነው!
…እዚያ ውዬ ስመለስ ጓደኞቼ፡- ‹‹ለመሆኑ የሰኞውን ፈተና ምን ብለህ ልትሠራው ነው?›› ይሉኛል፤ አልበሽቅም፤ ቀድሜ ስለማነብብ ፈተና ደረሰ ብዬ አልንደፋደፍም።
ሦስት፡-
ዲላ…
ለትምህርት ዲላ ነበርኩ፤ ዲላ ብትሄድ እንደ አየሩ ሙቀት ሕዝቡ ሞቅ ያለ ፍቅር ይለግስሃል! ዲላን በተመለከተ በጥሩ የምተዝተው ነገር አለኝ፤ ልቤ ለዲላ ሠላምን ይመኛል!...
ታዲያ፣ ዲላ እያለን ወጥ ቀቃይ ፈልገን ደላላ ጋር ሄድን፤ 5ኛ መንገድ አካባቢ ያገናኝዋችኋል ተባልን፤ አልተሳካም፤ ወደ ቴሌ ሰፈር አቀናን፤ ሰመረ፤ ደላላው በምላሱ እንኳን ሰው አውሮፕላን ይጠልፋል...
‹‹ወጥ የምትሠራልንን ፈልገን ነበር›› ከማለታችን ከአፋችን ቀልቦ፡-
‹‹ሙያተኛ ቢሉ ሞያተኛ ናት፤ የማትሰራው ወጥ የለም!››
‹‹እሺ እባክህ፤ ምን ምን ትሰራለች?››
‹‹ለምሳሌ የጾምም የፍስግም ሽሮ ትሰራለች››
‹‹ተው እንጂ!››
‹‹አልተውም!››
‹‹ደሞዝ ስንት ነው?››
‹‹13 ዓይነት ወጥ ስለምትሠራ አንድ ሺ ብር ነው››
‹‹እኛ የምንፈልገው 2 ዓይነት ብቻ ነው፤ አሥራ አንዱን ሌላ ቦታ እየሠራች ትምጣ፤ የሁለቱን ዋጋ ብቻ ንገረን››
ተስማምተን ስንወጣ እዚያው አካባቢ አሁን ሥሙ የጠፋኝ መጻሕፍት ቤት አገኘሁ፤ ገባን፤ አዲስ አድማስ አለች…
‹‹በኪራይ እንጂ አይቻልም›› አለኝ፤
በእጄ የነበረውን አንድ መጽሐፍ እያቀበልኩት፡-
‹‹ይኼንን ያዝና አድማስን አውሰኝ›› አልኩት…
…ወዳጆች ሆንን፤ የኢትዮጵያን አድማሶች በአዲስ አድማስ በኩል ቃኘሁ…
አራት…
አምደኝነት…
….ዩኒቨርሲቲ አስተምራለሁ፤ ትምህርቴንም እማራለሁ፤ ትልቁ ደስታዬ ታዲያ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በአምደኝነት ማገልገሌ ነው…
ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በኩል ‹‹ስለ ሂስ እማልዳለሁ›› የሚል ርዕስ ያለው የመጀመሪያ ጽሑፌ ለኅትመት በቃ፤ ደስ አለኝ፤ ደስታዬ ገንዘብ ወይም ዝና አይደለም፤ ደስታዬ በልጅነት የማውቀው ጋዜጣ ላይ ሀሳቤን በማካፈሌ ያገኘሁት ስኬት እንደሆነ መዝግብ!
በእየሳምንቱ አንድ ጽሑፍ ጀባ እላለሁ፤ ዓይነቱ ሥነ-ጽሑፋዊ ሂስ፣ የሙዚቃ ዳሰሳ፣ አጫጭር ታሪኮች፣ የመጻሕፍት ዳሰሳ፣ የጉዞ ማስታወሻዎች፣ አስተያየቶችና ሌሎች ምልከታዎችን ያቀፈ ነው፤ አንድ አርቲክል ለማሰናዳት ብዙ ማንበብ፣ መፈተሽና መወያየት አለብኝ፤ ይኼ ነው ጥቅሙ!
ችክ ብዬ ሀሳቤን ለመጫን ሳይሆን ሀሳቤን ለማስተላለፍ እጽፋለሁ፤ ስንጽፍ ዓላማ ይኖረናል፤ መማር ማስተማር አንዱ ነው፤ መወያየት መቻል ትልቅ ቁምነገር ነው፤ ለማስተማር ብሎም ለመማር አርቲክል አዘጋጃለሁ፤ ዮናስ ታምሩ ገብሬ ለተለየ ዓላማ ሳይሆን ለመወያየትና ለሥነ-ጽሑፋችን ዕድገት ይጽፋል ብለህ ብታስብ ያዋጣል፤ ጤና እና ጊዜ እስካለኝ ድረስ ለመጻፍና ለማገልገል ቃሌን እንሆኝ! አመሰግናለሁ!!
* * *
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።

Read 386 times